Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ምሩፅ የቦንጋው ‹‹ማርሽ ቀያሪ››

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከስድስት ዓመት በፊት የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ነበር፡፡ በሙያው ገበሬዎችን ሲያግዝ ቆየ፡፡ እንደግብርና ባለሙያነቱ ስለግብርና ምክርና ድጋፍ ሲያደርግ ኖረ፡፡ ቆየና ግን ወደ ራሱ የግብርና ሥራ ፊቱን አዞረ፡፡ ንብ አናቢው ምሩፅ በቡና እርሻና በሌሎችም ግብርና ነክ ሥራዎቹ በከፋዋ መናገሻ ቦንጋ ከተማ በሰፊው ይታወቃል፡፡ ወጣቱ ምሩፅ ሀብተማርያምና ቤተሰቡ የሚኖሩበት አንድ ተኩል ሔክታር መሬት በርካታ ዘመናዊ፣ መካከለኛና ባህላዊ የንብ ቀፎዎች ሲኖሩት፣ በዘመናዊ መንገድ የተጣራ ማር ያመርትበታል፡፡ ዝናውን የሰሙ ጃፓናውያንም ገበያ ፈጥረውለታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚያመርተው የማር ጥራት ጃፓናውያን ከሚፈልጉት የጥራት ደረጃ ላይ የደረሰ ከመሆኑም ባለፈ ተፈጥሯዊ ጣዕሙ ቢያማልላቸውም፣ በአቅርቦቱ ደስተኞች መሆን እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡ ዝቅተኛ መግዛት የሚፈልጉት መጠን በዓመት 300 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ምሩፅ ግን በግማሽ ተወስኖ 150 ኪሎ ግራም ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ይህንን ሁሉ በራሱ ጥረት ብቻ ሲያደረግ እንደቆየ ይገልጻል፡፡ ይህንን ጥረቱንና በቦንጋ ከተማ ያለውን ዕውቅና ያዩ ጃፓኖች ቀረቡት፡፡ በተለይ በበጎ ፈቃደኝነት በከፋ ዞን ከሚንቀሳቀሱት ጃፓናውያን አንዷ የሆነችው ኢሪ ሒራያማ በገበያ ማፈላለጉ ተግባር ምሩፅን እያገዘች ከጃፓን ገዥዎች ጋር አገናኝታዋለች፡፡ የምሩፅ የቦንጋ ማር ጃፓናውያን ዘንድ የማይገኝ ጣዕምና ይዘት እንዳለው የጃፓን ኩባንያዎች ማረጋገጣቸውን ኢሪ ገልጻለች፡፡ ከአዲስ አበባ 460 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው ቦንጋ ከተማ የሚመረተውን ማር ላቢዩ የተባለ የጃፓን ሱቅ እየገዛ ይገኛል፡፡ የሚያመርተውን በሙሉ እየገዙት ከመሆኑም አልፎ ጃፓናውያን ተጠቃሚዎች አስተያየታቸውን በኢሜል እየገለጹለት እንደሚገኝ፣ ሕፃናት ሳይቀር ማሩን ቀምሰው እንደወደዱለት መልዕክት ልከዋል፡፡ ምሩፅ ከራሱና ከቦንጋ አልፎ ኢትዮጵያን የሚወክልበት ምርት ለማቅረብ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ እንደማሩ ሁሉ በቡናውም መስክ ከፋ የምትታወቅበትን ጣዕም የተሞላ ቡና ለማምረት በርካታ የቡና ችግኞችን አፍልቶ ተክሏል፡፡ የከፋ ዞን የቡና መገኛ መሆኑን በሚያመላክት መልኩ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም በቦንጋ እየተነገባ ይገኛል፡፡ የሙዚየሙ መሠረት ድንጋይ በ1999 ዓ.ም. የተጣለ ቢሆንም ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው በዚህ ዓመት ውስጥ ምናልባትም ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ለግንባታው 60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የቦንጋው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም፣ የመላ አገሪቱን ባህላዊና ቁሳዊ ሀብቶች ለማንፀባረቅ ያለመ ተቋም ነው፡፡ በዚህ ሙዚየም የወደፊት አሠራር ላይ ለሚሳተፉ የሙዚየም ባለሙያዎች ሥልጠና ከሚሰጡት መካከል ወጣቱ በጎ ፈቃደኛ ጃፓናዊ ሒዳኪ ኦትሱዋ ይገኝበታል፡፡ ሒዳኪ ወደፊት በሚከፈተው ሙዚየም ውስጥ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው ለሚታሰቡ ሰዎች፣ የቅርስ አጠባበቅ፣ አመዘጋገብና አያያዝ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ሱባሳ ሐጊዋራም በግብርናና በአካባቢ ጥበቃ መስኮች ላይ ለተማሪዎች ሥልጠና በመስጠት ይታወቃል፡፡ በቀድሞው ሾታ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት ቢሻው ወልደዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚማሩ፣ የአካባቢ ጥበቃ ክበብ አባላት ለሆኑ ተማሪዎች፣ የችግኝ አፈላል፣ የደን ክብካቤና የመሳሰሉትን ሥልጠናዎች በመስጠት ያግዛል፡፡ በአካባቢው ጉብኝት ያደረጉ የጃፓን ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች ለዝግባ ዛፍ የሚውል ችግኝ ለማፍላት ተማሪዎች ዘር ሲተክሉ ታድመዋል፡፡ በአገሪቱ አራት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተሰራጭተው ከሚገኙት 48 ያህል በጎ ፈቃደኛ ጃፓናውያን መካከል በርካቶች በትምህርት ቤቶች፣ በአካባቢና በመሳሰሉት መስኮች ላይ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ የቡና ታሪክን ከከፋ መነሻ የሚያደርገው ይህ ሙዚየም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩትን ባህላዊ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓቶችና መገልገያዎችን ለማሳየት ያለመ ነው፡፡ ሕንፃው ብቻ በ2826 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ከመሆኑም በላይ የሕንፃው ምሰሶ፣ የዘነዘናና የሙቀጫ ቅርፅ እንዲኖረው ተደርጎ ታንጿል፡፡ ምንም እንኳ ከፋ ከሚለው ቃል ‹‹ኮፊ›› የሚለው የእንግሊዝኛውን ስያሜ እንደወጣ ቢነገርም፣ በአንፃሩ ጅማዎች የቡና መገኛ መሆናቸውን የሚያሳውቁባቸው አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ፡፡ በቦንጋና በጅማ ከተማ መካከል የሚታየውን የቡና መገኛ ሥፍራነት ጥያቄን ምላሽ የሚሰጡ ወጥ የታሪክ ሥራዎችና አዋቂዎች ምርምር ማድረግ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡ ከዚህ ባሻገር ምንም እንኳ ቦንጋ ከተማ ለከተማነት የሚመጥን ገጽታ ባይታይባትም በውስጧ ቱሪስታዊ መስህቦችን አቅፋለች፡፡ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ከከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውና 67 ሜትር ቁልቁል የሚወረወረው የገርቻ ፏፏቴ አስገራሚ መስህብነት አለው፡፡ ፏፏቴውን ለማየት በእግር እስከ 30 ደቂቃ መጓዝንና ሽቅብ ቁልቁል ማለትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ የተፈጥሮን መስህቦችና የመልክዓ ምድሮችን አቀማመጥ ለማድነቅ ለሚመጡ ቱሪስቶች የሰጠ ቦታ ነው፡፡ አካባቢውን የዕረፍት ቀናትን ተገን አድርገው የሚመጡ የአገሬው ሰዎች የመዝናኛ ቦታ አድርገው ያዘወትሩታል፡፡ ሌሎች ደግሞ አካባቢውን ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች እንዲመች አድርጎ በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ሊያደርገው የሚችል አካል መጥፋቱ ያስገርማቸዋል፡፡ ከዚህ ፏፏቴ ባሻገር በቦንጋ ከተማ የሚገኘው ማኪራ የተባለ ሥፍራ ዋናው የቡና መገኛ ሊሆን፣ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩና የሸበቱ የቡና ዛፎች መገኛ ነው፡፡ የጅማን ያህል ባይሆንም በከፋም ሕዝቡ ከጫካ ቡና መጠነኛ ጥቅም ለማግኘት ሲሞክር ይታያል፡፡ ከፋ በብዛት በደናማነቱ የሚታወቅ ዞን ሲሆን፣ በተለይ በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ ግን የደን ይዞታዎች እየሳሱ መምጣታቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎችና ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቢሻው ወልደዮሐንስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚገልጹት ነው፡፡ የከፋ ዞን አስተዳደር ያሰራጨው መረጃ እንደሚጠቁመው ከፋ የጫካ ማር፣ የሻይ ልማት፣ የቅመማቅመምና ሌሎችም የግብርና ውጤቶች መገኛ ነው፡፡ በቡና ረገድ በጓሮ፣ በባለሀብት የለማና በጫካ ቡና የሚከፋፈል ምርት በዞኑ ይገኛል፡፡ በጓሮና በጫካ እንዲሁም በከፊል የጫካ ቡና የሆነው የቡና መጠን ከ93 ከመቶ በላይ ድርሻ አለው፡፡ በእንስሳት ረገድም የከፋ በግ ከሌሎች የአገሪቱ ዝርያዎች አኳያ በሥጋ ይዘቱና ጣዕሙ የተሻለ ሆኖ መውጣቱ ለዞኑ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል፡፡ በጃፓን ኤምባሲ ሚኒስትር ቆንጽላ ኬንጂ ዮኮታ የመሩትና ለሦስት ቀናት በጅማና በቦንጋ ከተሞች ቆይታ ያደረገው የልዑካን ቡድን፣ በሁለቱ ከተሞች ውስጥ የጃፓን መንግሥት በሚሰጣቸው ድጋፎች የሚካሔዱ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ጎብኘቷል፡፡ ኬንጂ ዮኮታ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ በተለይ በጅማ የጫካ ቡናና የደን አጠባበቅ ላይ መንግሥታቸው ከሚሰጠው ድጋፍ ባሻገር በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ የተፈጥሮ ቡና ላይ የሚያተኩር የኢቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ይፈጠራል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ መስክ የሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የቦንጋው ምሩፅና መሰሎቹም ዛሬን ከተፈጥሮ እየታገሉ ነገን ሌላ ቀን ለማድረግ የሚያሳዩት ትጋት ነገን ያስናፍቃል፡፡ ምሩፅ ከፈተናዎቹ ሁሉ እንደልቡ ለማደግ ያላስቻለው የፋይናንስ እጥረት መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህም ሆኖ በርካታ ሠራተኞችን ቀጥሮ በማሠራት፣ የእርሻ ማሳያውን የሠርቶ ማሳያ በማድረግ፣ እሱ ወደ እርሻ ሲገባ አይዞህ ባይ በማጣት መቸገሩን ያስታውሳል፡፡ ሌሎች ላይ እሱ የደረሰበት እንዳይደርስ ለማገዝ ማሳውን ለዚህ ሥራ ማዘጋጀት ይፈልጋል፡፡ አሁን ላይ ከአንድ ቀፎ የሚያገኘውን 20 ኪሎ ግራም የተጣራ ማር ወደ 50 ኪሎ ግራም ማድረስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመተግበርና ለጃፓን ገበያ በብቃት ለማቅረብ የወጠነው ነው፡፡ ስያሜውን ያገኘው ማርሽ ቀያሪው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር (ምሩፅ ዘ ሺፍተር ይሉታል ነጮቹ) ታሪክ በሠራበት የሩጫ ውድድር ወቅት በመለወዱ፣ የቦንጋው ምሩፅ የአትሌቱን ስም ወላጆቹ ሰጥተውታል፡፡ የግብርናው ምሩፅ ለመሆን እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች