Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ኢትዮጵያ እስካሁን የሚመጥናትን ፖለቲካ አላገኘችም››

  አቶ ገብሩ አሥራት፣ አንጋፋ ፖለቲከኛ

  ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ አካጂጃለሁ ባለና ከሁለት ዓመት በፊት ለተነሳ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ጀምሬአለሁ ባለ ማግሥት አዳዲስ የፖለቲካ ክስተቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል በተነሳ ግጭት በአሰቃቂ መንገድ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካቶች ተፈናቅለዋል፡፡ በርካታ ንብረት ወድሟል፡፡ በዚህ አሳዛኝ ክስተት ሳያበቃ በተለይ በኦሮሚያ ከዚህ ቀደም እምብዛም ግጭት በማይታባቸው አካባቢዎች ጭምር ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ተቃውሞ ተስተውሏል፡፡ በአንፃሩ የፌዴራል መንግሥት ዘገምተኛ፣ ክልሎች ደግሞ ልቆ ለመውጣት የመንቀሳቀስ አዝማሚያም እያሳዩ ነው፡፡ የክልሎች ልቆ የመውጣት እንቅስቃሴ ከሚያዙት የፀጥታ ኃይል አንፃር አሳሳቢ እየሆነ ባለበት ወቅት፣ ከኦሕዴድና ከብአዴን መሥራቾች መካከል የተወሰኑት ራሳቸውን የማግለል እንቅስቃሴ ማሳየታቸው የአገሪቱ ፖለቲካ ወዴት እየሄደ ነው? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡  በአጠቃላይ የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ ይህ ነው ለማለት አስቸጋሪ የሆነባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በወቅታዊ  ጉዳዮች ላይ ውድነህ ዘነበ አቶ ገብሩ አሥራትን አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ ገብሩ ቀደም ሲል የሕወሓት/ኢሕአዴግ ነባር አመራርና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በተቃውሞ ገራ የተሠለፈው አረና ትግራይ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ሥራ አስፈጻሚ አባል ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡  

  ሪፖርተር፡- የዛሬ ዓመት ከእርሶ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገን ነበር፡፡ በዚያ ወቅት መንግሥት የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ጥልቅ ተሃድሶ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር፡፡ ነገር ግን እርስዎ በጥልቅ ተሃድሶው ለውጥ እንደማይመጣ ተናግረው ነበር፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው የተደረገ በመሆኑ አሁንም በቀድሞው አቋምዎ ላይ ነዎት?

  አቶ ገብሩ፡- በትክክል፡፡ ካሁን በፊትም እንደገለጽኩት ጥልቅ ተሃድሶ ለመሸንገልና ሕዝቡን ለማታለል የታወጀ ነው፡፡ ጊዜ ለመግዛት ነው፡፡ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ገልጬ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን የአገሪቱን ሁኔታ ስናየው በፊት ከነበረበት የባሰ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው፡፡ አሁን የምናየው ሁኔታ እንኳ ለተራው ዜጋ ለፖለቲከኛም አሳሳቢ ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው የመንግሥት ባለሥልጣናት እጅ ያለበት የሕዝብ ዕልቂትና  መፈናቀል እየታየ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች፣ እንዲሁም በደቡብና በኦሮሚያ፣ በአፋርና በትግራይ ባለፈው ዓመት በአማራና በኦሮሚያ የነበረው የዜጎች መፈናቀል አሁን አድማሱ ሰፍቶ ቀጥሏል፡፡ ይህ የሆነው መንግሥት ባለበት አገር ነው፡፡ ወይ የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ይህን ልዩ የሚያደርገው የመንግሥት እጅ ያለበት በመሆኑ ነው፡፡ የክልል መንግሥታት፣ የፌዴራል መንግሥት አሉ፡፡ እነዚህ ባሉበት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ማለት በአገሪቱ ሕግ የሚያስከብርና የሚቆጣጠር መሪ አለ ወይ የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶ ማግሥት ይህ መከሰቱ አሳሳቢ ነው፡፡

  እኔ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁኔታዎች አልተለወጡም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ለማረጋጋት ተሞክሯል፡፡ መረጋጋት የሚመጣው በኃይልና በአዋጅ ሳይሆን ሰዎች ተቀብለውት፣ በዜጎች መካከል ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ ሲሆን ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው ሌላው ጉዳይ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን፡፡ ሙስናን እንዋጋለን የሚለው መፈክር ነወ፡፡ ሙስና ሲባል እኔ የማውቀው አንድ ሚሊዮን ሁለት ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በጣም የተወራለት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ (16 ሚሊዮን ዶላር ነበር)፡፡ አሁን ቢሊዮን ገብቷል፡፡ ይህም ትንሽ ምርመራ ተደርጎ የተገኘ ነው፡፡ በደንብ ቢቆፈር ምን ያህል የአገር ሀብት እየተዘረፈ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የሙስና ጉዳይ እየባሰበት ነው፡፡ ከከፍተኛ ባለሥልጣን እስከ ቀበሌ አመራር ድረስ ያለው መዋቅር በዝርፊያ ሰምጧል፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው ይበልጥ ዘራፊዎች እንዲጠናከሩ ያደረገ እንጂ የፈየደው ነገር የለም፡፡

  ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ሀብት ዜጎች እንዳይፈሩ ተደርጎ ስለበር ብዙም እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ከኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ በኋላ አዳዲስ ባለፀጋዎች ተፈጥረዋል፡፡ የመንግሥት ደመወዝተኛ የነበሩ አሁን በሚሊዮን የሚያገላብጡ፣ መነሻቸው አነስተኛ ገንዘብ የሆነ አዳዲስ ቢሊየነሮች ተፈጥረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለፍተው ያገኙ እንዳሉ ሆኖ፣ ሙስናም እንዳለ አመላካች ክስተቶች አሉ፡፡ ከጅምሩ ይኼን ችግር መቅጨት አይቻልም ነበር?

