ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ያስቆጠረው የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አቶ ጌታቸው ሽፈራው፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በጽኑ እስራት እንዲቀጡ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 18 እና 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ሰጠ፡፡
የግንቦት ሰባት አባል ከሆኑት አቶ አበበ ገላው ጋር በመገናኘት የአመፅ ቅስቀሳ በማድረግ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ተግባር ፈጽመዋል ተብለው የቀረበባቸው ክስ ተቀይሮ በመደበኛ ወንጀል ክስ ሲከራከሩ የከረሙት አቶ ጌታቸው፣ የቀረበባቸውን ክስ ሊያስተባብሉ እንዳልቻሉ ተገልጾ ጥፋተኛ በመባላቸው ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል፡፡
አቶ ጌታቸው እጃቸው ከተያዘ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በእስር ላይ በመቆየታቸው፣ የተፈረደባቸውን ጊዜ ማጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ከእስር ሊለቀቁ ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (6)ን ተላልፈዋል ተብለው ጥፋተኛ የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬም፣ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በስድስት ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
አቶ ዮናታን ጥፋተኛ የተባሉት በራሳቸው የፌስቡክ አድራሻቸው ሽብርተኝነትን የሚያበረታታ መጣጥፍ በማሰራጨት፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተቀሳቅሶ የነበረውን ሁከትና ረብሻ እንዲባባስ በማድረግ የኦነግን ዓላማ አራምደዋል የሚለውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው መሆኑን ፍርድ ቤት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም አቶ ዮናታን ያቀረባቸው ሦስት የቅጣት ማቅለያዎች በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ወንጀሉ ታስቦበት የተፈጸመ መሆኑን ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በክሱ የገለጸ ቢሆንም፣ የደረሰውን ጉዳት በማስረጃ ሊያሳይ ባለመቻሉ የወንጀሉን ደረጃ ዝቅተኛ በማድረግ በስድስት ዓመታት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አላቀረበም፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው የቅጣት ፍርድ ቅር መሰኘታቸውን የገለጹት የአቶ ዮናታን ጠበቃ፣ ‹‹የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማ ቀርበው በኦሮሚያ በተደረገው ረብሻና ብጥብጥ እንቅስቃሴ ጀርባ አንድም ሌላ አካል እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ማሞም ያንኑ አረጋግጠው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ማስረጃ በቀረበበት ሁኔታ ደንበኛዬ በሽብር ተግባር ወንጀል ቅጣት የተጣለባቸው ያላግባብ ነው፤›› በማለት ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