Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር ለሕግ የበላይነት ተገዢ መሆን ያስፈልጋል!

  ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሰብዓዊ ፍጡር በመሆናቸው ብቻ የሚጎናፀፉዋቸው ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ሕጎችም ሆነ በአገሮች ሕገ መንግሥቶች ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች ለሰው ልጆች የምግብ፣ የአየር፣ የውኃና የፀሐይ ብርሃን ያህል ያስፈልጓቸዋል፡፡ እነዚህ መብቶች ሲጣሱ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ፅኑ ሕመም ይገጥማቸዋል፡፡ ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በአመለካከትና በመሳሰሉት ልዩነት ሳይደረግባቸው የሚቋደሷቸው የተፈጥሮ በረከቶችም ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት አግኝተው በበርካታ አገሮች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ በእኛ አገር ደግሞ የሕገ መንግሥቱን አንድ ሦስተኛ ክፍል የያዙት እነዚህ መብቶች ናቸው፡፡ በሚገባ ሠፍረዋል፡፡ ተግባር ላይ ግን ለማዋል አልተቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ ስም ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ይብጠለጠላል፡፡ ዜጎች በነፃነት የመሰላቸውን አመለካከት ከመያዝና ከማሠራጨት ጀምሮ በበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይብከነከናሉ፡፡ ነገሩ ሁሉ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› ከመሆን አልዘለለም፡፡

  ኢትዮጵያ አገራችን ስመ ገናና ጥንታዊ ሥልጣኔ የነበራት፣ በታሪኳ አንድም ጊዜ የሰው አገር ወርራ የማታውቅ፣ ለወረራ የመጡባትን በጀግንነት አሳፍራ በመመለስ የምትታወቅ፣ ለመላው ዓለም ጥቁሮች መመኪያ የሆነውንና በነፃነት ፋና ወጊነት የሚወደሰውን በአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓደዋ ተራሮች አንፀባራቂ ድል የተቀዳጀች፣ ለእናት አገሩ ደረቱን ለጦር፣ እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ የሚፋለም ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ምድር ናት፡፡ ይህ ሕዝብ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ ልዩነት ሳይገድበው ተጋብቶና ተዋልዶ በመዋሀድ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን ያፀና የአንድነት ተምሳሌት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በየዘመናት የተነሱ ገዢዎች በአግባቡ አልያዙትም፡፡ በአግባቡ አልመሩትም፡፡ ሰብዓዊ ፍጡርነቱን እየዘነጉ ያልተገቡ ተግባራት ሲፈጽሙበት ኖረዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ለረሃብ፣ ለበሽታ፣ ለማይምነትና ለኋላ ቀርነት ተዳርጓል፡፡ አሁንም ድረስ ከድህነት ጋር ይታገላል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ለፖለቲካ ሥልጣን ሲባል በሚደረጉ ሽኩቻዎች ምክንያት ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ በሕግ ቢደነገጉም ማስፈጸም የተራራ ያህል ከብዷል፡፡ ከሕዝብ ይልቅ ሥልጣን በልጧል፡፡ ‹‹በድሮ በሬ ያረሰ የለም›› ተብሎ በሚተረትበት አገር በድሮ አስተሳሰብ መጓዝ ዕጣ ፈንታ ሆኗል፡፡

  ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ የመጡበት ዓላማ ደግሞ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር ለመምከር ነው፡፡ እሳቸው በሚደርሱበት ድምዳሜ መሠረት የሚቀርብ ሪፖርት ወደፊት በስፋት ይወጣል፡፡ እሳቸውም እዚህ በመጠኑ የተናገሩት አለ፡፡ የእሳቸው ጉዳይ እዚህ ላይ ገታ ይደረግና እስቲ አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡ እ.ኤ.ኤ. በ1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጌዎች ሲፀድቅ፣ የድርጅቱ መሥራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ አንዷ ፈራሚ ነበረች፡፡ በዚህም በአፍሪካ ግንባር ቀደም አገር ነበረች፡፡ ይህንን ጥሬ ሀቅ በእዝነ ህሊና ለሚያስብ ማንም ቅን ዜጋ የኢትዮጵያ ጉዳይ በጣም ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽኖች ፈራሚ መሆኗም ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን በመመሥረት ለአፍሪካውያን የጋራ መሰብሰቢያ የሆነች አገር ናት፡፡ ግን ይህ ሁሉ አኩሪ ገጸ ታሪኳ ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ችግሮች ጋር ተለውሶ ሲርመጠመጥ ውስጥን ያማል፡፡ ቁጭት ውስጥ ይከታል፡፡

  ያለንበት ዘመን በረቀቁ ምጡቅ ሐሳቦች አማካይነት እጀግ ዕፁብ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሥራ ላይ ሲያውል እያየን ነው፡፡ ተጠቃሚም እየሆንን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን አጀብ የሚያሰኝ መረጃ ተሰምቷል፡፡ በአዕምሮአችን የምናስበውን ወዲያው ወደ ጽሑፍ የሚቀይር ቴክኖሎጂ፣ በፌስቡክ ተመራማሪዎች አማካይነት ለሰው ልጆች በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ሰዎችን ከሰዎች የማይለይ፣ ለሁሉም ተደራሽ የሚሆንና ልዩ ደስታ የሚፈጥር ግኝት በዓለም ዙሪያ በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ እኛ ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ከዓለም ታላላቅ አገሮች ተርታ ቆመን ለሰው ልጆች ነፃነት ድምፃችንን በማሰማት፣ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን እንዳልፈረምንና አፍሪካውያን ወገኖቻችን እንዳልቀኑብን፣ ዛሬ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና ድህነትን በመዋጋት ዘመቻ ስም ስንፍገመገም ግርም ይላል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በተደጋጋሚ ያገኘናቸውን መልካም አጋጣሚዎች መጠቀም እያቃተን ዛሬም ዴሞክራሲን ለማስፈን በራሳችን ላይ እንቅፋት ሆነናል፡፡ በስመ ታዳጊ አገርነት ከዘመናት ችግሮች መላቀቅ አቅቶን የዓለም መሳለቂያ ነን፡፡ ይህም ያንገበግባል፡፡ በሐሳብ መዋጮ አገር መገንባት እያቃተን በሐሳብ ነፃነት ላይ መሰናክል እንሆናለን፡፡ ሐሳቦች እንዲገደቡ እንቅልፍ አጥተን እናድራለን፡፡

  ለዚህ ችግር መንግሥት ዋነኛው ተጠያቂ ነው፡፡ በተለይ ላለፉት 26 ዓመታት አገሪቱን እየመራ ያለው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ይጠየቃል፡፡ እሱ የሚመራው መንግሥት ሌላው ቀርቶ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩትን መሠረታዊ የሚባሉ መብቶች ማስከበር አልቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ ነው፡፡ ለአመፁ መነሻ ምክንያት ምንም ይሁን ምን በዋነኛነት የሚገለጸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መብዛት ነው፡፡ ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ የሚያዳምጥና ምላሽ የሚሰጥ መጥፋቱ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ላይ መዛባት መፈጠሩ፣ በሙስና አገር የሚዘርፉ ጥቂቶች መፏለል፣ የምርጫ ሥርዓቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት የሕዝብ ኩርፊያ መፈጠሩ፣ በአጠቃላይ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚፈይዱ ተግባራት ወደ ጎን ተብለው የአንድ ጎራ መግነን ሕዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ ይህ ቁጣ ደግሞ መስመሩን ስቶ ለበርካታ ወገኖች ሕልፈት፣ አካል ጉድለት፣ እንግልትና ለከፍተኛ የአገር ሀብት ወድመት መንስዔ ሆኗል፡፡ በዚህ ዘመን ይህ ተገቢ ነበር? በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ሲገባ ሞትና ውድመትን ምን አመጣው?

  አሁንም የአገርና የሕዝብ ጉዳይን ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ አገር ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት የምታገኘው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለም፡፡ የሕዝብ ፍላጎት በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲፈጸም ነው፡፡ የሕዝብ ይሁንታ ያላገኘና የዕለት ተዕለት ሕይወቱን የማይቀይር ብልሹ አሠራር ያመጣው ነገር ቢኖር ውድመት ብቻ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር እየተጣሉ ማስተዳደር አይቻልም፡፡ ይልቁንም ለሕግ የበላይነት በመገዛትና ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር፣ ለአገሪቱ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ሲባል መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠቅማል፡፡ ይህ ሒደት ዕውን ይሆን ዘንድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወዘተ የሚሳተፉበት ትልቅ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ እንደነበረው ሁሉ፣ በዚህ ዘመን ደግሞ በገዛ አገራቸው ጉዳይ ላይ በአንድነት መምከር ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት መግባባት ላይ መድረስ ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ባለበት ሁኔታ ለመቀጠል መሞከር ፋይዳ የለውም፡፡  እየተለወጠች ካለች ዓለም ጋር መለወጥ አለመቻል ለአገር ህልውና አደጋ አለው፡፡ በተለይ ሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ ውስጥ ለውጥ ማሰብ ተላላነት ነው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ቅድሚያ ራሳቸውን ለሕግ ያስገዙ፡፡ ከዚያ በሰከነ መንገድ ለመነጋገር ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ በዚህ መንፈስ መመራት ይገባል፡፡ በመሆኑም ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር ለሕግ የበላይነት ተገዢ መሆን ያስፈልጋል!        

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...