Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ማኅበር እንዳያመርትና እንዳያሠራጭ ታገደ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ማኅበሩ የደረጃዎችን ምልክት እንዳይጠቀም ዕግድ ተጥሎበታል

  ‹‹እኛ የሰማነውም ሆነ የደረሰን ነገር የለም››

  አቶ ሀብቱ ሐጎስ፣ የአፋር ጨው ማምረቻ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ

       ከካባዳ ጨው አምራቾች ማኅበር ጥሬ ጨው በመረከብ፣ በማቀነባበርና አስፈላጊውን መሥፈርት በማሟላት ለምግብ የሚውል ጨው ለማቅረብ የተቋቋመው አፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ምንም ዓይነት ምርት ከማምረትም ሆነ ወደ ገበያ ከማሠራጨት መታገዱ ታወቀ፡፡

  በማኅበሩ ላይ የዕግድ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማኅበሩ የሚያመርተው ጨው አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጨው ደረጃ መሥፈርትን ማሟላት ባለመቻሉ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

  ባለሥልጣኑ ሥራው በምግብና መጠጥ ማምረቻ ድርጅቶች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለኅብረተሰቡ የሚቀርብ ምርት ደኅንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጾ፣ በዚሁ መሠረት ማኅበሩ የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ባለሙያዎቹን ወደ ማምረቻው ሥፍራ መላኩን አስታውሷል፡፡ የተላከው የባለሙያ ቡድን አስፈላጊውን የቅድመ ናሙና ምርመራ በማድረግ በማኅበሩ ላይ የተገኙ ክፍተቶች መኖራቸውን ከገለጸ በኋላ፣ ማኅበሩ ማስተካከያ ለማድረግ በመስማማት ጊዜያዊ የብቃት ማረጋገጫ ተሰጥቶት እንደነበር በዕግድ ደብዳቤው ላይ አስታውሷል፡፡

  ባለሥልጣኑ በሰጠው የማስተካከያ ቀነ ገደብ መሠረት በድጋሚ የቁጥጥር ሥራ ያደረገ ቢሆንም፣ ማኅበሩ እንዲያስተካክል የታዘዘውን ወይም በተስማማው ክፍተት ላይ ምንም ነገር አለመሥራቱንም እንደተገነዘበም ጠቁሟል፡፡ ሌላው ባለሥልጣኑ በዕግድ ደብዳቤው ላይ የጠቆመው፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በላከለት የላብራቶሪ ፍተሻ ማኅበሩ የሚያመርተው የጨው ምርት አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጨው ደረጃ መሥፈርትን እንደማያሟላ ነው፡፡ ድርጅቱ ለማኅበሩ ሰጥቶት የነበረውን በጨው ምርቱ ላይ እንዲለጥፍ ፈቅዶለት የነበረውን በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን አስገዳጅ ደረጃ እንደማያሟላ በመግለጽ የተሰጠውን ምልክት የመጠቀም ፈቃድ እንዲመልስ፣ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ማሳወቁንም ገልጿል፡፡ በመሆኑም የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከመጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ችግሮቹን እስከሚያተካክል ድረስ፣ ምንም ዓይነት ምርት ከማምረትም ሆነ ወደ ገበያ ከማሠራጨት መታገዱን አስታውቋል፡፡

  የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ አቶ ሰኢድ ያሲን የተባሉ ባለሀብትና የካባዳ ጨው አምራቾች ማኅበር በጋራ ያቋቋሙት ድርጅት ቢኖርም፣ ለካባዳ ጨው አምራቾች በቂ ጥሬ ጨው ምርት እያቀረቡ ቢሆንም ተገቢው ክፍያ በወቅቱ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ማኅበሩን በማውገዝ ለአፋር ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር በፊርማ የተደገፈ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

  ከባለሀብቱ አቶ ሰኢድ ጋር የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት መስማማታቸውን ያስታወሱት አምራቾቹ፣ አቶ ሰኢድ የአምራቾች ወኪል እንዲሆኑ እንጂ፣ ባለሀብቱ ገና በሒደት ላይ የሚገኘው ፋብሪካ ሳይመሠረት የካባዳን ሥራ በሙሉ እንዲረከቡ ባለመሆኑ የሚቃወሙ መሆኑን ለፕሬዚዳንቱ ባቀረቡት አቤቱታ አሳውቀዋል፡፡ በመሆኑም የአምራቾች ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ገልጸው፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የማኅበሩን ህልውና ከአደጋ እንዲታደጉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

  በባለሀብቱ አቶ ሰኢድ 51 በመቶና በካባዳ ጨው አምራቾ 49 በመቶ ለተቋቋመው አፋር የጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለ ቢሆንም፣ እስካሁን አምራቾች የሚቀበለውን ጥሬ የጨው ምርት የሚያቀነባብረውና አዮዲን የሚረጨው በ1998 ዓ.ም. 83 በመቶ የመንግሥት ልማት ድርጅት በሆነው ማዕድን ኮርፖሬሽንና 17 በመቶ ደግሞ የኤፈርት ድርጅት የሆነው ኢዛና በጋራ ያቋቋሙት የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ማሽን በኮሚሽን በመከራየት መሆኑ ተገልጿል፡፡

  የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ ሐጎስን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ባለሥልጣኑ ምርት እንዳይመረትም ሆነ እንዳይሠራጭ ስለማገዱ የሰሙት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ግን የብሔራዊ ደረጃ ምልክት እንዳይጠቀሙ በማለት የጻፈው ደብዳቤ እንደደረሳቸውና ምላሽ መስጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በአንድ ምርመራ ወይም በአንድ ጊዜ ናሙና ውጤት ላይ ይደርሳል የሚል እምነት ስለሌላቸው፣ ተከታታይ ናሙና በመውሰድ እንዲያረጋግጡ በደብዳቤ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ ማኅበራቸው በሙሉ አቅም የሚሠራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠቀምበት የሚችለውን ያህል የጨው ምርት ማቅረብ የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

  መቀመጫው ካናዳ የሆነ ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የሚባልና አዮዲንን ጨምሮ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ለተጠቃዎች በተለያዩ መንገዶች እንዲደርሱ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ሲሆን፣ ከአፍዴራና ከተለያዩ ሥፍራዎች እየተመረተ ለሕዝብ ስለሚደርሰው የጨው ምርት ምን መሆን እንዳለበት እየመከረ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ አብነት ተክሌ፣ ‹‹ጨው ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አዮዲን በጥብጦ በአካፋና በእጅ በመርጨት የሚበቃ አይደለም፡፡ አዮዲን በባህሪው ይተናል፡፡ በመሆኑም ጨው በደንብ ታጥቦ፣ ደርቆና ተፈጭቶ በዘመናዊ ፋብሪካ ከባለ አሥር እስከ 50 ኪሎ ግራም በአዮዲን ከተረጨ በኋላ ላሚኔትድ በሆነ ከረጢት መታሸግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችል ሰመራ ከተማ ዘመናዊ የጨው ማምረቻ ፋብሪካ መገንባቱን የሚያውቁ ቢሆንም፣ ሕዝቡን ለማዳረስ እየሠራ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአፋር ጨው ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት አዲስ የጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ የግል ማኅበር ከአቶ ያሲን ሰኢድና ከካባዳ ጨው አምራቾች ጋር ለመመሥረት የመሠረት ድንጋይ መጣሉ ደስ የሚያሰኝ ቢሆንም፣ አሁን ግን ባለድርሻዎቹ ቅሬታ እንዳደረባቸው በቅርቡ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ማሳወቀቻውን አስረድተዋል፡፡

  ምንም ይሁን ምንም የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥታት ትኩረት በመስጠት ንፅህናውን የጠበቀ ጨው እንዲመረት በማድረግ፣ ለሕዝቡ ጤንነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አቶ ያሲን ሰኢድን ለማግኝት ሪፖርተር በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች