Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልአምስቱ የጭንቅ ቀናት በሰሜን ኮርያ

  አምስቱ የጭንቅ ቀናት በሰሜን ኮርያ

  ቀን:

  በሳሙኤል ጌታቸው

  አዲስ አበባ ከሚገኘው ኤምባሲው ጋር ሰሜን ኮሪያን ስለመጎብኘት ማውራት የጀመርነው ከወር በፊት ነበር፡፡ ከአንዱ ዲፕሎማት ጋር እንደ ቀልድ በተጀመረ ወሬ ከሌላው የዓለም ክፍል የተነጥላ የቆየችውን ሰሜን ኮርያን የመጎብኘት ዕድሉን በአጋጣሚ በማግኘቴ ተደስቼ ነበር፡፡ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ የማላገኘው ዕድል እንደሆነም ተሰምቶኛል፡፡ እነሱም የአገሪቱን ሌላኛውን ገጽታ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሚሆን አስበው ነበር፡፡

  ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያስፈልጉኝን እንደ ቪዛ ያሉ መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት ላይ ታች እያልኩ ይህኛው ጉዞዬ ከየትኛውም አገር ልምዴ ጋር የማይገናኝና ልዩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፡፡ ኒውዮርክ ከተማ ያሉ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ወይም ዱባይ ያሉ ትልልቅ የንግድ ማዕከላትን እያዩ ከመደነቅ የተለየ መሆኑን ባውቅም ከዓለም ተነጥላ ዓመታት ያስቆጠረችውን ይህችን አገር መጎብኘት ግን አንዳች ጉጉት አሳድሮብኝ ነበር፡፡ በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተወጥራ ያለች አገር እንደሆነችም አውቃለሁ፡፡ ይህችን አገር መጎብኘት ግን የተለየ ትርጉም የተለየ ግዝፈት እንዳለው ተሰምቶኝ ነበር፡፡

  ወደ ሰሜን ኮሪያ እንደምሄድ የሰሙ የሥራ ባልደረቦቼና  በቅርበት የሚያውቁኝ ወዳጆቼ ጥሩ ነገር እንደማይገጥመኝ በማስፈራራት ጭምር ነግረውኛል፤ ጉዞዬን እንድሰርዘውም ጎትጉተውኛል፡፡ ይሁንና በብዙኃኑ ዘንድ ስለአገሪቱ ያለው አመለካከት  ምዕራባውያን ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ ያደረጉት እንደሆነ ተሰምቶኝ ስለ ነበር እንኳን ጉዞዬን መሰረዝ እስክደርስ አስቸኩሎኝ ነበር፡፡ ውዬ ሳላድር እግሬ አገሪቱን እንደረገጠ ነበር ምነው በቀረብኝ ያልኩት፡፡

  እስከ ዛሬ ካደረግኳቸው ዓለምአቀፍ ጉዞዎች የሰሜን ኮርያ ጉዞዬ በጣም አድካሚና በጭንቀት የተሞላ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር ለአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያደረጉት ታዋቂው የሪፐብሊካን ሴናተር ጆን መኬይን፣ በአንድ ወቅት አንድም አሜሪካዊ ወደ ሰሜን ኮሪያ ለመሄድ በሚያደፋፍር ደረጃ ‹‹ደደብ›› ከሆነ ለሚደርስበት የደህንነት ሥጋት በሙሉ አሜሪካ ተጠያቂ እንደማትሆን ማረጋገጫ መፈረም አለበት ሲሉ የተናገሩት ንግግር ፍሬ ቢስ አለመሆኑን የተረዳሁት ብዙም ሳልቆይ ነበር፡፡ ሰሜን ኮሪያን መጎብኘት ከእብደት ይቆጠራልና የጆን መኬይንን ንግግር ለማንኛውም አሜሪካዊ አስገዳጅ ሊሆን ይገባል፡፡

  አገሪቱን እንድጎበኝ እድሉን ያመቻቸልኝ ዲፕሎማት እስከ ቻይና ድረስ ካለው የአውሮፕላን ትኬት በስተቀር ሙሉ ወጪዬን በኤምባሲው እንደሚሸፈን ነግሮኝ ነበር፡፡ እኔም በዚህ ተስማምቼ ለአንዳንድ ወጪዎች የሚያስፈልገኝን መጠነኛ ገንዘብ ይዤ ተነሳሁኝ፡፡ ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያስፈልገኝን ቪዛ ለማግኘት ግን 34 ዶላር ተጠየቅኩ፡፡ እኔም ስለሁኔታው ለዲፕሎማቱ ነገርኩት፡፡ እሱም ምንም ችግር እንደሌለውና ስመለስ ለቪዛ ያወጣሁት እንደሚመለስልኝ ነገረኝ፡፡

  ቤጂንግ እንደገባሁ በስሜ ትኬት ተቆርጦ እንደተቀመጠልኝ ተነግሮኝ ስለነበር ይህንኑ በመግለፅ ወደ ተርሚናሉ ላመራ ስል ነበር ዲፕሎማቱ እንደሸወደኝ የተረዳሁት፡፡ ኤርፖርቱ ውስጥ ያሉ አስተናጋጆችን ‹‹እናንተ ጋ ትኬት ተቀምጦልኛል፤›› ብዬ ወዴት እንደምሄድ ነገርኳቸው፡፡ አስተናጋጆቹም ግራ በተጋባ ሁኔታ ይመለከቱኝ ጀመር፡፡ በመጨረሻም ትኬቱን ራሴ ካልገዛሁ የተቀመጠ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ፡፡ በርካቶች ከዱባይ ቀጥሎ የተለያዩ አልባሳትና ሌሎችም ነገሮችን ለመግዛት ከሚያዘወትሯት ቻይና አንዳንድ ነገሮችን ለመግዛት 1000 ዶላር ይዤ ነበር፡፡ ከዚሁ ገንዘብ ላይ ለቲኬት 564 ዶላር እንድከፍል ተገደድኩኝ፡፡ የቀረኝን አብቃቅቼ እጠቀማለሁ በሚል ተስፋ ተሞልቼ አውሮፕላኑ ውስጥ የተለቀቀውን ወታደራዊ ሙዚቃ እያደመጥኩኝ ወደ ሩቅ ምሥራቋ ሰሜን ኮሪያ ጉዞ ጀመርኩኝ፡፡

  ፕዮንግያንግ ኤርፖርት የደረስኩት እዉቁ አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች  ዲኒስ ሮድማን ወደ ሀገሩ ሲመለስ ነበር፡፡ እሱን የማግኘት ፍላጎቴም ለጥቂት ሳይሳካ ቀረ፡፡ በፕዮንግያንግ ዓለምአቀፍ ኤርፖርት ብዙ በረራዎችን አያስተናግድም፡፡ ከአገር ውስጥ በረራዎች ውጪ ዓለምአቀፍ በረራዎች ከቤጂንግ አሊያም ከሩስያ የሚመጡ ናቸው፡፡ ብዙ መንገደኞች የሉትም፡፡ ተረስቶ የቆየ ይመስላል፡፡ በኤርፖርቱ ያየኋቸው የውጭ አገር ዜጎችም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ሌላው ያስገረመኝ ነገር በኤርፖርቱ የሚያስተጋባው ወታደራዊ ሙዚቃ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ውስጥ ለሰዓታት ሲደመጥ የነበረውም ይኸው ወታደራዊ ሙዚቃ ነበር፡፡

  ኤርፖርት ውስጥ ፍተሻ የሚያደርጉት አካላት ሰሜን ኮሪያን በአሉታዊ ጎኑ ይመስላሉ የሚሉትን ነገሮች በሙሉ አብጠርጥው ይፈትሹ ጀመር፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት፣ ታይም፣ ኒውስዊክ የተባሉትን ጋዜጦችና መጽሔቶች ለማንበብ ይዤ ነበር የሄድኩት፡፡ ስለ ሰሜን ኮሪያ የተፃፈ ነገር ካለ በሚልም እያንዳንዱን ጋዜጣና መጽሔት እያገላበጡ መፈተሽ ያዙ፡፡ የሞባይል ስልኬ ሳይቀር በስክሪን ማለፍ ነበረበት፡፡ በውስጡ ያሉ የተላላኳቸው መልዕክቶች ቃል በቃል መነበብ፣ ፎቶዎቹ ደግሞ መመርመር ነበረባቸው፡፡ ደግነቱ ሊያስከፋቸው ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ነገሮች በሙሉ መንገድ ላይ ጥዬ ስለነበር የከፋ ነገር አላጋጠመኝም፡፡

  ኤርፖርቱ ድረስ መጥተው የተቀበሉኝ አዲስ አበባ የሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ ተወካዮች ናቸው፡፡ እነሱን ሳገኝ በመጠኑም እፎይታ ተሰምቶኝ ነበር፡፡ በምቆይባቸው አምስት ቀናት የሚያስፈልገኝን ሁሉ ሊያደርጉልኝ የተመደቡት እነዚህ ሦስት ተወካዮች ናቸው፡፡ ሳገኛቸው የተሰማኝ ዕፎይታ ብዙም ሳይቆይ ነበር ወደ ጭንቀትና ፍርኃት የተቀየረው፡፡

  ቁጥጥራቸው እንደ ነፃ ሰው ሳይሆን ከባድ ወንጀል ፈፅሞ እንደተያዘ እስረኛ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፍላጎቴ የሚሟላው በእነሱ ይሁንታ ነው፡፡ ከእነሱ ፈቃድ ውጪ ከሰው ጋር ማውራት አሊያም ፎቶ መውሰድ አልችልም፡፡ ሁኔታው ግራ የሚያጋባና የሚያስጨንቅ ስሜት ፈጠረብኝ፡፡ የምፈልገውን ሳይሆን የፈለጉትን ነው የሚያሳዩኝ፡፡ የት መሄድ፣ ምን ማየት እንዳለብኝ የሚወስኑት እነሱ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አብረውኝ የነበሩት የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈጸም እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ ሌላው ቢቀር ምን እንደምፈልግ ሐሳቤን የሚጠይቀኝ አልነበረም፡፡   

  የመንግሥታቸውን ፕሮፓጋንዳ የሚነዛው ዕለታዊ ጋዜጣ አሳታሚ ቢሮ ጎን ከሚገኝ ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ሆቴል እንዳርፍ ተደረገ፡፡

  አጠቃላይ የሆቴሉ ግድግዳዎች ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው ምስሎችና መልዕክቶች የተሞሉ ነበሩ፡፡ ፓስፖርቴ የካናዳ ነበርና የተለያዩ አላስፈላጊና ግላዊ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ተገድጃለሁ፡፡ ስለቤተሰብ ሁኔታ፣ ትዳርን የተመለከተ ጥያቄዎችና ሌሎችም አላስፈላጊ ነገሮች እያነሱ በጥያቄ አዋከቡኝ፡፡ ደስ የማይል ስሜት ቢፈጠርብኝም ስሜቴን ደብቄ መመለስ ጀመርኩኝ፡፡

  ከተማው የአስተዳደሩ የግል መኖሪያ ቤት ይመስል በኪም ኤል ሱንግ ዳግማዊና በልጃቸው ኪም ጆንግ አል ምስሎች የተሞላ ነው፡፡ በየመንገዱ የሚታዩ ሰዎችም ሙሉ ለሙሉ ካኪ የለበሱና አንዳች ፍርኃት ያሳደረባቸው ነገር ያለ ይመስል ከፊታቸው ጭንቀት ይነበባል፡፡ እኔም በኢትዮጵያ የነበረውን ያለፈውን ዘመን የደርግ አገዛዝ አስታወሰኝና ፍርኃት ፍርኃት አለኝ፡፡ በሐሳብ ጭልጥ አልኩኝ፡፡ የሚደብት ስሜትም አሳደረብኝ፡፡

  በአገሪቱ የምቆይባቸው አምስት ቀናት በሙሉ በፕሮግራም የተያዙ ነበሩ፡፡ በሰሜን ኮሪያና በደቡብ መካከል ያለውን ድንበር ባስጎበኙኝ ወቅት ‹‹ኢምፔሪያሊስቱ›› [የአሜሪካ መንግሥት] ጦርነት ለማስጀመር ትንኮሳ እያደረገና ለ‹‹አሻንጉሊቱ›› [የደቡብ ኮሪያ መንግሥት] ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ በማጋነን ዓይነት ነገሩኝ፡፡ ጥያቄዎች እንድጠይቅም አበረታቱኝ፡፡ ነገር ግን የቱ ደስ እንደሚያሰኛቸው፣ ምን እንደሚያስከፋቸው እርግጠኛ ስላልሆንኩኝ ጥያቄ ለማንሳት ድፍረቱ አልነበረኝም፡፡ በሰሜን ኮሪያና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን ግጭት በተመለከተ ጠንከር ያለ ውይይት የተካሄደባቸውን ቦታዎች እንድጎበኝና ታሪካዊ ክፍሎችን እንድጎበኝ ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡

  ጁኔ ታወር የሚባለውን አካባቢ በጎበኘሁበት ወቅት ስለ ኪም ኤል ሱንግና ስለ ማዮንግዴ ልዩ ዕይታ እንዲሁም ስለ ኪም ኤል ሱንግ የትውልድ ሥፍራ ነገሩኝ፡፡ ድህነትን እንዴት አሸንፎ መውጣት እንደቻለና ዘለዓለማዊ መሪያቸው መሆን እንደቻለም በስሜት አብራሩልኝ፡፡ ኪም በድህነት ይኖርበት በነበረና በዚህ አካባቢ ይጠጣው የነበረውን የጉድጓድ ውኃም ተመልክቻለሁ፡፡ ለኪም ልዩ ጥንካሬና ጥበብን እንደሰጠው የሚታመንበትን ይህንን የጉድጓድ ውኃ ቀድቼ እንድጠጣም ተነገረኝ፡፡ ሌሎች አብረውኝ የነበሩትም ውኃውን ስለጠጡ አለምንም ሥጋት ጠጣሁት፡፡

  ከዚያም የተለያዩ ዱር እንስሳት ወደሚገኙበት ፓርክ ወሰዱኝ፡፡ ፓርኩ የተለያዩ አገር መሪዎች ለኪም ኤል ሱንግ የሰጧቸው እንስሳቶች መኖሪያ ነው፡፡ በወታደራዊ አገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በስጦታ ለኪም አል ሱንግ ያበረከቱትን ጦጦችም አይቻለሁ፡፡

  የድል አድራጊው አባት አገር ነፃነት ሙዚየም (The Victorious Father Land Liberation War Museum) የተባለውን የጦር ሙዚየም በጎበኘሁበት ወቅት ፓብሎ የተባለ የአሜሪካ የጦር መርከብ አየሁኝ፡፡ መርከቡን ስለ መለሱበት አጋጣሚዎች የአሜሪካ ሰላዮችን ባህር ላይ ሆነው ሲሰልሉ እንዳጋጠሟቸውና ሰላዮቹን እንደማረኳቸው፣ አሜሪካ ይቅርታ ካልጠየቀች በቀር ሁሉንም እንደሚረሽኗቸው መናገራቸውን፣ በዚህ መሠረትም ወታደሮቹ በደብዳቤ ለሠሩት ‹‹ትልቅ ስህተት›› ይቅርታ መጠየቃቸውን የነገሩኝ አሳማኝ እንዲሆን የተላላኩትን በእጅ የተጻፈ ደብዳቤ በመረጃነት በማያያዝ ነበር፡፡ በዚህ ሙዚየም ያስቀመጧቸው ነገሮች በሙሉ በጦርነት ማሸነፍ የቻሉበትን ብቻ ነው፡፡ በተለይ አሜሪካን ያሸነፉባቸውን ጦርነቶች አጋንነው የማሳየት ነገር አለባቸው፡፡ የገደሏቸውን የአሜሪካ ወታደሮች በፎቶም ሆነ በቪዲዮ ቀርፀው ያስቀምጣሉ፡፡ ይህንን ያህል የአሜሪካ ወታደር ገድለናል ሲሉ በኩራት ያወራሉ፡፡ ከእነሱ ወገን ምን ያህል እንደሞተ ግን አይናገሩም፡፡ ፈራ ተባ እያልኩኝ አስጎብኚዬ የነበረችውን ወጣት ከእናንተ ምን ያህል ወታደር ሞተ ብዬ ጠይቄያት ነበር፡፡ ‹‹እሱ እኔ ማወቅ የሌለብኝ መረጃ ነው፤›› ብላ ስትመልስልኝ መስመር ተላለፍኩኝ እንዴ በሚል ደንግጬ ዝም አልኩኝ፡፡ ፎቶ እንዳነሳ ተፈቀደልኝና በሙዚየም ያሉ ጌጣጌጦችን ፎቶ ወሰድኩኝ፡፡ ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን ብዬ በሥጋት ተሸብቤና ስህተት ላለመሥራት በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተንቀሳቀስኩኝ ባለሁበት ቅፅበት ለሰሜን ኮሪያ ያለኝን አድናቆት በጽሑፍ እንድገልጽ ተጠየቅኩኝ፡፡

  ነገሩ የተገላቢጦሽ ቢሆንም አስጎብኚዎች እስክጽፍ ድረስ ቆመው እያዩኝ ነበርና ለመጻፍ ተገደድኩኝ፡፡ ምን ሊያስቆጣቸው እንደሚችል አላውቅምና በተቻለኝ መጠን የጻፍኩት ነገር ግልጽ እንዳይሆን አድርጌ ጻፍኩኝ፡፡

  የጻፍኩት ነገርም ወዲያው ነበር በቋንቋቸው ተተርጉሞ ምን ማለት እንደሆነ የተገመገመው፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት ከምሳ በኋላ የሶሻል ሳይንስ ምሁራን ወደ ሚገኙበት አንድ ተቋም ወሰዱኝ፣ በፖለቲካና አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከኤክስፐርቶች ጋር እንዳወራ ነበር የወሰዱኝ፡፡ ነገር ግን ፕሮግራሙ ምን እንደሆነ ስላልነገሩኝ በኮሚኒዝም ላይ አንዳንድ ነጥቦችን አንስቶ ለማውራት የሚረዳኝን ያህል ዝግጅት አላደረግኩኝም ነበር፡፡ ስለዚህም እነሱ ሲያወሩ አድማጭ መሆን መረጥኩኝ፡፡ ስለ ኮሚዩኒዝም ጥሩነትና ለሰፊው ሕዝብ ትልቅ ደስታ እንዳመጣም አስተማሩኝ፡፡ በመጨረሻም ኮሚኒዝምን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እንድረዳቸው ሐሳብ ሲያቀርቡልኝ ክው አልኩኝ፡፡

  በጭንቅላቴ በደርግ አገዛዝ ዘመን በኢትዮጵያ የነበረውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሌሎችም ማኅበራዊ ቀውሶች እንዲሁም ወጣቶችን አለፍላጎታቸው በግዴታ እንዲዘምቱ የሚገደዱበትን ሁኔታ እያሰብኩኝ ነበር፡፡ በተለይም ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንኳን ያላጠናቀቀውን አጎቴን ወደ ጦርነት እንዳይዘምት በመደበቋ ምክንያት ታስራ የነበረችው አያቴ ትዝ አለችኝ፡፡ በዚያ ወቅት የነበረው የሰዓት እላፊ አዋጅ ይመላለስብኝ ጀመር፡፡ እስቲ በዚህ ዘመን የነበረውን ነገር የትኛው ሰው ይናፍቃል? የትኛውስ ይደነቃል ብዬ ግራ ተጋባሁ፡፡ ደስ የማይል ስሜትም ወረረኝ፡፡

  ሻይ ለመጠጣት ከአንደኛው ሳይንቲስት ቤት የመሄድ ዕድሉን አግኝቼ ወደዚያው አመራን፡፡ መኖሪያ ቤታቸውን እያስጎበኙኝ ታላቁ መሪያቸው የሰጧቸው እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ቤቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ዕቃዎችም ከመሪያቸው የተበረከተላቸው እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ሳይንቲስቶች ምን ያህል ደሃ ቢሆኑ ነው መንግሥት በሚደጉማቸው በቁጠባ ቤቶች የሚኖሩት፣ በሌላው ዓለም እነዚህ አፓርትመንቶች ለድሃው የማኅበረሰቡ ክፍል የተዘጋጁ እኮ  ናቸው ስል ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡

  ፒዮንግያንግ የተባለውን የወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል በጎበኘሁበት ወቅት ሕፃናቱ ኪም ጆንግ ኡንን የሚያወድስ መዝሙር ዘመሩልኝ፡፡ ጆንግቻን የተባለውን በኅብረት ሥራ ማኅበር የተያዘው እርሻ እየጎበኘሁ በአንድ ወቅት ኪም ጁንግ ኡን ተቀምጦበት የነበረውን ወንበር አሳዩኝ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከተቀመጡበት በኋላ ባለበት ክብርና ግዝፈት ለማቆየት በቆንጆ ልብስ ሸፍነውታል፡፡ እንድቀመጥበትና እንድሞክረው አበረታቱኝ፡፡

  ከመካከላቸው እንዱ ቅር ቢለውስ ብዬ ስለፈራሁ አልቀመጥም ብዬ ድርቅ አልኩ፡፡ አገሪቱ የመሪያቸው የግል ቤቱ እስክትመስል ድረስ በየመንገዱ ፎቶው ተሰቅሎ ይታያል፡፡ በየሄድኩበት ስለሱ ይዘመራል፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ወታደራዊ ሙዚቃዎችን እየዘፈኑ ሲጨፍሩ ሰምቼ ከእንቅልፌ ብንን ብዬ ተነሳሁ፡፡ የሚያማምሩ ባህላዊ አልባሳትን የለበሱ ሰዎች ከሆቴሉ ፊት ለፊት ሲጨፍሩ አየሁ፡፡ ከአልጋዬ ላይ በድንጋጤ ዘልዬ ተነሳሁ፤ አገሪቱ በሌላ ኃይል የተወረረችና ነፃ ልትወጣ መሰለኝ፡፡ በለውጥ ላይ ያለች አገር ውስጥ በታሪካዊ ቅጽበት ውስጥ የተገኘሁ መሰለኝ፡፡ ነገር ግን አልነበረም፡፡ ኪም ጁንግ ኡን ከሠራተኞች ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጋር የተቀላቀሉበት ዕለት ክብረ በዓልን እያከበሩ እንደሆነ የተረዳሁት ብዙም ሳልቆይ ነበር፡፡ ዕለቱ በሰሜን ኮሪያ ከሕዝብ በዓላት አንዱ በመሆኑ ይከበራል፡፡ ይህ አገሪቱ በግለሰብ እንጂ በሕዝቡ ማንነት ላይ የተገነባች አለመሆኗን ማሳያ ነው፡፡ በሰሜን ኮሪያ እ.ኤ.አ. በ2016 ከሆቴሉ ውስጥ ባነር ሰርቀሃል በሚል ለእስር ስለተዳረገውና ከቀናት በፊት ሕይወቱ ስላለፈው ኦቶ ወረምባየር ያለኝ አመለካከት ምን እንደሚመስልና ስለፈጸመው ድርጊት ምን እንደማስብ ጠየቁኝ፡፡ መስማት የማይፈልጉትን ምላሽ ብሰጣቸው ምን ሊፈጠርብኝ እንደሚችል እያሰብኩኝ ተጨነቅኩ፡፡ በኋላ ላይ እንደምንም ብዬ በሰጠሁት መልስ በጣም ስላፈርኩኝ ረዘም ያለ ሻወር ወስጄ ራሴን ለማጽዳት ተገድጄ ነበር፡፡          

  ለቪዛ፣ ለአውሮፕላን ትኬት በሚል የተጀመረው ወጪ ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ሁሉም ወጪ እንደሚሸፈን ቢነገረኝም ቃላቸውን ግን አልጠበቁም፡፡ አንዳንድ ነገር እገዛበታለሁ ብዬ የያዝኩት 1000 ዶላር ባይኖረኝ ኑሮ ምን ልሆን እንደምችል መገመት ይከብዳል፡፡ ለአልጋና ለምግብ አስከፍለውኛል፡፡ በመጀመርያ የምግብ ወጪ የራሳቸው መስሎኝ ነበር፡፡ ከአስጎብኚዎቼ ጋር ምግብ አዘን እየተመገብን ሳለ ከፋዩ እኔ እንደሆንኩ ነገሩኝ፤ ደነገጥኩ፡፡ የራሴን ብቻ ሳይሆን የእነሱንም ከፍዬ የማበላው እኔው ነበርኩ፡፡ በአንደኛው አስጎብኚዬ ስም ከኢትዮጵያ ገንዘብ እንዳስልክም ግፊት ያሳድሩብኝ ጀመረ፡፡ ኤምባሲው ሰሜን ኮሪያን እንድጎበኝ ሲልከኝ ምንም ዓይነት ወጪ እንደማይኖርብኝ ነግሮኝ ነበር፤ በመሆኑም ለምን ገንዘብ እንደጠየቁኝ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሁኔታው በጣም አስጨነቀኝ፣ ጉብኝቱን አቋርጬ ለመምጣትም እንዳስብ አስገደደኝ፡፡ ገንዘብ አስልክ የሚለው ግፊት እየጠነከረ ሲመጣ የቆይታ ጊዜዬን አሳጥሬ ወደ አገሬ መመለስ እንደምፈልግ ነገርኳቸው፡፡ ምላሻቸው ግን አይሆንም ነበር፡፡ እንደ ጓደኛ የቆጠርኳቸው አስጎብኚዎቼ አጋቾቼ መስለው ታዩኝ፡፡ በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ ተንበርክኬ ፀለይኩ፡፡

  ገንዘብ አውጥቼ እንዳልሰጣቸው በአቅራቢያው የሚገኝ ባንክ የለም፡፡ ፓስፖርቴም አስጎብኚዎቼ ጋ በመሆኑ ብቻዬን መንቀሳቀስ አልችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከተያዘልኝ ክፍል ወጥቼ እንግዳ መቀበያው አካባቢ ሻይ ለመጠጣት ስል እንኳ አስተናጋጆቹ ወደ አስጎብኚዎቼ ስልክ ይደውሉና እንዲመጡ ያደርጓቸዋል፡፡ የባይተዋርነት ስሜት ተሰማኝ፤ ሳያንኳኩ ወደ መኝታ ቤት ዘው ብለው ይገቡና አልጋዬ ላይ ቁጭ ብለው ያዋሩኛል፡፡ ነገሮች ከባድ ነበሩ፡፡ የአስጎብኚዎች ውሎ አበል ሳይቀር እንድከፍል ነበር የተጠየቅኩት፤ በመጀመርያ 2,000 ዶላር ጠየቁኝ፤ ከዚያም እየቀለዱ እንደሆነና 1,500 ዶላር ከዚያም 1,000 ዶላር አምጣ አሉኝ፡፡ ብዙም ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር የመቀለድ ስሜት ውስጥ አልነበርኩም፤ በመሆኑም ገንዘብ ካልተከፈለ እንደማልለቀቅ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡

  ስለሆነም ኢትዮጵያ ወደሚገኙት የሥራ አለቆቼ ዘንድ በተደጋጋሚ ጊዜ ስልክ መደወል ጀመርኩኝ፡፡ ይሁንና ኢንተርኔትና የስልክ መስመሩ በጣም ደካማ በመሆኑ በቀላሉ ሊሳካልኝ አልቻለም ነበር፡፡ ከዚያም ለአንደኛው አስጎብኚዬ ስነግረው ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ስልኬ ሠራ፡፡ የጋዜጣውን አዘጋጆች ማናገር ቻልኩ፡፡ ስላለሁበት ሁኔታም በዝርዝር አስረዳኋቸው፡፡ ያለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለትም ወደ አገሬ ተመለስኩኝ፡፡ ስለ ቆይታዬ የሰሙ ሰዎች በጉጉት ሲጠባበቁኝ ነበር ያገኘኋቸው፡፡ ከመጣሁ በኋላ ከአለቆቼ የሰማሁት ነገር ግን እጅግ አስገረመኝ፡፡

  አዲስ አበባ ያሉ የጋዜጣውን አዘጋጆች ማግኘት የቻልኩት ከብዙ ሙከራ በኋላ እሑድ ከሰዓት በኋላ ነበር፡፡ የእረፍት ቀን እንደመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘት እንደማልችል ገምቻለሁ፡፡ ነገር ግን በአጋጣሚ እኔን ወደ ሰሜን ኮሪያ እንድሄድ ያግባባኝ የኤምባሲውን ዲፕሎማት አዘጋጆቹ በዚያኑ ዕለት በስልክ አገኙት፡፡ የስልክ መስመሩ አስተማማኝ ባለመሆኑ አዲስ አበባ ያሉት ባልደረቦቼ የሚያውቁት (የነገርኳቸው) በአፋጣኝ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደምፈልግና አዲስ አበባ ያለው ኤምባሲ ባልደረባ ፒዮንግያንግ አብረውኝ ካሉት ጠባቂዎቼ ጋር ተነጋግሮ ወደ ኤርፖርት እንዲወስዱኝ እንዲጠይቁት ነበር፡፡ በዚህ መሠረቱ አዘጋጆቹ የኤምባሲውን ሰው ወደ ኤርፖርት እወስድ ዘንድ እንዲተባበረኝና ወደ ኢትዮጵያ ባፋጣኝ እንድመለስ ጠየቅኩት፡፡ በኋላ እንደሰማሁት ከኤምባሲው ባልደረባ ያገኙት መልስ በእጅጉ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ እሱም ‹‹ሳሙኤል የመመለሻ ጊዜው ሳይደርስ ሰሜን ኮሪያን መልቀቅ አይችልም፤›› የሚል ነበር፡፡ ማንኛውም ሰው ያውም በራሱ ፈቃድ አንድ አገር ለመጎብኘት ሲሄድ ካሉት መሠረታዊ መብቶች ዋነኛው በፈቃዱ እንደሄደ፣ በፈለገበት ጊዜ አገሪቱን ለቆ መውጣት መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የሰሜን ኮሪያ ጎብኚ ግን መመለሻ ጊዜው እስኪደርስ ኤርፖርት ድርሽ ማለት አይችልም፡፡ ይህ አዲስ አበባ ላሉ ባልደረቦቼ ለመረዳት የሚከብድ በመሆኑ የተሰጣቸውን መልስ በቅጡ ለመረዳት ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ማድረጋቸውን አጫውተውኛል፡፡ እንደውም ጉብኝቱን ሳይጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ለምን ይመጣል የሚል አስገራሚ ጥያቄ የተሠነዘረላቸው እነዚህ አዘጋጆች የተለያዩ ምክንያቶችን ፈጥረው ሲወተውቱ መክረማቸውን እገምታለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል አስረግጬ የምነግራቸው ነገር፣ ከሰሜን ኮሪያ እግሬ ሳይወጣ የኤምባሲውን ሰው እንዳያስቀይሙት ነበር፡፡ ለነገሩ እነሱም ይህንን አልሳቱትም፡፡ የእኔ ተደጋጋሚ ጥሪን ተከትሎ እነሱም ከኤምባሲው ሰው ጋር በተደጋጋሚ በስልክ በመነጋገር ቀጠሉ፡፡ ከሰኞ በኋላ ግን ለመግባባት የሚያስችል እንግሊዝኛ ችሎታ የነበረው ይኸው የኤምባሲው ዲፕሎማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቋንቋ ይከብደኛል በሚል ፈሊጥ ለመግባባት አስቸጋሪ ሁኔታን መፍጠር ጀመረ፡፡

  በዚህ መሀል እኔ ለፒዮንግያንግ አለብህ የተባልኩትን ገንዘብ ተደራድሬ (ተማፅኜ) ወደ 1000 ዶላር ካወረድኩ በኋላ ገንዘቡ ለኤምባሲው እንዲከፈል ወደ አዲስ አበበ ጥሪ አስተላለፍኩ፡፡ የገንዘብ ጉዳይን ይዤ ስልክ ስደውል በአስገራሚ ፍጥነት አዲስ አበባ መገናኘት መቻል እያስደመመኝ ገንዘብ ተልኮ እንዲለቀቅ አሁንም በባልደረቦቼ ላይ በስልክ ግፊት አደረግኩ፡፡

  በኋላ እንደሰማሁት ገንዘብ ለመክፈል ወደ ኤምባሲው ስልክ የደወሉት ባልደረቦቼ የአዲስ አበባው የሰሜን ኮሪያ ሰው ስለሚጠበቀው ክፍያ በቂ መረጃ ነበረው፡፡፡ በመሆኑም 1000 ዶላር በዚያኑ ዕለት ወደ ኤምባሲ ይዘው እንዲመጡና በብር መክፈልም እንደሚቻል ይገልጹላቸዋል፡፡ ከሰዓት ቦሌ የሚገኘው የኤምባሲው ቅፅር የደረሱት ባልደረቦቼ ከሰሜን ኮሪያውያን ውጪ አንድም ኢትዮጵያዊ የማይታይበት ግቢ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የመጡበት ጉዳይ የሚታወቅ በመሆኑ ከኤምባሲው የጥበቃ ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ የኤምባሲው ሰው ተጠርቶ መጣ፡፡ እንደመጣም ገንዘቡን ተቀብሎ መቁጠር ጀመረ፡፡ ነገር ግን የተሰጠው ገንዘብ በቂ ያለመሆኑን፣ ይህም ምክንያቱ በሕጋዊ የባንክ ምንዛሪ አስበው ስለመጡ መሆኑን ነገራቸው፤ በጥቁር ገበያ ምንዛሪ ምጣኔ መሠረት 4000 ብር ልዩነት እንዳለና ይህንን ማሟላት ካልቻሉ እንደማይቀበላቸው ጨምሮ ያስረዳቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰውየው በወሰነው የዕለቱ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ (27 ብር ለአንድ ዶላር) ሒሳብ ታስቦ እንዲጨምሩ ተጠየቁ፡፡ እንደ ባልደረቦቼ ከሆነ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቁት በመሆኑ ወደ ቢሮ ተመልሰው ሒሳቡን ማስተካከል ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም የኮሪያው ድራማ ማለቂያ ገና ነበር፡፡ ተመልሰው የተጠየቁትን ቀሪ ለማስረከብ ሲዘጋጁ የኤምባሲው ሰው በድጋሚ ይቅርታ ጠይቆ የዕለቱ ጥቁር ገበያ ምንዛሪ 28 ብር ለአንድ ዶላር መሆኑን አዲስ መረጃ እንዳገኘና በዚያ መሠረት በድጋሚ ማስተካከል እንዳለባቸው ነገራቸው፡፡

  በመጨረሻ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ በድጋሚ ሳይጨምር የተጠየቁትን 28 ሺሕ ብር ከፍለው እኔን ወደ አገሬ አውሮፕላን ላይ እንዲያሳፍርላቸው ተማፅነው ወደ ቢሮ ተመለሱ፡፡

  ከሁሉም ከሁሉም የሚያስደምመው ግን እኔን ለማስለቀቅ የተከፈለው ክፍያና ይህም በጥቁር ገበያ ምንዛሪ ታሰቦ ለመሆኑ የሚገልጽ የኤምባሲ ማኅተም ያለበት ደረሰኝ መቆረጡ ነው፡፡ ምንም እንኳን በኮሪያኛ ቋንቋ የተጻፈውን ደረሰኝ ሙሉ በሙሉ መረዳት ባልችልም፡፡ የታገቱ ቱሪስቶች ማስለቀቂያ ክፍያን የሰሜን ኮሪያ የሒሳብ ባለሙያዎች እንዴት እንደሚያወራርዱት ማሰብ ይከብደኛል፡፡ ምናልባትም አገሪቱ ከምትገነባው የኑክሌር ሳይንስ ረቂቅነት የማይተናነስ ይመስለኛል፡፡             

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...