Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተት አገሪቱ ያልተጠበቁ ወጪዎች እያወጣች ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በተለያዩ ቦታዎች የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተወሰነላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው፣ አገሪቷን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማስወጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡

  በተለይ በአማራ ክልል እየተነገቡ ያሉት ርብ፣ መገጭና ሰርባ፣ በአፋር ክልል ከሰምና ተንዳሆ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ድንበር የሚገኘው ጊዳቦ መስኖ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ባለባቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ጉዳታቸው እያመዘነ ነው፡፡

  የተንዳሆና የከሰም ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የተጀመሩት በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ እነዚህን የግድብ ፕሮጀክቶች በ1.6 ቢሊዮን ብር ወጪ በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ሥራው ተጀምሮ ነበር፡፡ ዲዛይን፣ ቁጥጥርና ግንባታው በቀጥታ ለቀድሞዎቹ የመንግሥት የውኃ ሥራዎች ቁጥጥርና ሱፐርቪዥን ኢንተርፕራይዝ (የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን) እና ለውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ (ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን) ያለጨረታ ተሰጥቷል፡፡

  ነገር ግን እነዚህ ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመት ይጠናቀቃሉ ቢባልም አሥር ዓመታት በልተዋል፡፡ ወጪያቸውም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡

  የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነገደ አባተ (ዶ/ር)፣ ፕሮጀክቶቹ እጅግ መዘግየታቸውንና ከተያዘላቸው በጀት ውጪ እንዳስወጡ አምነዋል፡፡

  ‹‹ይህ ሊሆን የቻለው ፕሮጀክቶቹ ገና ከጅምሩ ችግር ስለነበረባቸው ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ሁለቱ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ የተፈለገው በአንድ ጊዜ ጥናታቸው፣ ዲዛይናቸውና ግንባታቸው እንዲካሄድ ነው፡፡ ለግንባታው የተመደበው 1.6 ቢሊዮን ብር ደግሞ በወጪ መጋራት ሥሌት ማለትም ይህ ገንዘብ የሚመለሰው ግድቡ አልቆ ውኃውን ለስኳር ፕሮጀክቶች በማቅረብ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ይህ ትክክለኛ አካሄድ አልነበረም፡፡ ወደ ሥራ ሲገባ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ግንባታውንም ለብቻ ማካሄድ ስላልተቻለ በርካታ የመንግሥትና የግል ኩባንያዎች እንዲገቡበት ተደርጓል፡፡ በዚህ ሒደት የውጭ ምንዛሪ፣ የነዳጅ ዋጋና የግንባታዎች ወጪ ጨምሯል፤›› ሲሉ ፕሮጀክቶቹ የዘገዩበትንና ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጡ የቻሉበትን ምክንያቶች ተናግረዋል፡፡

  አሳዛኙ ነገር ግን የተንዳሆ ግድብ 60 ሺሕ ሔክታር መሬት ማልማት የሚያስችል ሆኖ ቢገነባም፣ ሊጠናቀቅ የቻለው ግን ለ30 ሺሕ ሔክታር መሬት የተዘጋጀ የመስኖ መሬት ብቻ ነው፡፡ ‹‹በመሬት ዝግጅት ወቅት ቀደም ብሎ ያልታዩ ማኅበራዊ ችግሮች በመፈጠራቸው፣ ሁለተኛውን ዙር 30 ሺሕ ሔክታር ማልማት እንዲቆም ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

  በአማራ ክልል በተለይ የጣና ሐይቅን ውኃ ይዘት የተረጋጋ እንዲሆን በማድረግ የመስኖ ሥራዎችን ማካሄድ ያስችላሉ ተብለው የተጀመሩት ርብ፣ ሰርባና መገጭ መስኖ ፕሮጀክቶች ተመሳሳይ ችግር ተጋርጦባቸዋል፡፡  

  እነዚህ ፕሮጀክቶች በ1999 ዓ.ም. የተጀመሩ ቢሆንም፣ ከአሥር ዓመት በኃላም ቢሆን አገልግሎት መስጠት አልቻሉም፡፡ ርብ የመስኖ ፕሮጀክት ግድቡ ብቻ ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል፡፡ ነገር ግን ለመስኖ የሚሆኑት ካናሎች ግንባታ ገና 45 በመቶ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ አገልግሎቱ አሁንም መቼ እንደሚጀምር አልታወቀም፡፡

  በተጨማሪም 36 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከአሥር ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ሊያለማ የሚችለው የምዕራፍ ሁለት ካናል ግንባታ ፕሮጀክት ገና አልተጀመረም፡፡

  የመገጭ መስኖ ግድብ ግንባታ ገና 46 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ሰርባም እንዲሁ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው በጀት ውጪ 6.4 ቢሊዮን ብር ወጪ ጠይቀዋል፡፡

  ሌላኛው ፕሮጀክት ጊዳቦ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ግድቡ ሲጀመር ሰባት ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲያለማ ነበር፡፡ በኋላ ፕሮጀክቱ እንዲያድግና አሥር ሺሕ ሔክታር እንዲያለማ ተወስኗል፡፡

  ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፣ በውሳኔው መሠረት የመጀመርያው ግድብ የተቀየረ ሲሆን፣ ዲዛይኑ ብቻ ሁለት ዓመት ዘግይቷል፡፡ በኮንስትራክሽን ሒደቱም እንዲሁ ግንባታው አንድ ዓመት ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ በዋጋ በኩል እንዲሁ ቀድሞ ከተያዘው በጀት በተጨማሪ የነዳጅ፣ የማሽንና የዶላር ምንዛሪ በመጨመሩ ተጨማሪ ወጪ መጠየቁን ገልጸዋል፡፡

  በአጠቃላይ በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው፣ አገሪቱን ከፍተኛ ወጪ እያስወጡ መሆኑን ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡

  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደመነ ዳሮታ፣ ‹‹የአዋጭነት ዲዛይን አልቆ ወደ ግንባታ እንግባ ካልን ድህነትን ማራዘም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በፋይናንስና በቴክኒክ ክፍተት ተፈጥሮ መጓተት አጋጥሟል፤›› ያሉት አቶ ዳመነ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ግን ከፕሮጀክቶች ብዙ ተምረናል፡፡ እነዚህም ችግሮችም እየተፈቱ ነው፤›› ሲሉ መሻሻሎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡  

  ፕሮጀክቶቹ በሒደት ብዙ ልምድና ትምህርት የተገኘባቸው በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ በሚጀመሩ ፕሮጀክቶች ይህ ስህተት እንደማይደገም ትምህርት እንደተወሰደ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡    

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች