Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  መደበኛ ያልሆኑ ንግዶችና በሥጋት የታጠረ ጉዞዋቸው

  በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ ቢዝነሶች እጅግ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እንደውም መደበኛ ከሚባሉ ቢዝነሶች የበለጠ በአነስተኛ ደረጃ የሚሠሩ ቢዝነሶች በስፋት ይታያሉ፡፡ ምናልባትም ከመደበኛው ወይም በሕጋዊ መንገድ ከሚካሄዱ ግብይቶች ያላነሰ የገንዘብ ዝውውር ያካሂዳሉ ተብለውም ይታመናል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሚተዳደሩባቸው እነዚህ ትናንሽ ወይም መደበኛ የማይባሉ ቢዝነሶች ንግድ ፈቃድ ወጥቶባቸው የሚሠሩ ባለመሆናቸው፣ ለሸማቾች የሚያቀርቧቸው ምርቶች የጥራት ደረጃ አይመዘንም፡፡ ከእነዚህ ቢዝነሶች ጋር የምንገበያየው በመተማመን ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጣቸውም ቢሆን ቁጥጥር አይደረግበትም፡፡ የዋጋ ቁጥጥርም አያውቃቸውም፡፡ የዋጋ ተመናቸውም በዘፈቀደ የሚወጣና የሚወርድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እጅግ በርካታ ሸማቾች የሚጎበኙዋቸውና የሚጠቀሙባቸው ሆነው ዘልቀዋል፡፡ እንደ አነስተኛ ቢዝነስ ታይተው እየተሠራባቸው ካሉት መካከል የጉሊት ችርቻሮ፣ የመንገድ ላይ ንግድ፣ ጠላ ቤቶች፣ ጠጅ ቤቶች የመንገድ ላይ ምግብ ቤቶች፣ ሻይ ቤቶች፣ በየመንደሩ በአነስተኛ ሱቆች የሚሸጡ የባልትና ውጤቶች፣ በየቤቱ የሚሸጥ እንጀራ፣ ዳቦ፣ አንባሻና የመሳሰሉ ግብይቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የጀበና ቡና ሽያጭ፣ በየቤቱ በግል ከብት አርቢዎች በኩል እየተመረተ በሊትር ተለክቶ የሚሸጥ ወተትና የወተት ውጤትና ሌሎችም እንደ መደበኛ ያልሆነ ንግድ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፈቃድ ወጥቶላቸው እየተሠራባቸው ለሸማቾች ምርቶቻቸውና አገልግሎቶቻቸውን የሚያቀርቡ ባይሆንም፣ እንዲህ ባሉ ቢዝነሶች ላይ የተሠማሩና የእነዚህን አገልግሎት የሚጠቀሙ ተገልጋዮችና ተጠቃሚዎች ቁጥር ምናልባትም በሕጋዊ መንገድ ግብይት ከሚደረግባቸው ተቋማት የበለጡ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በአጭሩ ሚሊዮኖች ከእነዚህ የአነስተኛ ወይም እንደ መደበኛ ከማይቆጠሩ ቢዝነሶች ጋር የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ዘርፍ እየተስፋፋ ነው፡፡ እነዚህ አነስተኛ ቢዝነሶች ለሽያጭ የሚቀርቧቸው ምርቶች የጥራት ደረጃቸው ለአደጋ የሚዳርግ ወይም ጥራቱን ያልጠበቀ መሆን አለመሆኑ ስለማይታወቅ፣ አደጋ ሲያደርሱ እንኳን የሚታወቅበት መንገድ የለም፡፡ እያንዳንዱ አነስተኛ የቢዝነስ ዘርፎች ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳቶች መዘርዘር አይቻልም፡፡ ይሁንና የሚያቀርቧቸው ምርቶች በጥንቃቄ ካልተያዙ ሊያስከትሉ የሚችሉት ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ ለማሳያ ያህል አንዳንዱን እንደ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በየሱቁና በየመንደሩ የሚቀርበውን እንጀራ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በእያንዳንዱ መንደር እንጀራ በተለይ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ለገበያ እየቀረበ ነው፡፡ የእንጀራ ገበያ እያደገ በርካታ ተገልጋዮችም እንጀራ የመግዛት ልምዳቸው እየሰፋ መምጣቱን ለመታዘብ ይቻላል፡፡ በምኖርበት ኮንደሚኒየም ሳይት በቅርብ የማያውቃቸው ስድስት መደብሮች ውስጥ ያየሁትን በአስረጅነት ማቅረብ እችላለሁ፡፡ ስድስቱም ሱቆች እንጀራ ከሚያቀርቡላቸው ግለሰቦች ተረክበው የተወሰነ የትርፍ ህዳግ ይዘው ይሸጣሉ፡፡ ስድስቱም ሱቆች ጠዋት ላይ 400 እንጀራ ይረከባሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተሽጦ ያልቃል ወይ? እስክል ድረስ ተከምሮ የሚመጣው እንጀራ ማታ ወደቤቴ ስመለስ ባዶ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ ነገሩ ገርሞኝ አንድ ሁለቱን ባለመደብሮች ጠጋ ብዬ ያ ሁሉ እንጀራ አለቀ ብዬ ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እንደውም ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ያስመጡ ስለመሆኑ ነገሩኝ፡፡ እንጀራ አድሮባቸው አያውቅም፡፡ ጥያቄ ስለሚበዛም በተደጋጋሚ ያዛሉ፡፡ ይሸጣሉ፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር የእንጀራ ገበያ ደርቷል፡፡ በአማካይ የመሸጫ ዋጋው ሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው፡፡ አራት ብርና ሦስት ብር የሚሸጥባቸው መደብሮችና ቦታዎች አሉ፡፡ እዚህ ላይ በደንብ መረዳት ያለብን የእንጀራ ሽያጭ ከዳቦ ሽያጭ የማይደራረስ መሆኑ ነው፡፡ እንደውም አሁን ብዙ ዳቦ መሸጫዎች እንጀራንም አጣምረው መሸጥ የመጀመራቸው ሚስጥር ይኸው አዋጭ የመሆኑ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ምሳሌ ያቀረብኳቸውን ስድስት መደብሮችን በተደጋጋሚ ጠይቄ የተረዳሁትም ከዳቦ የበለጠ የእንጀራ ሽያጭ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ አራቱ መደብሮች ዳቦ ስለማያገኙ አያቀርቡም፡፡ ቢያገኙም ትርፍ የሌለው ነው ብለው ስለሚያምኑ ብዙም የሚጨነቁበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተዘጋጅቶ ለገበያ የሚቀርበው እንጀራ የጥራት ደረጃ የተለያየ ነው፡፡ ከሦስቱ መደብሮች በአንድ ቀን አንዳንድ እንጀራ ገዝቼ ወደ ቤት በመውሰድ ስለእንጀራ የሚያውቁ ቤተሰቦቼን ከሦስቱም መደብሮች የገዛኋቸው እንጀራዎች አንድነትና ልዩነትን እንዲያስረዱኝ ሞክሬ ነበር፡፡ ሦስቱም እንጀራዎች ከንፁህ ጤፍ የተሠሩ አለመሆኑን አረጋገጡልኝ፡፡ ‹‹ይኼ በቆሎ ተቀላቅሎበታል፤ ይሄ ደግሞ ማሽላ አለው፤›› ብለውኛል፡፡ አንደኛው ደግሞ ጥሩ ትንፋሽ ያለው ‹‹እፍ ቢለው›› የሚንሳፈፍ ይመስላል፤ ምክንያቱም እጅግ ስስ ነው፡፡ ከንፁህ ጤፍ መዘጋጀት አለመዘጋጀቱን ለማወቅ ከፈለግህ ደግሞ ጠዋት እየው ብለውኝ ነበርና እንደተባልኩት ማታ የገዛሁዋቸውን እንጀራዎች ስመለከት ደርቀው አግኝቻቸዋለሀ፡፡ ገርጥተዋልም፡፡ ይህ ሸማቹ በሰፊው የሚጠቀምበት እንጀራ በዚህን ያህል ዋጋ ሲገዛ በትክክል የጤፍ መሆን አለመሆኑን አረጋግጦ ለመግዛት እንኳን አስቸጋሪም ሆኗል፡፡ ከጤፍ ውጪ ያሉ እህሎች ከተቀላቀሉበትም ይህ ተቀላቅሎበታል ተብሎ ዋጋው ሊቀንስ ይገባ ነበር፡፡ ይህ ግን ሲሆን አናይም፡፡ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ እንጀራው ቆምጥጦ ለጨጓራው ፀር የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለም እንዳንዘነጋ፡፡ ይህ ከሆነ ለሚሊዮኖች እየቀረበ ያለው እንጀራ የጥራት ደረጃ ሊኖረው እንደሚገባ ያመላክተናል፡፡ ባልተገባ መንገድ ለመበልፀግ ሲባል ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች ቢኖሩበትስ? አሁን ባለው ገበያ ከእንጀራ ያነሰ ገበያ ያለው ዳቦ ግን የጥራት ደረጃና ልኬት ወጥቶለታል፡፡ ይህንን ያህል ግራም ያለው ዳቦ መሸጥ ያለበት በዚህን ያህል ነው ተብሎ ቁጥጥር ይደረግበታል፡፡ እንጀራ ግን በዚህ ያህል ደረጃ ክትትል አይደረግበትም፡፡ ለምን? ከእንጀራ ውጪ በየቤቱ የሚዘጋጁ የባልትና ውጤቶችም በተመሳሳይ የሚታዩ ናቸው፡፡ በርበሬ፣ ሽሮ፣ በሶ እንዲሁም ሳምቡሳና በዘይት የሚጠበሱ ብስኩቶችን ስናስብ አዘገጃጀታቸው ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው፡፡ በተለይ እንደ በርበሬና ሽሮ ያሉ ምርቶች ብዙ ተጠቃሚ ያላቸውና በየዕለቱ የምግብ ገበታዎች ላይ የምንመገባቸው ምግቦች የሚሠሩባቸው ናቸው፡፡ ግን እነዚህም እንዴት እንደተዘጋጁ አይታወቅም፡፡ በርበሬው ሸክላ ይከለስበት፤ ሽሮው ርካሽ የሆነ ተመሳሳይ ባዕድ ነገር ይግባበት ባናውቅም አምነን ገዝተን እንጠቀምባቸዋለን፡፡ በተለይ ከተሜው እንደቀድሞው በቤቱ ማዘጋጀትን እያቀዘቀዘው በመሆኑ፣ በየመደብሩ ለገበያ የሚቀርቡ የታሸጉ በርበሬና ሽሮ ተጠቃሚ ከመሆኑ አንፃር ደረጃቸው ሊታወቅ አይገባም? እንዲህ ያሉ ምርቶች በዘፈቀደ እየተሸጡ በፋብሪካ ብቻ የተመረቱ ምርቶች የጥራት ደረጃ እየወጣላቸው ቁጥጥር ይደረግባቸዋል መባሉስ ምን ያህል አግባብ ይሆናል? የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ስላለፈ ከሼልፍ እንዲነሱ እያደረግን ነው ማለቱስ የሚያዋጣ ይሆናል? የበርበሬና የሽሮ የመጠቀሚያ ጊዜ ምን ያህል ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ ሊመለሱ ይገባል፡፡ ስለዚህ የጥራትና ደረጃ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ቁጥጥሩንና የደረጃ ምዘናውን መስጠት ያለበት እስካሁን ሲሠራበት በቆየው መንገድ ሳይሆን ኅብረተሰቡ በብዛት እየተጠቀመባቸው ያሉ እንዲህ ያሉ ምርቶችን ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡ የጥራት የደረጃና የልኬት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች እይታም ኅብረተሰቡ በብዛት ከሚጠቀምባቸው ምርቶች ጋር መያያዝ እንዳለበት በማመን ዕቅዱ እነዚህንም ምርቶች ማካተት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉንም መደበኛ ባልሆኑ ምርቶች ላይ አሁኑኑ መዝመት ባይቻልም ወይም አሁኑኑ ቁጥጥሩ ይጀመር ብሎ መናገር ባይችልም ቢያንስ እንጀራ፣ የባልትና ውጤቶችና የመሳሰሉ ምርቶች ላይ የጥራት ደረጃ ልኬት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ በየመንደሩ የሚሸጠው ወተት ውኃ ተቀላቅሎበት ሲሸጥ ጠያቂው ማነው? በየመንደሩ ጥራቱን ባልጠበቀ ዘይት ተጠብሰው ካማሩ ካፌዎች ባለመስታወት ሸልፎች ላይ የሚሸጡ ብስኩቶች እንዳሉስ ይታወቅ ይሆን? ነገሩን የዚህን ያህል መፈተሽ አለብን፡፡ መጠጥ የሚበረታታ ባይሆንም በባህላዊ መንገድ የሚመረቱና የሚቀርቡ መጠጦች ከተጠቃሚዎች ብዛት አንፃር ሲታይ ያሳስባል፡፡ በአንፃሩ ግን በጠርሙዝ የሚታሸጉ መጠጦች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ የቢራ ተጠቃሚ ነው ወይስ የጠላ፣ የአረቄና የጠጅ ተጠቃሚ የሚበዛው? ስንል፣ ነገሩ ምን ያህል ሊያሳስብ እንደሚችል ሳያመላክት አይቀርም፡፡ ስለዚህ ነገሩ ትንሽ ቢመስልም የዜጎች ጉዳይ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ዘርፎችን መፈተሹ ያሻል፡፡ ቢያንስ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ስለሚያስፈልጉ፣ የአነስተኛ ቢዝነሶች ጉዳይ ይታሰብበት፡፡ በተለይ በየዕለቱ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚመረቱ ምርቶች እንዴት ቁጥጥር ይደረግባቸው የሚለው ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቆጣጠሪ አካላት የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዳቦ ደረጃ ማውጣት ከተቻለ ለእንጀራና ለበርበሬ ማውጣት ይከብዳል ተብሎ አይታመንም፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት