Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የሕዝብን ብሶት የማያዳምጥ የሕዝብ ተወካይ መሆን አይችልም!

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዘመን ሁለተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ ዓርብ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ተጠናቆ አባላቱም ተሰናብተዋል፡፡ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54 መሠረት የምክር ቤቱ አባላት የመላው የአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው እንደሆነ  ተደንግጓል፡፡ ማንኛውም የምክር ቤት አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት እንደማይከሰስ፣ ዕርምጃ እንደማይወሰድበትና የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ሲያጣበት በሕጉ መሠረት ከምክር ቤት አባልነት እንደሚወገድ ተደንግጓል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ በውክልና የሰጠውን የሕግ አውጭነት ሥልጣን ተግባራዊ ሲያደርግ፣ አባላቱ ደግሞ የሕዝብን ውክልና መሠረት በማድረግ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ቋሚ አሠራር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወክለነዋል የሚሉትን ሕዝብ እያገለገሉ ነው ወይ? ሕዝቡ ውስጥ የሚብላሉ መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን ይዘው በመምጣት በፓርላማ ይከራከራሉ ወይ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ ዝም ጭጭ ነው፡፡

  የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባዎች ሲደረጉ ከተወሰኑ ተወካዮች በስተቀር የብዙዎቹ ተሳትፎ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ አንገብጋቢ የሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ለምክር ቤቱ ቀርበው የተጧጧፈ ክርክር ሊደረግባቸው ሲገባ፣ በውስን የምክር ቤት አባላት መካከል በሚደረጉ የሐሳብ ልውውጦች ይጠናቀቃሉ፡፡ አንድ የምክር ቤት አባል ቢያንስ የመራጮቹን ፍላጎት ወክሎ መገኘቱን በመገንዘብ አገሩን የማገልገል ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህም መሠረት በፓርላማ ውስጥ በሚደረጉ ውይይቶች ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡ በሚረቀቁ ሕጎችም ሆነ የመንግሥት አስፈጻሚ አካልን ለመቆጣጠር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በመንግሥት ሥራ ውስጥም ሆነ በምክር ቤት አባልነት ሲያገለግል መቼም ቢሆን የወከለውን ሕዝብ መርሳት የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር የሕዝብ  ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ራሳቸውን ይገመግማሉ ወይ? እርስ በርስስ ይገማገማሉ ወይ? ይኼ በጥልቀት መፈተሽ አለበት፡፡

  በአምስቱ የምክር ቤት ዘመናት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሻለ ደረጃ ነፍስ ዘርቶ ይንቀሳቀስ የነበረው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተመራጮች በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ከሁለት ግለሰቦች በስተቀር ምክር ቤቱ በገዥው ፓርቲና በአጋሮቹ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር ውሎ፣ ይኼ ነው የሚባል ክርክር ታይቶ አይታወቅም፡፡ አልፎ አልፎ ውስን ክርክሮች ለመታየት ቢሞክሩም በመጨረሻ በሙሉ ድምፅ ሲፀድቁ ነው የሚታየው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መነሳት ያለባቸው በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ በርካታ ጥያቄዎችን ተሸክሞ መምጣቱ አይረሳም፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው በማጣቱ ብቻ በተቀሰቀሰው አመፅ በርካታ ዜጎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ብዙዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ መንግሥትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ በራሱ በኩል ያለውን ችግር በማመን ተሃድሶ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠኝ ጠፋ ሲል ተወካዮቹ የት ነበሩ? ምን ሠሩ? ምን ፈየዱ? መባል አለበት፡፡ ሕዝብ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በፍትሕ፣ በሙስና፣ በብልሹ አሠራሮችና በመሳሰሉት ላይ ጥያቄዎች አሉት፡፡ በዴሞክራሲያዊና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ቅሬታ አለው፡፡ በገዛ ራሱ ኑሮ ላይ ጭምር የሚያነሳቸው በርካታ ጉዳዮች አሉት፡፡

  በዓመት ሁለቴ ለእረፍት የሚበተነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደግሞ ከሕዝብ ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡ በዓመቱ አጋማሽና መጨረሻ ላይ ወደ መረጣቸው ሕዝብ ሲሄዱና ሲወያዩ ግን አይታይም፡፡ አልፎ አልፎ የተወሰኑ ሙከራዎች ቢታዩም በጣም አናሳ ናቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የወከላቸው ሕዝብ ዘንድ ወርደው ምን እንደሚፈልግ በአፅንኦት መጠየቅ ሲገባቸው ይህንን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ሕዝቡ ዘንድ በጥልቀት ገብተው መነጋገር ቢችሉ ግን በምክር ቤት ጠንከር ያሉ ሐሳቦችን ይዘው ለመቅረብና ለመከራከር ዕድሉን ያገኙ ነበር፡፡ ከከተማ ነዋሪዎች፣ ከነጋዴዎች፣ ከመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች፣ ከተማሪዎች፣ ከመምህራን፣ ከአርሶ አደሮችና ከአርብቶ አደሮች፣ ወዘተ. ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ቢወያዩ ሕግ በማውጣት ሒደትም ሆነ በተለያዩ ውሳኔዎች ላይ ጠቃሚ ግብዓቶችን ያገኛሉ፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን የራሳቸውም ተሳትፎ ተገድቧል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎች ይባክናሉ፡፡ ትምህርት ቤቶችን፣ የንግድ ተቋማትን፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን፣ እርሻዎችንና የመሳሰሉትን በአካል ተገኝተው ካልጎበኙ እንዴት ሕዝብ ወክለናል ይላሉ? ሕዝብ ውስጥ የሚብላሉ ጉዳዮችን እነሱ ካላስተጋቡ እንዴት ነው ወኪል የሚባሉት?

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሕዝብ ውስጥ ሲገኙ ለማመን የሚከብዱ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ከበርካታ ሰዎች ጋር ይገናኛሉ፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን ያስተናግዳሉ፡፡ ወደ ፓርላማ ሲመለሱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳች ላይ የበሰሉ ሐሳቦችን በማቅረብ ይወያያሉ፣ ይከራከራሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ጥራት ያላቸው ሕጎች እንዲወጡ፣ ለትርጉምና ለአላስፈላጊ ድርጊቶች የተጋለጡ ሕጎች እንዲቀሩ ያደርጋሉ፡፡ በሕዝብ ዘንድ ሊኖራቸው የሚገባው አመኔታም ይጨምራል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ወቅት ጥቂት ሰዎች ብቻ ሐሳብ ሲሰጡ የሚታየው፣ ብዙዎቹ የምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ነው፡፡ ሕዝብ በአንድ ፓርቲና አጋሮቹ ብቻ የተሞላ ምክር ቤት በመኖሩ እየተከፋ ባለበትና የምርጫ ሥርዓቱ ችግር መሆኑ ተረጋግጦ ለውጥ ይደረጋል ሲባል፣ ሕዝብ ዘንድ ወርዶ መሠረታዊ ችግሮች ላይ ለመነጋገር ዳተኛ መሆን ተገቢ አይደለም፡፡ በቅርቡ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ስለሚኖራት ልዩ ጥቅም በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ በፓርላማ ውይይት ሲደረግ የክልሉ ገዥ ፓርቲ (ኦሕዴድ) አባላት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ፣ አዲስ አበባን ወክለው ምክር ቤቱ ውስጥ የነበሩ 23 አባላት ድምፅ አለመሰማት በራሱ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ቢያንስ እንደ ከተማ ነዋሪዎች ተወካይነታቸው ሐሳብ አለመሰንዘራቸው ጥያቄ ቢነሳበት ምን ይገርማል?

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ሕጎችን ያፀድቃል፡፡ እነዚህ ሕጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ በምክር ቤቱ አባላት አብላጫ ድምፅ የሚፀድቁ ውሳኔዎችና ሕጎች በሚገባ ፍጭት ካልተደረገባቸውና የሕዝቡን ፍላጎት ከሞላ ጎደል ማሟላት ካልቻሉ ችግሩ የአገር ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሕዝብን ፍላጎት ማንፀባረቅ ካልቻሉ ደግሞ ተወካይነታቸው ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር እንዲደረግ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚፈጸም ሙስና እንዲጋለጥ፣ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ በሚቀርበው ሪፖርት የሚታየው የተቋማት ሕገወጥ አሠራር እንዲታረምና አጥፊዎች በሕግ እንዲቀጡ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ እየተጠቀሙ ሕዝብ የሚያስለቅሱ ሹማምንት ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና የመሳሰሉትን ለማስፈጸም ካልተጉ የሕዝብ ውክልናቸው የይስሙላ ይሆናል፡፡ የሕዝብ አመኔታ በሌለበት ደግሞ ኃላፊነትን ለመወጣት አዳጋች ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት ቢደነገግም፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመጥፋቱ ብቻ ሕዝብ ለምሬት ተዳርጎ አገር የሚያወድም ሁከት  ተከስቶ ነበር፡፡ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት አንፃራዊ መረጋጋት ቢፈጠርም፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ካልተፈጠረ በስተቀር መዝናናት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሕዝብን ብሶት አዳምጡ፡፡ ከሕዝብ ጋር በቀጥታ በመገናኘት ፍላጎቱን ሰምታችሁ ተማገቱለት፡፡ ሕጉ እንደሚለው ተገዥነታችሁ ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለህሊናችሁ ይሁን፡፡ የሕዝብን ብሶት የማያዳምጥ የሕዝብ ተወካይ መሆን አይችልም!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...