Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  [ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ውስጥ ሆነው ቴሌቪዥን እያዩ ሳሉ ጸሐፊያቸው ገባች]

  [ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ውስጥ ሆነው ቴሌቪዥን እያዩ ሳሉ ጸሐፊያቸው ገባች]

  • ለምን መጣሽ?
  • ክቡር ሚኒስትር ሥጋት ገብቶኝ ነው፡፡
  • የምን ሥጋት?
  • የሚወራውን አልሰሙም እንዴ?
  • አንቺ ንገሪኛ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ፓላርማ የነበረውን ውይይት ማለቴ ነው፡፡
  • ስለምን ጉዳይ?
  • ሚኒስትሮች ካጠፉ ከሥልጣናቸው ይነሳሉ ስለተባለው ነዋ?
  • አይ አንቺ?
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የሚያጠፋማ መነሳቱ የት ይቀራል?
  • አልሰሙም ማለት ነው?
  • ምንድነው የምሰማው?
  • በተደጋጋሚ የሚያጠፉ በፊት ዝም ይባሉ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አሁንም ይኖራሉ፡፡
  • እርስዎስ?
  • እኔን ማን ይነካኛል?
  • ባለፈው ዓመት ፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ. . .
  • እና?
  • መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ተነግረዎት ነበር እኮ?
  • ስለዚህ?
  • በተደጋጋሚ ተነግሮዎት ካላስተስተካከሉ ከኃላፊነት ይነሳሉ ብዬ ነው፡፡
  • ማን ነው የነገረሽ?
  • ዜና ላይ ነው የሰማሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሌላስ ምን ተባለ?
  • ፓርላማው በሚኒስትሩ ላይ አመኔታ ካጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነሳው ማሳሰቢያ ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
  • ተግባራዊ ሲደረግ ዓይቼ አላውቅም እባክሽ፡፡
  • አሁን ግን ጥያቄው እየገፋ ሲመጣ ተግባራዊ መደረጉ አይቀርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ዝም ብለሽ አትቃዢ፡፡
  • ኧረ እየቃዠሁ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ታዲያ ምን እየሆንሽ ነው?
  • ኧረ ሌላም ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ሰማሽ?
  • ሳቄ ነው የመጣው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን አሳቀሽ?
  • እርስዎም ቢሰሙት ሊስቁ ይችላሉ፡፡
  • ምኑ ነው የሚያስቀኝ?
  • የሚያኮርፉ ሚኒስትሮች አሉ ተብሏል፡፡
  • ለምንድነው የሚያኮርፉት?
  • አንዳንዶቹ በጥያቄ ሲፋጠጡ ዘመቻ ተከፈተብን ብለው ነው አሉ፡፡
  • ሌሎቹስ እባክሽ?
  • ሌሎቹማ. . .
  • እህ?
  • ለምን ተነካን እያሉ ያኮርፋሉ አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሃ. . . ሃ. . . ሃ. . .
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰው እኮ ካልነኩት አያኮርፍም፡፡
  • እርስዎ ግን በሆነው ባልሆነው ያኮርፉ የለ?
  • እኔ?
  • እኔ የፈራሁት. . .
  • አንቺ የፈራሽው?
  • ፓርላማ ላይ ስለርስዎ የተወራ ነው የመሰለኝ፡፡
  • መናጢ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ በቦርድ ሰብሳቢነት ከሚመሩት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጋር እየተነጋገሩ ነው]

