Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የግል ተወዳዳሪዎች ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ዘንድሮ 20ኛ ዓመቱን የደፈነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ የመንግሥት ሥልጣን በሕዝቦች ይሁንታ በሚመረጡ ተወካዮች አማካይነት ወይም በፓርላሜንታዊ ሥርዓት እንደሚመሠረት ይደነግጋል፡፡ ይህንንም መሠረታዊ ድንጋጌ ተከትሎ ማንኛውም ከ21 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ የመምረጥ፣ እንዲሁም ከአሥር ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ የመመረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት አግኝቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀና ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1987 ዓ.ም. በአገሪቱ በተካደው አገር አቀፍ ምርጫ፣ የግለሰቦች በፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጐትና ሚና ከምንጊዜውም በላይ ጐልቶ ይታይ እንደነበረ በወቅቱ የነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በወቅቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የላላ ድርጅታዊ መዋቅርና የአቅም ችግር፣ እንዲሁም የኅብረተሰቡ ለሰላማዊ ድርጅታዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ያለው ግንዛቤ አናሳነት ለግል ተወዳዳሪዎች የጐላ የፖለቲካ ሚና አስተዋጽኦ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በወቅቱ ከነበሩት ሰባት ፓርቲዎች መካከል አራቱ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደረሰብን ባሉት ተፅዕኖ ራሳቸውን ከምርጫው ሲያገሉ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በመባል ይታወቅ የነበረው በአቶ ነብዩ ሳሙኤል የሚመራው ፓርቲ ብቻ በመጀመሪያው ምርጫ ተሳታፊ ነበር፡፡ በወቅቱ በተካሄደው ምርጫ 2,714 ዕጩ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዕጩ ተወዳዳሪዎቹ መካከል 1,881 የሚሆኑት ከ58 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ 58 ፓርቲዎች አብዛኞቹ የገዥው ፓርቲ አጋርና ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ከተጠቀሱት ዕጩ ተወዳዳሪዎች የተቀሩት ማለትም 960 የሚሆኑት ግን የግል ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን የፓርላማ ወንበር ማግኘት የሚያስችላቸውን አሸናፊ ድምፅ ያገኙት አሥር የግል ተወዳዳሪዎች ቢሆኑም፡፡ ሁለተኛው አገራዊ ምርጫ የተካሄደው ኢትዮጵያ በኤርትራ መንግሥት የተቃጣባትን ወረራ ለመመከት ጦርነት ውስጥ በገባችበት በ1992 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዚህ የምርጫ ወቅት የነበረው የግል ተወዳዳሪዎች ተሳትፎ በውጤት ጭምር የተሻለ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ ምክንያት በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ከአገር አቀፍ ምርጫው ዘግይቶ ነበር፡፡ በመሆኑም በነሐሴ ወር 1992 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ በፌዴራል ፓርላማ ውስጥ ክልሉ ያለውን 23 መቀመጫና የክልሉ ምክር ቤት 168 ወንበሮችን ለማሸነፍ ከተወዳደሩት ፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ 156 የግል ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን በዕጩነት ማቅረባቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በሶማሌ ክልል የነበረው የግል ተወዳዳሪዎች ተሳትፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ላለው የግል ዕጩዎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ጉልህ ማሳያ ይሆናል፡፡ በወቅቱ 460 የግል ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን በዕጩነት አቅርበው ነበር፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ የወቅቱ የምርጫ ውጤት መሠረት 13 የግል ተወዳዳሪዎች የፓርላማ መቀመጫን ሲያገኙ፣ ከ17 ተቃዋሚ ፓርቲዎች 12 ያህሉ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምርጫዎች ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ ውክልናና አማራጭ የፖለቲካ ሐሳብ መፍለቂያዎች የግል ተወዳዳሪዎች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የግል ተወዳዳሪዎች ከ1997 በኋላ ሦስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሽና በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ ጐኑ አሻራውን ያሳረፈ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የግል ተወዳዳሪዎችን ሚና መቃኘት እንደመሆኑ፣ ከ1997 የምርጫ ዘመን በኋላ የግል ተወዳዳሪዎች የነበራቸው ተፅዕኖ ይዳስሳል፡፡ ምርጫ 1997 ከመጀመሩ ጥቂት ጊዜያት ቀደም ብሎ በአገሪቱ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ‘አክቲቪስቶች’ ራሳቸውን በአንድ ለማደራጀትና ተፅዕኖአቸውን ለማጐልበት ያደረጉት ሥልታዊ እንቅስቃሴ፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ደብዛ ያጠፋ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተናጠልና ጥንካሬ በሌለው ሁኔታ የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ፓርቲዎች ራሳቸውን አቀናጀተው በምርጫው ለመሳተፍ ያደረጉት እንቅስቃሴ፣ በገዥው ፓርቲ የጐላ የፖለቲካ ተፅዕኖ ተሞልቶ የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት መፈተን ችሎ ነበር፡፡ በእጅጉ አጨቃጫቂ በነበረው በዚህ አገር አቀፍ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት የቻሉት ብቸኛው የግል ተወዳዳሪ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ናቸው፡፡ ከአጠቃላይ 547 የፌዴራሉ ፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ 327 የሚሆነውን ኢሕአዴግ ሲያገኝ፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) 109 መቀመጫዎች፣ የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኅብረት) 52 መቀመጫዎች፣ እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) 11 መቀመጫዎች በማግኘት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 172 መቀመጫዎችን በመያዝ በግል ተወዳዳሪዎች ተይዞ የነበረውን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ከሞላ ጐደል እንደዋጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ላይም ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ተፅዕኖ የጐላ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በፖለቲካ ውስጥ ሚናቸውን ለማጉላት ከሚያደርጉት ትግል በተጨማሪ፣ በመንግሥት የሚቀርብባቸውን የወንጀል ክስ መከላከል የወቅቱ ፈተናቸው ነበር፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ በመሆንም ከግል ተወዳዳሪዎች የተሻለ ተፅዕኖ ቢፈጥሩም፣ በመጨረሻ የፓርላማ መቀመጫ በማግኘት ረገድ ውጤታቸው ኢምንት ነበር፡፡ በ1997 ምርጫ ራሳቸውን በዕጩነት ያቀረቡ የግል ተወዳዳሪዎች 353 የነበሩ ቢሀንም፣ ከላይ ለመግለጽ እንደ ተሞከረው በፓርላማ መቀመጫ ያገኙት ዶ/ር ነጋሶ ብቻ ነበሩ፡፡ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ራሳቸውን በዕጩነት ያቀረቡ የግል ተወዳዳሪዎች ቁጥር ከምን ጊዜውም በታች በማሽቆልቆል 34 መሆኑን ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህ በአራተኛው የምርጫ ዘመን ከተወዳደሩ የግል ዕጩዎች መካከል የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የቻሉትም በደቡብ ክልል በካፋ ዞን በቦንጋ ከተማ የተወዳደሩት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ይገኙበታል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የፓርላማው መቀመጫ 99.6 በመቶ በገዥው ፓርቲ (አጋሮቹን ጨምሮ) የተያዘ ሆኗል፡፡ አምስተኛው አገራዊ ምርጫ በዚህ ዓመት በግንቦት ወር እንደሚካሄድ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቦርዱ ባስታወቀው የጊዜ ሰሌዳ መሠረትም የግል ተወዳዳሪዎች መመዝገቢያ ወቅት ተጠናቆ፣ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ የግል ተወዳዳሪዎች በዚህ በአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚኖራቸው ሚና ለመወዳደር በተዘጋጁ ግለሰቦች ይወሰናል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ግለሰቦች ወይም ቢያንስ ካለፈው የምርጫ ዘመን ጋር የሚጣጣም ቁጥር የሚጠበቅ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በዚህ የምርጫ ዘመን የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ራሳቸውን ዕጩ ያደረጉ የግል ተወዳዳሪዎች አምስት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ በአዲስ አበባ፣ አንድ በደቡብ ክልልና ሦስት በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የግል ፖለቲከኞች የምርጫ ተሳትፎ በአፍጢሙ እየተደፋ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ለምን? ከምርጫ 1997 በኋላ መንግሥት የተለያዩ የምርጫ ሕጎችን አውጥቷል፣ የነበሩትንም አሻሽሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1999 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግና በ2002 ዓ.ም. የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ይገኙበታል፡፡ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ የዕጩዎች ብዛትን ስለመለየት በሚደነግገው አንቀጽ 49 ሥር አራት ንዑስ አንቀጾችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው ንዑስ አንቀጽ በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡ በንዑስ አንቀጽ ሁለት ሥር የዕጩዎች ብዛት ከ12 ከበለጠ በቅድሚያ በዕጩነት እንዲመዘገቡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ለቀረቡ ዕጩዎች ዕድሉን ይሰጣል፡፡ በፓርቲዎች የቀረቡት ዕጩዎች ከ12 በላይ ከሆኑ ባለፈው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ላገኙ ከስድስት የማይበልጡ ድርጅቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ ይፈቅዳል፡፡ በፖለቲካ ድርጅቶች (ፓርቲዎች) የቀረቡ ዕጩዎች ከአሥራ ሁለት በታች ከሆኑ፣ የተቀሩት ቦታዎች ባለፈው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ባገኙ የግል ተወዳዳሪዎች እንዲሞላ ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሙሉ በሙሉ የግል ተወዳዳሪዎችን ሚና የሚቀንስና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ ማቅረብ ሳይችሉ ሲቀሩ ብቻ የተሳታፊነትን ዕድል የሚሰጣቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ በ2002 ዓ.ም. የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ተፈጻሚነቱ በግል ተወዳዳሪዎችም ላይ ቢሆንም፣ በዚሁ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት በሚቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ውስጥ የግል ተወዳዳሪዎች የሚኖራቸው ሚና ታዛቢነት ብቻ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ በአዋጁ ከተሰጡት ሥልጣኖች አንዱ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ደንቦችና መመርያዎችን አስመልክቶ ረቂቅ ሐሳብ በማዘጋጀት ለቦርድ ማቅረብ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ወሳኝ ኃላፊነት ውስጥ ግን የግል ተወዳዳሪዎች ከታዛቢነት ያለፈ ሚና አይኖራቸውም፡፡ መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠው የፋይናንስ ድጋፍ የሚከፋፈልበት ደንብ የወጣው በ2001 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይህም ድንጋጌ የግል ተወዳዳሪዎችን አያካትትም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታና በፓርላማ የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ መንግሥት የግል ተወዳዳሪዎችን እንደማያበረታታና በፖለቲካ ውድድር ውስጥ እንዲኖሩ እንደማይፈልግ ከሁለት ዓመት በፊት ምርጫ ቦርድ ለጋዜጠኞች በሰጠው ሥልጠና ላይ ተገኝተው አብራርተው ነበር፡፡ የሰጡት ምክንያትም ለአገሪቱ የሚጠቅመው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መሆኑንና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቦርዱ የግል ተወዳዳሪዎችን በገንዘብ እንደማይደግፍ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ‹‹የግል ተወዳዳሪዎች (ዕጩዎች) በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና ቦርዱ ዝቅ አድርጐ አይመለከትም፡፡ ነገር ግን ከዚያ በላቀ በፓርቲዎች ሚና ላይ ያተኩራል፤›› ብለዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፉክክር ጐልቶ የግል ተወዳዳሪዎችን በዋጠበት ወቅት በብቸኝነት ፓርላማውን የተቀላቀሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ከሪፖርተር ጋር በኢሜይል ባደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ፣ በተወዳደሩበት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ደንቢዶሎ የተፎካከሩዋቸው የገዥው ፓርቲ አካል የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ተወካይ፣ በአሁኑ ወቅት በአምባሳደርነት እያለገሉ የሚገኙት አቶ ሰለሞን አበበ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ‹ከኦሕዴድ ዕጩ ተወዳዳሪ ይልቅ የገንዘብ እጥረት እክል ሆኖብኝ ነበር፡፡ ተፎካካሪዬንማ በሚወዳደርበት ቀበሌ ጭምር አሸንፌዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ለምረጡኝ ዘመቻ ወደሚወዳደሩበት አካባቢ በሚሄዱበት ጊዜ የሚያርፉት እህታቸው ቤት እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ነጋሶ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ጓደኞቻቸው የገንዘብ መዋጮ አድርገው እንደረዷቸውም አልሸሸጉም፡፡ በ2002 ዓ.ም. በኢሕአዴግና አጋሮቹ የተሞላውን ፓርላማ የተቀላቀሉት ብቸኛው የግል ተወዳዳሪና በተለያ የንግድ እንቅስቃሰዎች ውስጥ የሚሳተፉት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. የበጀት ዓመቱን የመንግሥት ዝርዝር የሥራ ዕቅድ ለፓርላማው ለማቅረብ ለተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያቀረቡት ጥያቄም ይህንኑ የገንዘብ ድጋፍ የተመለከተ ነበር፡፡ በርካቶች እንደሚያስታውሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መልስ ዶ/ር አሸብርም ሆነ ሌላ የግል ተወዳዳሪ በግል ፖለቲካ ውስጥ ከመሳተፍ ይልቅ፣ የመረጠውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲቀላቀል የሚመክርና መንግሥት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የማጐልበት ኃላፊነቱን በቅድሚያ እንደሚወጣ የሚያስረግጥ ነበር፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች መንግሥት የተከተለው መንገድ በፖሊሲ ደረጃ ከሚከተለው የቡድን መብት (ግሩፕ ራይት)፣ እንዲሁም ይህንኑ ከሚያስተጋባው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አንፃር ሲነፃፀርም ህፀፅ የለውም ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በገዥው ፓርቲ ጫናም ሆነ በመንግሥት ተፅዕኖ ወይም በራሳቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች የተበታተነና የተዳከመ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ይሁንታ አግኝተው በፓርላማ አማራጭ የፖለቲካ ድምፆችን ማሰማት ያልቻሉበት ደረጃ መድረሱ በ2002 ምርጫ በገሀድ ታይቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ገዥው ፓርቲን ያልመረጡ ዜጐች ድምፅ እንዴት ይደመጣል የሚለው ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጐላ የመጣበት ወቅት ሆኗል፡፡ (ነዓምን አሸናፊ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -