Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የታየው የስደተኞች ቀውስ እንደገና እንዳይከሰት ተሠግቷል

  ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የታየው የስደተኞች ቀውስ እንደገና እንዳይከሰት ተሠግቷል

  ቀን:

  – ወደ አገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡ 20 ሺሕ ብቻ ናቸው

  – የምሕረት ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ 45 ቀናት ብቻ ቀርተውታል

  ሳዑዲ ዓረቢያ በሕጋዊ መንገድ ያልገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የአገሪቱን መንግሥት የምሕረት አዋጅ በተገቢው ሁኔታ ባለመጠቀማቸው ምክንያት፣ ከዚህ ቀደም የታየው ዓይነት ቀውስ እንዳይፈጠር ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ ችግሩ መንግሥትን እጅግ እንዳሳሰበ ቢገለጽም፣ መንግሥት ለስደት ተመላሾች የሚገባውን ቃል አያከብርም ተብሎ ተተችቷል፡፡

  በቅርቡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሰነድ አልባ ስደተኞች ያለ ምንም ቅጣት ከአገሪቱ እንዲወጡ ያስቀመጠው የሦስት ወራት ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ 45 ቀናት ብቻ  የቀሩት ቢሆንም፣ እስካሁን  የኢትዮጵያውያኑ ተመላሽ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ20 ሺሕ እንደማይበልጥ ተጠቁሟል፡፡

  ዓርብ ግንቦት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የተመላሾች አስተባባሪ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሚኒስትር ዴኤታው አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ከሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ጋር በጋራ በመሆን ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር  ውይይት አድርገዋል፡፡

  ‹‹ከሳዑዲ ዓረቢያ አለመውጣት አማራጭ አይደለም፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ መንግሥት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የማንቀሳቅስና የማስተባበር ሥራ እያከናወነ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ በአጥጋቢ ቁጥር የምሕረት አዋጁን እየተጠቀሙ በአለመሆናቸው የሚያሳሰብ ነው ብለዋል፡፡

  ስደተኞቹ በፍጥነት ያልመጡትና የምሕረት አዋጁን ያልተጠቀሙባቸው በርካታ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ብዙዎቹ አዋጁ ተግባራዊ ሊሆን ስለማይችል ሌሎች ከወጡ በኋላ የተሻለ ገንዘብ ይገኛል እንደሚሉ፣ የቤተሰብ ጫናና መዘናጋት ተጠቃሽ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአካባቢው የሚገኙ ሕገወጥ ደላሎች እንደዚህ ዓይነት ወሬዎችን በማስወራት፣ ዜጎች በሰላም ወደ አገራቸው እንዳይመጡ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

  የምሕረት ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቁ የቀሩት 45 ቀናት ብቻ ቢሆኑም፣ በአካባቢው የኢትዮጵያ መንግሥት ባቋቋማቸው ሰባት የምዝገባ ጣቢያዎች እስካሁን የተመዘገቡት 20 ሺሕ ተመላሾች ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዚህ በፊት በ2005 ዓ.ም. በተመሳሳይ ከሳዑዲ ዓረቢያ ያጋጠመው ዓይነት ከፍተኛ የሆነ የሞት፣ የአካል መጉደልና እሱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ እንደገና የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

  እስካሁን የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ አቶ መለስ  በበኩላቸው፣ ጉዳዩ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍልና ቤተ ዘመድ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ቆሼ ላይ የደረሰው አደጋ ድንገተኛ ነው፡፡ ይኼኛው ግን እያየነው እየመጣ ያለ ጎርፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ከሚዲያ ባለሙያዎች አንዳንድ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ በተለይ ቀደም ሲል የሳዑዲ ተመላሾችን ለማስተባበር የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ምን እንደሠራ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ሥራው አይታወቅም፣ የተገባላቸውን ቃል ተስፋ አድርገው የመጡ ተመላሾች ተበትነው ቀርተዋል፣ ይህም ተመላሾቹ ወጣቶች ወደ አገር ቤት እንዳይመለሱና ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

  አስተያየት ሰጪዎቹ ክልሎች ቃል እንደሚገቡት በተግባር እንደማይሠሩ፣ ከዚህ በፊት በስንት ችግር ከመጡ ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ ተመልሰው መሄዳቸውንና መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዳላበጀ በመጠቆም ተችተዋል፡፡

  በተለይ ‹‹እዚህም ሞት  እዚያም ሞት›› የሚል ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በስደተኞቹ ዘንድ እንዳለ አስተያየት የቀረበ ሲሆን፣ መንግሥት ቢመለሱ ለማስተናገድ ምንም የተለየ ፓኬጅ ባለማዘጋጀቱ ትችት ቀርቦበታል፡፡

  ከሁሉም በላይ ግን ቀደም ሲል የተጀመረውና በርካታ ዓመታት ያስቆጠረው  ዜጎች መብታቸው ተከብሮላቸው ወደ አካባቢው በሕጋዊ መንገድ ተጉዘው እንዲሠሩ ያስችላል የተባለ አዋጅ እስካሁን ሥራ ላይ ባለመዋሉ ትችት የቀረበ ሲሆን፣ ለአዋጁ አፈጻጸም አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ አይስተዋልም ተብሏል፡፡

  በተለይ የሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች የምሕረት አዋጁን ተጠቅመው  አገር ቤት ቢመጡ አሻራ ሳይሰጡ ስለሆነና ተመልሰው በሕጋዊ መንገድ እንዲሄዱ የሚፈቅድ በመሆኑ፣ አዋጁ ተግባራዊ ቢደረግ ስደተኞቹን ወደ አገር ቤት በቶሎ ለማምጣት ተስፋ ይሆን ነበር ተብሏል፡፡

  በሳዑዲ ዓረቢያ በመቶ ሺሕ የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ ስደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ አሰቃቂ የሆነውን የባህርና የበረሃ ጉዞ ሲያደርጉ ከሞት የተረፉ ናቸው፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...