  አቶ ገብሩ፡- እዚህ ላይ መታየት የለበት ሙስናን እንዴት ነው መዋጋት የሚቻለው? እንዴት ነው መቀጨት ያለበት? ሲባል ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር የሚታይ ነው፡፡ ሙስና፣ ብልሹ አሠራር፣ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መዋጋት የሚቻለው የተስተካከለ የፖለቲካ ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡ የተስተካከለ ሥርዓት ሲባል ቢያንስ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፣ አሳታፊ መሆን አለበት፣ ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ያለው የአንድ አምባገነን ፓርቲ ሥርዓት ነው፡፡ የአንድ አምባገነን ሥርዓት ደግሞ ከሙስና አይፀዳም፡፡ እንዲያውም እየባሰበት ነው የሚሄደው፡፡ ምክንያቱም ይህን ሙስና ለመቆጣጠር የሚችሉ ተቋማት በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ፣ ፓርላማው፣ ሥራ አስፈጻሚው ሁሉ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ ሌሎች ከዚህ ውጪ ያሉ ሲቪክ ማኅበራት፣ ሚዲያዎች ሁሉ በተፅዕኖ ውስጥ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሙስናው መንሰራፋት አገሪቱ በአንድ አምባገነን ፓርቲ ሥር በመተዳደሯ ነው፡፡ ነፃነት በመጥፋቱ ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ ለውጥ ማምጣት አይችልም፡፡ ብርሃን ሲኖር ነው ዘራፊ የሚታየው፡፡ ብርሃኑን ኢሕአዴግ ጋርዶታል፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሽርኮቻቸው ጋር ሆነው የዚህችን አገር ሀብት እየዘረፉ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚህ አገር ንግድ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ አካላት መነሻቸው አነስተኛ ካፒታል ነበር፡፡ ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር የተነሱ ባለፀጎች ብዙ ናቸው፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ የወደፊቶቹን ባለፀጋዎች ይመለምል ነበር? ይኼ እንዴት ሊጠፈር ቻለ? ነጥሎ የመምታት አካሄድም አለ፡፡ ይኼ የሚከሰተው ለምንድነው?  

  አቶ ገብሩ፡- ፓርቲው ራሱ እንደ መዋቅር በሙስና ውስጥ የተዘፈቀ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በል፣ ልማታዊ መንግሥት በል መሠረቱ ሙስና ነው የሆነው፡፡ መሬት እየዘረፈ የሚቸበችበው የመንግሥት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ተመሳጥረው ነው፡፡ አገሪቱ ውስጥ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እኮ ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው ሆነዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ የዝርፊያ ማዕከላት ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ የስኳር ኮርፖሬሽን የረባ ነገር አልሠራም፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ላይ እስካሁን የታየ ነገር የለም፡፡ በዚህ ውስጥ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ኮንትራክተሮች አሉ፡፡ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ መመሳጠር ሲኖር ከዝርፊያ ባሻገር በአገሪቱ ሊሠራ የነበረው ውጤታማ አይሆንም፣ የሚታየውም ይኼው ነው፡፡ ውጤታማ መሆን ያልተቻለበት፣ ምርታማ ሊኮን ያልተቻለበት ሁኔታ ነው እያየን ያለው፡፡ ስለዚህ እየተዘረፉ ያለው በመንግሥትና በእነዚህ ተዋናዮች መካከል ባለ ግንኙነት ነው፡፡ የሙስና ትግል ሲባል እንዲሁ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚወሰድ ዕርምጃ ነው፡፡ ሕዝቡ ሲያማርር የተወሰኑት ኃይል የሌላቸው ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ድሮም ቢሆን እንደዚህ ነበር፡፡ በእርግጥ ለፍተው ጥረው ሀብት የፈጠሩ የሉም አይባልም፡፡ ይኼ ግን ረዥም ጊዜ ይፈጃል፡፡ በአጭር ጊዜ ቢሊየነር የመሆን ጉዳይ ጤነኛ አካሄድ አይደለም፡፡ በዚህ አገር ዴሞክራሲ እንዳይኖር፣ ነፃነት እንዳይኖር፣ ፍትሕ እንዳይኖር ምክንያት እየሆኑ ያሉት እነዚህ ተዋናዮች ናቸው፡፡ ሥርዓቱም እነዚህ ተዋናዮች እንዳይነኩ የሚጠብቅ ነው፡፡ ይህ ኢሕአዴግ በሚያስተዳድራቸው በሁሉም አካባቢዎች ያለ ነው፡፡ አንድ ሁለት ሰዎች አቅም የሌላቸው፣ ኃይል የሌላቸው መስዋዕት ይሆናሉ፡፡ ሌላው ግን አይነካም፡፡

  ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የፖለቲካ ክስተቶች እየታዩ ነው፡፡ እርስዎ በፖለቲካው ውስጥ የቆዩ እንደ መሆንዎ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ንፋስ እየነፈሰ ነው ማለት ይቻል ይሆን?

  አቶ ገብሩ፡- በትክክል፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ሦስት ያህል ተዋናዮች አሉ፡፡ አንዱና ትልቁ ተዋናይ ሕዝብ ነው፡፡ ሁለተኛው መንግሥት ነው፡፡ ሦስተኛው የተቃዋሚዎች ኃይል ነው፡፡ በእነዚህ ተዋናዮች አዳዲስ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ ያልነበሩ ክስተቶች በግልጽ ታይተዋል፡፡ በተለይ ከሁለት ዓመት ወዲህ በሕዝብ በኩል አልገዛም ባይነት ጠንክሮ ወጥቷል፡፡ ኢሕአዴግ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለ፣ ሕዝቡ ደግሞ በጣም ስለተማረረ እንቅስቃሴው በግብታዊነት ቢሆንም አልገዛም ባይነቱን አቀጣጥሎታል፡፡ አሁን እንደምታየው በአዲስ አበባ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ አይፈቀድለትም፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ግን ሕዝብ ያለ ፈቃድ፣ መንግሥትን ሳይጠይቅ ሰለማዊ ሠልፍ የሚያደርግበት ክስተት አለ፡፡ ይህ የሚያሳየን መንግሥት ሕዝቡን ለመቆጣጠር ያደራጃቸው አንድ ለአምስትና የልማት ሠራዊት የመሳሰሉ አደረጃጀቶች እንደፈረሱ ነው፡፡ ሕዝቡ እነዚህን አደረጃጀቶች አፈራርሷቸዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ በተወሰነ ደረጃ በትግራይ ፈራርሰዋል፡፡ ሕዝቡን ጠፍረው የያዙት እነዚህ አደጃጀቶች ፈራርሰዋል፡፡ ሕዝቡ በራሱ ትግል ነፃነቱን አውጇል፡፡ አሁን ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልግ ለተከታታይ ቀናት ሰላማዊ ሠልፍ የሚደረግባቸው ቦታዎች ተበራክተዋል፡፡ በሕዝብ በኩል አልገዛም ባይነቱ ጠንክሯል፡፡ ይህ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የኢሕአዴግ አባል አለ በሚባልበት አገር፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አሉ በሚባል አገር፣ ሕዝብ ነፃነቱን አውጇል፡፡

        ሁለተኛው የገዥው ፓርቲ (መንግሥት) የመቆጣጠር አቅም ተዳክሟል፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ነው ይኼ ሁሉ መፈናቀል፣ ይህ ሁሉ ግጭት እያየን ያለነው፡፡ መንግሥት እንደ ቀድሞው ሕዝቡን ተቆጣጥሮ የመግዛት አቅሙ የተዳከመ ሆኗል፡፡ መንግሥት መሥራት ከሚገባው ግዴታ አንዱ የሕዝቡን ሰላም ማስጠበቅ፣ ደኅንነቱን መጠበቅ፣ ንብረቱን መጠበቅ ነበር፡፡ መንግሥት ይህን ማድረግ አልቻለም፡፡ መንግሥት ላልቷል፡፡ መንግሥት እንደ ቀድሞው የሚገዛበት ሁኔታ የለም፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ የመንግሥት ሁኔታ ማዕከላዊ መንግሥቱ ክልሎችን መቆጣጠር የተሳነው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ክልሎች ጠንክረው የወጡበት፣ ክልሎች እርስ በርሳቸው የማይስማሙበት፣ እርስ በርሳቸው አተካራ የገቡበት፣ እርስ በርስ የሚጋጩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶቹን መቆጣጠርበት ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መንግሥት እንደ ቀድሞ የተለመደውን ሥራ ለመሥራት የተቸገረበት ሁኔታ በግልጽ ታይቷል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ፣ በደቡብና በኦሮሚያ መካከል በሌሎችም እየታዩ ያሉ ግጭቶች መንግሥት እየተዳከመ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል መታየት ያለበት በተቃዋሚዎች በኩል ያለ ክስተት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚዎች እንዳይበረቱ ዋነኛው መንግሥት የተከተለው መንገድ ነው፡፡ በዚህ አገር የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እንዲጠናከር ሀቀኛ ተቃዋሚዎች እንደ ጠላት የተፈረጁበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አፈናው በጣም አይሎ ሕዝቡ ጭራሽ እንዳይላወስ፣ መብቱን እንዳያስከብር በጣም የተደፈቀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች የራሳቸውን መብት ለማስከበር መንቀሳቀሳቸው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡

  በዚህ ሁኔታ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች፣ ምክንያታዊ ተቃዋሚዎች፣ ዓላማ ያላቸውና ለዚህች አገር የሚያስቡ ተቃዋሚዎች ቦታ የላቸውም፡፡ እንደ ጠላት ተቆጥረዋል፡፡ መንግሥት እነዚህን ያሳድዳቸዋል፣ ያስራቸዋል፡፡ ይህ በሆነበት የሚፈጠረው የፖለቲካ ዕድገት ፅንፈኝነት ነው፡፡ መካከለኛ አመለካከትና ነፃነት በተዳፈነበት ወቅት ፅንፈኝነት ይበዛል፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የፖለቲካ አቅጣጫዎች በማኅበራዊ፣ በፖለቲካ፣ በፍትሕና በመሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነበር ሕዝብ ሲነጋገር የቆየው፡፡ አሁን ግን በዘር ላይ ሆነ፡፡ ይህ ክስተት ለኢትዮጵያ አደጋ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንዲሁ ለይስሙላ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት ይበል እንጂ መደበቂያው ብሔር ነው፡፡ ብአዴን መደበቂያው የአማራ ሕዝብ፣ ሕወሓት መደበቂያው የትግራይ ሕዝብ፣ ኦሕዴድም እንዲሁ መደበቂያው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ አገራዊ ፖለቲካ ተዳፍኗል፡፡ የፅንፍ ፖለቲካ ተስፋፍቷል፡፡ ፓርቲዎቹ ሁሉ ቅድሚያ ለየአካባቢያቸው ሰጥተዋል፡፡ የጋራ አገራዊ ጉዳይ ተዳፍኗል፡፡ ይህ አደገኛ ፖለቲካ ነው፡፡ ምክንያታዊ ፖለቲካ ጠፍቷል፡፡ ተዳፍኗልም፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ወደኋላ እየተመለሰ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ማዕከላዊ መንግሥት የመዳከም አዝማሚያ እያሳየ በመሆኑ ክልሎች ደግሞ በአንፃሩ ጠንክረው እየወጡ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ክልሎች አዳዲስ ሐሳብ፣ አዳዲስ ቅርፅ የመፍጠር ሁኔታ እያሳዩ ለማዕከላዊው መንግሥት አለመታዘዝም እየተንፀባረቀ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ ይህን አስተውለዋል?

