Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊአራጣ በማበደር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የኬኬ ባለቤት የመከላከያ ምስክር ማሰማት ጀመሩ

  አራጣ በማበደር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የኬኬ ባለቤት የመከላከያ ምስክር ማሰማት ጀመሩ

  ቀን:

  በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 አራጣ በማበደር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡

  አቶ ከተማ እንዲከላከሉ ውሳኔ የተሰጣቸው አራጣ የማበደር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ዮሐንስ ጌታነህ (በሕይወት የሉም) የተባሉ ነጋዴን ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2001 ዓ.ም.  ድረስ ባሉ ጊዜያት፣ በሕግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ በተለያዩ ቀናት በተጻፉ ሦስት ቼኮች 111,705,397 ብር አራጣ አስከፍለዋል ተብለው ነው፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ሊያስመሰክር በመቻሉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እንዲከላከሉ በሰጠው ውሳኔ ምክንያት አቶ ከተማ አራት የመከላከያ ምስክሮችን ቆጥረዋል፡፡

  ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ ከተማ ያቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች እንዳይሰሙ ተቃውሞ አቅርቦ ነበር፡፡ የመቃወሚያ ምክንያቱ ደግሞ አቶ ከተማ ያቀረቡት የሰነድ ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ ሊቀርብ የማይገባ መሆኑንና ለእሱም የደረሰው ዘግይቶ በመሆኑ አለመዘጋጀቱን በመግለጽ ነው፡፡ ያልተመሳከሩ ማስረጃዎች መቅረባቸውንና በፍርድ ቤቱ መሥሪያ ቋንቋ ያልተተረጎሙ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ የማስረጃ ሰነዶች መቅረባቸውን በማከል መቃወሚያውን አጠናክሯል፡፡ በመቀጠልም ቀደም ብሎ ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት ያቀረባቸውን ግለሰብ ሰብዓዊ መብት የሚነካ ቃላትም መጠቀማቸውን በመጥቀስ አቶ ከተማ ያቀረቡትን የሰነድ ማስረጃ ተቃውሟል፡፡

  የአቶ ከተማ ጠበቆች ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ተቃውሞ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ የምስክሬን ሰብዓዊ መብት ይነካል›› ያሉት በየሰነድ ማስረጃነት ላይ የተጠቀሰው ቃል ‹‹መጎትጎት›› የሚል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ‹‹ማሳሰብ መገፋፋት›› ከሚል ውጪ ትርጉም እንደሌለውና አስፈላጊ ከሆነ መዝገበ ቃላት በማቅረብ ለፍርድ ቤቱ ማሳየት እንደሚችሉ በመናገር የዓቃቤ ሕግ ተቃውሞን አጣጥለውታል፡፡ በሌላ በኩል ዓቃቤ ሕግ አለመዘጋጀቱን አስመልክቶ ላቀረበው ተቃውሞ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የመከላከያ ምስክር የምናቀርበው እኛ ነን፡፡ እሱ ምስክሮቹን ማናገር አይችልም፡፡ ከምናቀርባቸው ጥያቄዎች ተነስቶ መስቀለኛ ጥያቄ ከማቅረብ ባለፈ የምን መዘጋጀት ነው የሚያስፈልገው?›› በማለት ጥያቄ በማቅረብ የተቃውሞ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ካቀረቡት ሰነድ ጋር በተገናኘ ተቃውሞ ማንሳቱን ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ አስታውሰው፣ ካቀረቧቸው አራት የመከላከያ ምስክሮች ውስጥ ሁለቱ ስለሰነድ የሚመሰክሩት ነገር እንደሌለ በማስረዳት እንዲመሰክሩላቸው አመልክተዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰነድ ላይ የማይመሰክሩት የመከላከያ ምስክሮች ቢመሰክሩ የሚያስከትል ችግር ካለ እንዲያስረዳ ዓቃቤ ሕግን ሲጠይቀው ተቃውሞ እንደሌለው በመግለጹ፣ ጠበቆቹ የመከላከያ ምስክሮች ስለሚመሰክሩላቸው ነገር ጭብጥ እንዲያሲዙ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

  የመከላከያ ምስክሮቹ የሚመሰክሩት አቶ ከተማ የተከሰሱበት አራጣ ማበደር ወንጀል አራጣ እንዳልሆነ የሚያስረዱላቸው መሆኑን በጭብጥነት አስያዙ፡፡

  የአቶ ከተማ የመጀመሪያ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት የተከሳሽና አራጣ ተበድረዋል የተባሉት አቶ ዮሐንስ ጌታነህ የቅርብ ጓደኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ያስመዘገቡት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ተስፋዬ ቁንቢ ይባላሉ፡፡ የአቶ ከተማ ጠበቆች ለመከላከያ ምስክሩ በዋናነት ጥያቄ ያቀረቡላቸው ስለአቶ ከተማ ክስ ስለማወቃቸውና አጠቃላይ ሁኔታ እንዲያስረዱ ነው፡፡

  አቶ ከተማ ከአቶ ዮሐንስ ጌታነህ ጋር በተያያዘ እንደተከሰሱ መሰማታቸውን ምስክሩ ገልጸዋል፡፡ ክሱ ከመመሥረቱ በፊት ግን እሳቸው ለሁለቱም ጓደኛ ከመሆናቸው አንፃር ሽምግልና ተቀምጠው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ሽምግልና የተቀመጡት በ2001 ዓ.ም. ሟች ዮሐንስ ደውለውላቸው ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንዲገናኙ ከነገሯቸው በኋላ ሲገናኙ፣ በአቶ ዮሐንስና በአቶ ከተማ መካከል መቀያየም እንደተፈጠረ እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ እንደነገሯቸው የገንዘብ መጠኑን ባይገልጹላቸውም ከአቶ ከተማ ገንዘብ ተበድረው ነበር፡፡ የተበደሩትን ገንዘብ አቶ ከተማ እንዲመልሱላቸው ሲጠይቋቸው ከባንክ ገንዘብ ተበድረው ለአቶ ከተማ ሳይከፍሏቸው ለሌላ ሰው በመክፈላቸው አቶ ከተማ ቅር እንደተሰኙ አስረድተዋቸው፣ የሚሸጥ ዕቃ ስላላቸው ሸጠው እስከሚከፍሏቸው ድረስ እንዲታገሷችው ሽምግልና እንደላኳቸው ምስክሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

  ምስክሩ አቶ ከተማን ሲጠይቋቸው ብድር መስጠታቸውን አረጋግጠው፣ ነገር ግን አቶ ዮሐንስ ሁለት ወርና ሦስት ወር እያሉ ሳይከፍሏቸው በመቅረታቸው ቅር መሰኘታቸውን እንደነገሯቸውና ይህንኑ ቃል ለአቶ ዮሐንስ መልሰው እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ በሌላ ጊዜ እሳቸው፣ አቶ አጥናፉና ሌላ አንድ ሰው ሆነው ሒልተን ሆቴል ተገናኝተው ባደረጉት ሽምግልና አቶ ዮሐንስና አቶ ከተማ ችግሮቻቸውን ከተነጋገሩ በኋላ፣ አቶ ዮሐንስ በመጋዘን ያላቸውን ዕቃ በማስገመት በባንክ አስይዘው ሊከፍሉ ከተስማሙ በኋላ ተሳስመውና ተግባብተው በተለያዩ በማግሥቱ አቶ ዮሐንስ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን እንደሰሙ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ለምስክሩ እነደነገሯቸው የነበራቸውን ገንዘብ መክፈል ይችሉ የነበረ ቢሆንም፣ ለሌላ ሰው መስጠታቸውን ሲነግሯቸው ለማን እንደከፈሉ ነግረዋቸው ከሆነ ጠበቆች ጠይቀዋቸው አቶ ዮሐንስ የተበደሩት አራጣ መሆኑንና ከበደ ተሠራ ከሚባሉ አበዳሪ እንደተበደሩ እንደነገሯቸው ተናግረዋል፡፡ ቼክ ሰጥተዋቸው ስለነበር ሊያስመቱባቸው እንደሚችሉ ስለነገሯቸው ለአቶ ከተማ ሊሰጡ የነበረውን አሥር ሚሊዮን ብር ለአቶ ከተማ መስጠታቸውን ነግረዋቸው፣ አቶ ከተማ እንዲታገሷቸው እንዲነግሩላቸው ሽምግልና እንደላኳቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ስለሥራ ሲነግሯቸው ሥራ የምንሠራው እንደ አቶ ከበደ ተሠራ ዓይነት አራጣ አበዳሪዎች በመበደር መሆኑንም እንደነገሯቸው ምስክሩ አክለዋል፡፡ ሌላ የሚያውቁት ነገር እንዳለ እንዲያስረዱ ጠበቆች ሲጠይቋቸው አቶ ዮሐንስ የነገሯቸው የአቶ ከተማን ምርት እንደሚያከፋፍሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  ጠበቆች ጥያቄያቸውን እንዳበቁ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበላቸው ‹‹በሽምግልና ወቅት እነማን ነበሩ?›› የሚል መስቀለኛ ጥያቄ እሳቸው የአቶ ዮሐንስ ወንድም አቶ አጥናፉ ጌታነህና ሌሎች ሰዎች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ እንዴት እንደ ሞቱ ስለማየታቸው ተጠይቀው ሁለቱን ባስማሙ በማግሥቱ እሳቸው ወደ አሜሪካ በረራ ስለነበራቸው በዝግጅት ላይ እያሉ አቶ ዮሐንስ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ከመስማታቸው ውጪ ያዩት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ የማይቀሩበትና እሳቸውም ቢቀሩ ከሕይወት ጋር የተያያዘ ነገር ሊደርስባቸው ስለሚችል እያዘኑ መሄዳቸውንና ስለአቶ ዮሐንስ አሟሟት ከስድስት ወራት በኋላ እንደሰሙ ገልጸዋል፡፡ የማጣሪያ ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሲያቀርብላቸው ከላይ እንደመሰከሩት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ሁለተኛ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት ደግሞ ከአቶ ከተማ ጋር ከ40 ዓመታት በላይ በአቶ ከተማ አማካይነት ካወቋቸው ጊዜ አንስቶ ከአቶ ዮሐንስ ጌታነህ ጋር ከ30 ዓመታት በላይ የቅርብ ጓደኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት፣ አቶ ሲራክ ትዕዛዙ የሚባሉ ምስክር ናቸው፡፡

  አቶ ከተማ በምን ምክንያት እንደተከሰሱ ማወቅ አለማወቃቸውን የተጠየቁት ምስክሩ፣ ‹‹አውቃለሁ፡፡ ከአራጣ ጋር በተያያዘ መሆኑን ሰምቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ለማን አራጣ እንዳበደሩ ሲጠየቁ ስለአራጣ ብድሩ የሚያውቁት እንደሌለ ገልጸው፣ ከዮሐንስ ጌታነህ ጋር በተያያዘ መሆኑን እንደሰሙ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ መቼ እንደ ሞቱ ሲጠየቁ ከስምንት ዓመታት በፊት 2001 ዓ.ም. እንደሚመስላቸው በግምት ተናግረዋል፡፡ አቶ ከተማና አቶ ዮሐንስ ስላላቸው ግንኙነት ሲጠየቁ ‹‹በጣም ጓደኛሞች መሆናቸውን አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ሁለቱ ስለመኮራረፋቸው ተጠይቀው እንዳስረዱት፣ አቶ ከተማ ወንድም ሞቷቸው ነበር፡፡ በወቅቱ እንደ አቶ ዮሐንስ የሚቀርባቸው ጓደኛ እንደሌለ ስለማውቅ ‹‹አቶ ዮሐንስ የት ሄደ?›› የሚል ጥያቄ ጭሮብኝ ነበር፡፡ በለቅሶው ላይ ቢገኝም እንዳላቸው መቀራረብ ሳይሆን ራቅ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ነገሩ ግራ ስለገባኝ አቶ ዮሐንስን ወደ ውጭ ይዤው ወጣሁና ምን እንደሆነ ስጠይቀው ‹‹ብድር ተበድሬ ቃሌን ባለመጠበቄ ከተማ ቅር ብሎታል፤›› ብለው እንዳጫወቷቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ብድሩ በወቅቱ አለመክፈላቸው እንደፀፀተው እንደነገሯቸው አክለዋል፡፡ አሥር ሚሊዮን ብር ከባንክ ወስደው ለአቶ ከተማ ባለመመለሳቸው መሆኑንም ምስክሩ ከአቶ ዮሐንስ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብለው አቶ ዮሐንስ አቶ ከበደ ተሠራ ከሚባሉ ነጋዴ ተበድረው ስለነበር ከባንክ ያገኙትን አሥር ሚሊዮን ብር ለሳቸው መክፈላቸውንም እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለአቶ ከበደ ተሠራ ቼክ ሰጥተው ስለነበር መሆኑንም እንደነገሯቸው ገልጸዋል፡፡

  ለአቶ ከተማ እንዲያስረዷቸው አቶ ዮሐንስን መምከራቸውን ምስክሩ ገልጸው አቶ ዮሐንስ ግን፣ ‹‹ምን ብዬ? እኔ እንዴት አናግረዋለሁ?›› ሲሏቸው እሳቸው (ምስክሩ) ለአቶ ከተማ እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ከተማ፣ ‹‹ይህ ሰው አራጣ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው?›› ካሉ በኋላ ሊከፍሏቸው እንደሚገባ እንደ ነገሯቸውና ያንኑ ለአቶ ዮሐንስ መልሰው መንገራቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ አራጣ መበደራቸውን እንደነገሯቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ በመስቀልኛ ጥያቄ ምስክሩ አቶ ዮሐንስ የተበደሩት ብድር አራጣ ስለመሆኑ ማረጋገጣቸውን ሲጠይቃቸው ‹‹አረጋግጫለሁ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ራሳቸው እንደ ነገሯቸው አክለዋል፡፡ አቶ ከተማ አራጣ ስለማበደራቸውስ በማለት ዓቃቤ ሕግ ላነሳላቸው ጥያቄ ስለአራጣ የሰሙት ክስ ከተመሠረተ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ አቅርቦላቸው ምስክሩ ከላይ እንዳስረዱት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰነዱ ላይ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...