የኳታር ሼክ አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠረችው መግባባትና መተማመን የላቀና ስትራቴጂካዊ እንደሆነ ተናገሩ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2013 ሥልጣን የያዙት የኳታር አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ የአፍሪካን ምድር ሲረግጡ የመጀመርያቸው ሲሆን፣ ለአንድ ቀን በቆየ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮችና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክር የቴክኒክ ኮሚቴ ወደ ሚኒስቴር ደረጃ ከፍ እንዲል ወስነዋል፡፡ እንዲሁም በሁለቱም የአገር መሪዎች ደረጃ መደበኛ ምክክር እንዲደረግበት መስማማታቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ከመሪዎቹ ውይይት በኋላ አቶ ዓለም በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኳታር መንግሥትና ባለሀብቶች በተለይ በነዳጅ፣ በማዕድን ፍለጋና በታዳሽ ኃይል በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለኳታር አሚር ያቀረቡላቸውን ጥያቄ አሚሩ በሙሉ ልብ ተቀብለውታል፡፡
እንዲሁም ደግሞ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ በተለይ የእስልምና ታሪካዊ ማዕከላትን እንዲያበለፅጉ፣ በቱሪዝምና በሆቴል ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥያቄ እንደቀረበላቸው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ 24 ብሔራዊ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን፣ የኳታር መንግሥት ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ፓርኮችን ለማልማት ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ አሚሩ መናገራቸውን አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡
አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጉብኝቱ በተለየ ዕይታ መታየት ያለበት ነው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 20 ዓመታት ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሚባል ደረጃ ደርሷል፡፡
ኳታር በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካና ደኅንነት ከፍ ያለ ፍላጎትና ተሳትፎ ያላት ሲሆን፣ ከኤርትራ ጋር በነበራት የጠበቀ ግንኙነት ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2008 ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዋና አማካሪያቸው አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ዶሃ (የኳታር ዋና ከተማ) በመሄድ የዲፕሎማሲ ሥራ መከናወናቸው ይነገራል፡፡ ይህንን የዲፕሎማሲ ሥራ ተከትሎ ከ11 በላይ ስምምነቶች በሁለቱ አገሮች መፈረማቸው አይዘነጋም፡፡
የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ለአጭር ጊዜ እክል አጋጥሞት የነበረ መሆኑን ያስታወሱ አቶ መለስ ዓለም፣ በአሁኑ ወቅት ግንኙነታቸው በመተማመንና በመግባባት የላቀ ደረጃ መድረሱን አሚሩ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተፈረመ አዲስ ስምምነት ባይኖርም፣ ሁለቱ መሪዎች የአገሮቹ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ እንዲሆን በመወሰናቸውና ጉብኝቱ የተለየ ትርጉም እንደነበረው አቶ መለስ ዓለም አክለዋል፡፡ በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በጋራ ተቀናጅተው ለመሥራት መነጋገራቸው ታውቋል፡፡
በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ኳታር ኤርትራ ከሱዳንና ከጂቡቲ ጋር ዕርቅ እንድትፈጥር ጥረት ያደረገች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችው ግንኙነት ሙቀት በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የማስታረቅ ፍላጎት እንዳላት የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