  • ለፓርላማ የሚቀርበው ሪፖርት ተዘጋጀ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንደ አምና እንዳንወቀስ ደግሞ፡፡
  • አይ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምነው?
  • ብዙ ጉድለቶች ሳይመዘዙብን አይቀርም፡፡
  • ምን ማለትህ ነው?
  • ያውቁ የለ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምኑን ነው የማውቀው?
  • የግዥ ሥርዓታችን መመሰቃቀሉን. . .
  • እ. . .
  • የጨረታ አወጣጣችንና አመራረጣችን ለሙስና መጋለጡ. . .
  • እ. . .
  • የፋይናንሳችን መዝረክረክ. . .
  • እ. . .
  • በሪፖርት አቀራረባችን ውሸት መብዛቱ. . .
  • ይኼ ሁሉ ሲሆን አንተ የት የነበርክ?
  • ድርጅቱን እኮ እኔ ሳልሆን እርስዎ ነው የሚመሩት፡፡
  • እኔ እኮ የቦርድ ሰብሳቢ ነኝ፡፡
  • እኔ ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነኝ፡፡
  • እናስ?
  • እናማ አላሠራ እያሉኝ ነው፡፡
  • እኔ?
  • እኔ ነኝ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
  • ስለዚህ ሪፖርቱ ይህንን ሁሉ ይዟል እያልከኝ ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር ደስ እንዲልዎት ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡
  • በጣም ጥሩ፡፡
  • ፓርላማ ስንሄድ ያው የሚያስረዱት እርስዎ ነዎት፡፡
  • አንተ ደግሞ በጎደለ ትሞላለህ?
  • ምናለበት በሌላውም በጎደለ ቢሞሉኝ?
  • ለምሳሌ?
  • ከጨረታ ከሚገኘው ኮሚሽን. . .
  • ምን?
  • ከግዥና ከመሳሰሉትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አንተ ምን እያልክ ነው?
  • እኔም የድርሻዬን እያልኩ ነው፡፡
  • ይኼ ያዋጣል?
  • እርስዎስ ያዋጣዎታል?
  • ምኑ ነው የሚያዋጣኝ?
  • ፓርላማ ላይ ብንፋጠጥ ያዋጣዎታል?
  • ለምንድነው የምንፋጠጠው?
  • ጥያቄ እንደ ዶፍ ሲወርድ ነዋ፡፡
  • የሚመለከትህን ትመልሳለህ ገባህ?
  • ኧረ ምን በወጣኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • እና ምን ልትሆን ነው?
  • ዝም! ጭጭ! ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ደሜን አታፍላው እንግዲህ፡፡
  • እንዲህ ሲሆኑ እኮ ደስ ይለኛል?
  • ምን ስሆን?
  • ሲያኮርፉ፡፡
  • ይድፋህ!

  [ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው]

  • ምነው መንገዱ ጭር አለ?
  • ዛሬ እኮ በዓል ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የምን በዓል?
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምነው?
  • እኔን ይጠይቁኛል እንዴ?
  • አታናደኝ ንገረኝ፡፡
  • ዛሬ እኮ ሜይ ዴይ ነው፡፡
  • ነው እንዴ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይገርማል?
  • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
  • ጊዜው እንዲህ መንጎዱ?
  • የቱ ጊዜ ክቡር ሚኒስትር?
  • የወጣትነታችን ነዋ፡፡
  • ከሜይ ዴይ ጋር ምን አገናኘው ክቡር ሚኒስትር?
  • የታገልነው እኮ ሠራተኛውን ከብዝበዛ ለማላቀቅ ነው፡፡
  • ድንቄም. . .
  • ምን አልክ አንተ?
  • ገርሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ምኑ ነው የገረመህ?
  • እናንተ ታገልን ብትሉም አሁንም ጉልበታችን ይበዘበዛል፡፡
  • እንዴት እባክህ?
  • ለምሳሌ እኔ ያለ አበልና ተጨማሪ ሰዓት ክፍያ በበዓል እየሠራሁ አይደል?
  • እና ተጎዳሁ እያልክ ነው?
  • የእኔ ለጊዜው ይቅርና. . .
  • የማን ይወሳ ታዲያ?
  • ታገልንለት የምትሉት ሠራተኛ ዛሬም አበሳ ውስጥ ነው፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • ግማሹ የሚለፋውን ያህል ሩቡን አያገኝም፡፡
  • እሺ?
  • ግማሹ የመደራጀት መብቱ ተገፏል፡፡
  • እሺ?
  • ሌላው በገዛ አገሩ በውጭ አሠሪዎች ይደበደባል፡፡
  • ምን?
  • ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናት ጉልበት ጭምር ይበዘበዛል፡፡
  • ሌላስ?
  • የሥራ ቦታ ደኅንነት ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • ለአደጋ የሚዳርጉ ሥራዎች ተገቢዎቹ አልባሳትና መጫሚያዎች የላቸውም፡፡
  • ወይ  ጉድ?
  • ሌላም የባሰ አለ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • አካላዊ ጉዳትና ሞት በሽበሽ ነው፡፡
  • ወቸ ጉድ?
  • በዚህ ላይ ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ተገቢው ክፍያና ጥቅማ ጥቅም የላቸውም፡፡
  • አንተ ይኼንን ሁሉ በምን አወቅክ?
  • ከእናንተ ሪፖርት በተቃራኒ የሚወጡ መረጃዎችን እከታተላለሁ፡፡
  • ምን አልክ አንተ?
  • በቃ አይናደዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ብናደድ ምን አገባህ?
  • ሲናደዱ ልጅ ይመስሉኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ጅላ ጅል!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ደርሰው ከባለቤታቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

  • ፓርላማ የማቀርበው ሪፖርት ስላለ እስኪ አብረን እንናበብ፡፡
  • ይልቅ አንድ ዘዴ ልንገርህ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • እኔ አንድ የፓርላማ ጥያቄ አቅራቢ አባል ልሁን፡፡
  • ምን?
  • ለአንተ ይጠቅምሃል፡፡
  • ከዚያስ?
  • አንተ ሪፖርት ታቀርባለህ፡፡
  • እሺ?
  • እኔ ማስታወሻ እይዛለሁ፡፡
  • ከዚያስ?
  • አንብበህ ስትጨርስ ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡
  • ጥሩ ነው፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ የተዘጋጀውን ሪፖርት አንብበው ከጨረሱ በኋላ ባለቤታቸው ጥያቄ ጀመሩ]

  • ክቡር ሚኒስትር?
  • አቤት?
  • ይኼን ሪፖርት ካለፈው ዓመት የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?
  • የህዳሴ ግድቡ 6ኛ ዓመት በተከበረ ማግሥት በመቅረቡ ልዩ ያደርገዋል፡፡
  • አይቀልዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን አጠፋሁ?
  • የዘንድሮና የአምና ሪፖርት ይመሳሰላሉ ነው የተባሉት፡፡
  • በእርግጥ. . .
  • በእርግጥ ምን?
  • ከአምና የተንከባለሉ. . .
  • ምንድናቸው የሚንከባለሉት?
  • ትልልቅ ስኬቶችና መጠነኛ ጉድለቶች፡፡
  • ለምሳሌ በኦዲተር ጄኔራል የቀረበባችሁን 500 ሚሊዮን ብር የታለ ያወራረዳችሁት?
  • በሒደት ላይ ነን፡፡
  • ከመመርያ ውጪ ያለጨረታ የግንባታ ኮንትራት የሰጣችሁት ለምንድነው?
  • እሱም በሒደት ላይ ነው፡፡
  • ሒደት ምንድነው?
  • ፕሮሰስ ማለት ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር 500 ሚሊዮን ብር ሒሳብ አላወራረዳችሁም፣ ያላግባብ የአንድ ቢሊዮን ብር የግንባታ ኮንትራት ሰጥታችኋል፣ የ600 ሚሊዮን ብር ግዥ ያላግባብ ተፈጽሟል. . .
  • አለ አይደል?
  • ቆይ! ቆይ!
  • ምን?
  • በሠራተኞች ቅጥር፣ ምደባ፣ ሹመት፣ ዝውውርና ጥቅማ ጥቅሞች ኢፍትሐዊነት በዝቷል፡፡
  • እኛ እኮ?
  • እናንተ ምን?
  • አንቺ አሁንስ አበዛሺው [ተቆጡ]፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር እዚህ ከእኔ ጋር ጣጣህን ብትጨርስ ይሻልሃል፡፡
  • እሺ ቀጥይ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ልታዘዝ?
  • ትዕዛዙ ይቆይና በመደበኛ ሥራ ውስጥ ለምን ጣልቃ ይገባሉ?
  • የቦርድ ሰብሳቢ እኮ ነኝ፡፡
  • ከቦርድ አባላት ጋር ይወስናሉ እንጂ ለምን ጣልቃ ይገባሉ?
  • ማኔጅመንቱ ሲፈዝ ደስ ስለማይለኝ ነው፡፡
  • ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ማገዝ ሲገባዎ እርስዎ እኮ እጁን ነው የሚጠመዝዙት?
  • አንቺ ይኼ ፓርላማ ላይ ይነሳል ብለሽ ነው [ሥጋት ገባቸው]?
  • መልስ ብዬሃለሁ መልስ፡፡
  • ማኔጅመንቱ ሲልፈሰፈስ ምን ላድርግ ታዲያ?
  • በቃ አስፈጻሚ ስትባሉ ጉልበት ብቻ ነው የሚታያችሁ?
  • ጉልበት ከብልኃት ጋር ያዋጣል እኮ?
  • የእርስዎ ደግሞ በዛ፡፡
  • ምኑ ነው የበዛው?
  • የፈለጉትን እያዘዙ ያስፈጽማሉ፣ ኮሚሽንዎትንም ይቀረጥፋሉ፡፡
  • ማነ እኔ?
  • እኔ ነኝ ታዲያ?
  • አንቺ የእውነት አስመሰልሺው እኮ [ፈራ አሉ]?
  • እንዳትክደኝ ብቻ?
  • ምንድነው የምክድሽ?
  • ሪፖርቱን በጥንቃቄ ለሚያየው እኮ በርካታ ሚሊዮን ብሮች መሰወራቸው ግራ አይገባውም፡፡
  • አንቺም ጠረጠርሽኝ?
  • ከመጠርጠር በላይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • እኔንም የደበቅከኝ ብዙ ነገር አለ፡፡
  • ይኼ ሁሉ ሪፖርቱ ውስጥ አለ ነው የምትይኝ?
  • አንተ አላነበብከውም እንዴ?
  • አንብቤዋለሁ፡፡
  • በመስመሮቹ መካከል ያለውን ሐሳብ እንዴት መረዳት አቃተህ?
  • የሚወሳሰብ ነገር ደስ ስለማይለኝ ነው፡፡
  • እንግዲያው ተዘጋጅ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምኑ?
  • ለፓርላማ ጥያቄ ጊዜ ነዋ፡፡
  • ምን ይመጣል ብለሽ ነው?
  • አንተ ሰውዬ የት አገር ነው ያለኸው?
  • ምነው?
  • የሚባለውን አልሰማህም እንዴ?
  • ምን ተባለ?
  • ሪፖርቱ ችግር ካለበት አደጋ አለ፡፡
  • የምን አደጋ?
  • ከሚኒስትርነት መሰናበት እስከ መታሰር፡፡
  • ማን ነው ያለው?
  • ደግሞ ይኼ ማስፈራራትህን ተው፡፡
  • አንቺ ደግሞ አታናጂኝ፡፡
  • ኧረ የሚያስፈራሩና የሚያኮርፉ ሚኒስትሮች አሉ እየተባለ ነው፡፡
  • ይኼንን ነገር ማን ነው የሚያወራው?
  • በአደባባይ ሲነገር አልሰማህም እንዴ?
  • አሁንስ ደሜ ሊፈላ ነው፡፡
  • ይልቅ በረድ ብትል ይሻልሃል፡፡
  • እንዴት አድርጌ?
  • ፓርላማ ቀርበህ እቆናጠራለሁ ብትል ዋ!
  • በቃ ሳቅ በሳቅ እንድሆን አለማምጂኝ፡፡
  • ምን ላድርግ?
  • ኮርኩሪኝ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሥራ አጥነት ችግሮችን የመፍታት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም በዋና ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃና ቢሮዎች ላይ ያደረገውን ዕድሳት መርቀው በመክፈት ጉብኝት እያደረጉ ነው]

  እጅግ ውብ ዕድሳት ያደረጋችሁት! በእውነቱ በጣም ድንቅ ነው፡፡ አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በጣም ድንቅ ነው። ዕድሳቱን ያከናወነው ድርጅት ጥሩ ልምድ ያለው ይመስላል? ተቋራጩ ማን እንደሆነ አልነገርኩዎትም እንዴ? የትኛው ተቋራጭ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ በያዘው ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢጀመርም በስተመጨረሻ አጀንዳውን ስቶ ስለ መዋደድ እየተጨቃጨቀ...

  በዛሬው መደበኛው መድረካችን አጀንዳ የተለመደው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ይሆናል። ሌላ አጀንዳ የምታስይዙት አጀንዳ ከሌለ በቀር ማለቴ ነው። ክቡር ሚኒስትር... እሺ ...ቀጥል አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። መደበኛ አጀንዳው እንደተጠበቀ...