Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናክልሎች አስተያየት ሳይሰጡባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዳይፈረሙ በሕግ ሊወሰን ነው

  ክልሎች አስተያየት ሳይሰጡባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዳይፈረሙ በሕግ ሊወሰን ነው

  ቀን:

  የፌደራል መንግሥት በክልሎች የአስተዳደር ሥልጣን ውስጥ የሚፈጸሙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከክልሎቹ ሳይመካከር እንዳይፈርም በሕግ ገደብ ሊጣልበት ነው።
  ገደቡን የሚጥለው ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር ዕይታ ላይ ይገኛል።

  ረቂቅ ሕጉ ‹የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መወያያና ማፅደቂያ ሥነ ሥርዓት› የሚባል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የመዋዋልና የማፅደቅ ሥልጣን ለፌዴራል መንግሥት የሰጠ በመሆኑ መዘጋጀቱን በረቂቅ ሰነዱ ዓላማ ላይ ሰፍሯል። በተጨማሪም  ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የመዋዋል፣ የማፅደቅና ቀሪ የማድረግ ሥነ ሥርዓት ከሌሎች ሕጎች ጋር እንዲጣጣም ማድረግ በማስፈለጉ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ መዘጋጀቱን ይገልጻል። በዚህም መሠረት የክልል መንግሥታት ሚና በረቂቁ አንቀጽ አራት ላይ ሰፍሯል።

  ‹‹አፈጻጸሙ የክልሎችን አስተዳደራዊ ድጋፍ የሚጠይቅ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት፣ የሚመለከተው ክልላዊ መንግሥት አስቸያየት መጠየቅ አለበት›› የሚል መሥፈርት በንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ ተካቷል። የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ ደግሞ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ለማስፈጸም የሚያስችል ስምምነት በክልል ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ እንዲፈረም የፌዴራል መንግሥት ሊፈቅድ እንደሚችል ይገልጻል።

  ዓለም አቀፍ ስምምነት ማለት በአለም ዓቀፍ ሕግ የሚገዛ በኢትዮጵያና በሌላ አገር መካከል የተፈጸመ የሁለትዮሽ ስምምነት፣ በኢትዮጵያና በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አገሮች መካከል የተፈጸመ ባለብዙ ወገን ስምምነት፣ ወይም በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ድርጅት ወይም ድርጅቶች መካከል የተፈጸመ ስምምነት ስለመሆኑ በረቂቅ ሰነዱ ትርጓሜ ተሰጥቶታል። ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ማለት ደግሞ በዓለም አቀፍ ስምምነት አማካይነት በአገሮች አባልነት የተመሠረተ ስለመሆኑ ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

  ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስተቀር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙሉ ሥልጣን ውክልና ሰነድ ያልተሰጠው የመንግሥት ባለሥልጣን ዓለም አቀፍ ስምምነት መደራደርም ሆነ መዋዋል እንደማይችል ረቂቅ ሕጉ ይከለክላል። ይሁን እንጂ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የብድር፣ ዕርዳታና ተደራራቢ ቀረጥ የማስቀረት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲደራደርና እንዲዋዋል ረቂቅ ሰነዱ በልዩነት ይፈቅድለታል። ነገር ግን ስምምነቶችን ከመፈጸሙ በፊት የአገሪቱን ጥቅም የማስከበሩና ከሌሎች የአገሪቱ ሕጎችና  ፖሊሲዎች የተጣጣሙ መሆናቸውን የማረጋገጥ ግዴታ ይጥልበታል።

  የዓለም አቀፍ ስምምነት ድርድር እንዲጀመር ሐሳብ የሚያቀርብ የመንግሥት አካል ሚኒስቴሩንና የሚመለከቻቸውን ባለድርሻ አካላት ማማከርና ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ የማጥላቸውን ግዴታዎች፣ እንዲሁም የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያስረዳ ማብራሪያ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብ ማስፈቅድ እንደሚኖርበት በረቂቅ ሰነዱ ተካቷል።

  ሰነዱ በተጨማሪነትም የፀደቁ ስምምነቶች በማንኛውም ጊዜ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነኩ ሆነው ሲገኙ ቀሪ የሚደረጉበት አሠራር አስቀምጧል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...