Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መጣሱ እንዲጣራ የፀጥታው ምክር ቤት ወሰነ

  በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መጣሱ እንዲጣራ የፀጥታው ምክር ቤት ወሰነ

  ቀን:

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተፈጻሚነትን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ መወሰኑ ተገለጸ፡፡ የኤርትራ መንግሥት በተጣለበት ማዕቀብ ጥሰት ስለመፈጸሙ ክትትል እንዲደረግ፣ እንዲሁም አጣሪ ኮሚቴ ኤርትራ ድረስ በመሄድ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ ኢትዮጵያ ያቀረባችው ሐሳብ፣ በምክር ቤቱ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው ውሳኔ ላይ የተደረሰው ተብሏል፡፡

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ መንግሥት ላይ አስፈላጊው ምርመራ እንዲደረግ ያቀረበችው ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ ውሳኔው ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡

  የፀጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በኤርትራ መንግሥት ላይ በተደጋጋሚ ማዕቀብ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፣ በማዕቀቡ ተፈጻሚነት ላይ ጥያቄዎች ሲነሱ ነበር፡፡ በቅርቡ የአሜሪካ ባህር ኃይል ወደ ኤርትራ እያመሩ ነበሩ የተባሉ በኮንቴይነሮች የተጫኑ የጦር ሜዳ ሬዲዮኖች መያዙ ይታወሳል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ቢያስተባብልም ጆሮ ዳባ መባሉ አይዘነጋም፡፡

  ኢትዮጵያና ኤርትራ በባድመ ምክንያት በ1990 ዓ.ም. ጦርነት ከፍተው ኢትዮጵያ ባድመን በቁጥጥሯ ሥር ማዋሏ ይታወሳል፡፡ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ ላይ መስማማት ባለመቻሉ፣ ሁለቱ አገሮች ለሁለት ዓመት ከቆየው የደም አፋሳሽ ጦርነት ወዲህ እንደተፋጠቱ ነው ያሉት፡፡

  ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ከተመረጠች ጊዜ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ የተከሰቱ ግጭቶችን፣ ፍጥጫዎችና የአፍሪካ ቀንድ ቀውሶችን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ስኬታማ ሥራ እያከናወነች መሆኗንም አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡

  አቶ መለስ ጉዳዩን አስመልክቶ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና መሥራት ከጀመረች አራት ወራት ብቻ የሞላት ቢሆንም፣ በዚሁ ወቅት በዓለም ብሎም በአፍሪካ የተከሰቱ ትኩሳቶችና ግጭቶች ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ውጤታማ ሥራ ማከናወኗን ተናግረዋል፡፡

  የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮችን ውክልና አግኝታ ባለፈው ዓመት ለምክር ቤቱ ተለዋጭ አባልነት የተመረጠችው ኢትዮጵያ፣ ከራሷ የውጭ ጉዳይ መርህና ከአፍረካ ኅብረት አቋም አንፃር የቆዩ ግጭቶችና በቅርቡ እየተከሰቱ ያሉት  ፍጥጫዎች ተገቢ  የፖለቲካ መፍትሔ እንዲያገኙ እየሠራች መሆኑን ነው መግለጫው የሚያትተው፡፡

  የምክር ቤቱን ትኩረት ከሳቡ ወቅታዊ ጉዳዮች መካከል የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ የሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት እየተባባሰ መምጣትና የዓለም ኃያላን አገሮች (በተለይም የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት) በጉዳዩ ላይ ጎራ መለየታቸው፣ የየመን ቀውስ እየተባባሰ መምጣት፣ ሰሜን ኮሪያ ከሚሳይል ሙከራ ጋር በተያያዘ ከአሜሪካና ከደቡብ ኮሪያ ጋር የገባችበት ፍጥጫ ይገኙባቸዋል፡፡

  ቃል አቀባዩ አቶ መለስ እንደሚሉት፣ የምክር ቤቱ አባልነት የሌሎች አባል አገሮች ጥቅም ሳይጎዳ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር ዋናው ግብ ሆኖ፣ የአፍሪካ ኅብረት የምክር ቤቱን ይሁንታ እንዲያገኝና የዓለም ሰላምና ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን ኢትዮጵያ ዋና ዋና ግቦችን አንግባ ተንቀሳቃለች፡፡

  ከላይ ከተጠቀሱት ግጭቶችና ፍጥጫዎች፣ እንዲሁም በአፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ከሁለቱ የአፍሪካ ተለዋጭ አባል አገሮች ጋር (ሴኔጋልና ግብፅ) የተቀናጀ አቋም በመያዝ  እንደምትሠራም መግለጫው ያትታል፡፡

  የብሩንዲ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ የመካከለኛው አፍሪካ፣ የማሊ፣ የጋምቢያና የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት ማድረጓም ተጠቁሟል፡፡

  ለዓመታት የቆየው የሶሪያ የእርስ በእርስ ግጭትና የኃያላን አገሮች ጣልቃ ገብነት ጉዳይ የምክር ቤቱን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የአገሪቱ መንግሥታዊ ተቋማት መፈራረስ ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ አደገኛ ሁኔታ እንዳይፈጥር እንደምትሠጋ ተገልጿል፡፡ በጉዳዩ ላይ እጃቸው  ያለበት አገሮች ተመድ በያዘው ዕቅድ ብቻ ቀውሱ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንድያገኝ፣ እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ የምታደርገውን የኑክሌር ሙከራ እንድታቆምና የተመድ ውሳኔዎችን እንድታከብር የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

  እንዲሁም ደግሞ ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚመለከቱ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች የደቡብ ሱዳንና የሶማሊያ ጉዳዮች፣ ኢጋድ ከሚያደርጋቸው አቋም አንፃር ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

  በተለይ የሶማሊያ የፀጥታ ኃይል እንዲጠናከርና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደረግ በኢትዮጵያ የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን አክለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...