  አቶ ገብሩ፡- ይኼንን ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ነው የማየው፡፡ ያነሳኸው ጥያቄ መሠረታዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገር ነች፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሰፊ አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ የሚመጥናትን ፖለቲካ እስካሁን አላገኘችም፡፡ የብሔር ጥያቄ አጀማመሩ ከ40 ዓመት በፊት ነው፡፡ የብሔር ጥያቄና አገራዊ ጉዳይ በሚዛን ተቀምጠው አልሄዱም፡፡ ይህን ማስተዋል ይገባል፡፡ እንግዲህ የብሔር ጥያቄ እንደ ጥያቄ መመለስ ያለበት አግባብነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡ የብሔር ጥያቄ ከአገራዊ ጥያቄ አልፎ ከሄደ አደጋ አለው፡፡ አገራዊ ጉዳይ ለብሔር ጥያቄ ተገዥ ከሆነ አሁን የምናየው የውድድርና የፉክክር መድረክ ይሆናል፡፡ የጋራ እሴታችን፣ የጋራ ጥቅማችን፣ የጋራ ዕጣ ፈንታችን፣ የጋራ ጉዞአችን ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ነው እየታየ የለው፡፡ ኢሕአዴግ ይህን ነው እያጠናከረ የመጣው፡፡ ኢሕአዴግ የብሔር ጥያቄን ትክክለኛ ቦታ ላይ አስቀምጦ አልሄደም፡፡ ቅድሚያ የሰጠው የብሔር ጥያቄን ነው፡፡ አገራዊ ጉዳይን፣ የጋራ ጉዳይን ቦታ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁን እየተቀነቀነ ያለው ስለአገር ጉዳይ አያገባንም በማለት ጭምር ነው፡፡ በአገሪቱ ሰፊ ሀብት ያካበተው፣ በብዙ ክልሎች ሀብት ያፈራ አካል ሁሉ የሚያስበው ስለአካባቢው ብቻ ሆኗል፡፡ ይኼ የብሔር ጥያቄ ከአገራዊ ጥያቄ በልጦ፣ የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ሁለ በብሔራቸው ጉያ የሚወሽቁበት ሆኗል፡፡ ስለአገር ጉዳይ ደንታ የታጣበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

        ክልል ከክልል በሚለይበት ድንበር መጋጨት ሁሉ ተጀምሯል፡፡ በነገራችን ላይ የድንበር ጉዳይ ለእኔ እንደ ትልቅ የፉክክር ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ  ድንበር በየጊዜው ሲለዋወጥ ቆይቷል፡፡ በታሪካችን ብዙ ጊዜ በየአገዛዙ ሲለዋወጥ ነው የኖረው፡፡ በየአገዛዙ የድንበር አከላለል ሲለዋወጥ ቆይቷለ፡፡ አሁንም ተለውጧል፡፡ ለወደፊቱም ሊለወጥ የሚችል ይመስለኛል፡፡ ይኼ ግን በኢትዮጵያውያን መካከል የጦርነትና እርስ በርስ የመጠላላት መሠረት መሆን የለበትም፡፡ በሕዝቡ መካከል መሠረት ያጡ የፖለቲካ ድርጀቶች ሕዝቡን ወደዚህ አቅጣጫ መርተው እነሱ ግን ለሕዝቡ መቆማቸውን ለማሳየት የሚጥሩበት ሆኗል፡፡ እንዲያውም አንድ የኢትዮጵያ ዜጋ አገር አለኝ ወይ? ብሎ እንዲያስብ እያስገደደ ነው፡፡ አንድ የትግራይ፣ የአማራ፣ ወይም የሌላ ብሔር ሰው ኦሮሚያ ሄዶ ካልሠራ፣ ካልነገደ፣ አንድ የኦሮሞ ወይም የደቡብ ሰው ትግራይ፣ አማራ ሄዶ ካልሠራና ካልነገደ አገሬ ነው ብሎ ካልተንቀሳቀሰ፣ አገር የታለ? ዜጋ በነፃነት ካልተንቀሳቀሰ፣ ሀብቱን ካላንቀሳቀሰ የታለ አገር? የብሔር ጥያቄን እንደ ዋና ስትራቴጂ መውሰድ ግን ውድድርንና ሽኩቻ አጉልቶ፣ በመካከል ግጭት የሚፈጥር ነው፡፡ አገራዊ የሆነ እሳቤ ላይ እንከን የሚፈጥር ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የክልሎችን የፖለቲካ ሁኔታ ከኃይል አሠላለፍ ጋር ብናየው ለምሳሌ በፌዴራል ደረጃ መከላከያና ፌዴራል ፖሊስ አሉ፡፡ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ የከተማ ፖሊስ አለ፡፡ በክልሎች ደግሞ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ አሉ፡፡ ነገር ግን ክልሎቹ እነዚህን ኃይሎች ለፈለጉት ተግባር የሚያዙ በመሆናቸው ከኃላፊነት አንፃር ያለው አንድምታ ምንድነው? በክልሎች ለሚነሱ ችግሮች የእነዚህ ኃይሎች አስተዋጽኦ ምን ይመስላል? እዚህ ላይ እርስዎ ከነበሩበት ወቅት ጋር አሁን ያለውን ሁኔታ አነፃፅረው ቢገልጹልኝ?

  አቶ ገብሩ፡- ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ እንደ ፌዴሬሽን ከቆመ አደጋ ይኖረዋል፣ የፉክክር መድረክ ነው የሚሆነው፣ እንደ አቅጣጫ ግን ኢሕአዴግ ራሱ አንድ አገራዊ ፓርቲ ሆኖ ቢወጣ ሌሎችንም እንዲሁ አገራዊ ፓርቲ እንዲሆኑ አድርጎ ቢሄድ፣ አሁን ያለው ሁኔታ አይፈጠርም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ አሁንም ግንባር ነው፡፡ አሁንም ፌዴሬሽን ነው፡፡ ኢሕአዴግ የፓርቲዎች ፌዴሬሽን ነው፡፡ ሲመቻቸው በፌዴራል መንግሥቱ የተሻለ ቦታና ጥቅም ለማግኘት ይፎካከራሉ፡፡ ካልተቻላቸው በክልላቸው ያላቸውን ኃይልና ሥልጣን ተጠቅመው ያሻቸውን ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ በየትኛውም ፌዴራላዊ አገር ክልሎች የራሳቸው ፖሊስ ይኖራቸዋል፡፡ ችግር የለውም፡፡ የራሳቸው የፀጥታ ኃጥል ይኖራቸዋል፡፡ ልዩ ፖሊስ በፖሊስ ማዕቀፍ ሥር ሊታይ ይችላል፡፡ እንዲያውም ለእኔ በሕገ መንግሥትም በሌሎች ሕግጋትም ያልተመለሰው ሚሊሻ የሚባለው ታጣቂ ኃይል ጉዳይ ነው፡፡ ቁጥሩ በጣም ብዙ ነው፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ኃይል ነው፡፡ ይኼ ኃይል የፓርቲ አባልም ነው፡፡ እንደ መርህ ታጣቂ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን አልነበረበትም፡፡ ሚሊሻዎች የእነዚህ ድርጅቶች አባል በመሆናቸው ክልሎች ሠራዊትም አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለውጊያ የሚሄድ፣ ሊዋጋ የሚችል ትልቅ ኃይል ነው፡፡ እንዲያውም ከልዩ ኃይል የበለጠ ብዛትም ኃይልም ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ በፖለቲካ ድርጅት ሥር የሚተዳደሩና የሚታዘዙ በመሆኑ ችግር አለው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቱ መዋጋት ሲያስፈልገው የሚዋጋ ኃይል ነው፡፡ ይህ አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህ ክልሎች ከዚህ አንፃር ኃይላቸው ደልቧል፡፡

  ክልሎች አሁን ከክልል የዘለለ ራዕይ የላቸውም፡፡ አጥተዋልም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ከክልልም የወረደና አንድ አካባቢ ላይ ያተኮረ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ማዕከላዊውን መንግሥት የሚያዳክምና አገሪቱን በአጠቃላይ የሚያደክም አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ የዚህ ኃይል አንድ ጉዳይ ሆኖ ማዕከላዊው መንግሥት ተዳክሟል፡፡ ቀደም ሲል ኢሕአዴግ ጠንካራ አምባገነን መሪ ስለነበረው ጠፍሮ ይዟቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ተሰሚነት የሌለው ማዕከል በመፈጠሩ ክልሎች እንዳሻቸው እንዲሄዱ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህ ሁኔታ ለዜጎች የመፈናቀል ቀውስ ምክንያት ሆኗል፡፡ መተማመን እንዲጠፋ አድርጓል፡፡

  ሪፖርተር፡- በልዩ ኃይልና በሚሊሻ መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት ምንድነው? ደመወዝ የሚከፋፈለው ለየትኛው መዋቅር ነው? የእነዚህ ኃይሎች ጉልበት ገዘፍ ያለ እንደ መሆኑ አንድን ጦርነት በድል መወጣት የሚያስችል ብቃት አላቸው ይባላል፡፡ ከዚህ አንፃር ኃላፊነት በማይሰማው አካል ከተመሩ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እርስዎ የገዥው ፓርቲ አመራር ከነበሩበት ጊዜ ጋር አነፃፅረው ሁኔታውን ቢያስረዱን?

  አቶ ገብሩ፡- ሚሊሻ ደመወዝ አይከፈለውም፡፡ የአካባቢ ታጣቂ ኃይል ነው፡፡ ልዩ ኃይል የፖሊስ ኃይል ነው፡፡ በፊትም መዋቅሩ ነበር ‹‹ፈጥኖ ደራሽ›› ይባል ነበር፡፡ በንጉሡ ዘመነ መንግሥት በአገር ደረጃ ፈጥኖ ደራሽ ነበር፡፡ ነገር ግን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ይታዘዝ የነበረው በማዕከላዊው መነግሥት ነው፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ኃይሉን ማንቀሳቀስ ይችል ነበር፡፡ ፖለቲካውም እንደዚሁ ነበር፡፡ አሁን ያለው ልዩ ኃይል የሚታዘዘው በክልሎች ነው፡፡ እንደ ሠራዊት ነው አደረጃጀቱ፡፡ በክልሎች መካከል ያለው ፖለቲካ ሲበላሽ ይህ ኃይል መሰለፉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ኃይል እንደ ሰላማዊ ፖሊስ ነው? ወይስ ሠራዊት ነው? አቅሙ እስከየት ነው? እስከምን ድረስ መታጠቅ አለበት? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን በጋራ እናሳድጋት፣ እንምራት ብለን ካሰብን እነዚህ ሁሉ መታየት አለባቸው፡፡ ታጣቂ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን አለበት ወይ? ልዩ ፖሊስ ደግሞ አደረጃጀቱ እስከየት ድረስ ነው? የሚታጠቀውስ እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ መታየት አለበት፡፡ እንዳልከው በየአካባቢው ሚሊሻ የሚጠቀሙ አሉ፡፡ ክልሎች ለማፈናቀል ሚሊሻዎችን፣ ልዩ ኃይሎችን ይጠቀማሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ከማዕከላዊው መንግሥት መዋቅር ለመውጣት ሁለት ታዋቂ ነባር ታጋዮች (አቶ በረከት ስምኦንና አቶ አባዱላ ገመዳ) መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡ ይህ ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ፖለቲካ ችግር ውስጥ የገባበት እንደ መሆኑ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እርስዎን ይህ ክስተት ምን ያመለክትዎታል?

  አቶ ገብሩ፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ክስተቶች እየተለወጡ ሄደዋል፡፡ የሕዝቡ እንቅስቃሴና አልገዛ ባይነት እያየለ መጥቷል፡፡ መንግሥት ማስቆም የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይኼ ደግሞ አስደንጋጭ ነው፡፡ ይህ ለፖለቲከኛና የሕዝብ ተመራጭ ነን ለሚል አካል እጅግ ያስደነግጣል፡፡ ወክሎኛል ያልከው ሕዝብ ድምፅህን መስማት በማይፈልግበት ወቅት የመደናገጥና የመከፋፈል ስሜቶች ይፈጠራሉ፡፡ እኔ ሳየው ይኼ ጉዳይ በአገሪቱ ያለውን ችግር ከመፍታት አንፃርና ሁኔታዎችን ከመለወጥ አንፃር የታየ ልዩነት ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ይህ ግን አይደለም እየሆነ ያለው፡፡ ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ፣ የለሁበትም›› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የሚፈልጉ ባለሥልጣናት ናቸው መልቀቂያ እያስገቡ ያሉት፡፡ እነዚህ ቱባ ሰዎች በሥልጣን ሽኩቻ ባለመስማማት እንጂ የአገሪቱ ችግር በዚህ መንገድ ይፈታ በሚል ልዩነት አምጥተው አይደለም መሰናበትን የመረጡት፡፡ በሁለቱ ቱባ ሰዎች መልቀቂያ የለውጥ አቅጣጫ አልተመለከቱም፡፡ ለአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት የተለየ ነገር አምጥተው ይህን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ ተቀባይነት በማጣታቸው ተማረው እንደወጡ የሚያሳይ ነገር የለም፡፡ ያም ሆኖ ቅሬታ ማሰማት ይችላሉ፣ መብታቸው ነው፡፡ ግን የለውጥ አቅጣጫ ባለማቅረባቸው ከመልቀቃቸው የሚያተርፍ አለ ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ዋናው ጉዳይ አንድ ፓርቲ ሲዳከም ሽኩቻ ይበረክታል፡፡ ሕወሓት ውስጥ በአዲሶቹና በነባሮቹ አመራሮች መካከል ሽኩቻ አለ፡፡ ብአዴን ውስጥ አቶ በረከት የሚወክሉት ነባር ታጋዮችን ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ቅሬታ በነበሩ አካባቢ መኖሩን ያሳያል፡፡ የአቶ አባዱላም እንዲሁ ነው፡፡ በዋናዎቹ የኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲዎች ውስጥ አለመግባባት መኖሩን ያሳያል፡፡

  ሪፖርተር፡- ነባር ታጋዮች አሉ፡፡ የተተኩ አመራሮች አሉ፡፡ ሥልጣን የቱ አካባቢ ነው ያለው? አገሪቱ አሁን በማን እየተመራች እንደሆነ ማወቅ አለመቻላቸውን እየገለጹ ያሉ ብዙኃን ናቸው፡፡ እርስዎ ሥልጣን የት እንዳለ ያስባሉ?

  አቶ ገብሩ፡- የፖለቲካው የስበት ማዕከል የሚለውን እስካሁን መለየት አልተቻለም፡፡ እኔ እንደማስበው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሁሉንም ጠቅልለው ይዘው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከሥልት አንፃር ድርጅቱ ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ኢሕአዴግ አንድ ብርቱ አምባገነን አልፈጠረም፡፡ የሽኩቻ ሒደት ነው ያለው፡፡ በቀድሞውና በአሁኑ አመራሮችና በክልሎች መካከል ሽኩቻ አለ፡፡ ይኼ ነገር ኢሕአዴግ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ይገኛል፡፡ አገሪቱ የቆመችው በኢሕአዴግ አመራር ሳይሆን በመከላከያና በደኅንነት ኃይሉ ነው፡፡ የፖለቲካ ኃይሉና የመንግሥት መዋቅሩ ምንም ኃይል የለውም፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ አገር ከተቆጣጠረ 27 ዓመታት እየሞሉት ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ‹‹ግንባር›› ነው፡፡ መሥራቾቹም ‹‹ነፃ አውጪ፣ ንቅናቄ›› ናቸው፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አገር አቀፍ ፓርቲ የመሆን ዕቅድ ነበረው፡፡ ባህር ዳር በተካሄደው ዘጠነኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ አቶ ሥዩም መስፍን ይህን ጉዳይ አንስተውት ነበር፡፡ በአራት ፓርቲዎች ተዋጽኦ በምትመራው አዲስ አበባ ያሉ አመራሮች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ወጥ የፓርቲ ጉዳይ በኢሕአዴግ ቤት ምን ምልከታ ነበረው?

  አቶ ገብሩ፡- ኢሕአዴግ አንድ አገራዊ ራዕይ ያለው ፓርቲ እንደሚሆን ይነገር ነበር፡፡ በተለይ በማሌሊት ጊዜ፡፡ አንድ ግንባር ቀደም የላባደር ፓርቲ ይመሠረታል የሚል ሐሳብ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በግንባር የሚቆይ ሳይሆን አንድ ፓርቲ አድርጎ የማዋቀር ሐሳብ ነበር፡፡ ምክንያቱም የክልል ፓርቲ ሆኖ አገር መምራት አይቻልም፡፡ ያን ጊዜ  ግንባር ሆነው የተደራጁ ፓርቲዎች የመዋሀድ ፍላጎት አልነበራቸውም ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ግንባርን መሸጋገሪያ በማድረግ ለወደፊቱ አንድ ፓርቲ የማድረግ ሐሳብ ነበር፡፡ ግንባር እንደ መጨረሻ ከሆነ ግን ይህች አገር ለውጥ አይኖራትም፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አገራዊ ፓርቲ የሚሆንበት ስትራቴጂ አልተቀረፀለትም፡፡ እንዳልከው በባህር ዳርና ከዚያም በፊት ጉዳዩ ተነስቶ ነበር፡፡ ጉዳዩ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በተሰነጠቀበት ወቅት ተነስቶ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ይዋሀዳል ተብሎ መግለጫም ተሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡ እስካሁን መልስ ያላገኘ ጉዳይ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በተለያዩ ቦታዎች በሚነሱ የተቃውሞ ሠልፎች በብዛት የሚሰማው ሕወሓት ሥልጣን እንዲለቅ ነው፡፡ ሕወሓት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ተፅዕኖ አድራጊ ሆኖ ተስሏል፡፡ በእርግጥ ሕወሓት በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ተፅዕኖ እንዴት ይገለጻል? በክልሎች ውስጥ ጣልቃ ገብነቱ እስከምን ድረስ ነው? የትግራይ ሕዝብ ላይም የማነጣጠር አዝማሚያ ይታያል፡፡ እርስዎ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን አነፃፅረው ቢያስረዱን?

  አቶ ገብሩ፡- የአሁኑ የፖለቲካ አካሄድ አንድ ፓርቲ የሕዝቡን ድጋፍ ለመሻት ሲንቀሳቀስ የሚያነሳው ጉዳይ ራሱን የአንድ ክልል ተወካይ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ የአንድ ክልል ተወካይ ማድረግ ሳያበቃ ጠላትህ ሌላ ክልል ሌላ ሕዝብ ነው የማለት ጉዳይም አለ፡፡ እንዳልከው ፅንፍ የረገጡ ፖለቲከኞች ያነጣጠሩት ሕወሓት ላይ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ላይም ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ ጠላት አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ የፖለቲካው አስከፊ ገጽታ የምለው ሕዝብን እንደ ጠላት መቁጠርን ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ትግራይ ውስጥ ለምሳሌ በቅርቡ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ ከደድህነት ወለል በታች ካሉ ክልሎች ቀዳሚው (27 በመቶ) የትግራይ ክልል ነው፡፡ በትግራይ ያለው የድህነት ሁኔታ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር የከፋ ነው፡፡ የሙስናና የብልሹ አስተዳደር ሰለባ ነው፡፡ ትግራይ የመሠረተ ልማት ችግር ያለበት ክልል ነው፡፡ ነገር ግን ፅንፈኞች ሀብትህ ወደ ትግራይ ተጓዘ፣ የትግራይ ሕዝብ ተለውጧል፣ ትግራይ አውሮፓ መስላለች የሚሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን ይነዛሉ፡፡ በቀውስ ጊዜ ደግሞ የሚሰራጩ መረጃዎችን እንደ እውነት መቁጠር ይመጣል፡፡ ስለዚህ የፅንፍ ፖለቲካ ዞሮ ዞሮ ጤነኛ ያልሆነ አካሄድ እንዲመጣ፣ አንድን ሕዝብ ነጥሎ የመምታት ጉዳይ በአገሪቱ ፖለቲካ ችግር የሚፈጥር ነው፡፡

        በመጀመርያዎቹ ዓመታት የሁሉንም ፓርቲዎች ሚዛን ከተመለከትን ሕወሓት ያየለበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሌሎቹ ፓርቲዎች ኋላ ላይ ነው የተመሠረቱት፡፡ ኦሕዴድና ደኢሕዴን በኋላ ነው የተመሠረቱት፡፡ ጥንካሬውን ስትመለከተ ሕወሓት ጠንካራ ነበር፡፡ ነገር ግን በሒደት ሕወሓት ጥንካሬውን እያጣ ሄዷል፡፡ በፓርቲ ውስጥ፣ በፌዴራል መዋቅሮች ውስጥ የሕወሓት ተፅዕኖ እየቀነሰ ሄዷል፡፡ ሕወሓት እንደ ቀድሞ ሐሳብ ኖሮት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ አይደለም፡፡ በሐሳብ ደረጃም ተዳክሟል፡፡ አገሪቱን ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ተራማጅ ሐሳብ የለውም፡፡ ባለበት የቆመ፣ ወደ ኋላ እየተመለሰ ያለ ፓርቲ ሆኗል፡፡ እንኳንስ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይቅርና በትግራይም ተፅዕኖው ቀንሶ፣ መምራት ያልቻለበትና ይልቁንም የቆመበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ዛሬ ላይ ያለው ሕወሓት ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ አቅርቦ የሚያለቅስ ነው፡፡ ያም ሆኖ አንዳንዶቹ ምክንያታዊ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ጭምር የትግራይን ሕዝብና ሕወሓትን አንድ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ሁለተኛ ሌሎቹ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከደሙ ንፁህ እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ፡፡

  ኦሕዴድና ብአዴን በክልሎቻቸው ለሚፈጠረው ችግር ከደሙ ንፁህ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ይህ የፖለቲካ ችግር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር አንድን ፓርቲ ነጥሎ መኮነን አግባብ አይደለም፡፡ ሁሉም ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች በዝርፊያው፣ በግድያውም፣ በአፈናውም አሉበት፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ተከትለው እየሄዱ ያሉ ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አራቱም ፓርቲዎች ራሳቸውን ንፁህ አድርገው ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ችግር ሲፈጠር የትግራይ ሕዝብ ላይ ጣት መቀሰር ሊቆም ይገባል፡፡ ይኼ የትም አያደርስም፡፡ ችግሩን በጥሞና ያላየ እንቅስቃሴ የትም አያደርስም፡፡ ሕዝብ በየትኛውም መመዘኛ ጥፋት የለበትም፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህ ነው ለማለት አስቸግሯል፡፡ የመስኩ ምሁራን ለመተንተንም እንዲሁ መቸገራቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እርስዎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሁነኛ ቦታ የነበረዎት እንደመሆኑ ተንብዩ ብልዎትስ?

  አቶ ገብሩ፡- አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ አልሠራሁበትም፡፡ እንደ ግለሰብ ተንብይ ካልክ ግን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ የማያጠራጥር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ይውደደውም ይጥላውም ቀውስ ውስጥ ነው፡፡ በሕዝቡና በመንግሥት መካከል ያለው ቅራኔ በርትቷል፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ብቁ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ውስጥ ሽኩቻው በርትቷል፡፡ እያንዳንዱ የሚያስበው ስለራሱና ስለአካባቢው ብቻ ሆኗል፡፡ ሥልጣኑ እንዳይነካ፣ ያካበተው ሀብት እንዳይነካ ነው የሚጠባበቀው፡፡ ሕዝብ ከቁጥጥር ነፃ እየወጣ ነው፡፡ ራሱን እያስተዳደረ ባይሆንም አልገዛም እያለ ነው፡፡ እንግዲህ ሄዶ ሄዶ ምን ይሆናል ነው? ዋናው ነጥብ፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ኢሕአዴግ ከፖለቲካ አንፃር ያለቀለት ድርጅት ነው፡፡ መቼ ይወድቃል? የሚለውን በዚህ ቀን ልል አልችልም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ በኋላ ከፖለቲካ ቅቡልነት አንፃር አገር እገዛለሁ ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም፡፡ እየገዛ ያለው በደኅንነትና በመከላከያ ሠራዊት አማካይነት ነው፡፡ ኢሕአዴግ በፖለቲካ ቅቡልነት አይደለም አገር እያስተዳደረ ያለው፡፡ ይኼ እስከ የት ይወስደዋል? የሚለውን ጉዳይ በወቅትና በጊዜ መተንበይ ያስቸግራል፡፡ ግን በኢሕአዴግና በሕዝቡ መካከል ያለው ቅራኔ በመስፋቱ ድርጅቱ ተነጥሏል፡፡

  በኢትዮጵያ አንድ የጎደለ ነገር ቢኖር ኢሕአዴግን የመተካት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለሁሉም አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግም የሚተካው እንዳይኖር እጅግ ሠርቷል፡፡ አማራጭ ኃይሎች አልተጠናከሩም፡፡ እንዲጠናከሩ የሚያደርግ ምኅዳርም የለም፡፡ የራሳቸውም ድክመት አለ፡፡ ኢሕአዴግም እየኖረ ያለው በዚህ ክፍተት ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚለውን ሟርት እኔ አልቀበለውም፡፡ ኢትዮጵያ የኖረችው ኢሕአዴግ ስለመጣ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከኢሕአዴግ በፊትም ኖራለች፡፡ ሕዝብ አብሮ መኖር ይፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞች ግን ይህን የሚያላላ ድርጊት እየፈጸሙ ነው፡፡ ይህን ቀውስ ተጠቅመው የሚወጡ ፖለቲከኞች ይህንኑ መቃቃር እያራቡ ነው፡፡ ኢሕአዴግም አገራዊ አንድነቱን የሚያላላ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ይኼ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ሌሎች እንደሚሉት ትበታተናለች በሚለው አልስማማም፡፡ የሲቪል አስተዳደር ሲወድቅ ሌላው የሚመጣው ሠራዊቱ ነው፡፡ ይህ ሌላ ገጽታ ይሆናል በኢትዮጵያ ፖለቲካ፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ መዳከም ከሌሎች አገሮች ጋር በሚኖር ግንኙነት ምን ሊፈጥር ይችላል? ሰሞኑን እንደሚታየው በትልልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለግብፅ የሚወግን (በናይል ጉዳይ) ጽሑፍ እየወጣ ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ያለውም ግንኙነት እስካሁን የሻከረ እንደመሆኑ አንድምታውን እንዴት ይገልጹታል?

  አቶ ገብሩ፡- ኢትዮጵያ የባህር በሯን አሳልፋ የሰጠች ባህር አልባ አገር ናት፡፡ በጦርነቱ ጊዜ ኢትዮጵያ አንድ ማስጠንቀቂያ ደርሷታል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ከሌላት የጎረቤቶቿን ወደቦች መጠቀም እንደማትችል ተገልጾላት ነበር፡፡ ግን ከዚያ በኋላ የወጣው የአገሪቱ የውጭ ፖሊሲ ትኩረታችን ‹‹ድህነትን መዋጋት ነው›› የሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ድህነትን መዋጋት›› የሚለው ጉዳይ አሳቻ አቅጣጫ ነው፡፡ ድህነት ክስተት ነው፡፡ የመጥፎ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ የመጥፎ መሪዎች ውጤት ነወ፡፡ ድህነት ራሱ ጠላት ሊሆን አይችልም፡፡ ጠላት ከተባለ ጠላቱ ድህነት እንዲፈለፈል ሥር እንዲሰድ የሚያደርገው ኃይል ነው ጠላት፡፡ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ኢሕአዴግ ነው ተጠያቂው፡፡

        በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይህን ብለው ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚኖራት ግንኙነት የሚኖራትን ጥቅም የዘጋ ጉዳይ ነው፡፡ የባህር በር መጠየቅ ጦረኝነት ስለሆነ ወደ ውጊያ ይከተናል የሚሉ ማስፈራሪያዎች እየተደረደሩ አገሪቱ ባህር አልባ ሆና ቀርታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ብዙ ነው፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ ዓባይን ጨምሮ ወንዞቿ በሙሉ የኃይል (ጉልበት) ምንጭ ናቸው፡፡ እነዚህን ተጠቅሞ ኃያል ሆኖ መውጦት ሲገባ፣ ደካማ እንድትሆን ተደርጓል፡፡ ብዙ አገሮች አሰብ ላይ እየተረባረቡ ነው፡፡ የጦር ቤዝ እየመሠረቱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያ አቤቱታ እንኳን አላሰማችም፡፡ ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወታደራዊ ማዕቀብ ተጥሎባታል፡፡ ነገር ግን ወታደራዊ ሠፈሮች እየተገነቡባት ነው፡፡ ይህንን እንኳ አቤት አላለችም፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይን የመጠቀም መብት አላት የመደራደር ጉዳይ ነው፡፡ ግብፆች በውጭ ዓለም ተሰሚነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብለው ሲያስቡ ተጨማሪ ተፅዕኖ ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላትን ቦታ ማስጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ነገር  ግን ከበፊት ጀምሮ ይህ ጉዳይ እንዲነሳ አይፈለግም፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ኢትዮጵያ የግብፅን ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ያሉ አገሮችን ጫና የምትቋቋመው የማይቋረጥ የኃይል መሠረተ ልማት ሲኖራት ነው›› ሳሙኤል ተፈራ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ...

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ በጃፓን ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአፍሪካና በእስያ ጥናት ትምህርት...

  ‹‹ባንኮች በየዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ እያገኘን ነው እያሉ ከሚከፋፈሉ ካፒታል ማሳደግ ላይ በሚገባ መሥራት አለባቸው›› አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር

  በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ የፋይናንስ ተቋማት የትርፍ ምጣኔ እያደገ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የውስጥና የውጭ ችግሮች አሉ በሚባልባቸው ጊዜያት ሁሉ...

  ‹‹ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ ይህች አገር አሁን በምናያት መንገድ አትኖርም›› ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ የኢዜማ ሊቀመንበር

  ለረዥም ጊዜ በዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የኢዜማ ምርጫም የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ጥናቶችን በማበርከት የሚታወቁም ሲሆን፣ በተለይ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ...