Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ቤቶች ኮርፖሬሽን ነባር ይዞታዎችን ለማስጠበቅ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ሊዋዋል ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በቅርቡ በ33.1 ቢሊዮን ብር ካፒታል በድጋሚ የተቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ በመሀል ከተማ የሚገኙ ነባር ይዞታዎችን ለማስጠበቅ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የስምምነት ሰነድ ሊፈራረም ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በራሱ ይዞታ ሥር የሚገኙ ቪላ ቤቶችን በማፍረስ፣ ዘንድሮ ሦስት ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት እየተዘጋጀ ነው፡፡

  በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንና በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መካከል በዚህ ሳምንት ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቀው ስምምነት የኮርፖሬሽኑ ነባር ይዞታዎችን ከማስጠበቅ በተጨማሪ፣ አዳዲስ ግንባታ ለማካሄድ አመቺ ያልሆኑ ቦታዎችን በአመቺ ቦታዎች የመለወጥ ዓላማም ሰንቋል፡፡

  በ1967 ዓ.ም. የተቋቋመው የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር በብዙ መዋቅሮች ውስጥ አልፎ በመጨረሻ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ‹‹የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን›› በሚል ስያሜ በድጋሚ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡

  ኮርፖሬሽኑ በተቋቋመበት ወቅት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉት ይዞታዎች በልማት ምክንያት እየፈረሱ እንደመሆኑ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኮርፖሬሽኑ እንዲቋቋም በወሰነበት ዕለት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የሚገኙ ይዞታዎቹ እንዳይነኩ ጭምር ውሳኔ አሳልፏል፡፡

  በዚህ መሠረት የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ ለሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች በጻፉት ደብዳቤ የኮርፖሬሽኑን ይዞታ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው እንዳይሰጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

  በዚህ ላይ በመመርኮዝ ኮርፖሬሽኑና የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ስምምነት ለመፈራረም መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

  የኮርፖሬሽኑ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በስምምነቱ መሠረት የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በመልሶ ማልማት አካባቢዎች የሚገኙ የኮርፖሬሽኑን ይዞታዎች ከመገንባቱ በፊት ውይይት ይደረጋል፡፡ በተለይ ኮርፖሬሽኑ አዲስ ግንባታ ለማካሄድ የቦታው አቀማመጥና ስፋት አነስተኛ ከሆነ አስተዳደሩ የሚያስፈልገውን ካፈረሰ በኋላ፣ ላፈረሳቸው ይዞታዎች ሰፋ ያለ ተለዋጭ  ቦታ ለኮርፖሬሽኑ ይሰጣል፡፡

  ላለፉት 26 ዓመታት ከመኖሪያ ቤት ግንባታ ውጪ የተደረገው ኮርፖሬሽኑ፣ በ2010 በጀት ዓመት ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኮርፖሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት ሦስት ሺሕ አፓርትመንቶች በተለያዩ ቦታዎች ለመገንባት በጨረታ ሒደት ላይ ነው፡፡

  ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ራሱን በማደራጀት ላይ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ33.1 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል፣ በ11.04 ቢሊዮን ጥሬ ብር የተቋቋመ ግዙፍ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች