Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ወዳጃቸው እንኳን አደረሰዎት ለማለት ይደውልላቸዋል

  [ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ወዳጃቸው እንኳን አደረሰዎት ለማለት ይደውልላቸዋል]

  • እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማን ልበል?
  • አላወቁኝም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • አላወቅኩህም፣ ማን ልበል?
  • በድምፄም አለዩኝም?
  • ያው ብዙ ሰው ስለሚደውልልኝ ማንነትህን አላወቅኩትም፡፡
  • ኢንቨስተር ወዳጅዎን ረሱት?
  • ውይ ውይ አንተው ነህ እንዴ? ወዳጆቼ አዲስ ስልክ አምጥተውልኝ ስልክህን አላወጣልኝም፡፡
  • እኔማ በድምፄ ሳይለዩኝ ሲቀሩ በጣም ገርሞኝ እኮ ነው?
  • እንደነገርኩህ ረስቼህ ሳይሆን ስልክ ስለቀየርኩ ነው፡፡
  • ለመሆኑ በዓል እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • በዓልማ እንደ ድሮ ፈንጠዝያ ቀረ እኮ፡፡
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር? ምን ተፈጠረ?
  • የወጣውን መመርያ መቼም ዓይተኸዋል?
  • በዓል አታክብሩ የሚል መመርያ ወጣ እንዴ?
  • እኔ እኮ በዓል ሳከብር ሠርግ ነበር የሚመስለው፡፡
  • አሁን ታዲያ ምን መሰለ?
  • ስነግርህ በጣም ተቀዛቅዟል፡፡
  • ምነው ክረምቱ ነው ያቀዛቀዘው?
  • ምን እናንተም ባለሀብቶቹ ድምፃችሁን አጥፍታችሁ አቀዝቅዛችሁታል፡፡
  • እሱን እኮ ሆን ብለን ነው ያደረግነው፡፡
  • ሆን ብለን ስትል?
  • ሥልታዊ አካሄድ ነው፡፡
  • የምን ሥልታዊ አካሄድ ነው?
  • በአሁኑ ወቅት እየተፈጸመ ያለውን ነገር እያወቁ?
  • ምንድነው እየተፈጸመ ያለው?
  • ይኸው በርካታ ባለሥልጣናት እየታሰሩ አይደል እንዴ?
  • እሱስ ልክ ነህ፡፡
  • ቤት ራሱ መምጣት ያልፈለግኩት አቴንሽን እንዳልስብ ብዬ ነው፡፡
  • ባዶ እጅህንማ ከመምጣት በዚሁ በስልክ ብትጨርሰው ይሻላል፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ጊዜው እኮ ስለከፋ ብዬ ነው፡፡
  • ማለት እኔም ክፉ ሆኛለሁ እያልከኝ ነው?
  • ኧረ በፍፁም፡፡
  • ታዲያ የታል  ጎልድ ሌቭሉ፣ የታል በጉና በሬው?
  • በዚህ ወቅት ዓይን ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡
  • ስማ ልጆቼና ሚስቴ ቁም ስቅሌን እያሳዩኝ፡፡
  • ለምን?
  • ያስለመድከንን አምጣ ብለው ነዋ፡፡
  • ታዲያ አይገዙላቸውም ነበር?
  • ከየት አምጥቼ?
  • እ. . .
  • ስማ የሕዝቡ ችግር አሁን ነው የገባኝ፡፡
  • እንዴት?
  • አንድ ዶሮ በ400 ብር?
  • በ400 ብርማ ጫጩት ነው የሚገኘው?
  • የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ?
  • እንዴት?
  • እኔ 400 ብር ለአንድ ዶሮ ስጠየቅ፣ ሚስቴን የዶሮ ማርቢያ ልትከፍቺ ነው ወይ ብዬ እኮ ነው የተጣላኋት?
  • ክቡር ሚኒስትር ስነግርዎት በዚያ ብር ጫጩት ነው የሚገኘው፡፡
  • አንተም ይኼን እያወቅክ ነው በስልክ ብቻ እንኳን አደረሰህ የምትለኝ?
  • እኔማ አንድ ዕቅድ ይዤ ነው የደወልኩት፡፡
  • የምን ዕቅድ?
  • ይኼ ባህል መቅረት አለበት ብዬ አላምንም፡፡
  • የቱ ባህል?
  • ስጦታ የመሰጣጣት ባህሉ፡፡
  • ታዲያ ምን ይሻላል?
  • ባይሆን ለበዓል ስጦታ ሲሰጠዎት ሊነቁ ስለሚችሉ ቀኑ ይቀየር፡፡
  • ቀኑ መቼ ሊሆን?
  • ሕዝባዊ በዓላት ሲከበሩ ስጦታ ይሰጥዎት፡፡
  • ስለዚህ አንተ ስጦታህን መቼ ልታመጣ?
  • ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን!

  [የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር በጠዋት መጥቶ ወደ ቢሮ ሊወስዳቸው ሲል በቁጣ ያናግሩታል]

  • ምንድነው አንተ?
  • እንኳን አደረሰህ አይቀድምም ክቡር ሚኒስትር?
  • ብትደርስ ባትደርስ እኔ ምን አገባኝ?
  • ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር?
  • የእኔ ሙሰኛ መኪና ገዛህ እንዴ?
  • የምን መኪና ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ይኼን የያዝከውን ቆርቋሳ መኪና ነዋ፡፡
  • ታርጋውን አያዩትም እንዴ?
  • ምን ሆነ ታርጋው?
  • የመንግሥት መኪና እኮ ነው፡፡
  • እና ሌላ ሾፌር ነው ለእኔ የሚመጣልኝ?
  • እኔ ነኝ እንጂ የምወስድዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በዚህ መኪና?
  • ምን ችግር አለው?
  • መሠረታዊ የሆነ ችግር እንዳለ ነው የገባኝ፡፡
  • ችግሩ አልታየኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እዚህ መኪና ውስጥ እኔ ልገባ?
  • ይቅርታ አድርጉልኝ ችግሩ ግን አልታየኝም፡፡
  • እኔ አይደለሁም ልጆቼ እንኳን በዚህ መኪና አይሄዱም፡፡
  • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምኑን ነው የምተወው?
  • ሰሞኑን ምንድነው በሚዲያ የሰማሁት?
  • ምን ሰማህ?
  • በአዲሱ ዓመት ከተማው ውስጥ ቪ8 እንዳይነዳ ተብሏል እየተባለ አይደል እንዴ??
  • ታዲያ ምንድነው የሚነዳው?
  • በቃ እንደዚች ዓይነት አነስተኛ መኪና ነዋ፡፡
  • እኮ ለእኔ ይቺን?
  • ሚኒስትር ራሱ በቪ8 እንዳይሄድ ተብሏል አይደል እንዴ?
  • ምንድነው የምትዘባርቀው?
  • ክቡር ሚኒስትር እንደገባኝ ሚዲያ አይከታተሉም ማለት ነው፡፡
  • የትኛው ሚዲያ ላይ ነው እንደዚህ የተባለው?
  • ሁሉም ሚዲያ ላይ ነው የተነገረው፡፡
  • እኮ የትኛው ሚዲያ?
  • እኔማ ቢራ ቤት ነው የሰማሁት፡፡
  • አንተ ሰውዬ ይኼን የቢራ ቤት ወሬ ተው አላልኩህም?
  • ክቡር ሚኒስትር እኔ መታሰር አልፈልግም፡፡
  • ምን አድርገህ ነው የምትታሰረው?
  • መመርያ ጥሰሃል ተብዬ፡፡
  • ለአንተ መመርያ ተላልፎልሃል?
  • ቪ8 ከተማ ውስጥ አይነዳም ተብሏል፡፡
  • ዛሬ ፊልድ ብንወጣስ?
  • እኔ አበል ስላልተቀበልኩ ከተማ ውስጥ በዚህ ነው የምንቀሳቀሰው አልኩዎት እንግዲህ?
  • አንተ አልታዘዝም እያልከኝ ነው?
  • እርስዎም ለመመርያው አልታዘዝም እያሉ እኮ ነው?
  • ስማ እዚህ መኪና ውስጥ መታየት ስለማልፈልግ በፍጥነት ወደ ቢሮ እንሂድና መኪና እንቀይር፡፡
  • ምን ችግር አለው?
  • ክብሬ ይነካል፡፡
  • እንኳን ለእርስዎ ያኔ ንጉሡ ከምታምረው አውቶሞቢላቸው ወርደው በቮልስ ሄደዋል አይደል እንዴ?
  • ያለነው እኮ በደርግ ዘመን አይደለም፡፡
  • እሱን እንኳን ተውት፡፡
  • አንተ እንድዋረድ ፈልገሃል ማለት ነው?
  • እኔ መመርያ ማክበር ነው የምፈልገው፡፡
  • ለማንኛውም በጣም ተናንቀናል፣ እሱ ነው የገባኝ፡፡
  • እንደተረዳሁት የከፍታ ዘመኑ ለእርስዎ አልተመቸዎትም፡፡
  • ያልተጠየቅከውን አትቀባጥር፡፡
  • ለነገሩ የእኔ ሥጋት የከፍታ ዘመኑ እንዳይቀየር ነው፡፡
  • በምን?
  • በክፋት ዘመን!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ሀቀኛ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

  • በዓል እንዴት አለፈ ክቡር ሚኒስትር?
  • የዘንድሮ በዓልማ ቀዝቀዝ ያለ ነው፡፡
  • ለምን ቀዘቀዘ?
  • ያው ግርግሩም ያን ያህል የለም፡፡
  • እኔ ግን ደስ ያለኝ በዓል ይኼ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • በቃ ያለፈው ዓመት ብዙ ቀውሶች የነበሩበት ነው፡፡
  • ይኼኛውስ እንደሌለበት በምን አወቅክ?
  • ያው መንግሥትም የከፍታ ዘመን ብሎ ስላወጀ ተስፋ ሰጪ ዓመት ይመስለኛል፡፡
  • መቼስ አንተ ካልክ ይሁን፡፡
  • መቼስ ሲሉ ምነው?
  • አይ እኔ አንዳንድ ያልተዋጡልኝ ነገሮች አሉ፡፡
  • ምኑ ነው ያልተዋጠልዎት?
  • አየህ አገር የሚረጋጋው አመራሩ ከላይ ሲረጋጋ ነው፡፡
  • አመራሩ ሲረጋጋ ሲሉ?
  • እኛ ሳንጨነቅ፣ ረጋ ብለን ሥራችንን ስንሠራ ነው አገር የሚረጋጋው፡፡
  • አሁን ሥራ ቆሟል እንዴ?
  • ሥራማ በሚገባ ቆሟል፡፡
  • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
  • አሁን እኔ ምንም ዓይነት ነገር ፈርም ብትለኝ መፈረም አቁሜያለሁ፡፡
  • ለምን?
  • ነገ ምን እንደሚመጣ አውቃለሁ?
  • ክቡር ሚኒስትር አንድ ተረት እያስታወሱኝ ነው፡፡
  • የምን ተረት?
  • ይኼ ምን ያለበት ምን አይችልም የሚለውን ነዋ?
  • እኔ እንደዚያ እያልኩኝ አይደለም፡፡
  • ታዲያ ምን እያሉ ነው?
  • እኔ ዛሬ በቅንነት ሥራ ማስኬጃ ስፈርም ነገ ምን እንደሚመጣብኝ አላውቅም፡፡
  • እርስዎ የሚፈርሙበትን ነገር አያውቁትም እንዴ?
  • ስነግርህ መጨረሻዬ ቂሊንጦና ማዕከላዊ እንዲሆን አልፈልግም፡፡
  • ያልገባኝ ሳያነቡ ነው እንዴ የሚፈርሙት?
  • አየህ አንዳንድ ፀረ ልማት ኃይሎች ሊያጠቁን ይችላሉ፡፡
  • ሊያጠቁን ሲሉ?
  • በቃ እኛ በቅንነት የፈረምነውን ነገር በኋላ ጠምዝዘው ተጠያቂዎች ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡
  • አንብበው አይደል እንዴ የሚፈርሙት?
  • ስንቱን አንብበኸው ትችለዋለህ?
  • ሳያነቡ መፈረምማ የኋላ ቀርነት መገለጫ ነው፡፡
  • አይ እያንዳንዱን ነገር ላንብበው ብል ሥራ አይሠራም ብዬ ነው፡፡
  • እና ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ያው መንግሥት ነገሮችን እንደዚህ መቆጣጠር የለበትም፡፡
  • ምን ይደረግ እያሉ ታዲያ?
  • በቃ መንግሥት ነገሮችን ያፍታታ፡፡
  • ሲፍታታማ ይኸው ከአንድ መሥሪያ ቤት አምስት ሰዎች እየታሰሩ ነው፡፡
  • ባለሥልጣን ቢሞስን እኮ ዞር ብሎ አገር ነው የሚያለማው፡፡
  • መንግሥት ግን አንድ ስህተት የሠራ መሰለኝ፡፡
  • የምን ስህተት?
  • የሚሠሩ ወጣቶችን አንድ ለአምስት ሲያደራጅ አብሮ ሌሎችንም አደራጅቷል፡፡
  • ሌሎች ምኖችን?
  • ሌቦችን!

  [ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል]

  • አንተ የት ጠፍተህ ነው?
  • ወጣ ብዬ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኮ የት?
  • ወደ ዱባይ፡፡
  • አይ የደላው፣ እኛ እንደዚህ ተሳክቶልን ወጣ ብንል ደስ ይለኝ ነበር፡፡
  • ታዲያ ምን ችግር አለው ወጣ ብለው ይምጡ?
  • በዚህ ጊዜ ከአገር መውጣት እንደማንችል አታውቅም?
  • ለምን ተብሎ?
  • ይኸው እያንዳንዱ የውጭ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አልፎ ነው የሚፈቀደው፡፡
  • ይኼን አልሰማሁም ነበር፡፡
  • አዲስ መመርያ ተላልፏል፡፡
  • ለማንኛውም እንኳን አደረስዎት፡፡
  • ለምኑ?
  • ለአዲስ ዓመት ነዋ፡፡
  • ምን አዲስ ዓመት አለ ብለህ ነው?
  • እንዴት?
  • ይኸው ሰው ሁሉ ፈርቶ ስጦታ ያመጣ እንኳን የለም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የሕዝብ ጥያቄ ስላለ መንግሥት ይኼን ሙቀት ማቀዝቀዝ ፈልጎ እኮ ነው፡፡
  • ታዲያ እኛ ፍሪጆች ነን እንዴ? በዓል እኮ ባዷችንን ነው የዋልነው፡፡
  • ስነግርዎት ይኼ ነገር ማለፉ አይቀርም፡፡
  • ስማ አሁን እኮ ፖሊስ መጥቶ በማንኛውም ሰዓት ሊወስደኝ ይችላል፡፡
  • ኧረ ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ብረጋጋ ምን ይጠቅመኛል?
  • አሁን ስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ አለብን፡፡
  • የምን ስትራቴጂ ነው?
  • በቃ የጦፈ ጦርነት ማወጅ አለብን፡፡
  • ማን ላይ?
  • ጦርነት ማወጅ ብቻ ሳይሆን ማጥቃትም አለብን፡፡
  • እነ ማንን?
  • ፀረ ሙሰኞችን!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  በዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኝ ነፃ የትምህርት...

  በደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች ተገደሉ

  በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

  ፊፋ ከምርጫው በፊት የሥነ ምግባር ባለሙያ ሊልክ መሆኑ ተሰምቷል የኢትዮጵያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ በያዘው ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢጀመርም በስተመጨረሻ አጀንዳውን ስቶ ስለ መዋደድ እየተጨቃጨቀ...

  በዛሬው መደበኛው መድረካችን አጀንዳ የተለመደው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ይሆናል። ሌላ አጀንዳ የምታስይዙት አጀንዳ ከሌለ በቀር ማለቴ ነው። ክቡር ሚኒስትር... እሺ ...ቀጥል አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። መደበኛ አጀንዳው እንደተጠበቀ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዎና መንገሣቸውን እያነሱ ደስታቸውን ሲገልጹ አገኟቸው]

  እሰይ አገሬ... እሰይ አገሬ እልልል ምን ተገኘ ደግሞ ዛሬ? የአትሌቶቻችንን ድል ነዋ! በክፉ ሲነሳ የቆየውን የአገራቸውን ስም በወርቅ እያደሱ እኮ ነው?  አየሽ፣ መንግሥት የአገራችን ችግር ያልፋል ስሟም...