[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ነጋዴ ደወለላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ውይ በጣም ስፈልግህ ነው የደወልክልኝ፡፡
- በሰላም ነው የፈለጉኝ?
- ኧረ በጣም ለሰላም ነው፡፡
- አይ ያው ሰላም የሚለውን ቃል ከሰማሁት ራሱ ስለቆየ ነው የጠየኩዎት?
- እኔ እንኳን የደስታ ዜና ይዤ ነው፡፡
- በዚህ ጊዜ ምን የሚያስደስት ነገር አለ ብለው ነው?
- ሕንፃዬ ሊመረቅ ነው፡፡
- እ. . .
- ለምርቃቱ ልጠራህ ሳስብ ነው የደወልከው፡፡
- የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- የምርቃት ፕሮግራም አዘጋጅተዋል ማለት ነው?
- ቀላል ፕሮግራም እንዳይመስልህ ያዘጋጀሁት፡፡
- ማለት?
- ባንድ ሁላ ጠርቼአለሁ ስልህ?
- ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕንፃ ነው የሚመረቀው ወይስ ሌላ አገር?
- እዚህ ያለው ሕንፃ ነው እንጂ፡፡
- አገር ውስጥ የሉም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ከአገሬማ ወዴት እሄዳለሁ?
- ታዲያ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አያውቁም እንዴ?
- ከልማት ውጪ ምን አለ ብለህ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ከጥፋት ውጪ ለማለት ፈልገው ነው?
- ፀረ ልማት ሆነሃል ልበል?
- ክቡር ሚኒስትር ተው እንጂ፡፡
- ምኑን ነው የምተወው?
- አገሪቷ እኮ ታምሳለች፡፡
- ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን በል፡፡
- ይኸው የመንግሥት ጆሮ ተደፍኖ አይደል እንዴ?
- ምን እያልክ ነው አንተ?
- ያው መስማት ካቆማችሁ ሰነባበታችሁ ለማለት ነው፡፡
- ምንድነው የምትቀባጥረው?
- ክቡር ሚኒስትር ዛሬ ቀኑን ሙሉ ሳለቅስ ነበር፡፡
- ምነው ዘመድ ሞተብህ እንዴ?
- ከዘመድም በላይ ነው የሞተብኝ፡፡
- ማን ሞተብህ?
- አገር ናታ፡፡
- ሰውዬ ምንድነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ እኮ እያለቀ ነው፡፡
- የሶሪያ ሕዝብ ነው ያለቀው?
- እንዴ ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አልኩ?
- ሕዝብ በሕዝብ ላይ እየተነሳ እኮ ነው፡፡
- እሱማ ምልክቱ ነው፡፡
- የምን ምልክት?
- የመጨረሻው ዘመን ነዋ፡፡
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በዚህ ጊዜ ቀልድ ይቀለዳል እንዴ?
- ካልቀለዱማ አገሪቷ ከመፈራረሷ በፊት አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡
- አገር እኮ ዝም ብላ አትፈርስም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እያየነው ያለው ነገር ግን በጣም ያስፈራል፡፡
- ምን አየህ?
- ይኸው አገሪቷ በነውጥ ጎዳና መጓዝ ከጀመረች ሰነባበተች፡፡
- ጊዜያዊ ችግር ነው፡፡
- ጊዜያዊ ችግር ሲሉ?
- ዕድገታችን ያመጣው ችግር ነው ስልህ?
- የምን ለቅሶ መልሶ መላልሶ አሉ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ ላይ እየተከናወነ ስላለው ነገር ለመሆኑ በሚገባ ያውቃሉ?
- እህሳ?
- ለማንኛውም በሰሞኑን ግርግር የእኔም ሱቅ ተቃጥሏል፡፡
- ሱቅህ ስለተቃጠለ ነው አገሪቷ ልትፈርስ ነው የምትለው?
- ክቡር ሚኒስትር የወደመብኝ ንብረት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚያ ላይ በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡
- አየህ ሠርተህ ስትለወጥ ሰዎች ስለማይወዱ፣ ለዛ ነው ንብረት የሚያወድሙት፡፡
- እና አገሪቱ ለነጋዴዎች አትሆንም እያሉኝ ነው?
- ለነጋዴዎችማ አትሆንም፡፡
- ታዲያ ለማን ነው የምትሆነው?
- ለወንበዴዎች!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ብሎገር ጋ ደወሉ]
- አቤት ጌታዬ፡፡
- ሥራ እንዴት ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ወጥሬ ይዣለሁ፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- ይኸው ቀን አልል ማታ ፖስት ሳደርግ ነው የምውለው፡፡
- ለመሆኑ ምን ዓይነት ይዘት ያለው ነገር ነው የምትጽፈው?
- በተሰጠኝ መመርያ መሠረት ነዋ፡፡
- እኮ ምን ዓይነት ነው?
- ከተቻለ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ፡፡
- እሺ፡፡
- ካልሆነ ግን ቢያንስ በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ የሚፈጥር መሆን አለበት፡፡
- በሚገባ ገብቶሃል ማለት ነው፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ይኼን ለማድረግ የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- ይኸው የበሬ ወለደ ዓይነት ዘገባዎች እኮ ነው የምጽፈው፡፡
- ተቀባይነት እያገኘህ ነው ግን?
- እሱ ላይ አንደንድ ችግሮች አሉ፡፡
- በዚህ ወቅት ችግር መስማት አልፈልግም፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የሚከፈልህ እኮ ችግር እንድትፈጥር እንጂ ችግር እንድታሰማ አይደለም፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ የምን ችግር ነው የምታወራው?
- የበሬ ወለደ ጽሐፎች ያን ያህል ተቀባይነት እያገኙ አይደለም፡፡
- ስማ የምትጽፈው ጽሑፍ እውነት እንዲመስል የሚያደርጉ ሰዎችንም መልምለሃል አይደል?
- እሱማ መልምያለሁ ግን ትንሽ የበጀት ጭማሪ ያስፈልገኛል፡፡
- ተጨማሪ በጀት መንግሥት ራሱ መከልከሉን አልሰማህም እንዴ?
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር ወድጄ አይደለም?
- ምንድነው የምታወራው ሰውዬ?
- የጫት ወጪዬ ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ነው፡፡
- እና የጫት እርሻ ይገዛልህ?
- ከተቻለማ ደስ ይለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቀልዱን ትተህ ሥራህን በአግባቡ ሥራ፡፡
- ሌላም ችግር ግን ገጥሞኛል፡፡
- የምን ችግር?
- የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እየደረሱኝ ነው፡፡
- ስለ እሱ አትፍራ፣ አስፈላጊው ጥበቃ ይደረግለሃል፡፡
- ማስፈራሪያዎቹ ግን እንቅልፍ እየነሱኝ ነው፡፡
- እንቅልፍ ያጣኸው እየሠራህ መስሎኝ?
- ማለቴ ማስፈራሪያዎቹ እየበዙብኝ ነው ለማለት ነው፡፡
- ለማንኛውም ሕዝቡ ካልተተራመሰ እኛም የኮንትሮባንድ ሥራችን ይደናቀፋል፡፡
- አውቃለሁ ክብር ሚኒስትር፡፡
- ለአንተ የሚቆረጠውም ገንዘብ የሚጨምረው የእኛ ገቢ ሲጨምር ነው፡፡
- በትክክል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ሥራህን በትጋት ሥራ፡፡
- የምሠራውን ሥራ ከወደዱት ምን ያደርጉልኛል?
- እሾምሃለሁ፡፡
- ምን አድርገው?
- የጎበዝ አለቃ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስልክ ተደወለላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ ሰውዬ አይገባህም?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- በዚህኛው ስልኬ ለምን ደወልክ?
- ይቅርታ ያኛው ስልክ ዝግ ስለሆነብኝ ነው፡፡
- ሁለተኛውን ስልኬን የምከፍተው ማታ ማታ መሆኑን ረሳኸው?
- ረስቼው አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ለምን ደወልክ?
- አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡
- ዕቃው ተጭኗል አላልከኝም እንዴ?
- ዕቃውማ ተጭኗል፡፡
- ታዲያ ምን ተፈጠረ?
- ሾፌሩ ደውሎልኝ ነበር፡፡
- ምን አለህ?
- ዕቃው ተይዟል ብሎኛል፡፡
- ምን?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ ልምድ ያለህ ሰው አይደለህ እንዴ?
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ እንዴት ነው በድጋሚ ሊያዝብህ የቻለው?
- ክቡር ሚኒስትር ኬላዎች በጣም ጥብቅ ቁጥጥር እየተካሄደባቸው ነው፡፡
- ከዚህ በፊትስ ቢሆን ቁጥጥር መቼ ጠፋ?
- አዎ ግን ጉቦ እንኳን አልቀበልም እያሉ ነው፡፡
- እኔ ምን አገባኝ ታዲያ?
- ከአቅሜ በላይ ሆኖ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና አሁን ምን አድርግ እያልከኝ ነው?
- ከቻሉ እንዲደውሉ ነው፡፡
- ለማን?
- ለፖሊስ!
[ክቡር ሚኒስትር ዕቃቸውን ለያዘው ፖሊስ ደወሉ]
- ሄሎ!
- ማን ልበል?
- እስከዛሬ ስልኬን አታውቀውም?
- አላወኩም ማን ልበል?
- ክቡር ሚኒስትሩ ነኝ፡፡
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ባክህ?
- ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ ኬላ ላይ የተያዘ መኪና ነበር፡፡
- ስለእሱ ሪፖርት ፈልገው ነው?
- መኪናው እንዲለቀቅ ልነግርህ ነበር፡፡
- ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- መኪናው የተያዘው እኮ ኮንትሮባንድ ጭኖ ነው፡፡
- ዕቃው ኮንትሮባንድ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- ለመሥሪያ ቤታችን የሚያስፈልጉ ዕቃዎች ናቸው፡፡
- ሾፌሩ ራሱ ኮንትሮባንድ መሆኑን አምኗል እኮ?
- የምነግርህን አትሰማም እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ምን እየሠራሁ እንደሆነ እኮ አውቃለሁ፡፡
- አልታዘዝም እያልክ ነው?
- በፍፁም አላደርገውም፡፡
- ተናንቀናል ማለት ነው?
- ከተናናቅን ቆየን እኮ፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር ስለሆኑ የምፈራዎት መስሎዎት ነው?
- እኔ ጠፋሁ?
- ለማንኛውም በቅርቡ መጠየቅዎ አይቀርም፡፡
- ማን አባቱ ነው የሚጠይቀኝ?
- እርስዎ ግን ክቡር ሚኒስትር ነኝ ሲሉ አያፍሩም?
- እና ማን ነኝ ልበል?
- ክቡር ኪራይ ሰብሳቢ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዲፕሎማት ደወለላቸው]
- ክቡር ሚኒስትር በኋላ ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡
- ማን ነው የሚጠይቀኝ?
- አገሪቷ ወዴት እያመራች እንደሆነ ያውቃሉ?
- ወደ ዕድገት ነዋ፡፡
- እየቀለድኩ እኮ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?
- በዚህ ወቅት ቀልድ ያዋጣል ብለህ ነው?
- ታዲያ ሕዝቡ ለሚጠይቀው ጥያቄ መልስ ለምን አትሰጡም?
- ምላሽ መስጠት ጀምረናል እኮ፡፡
- የምን ምላሽ ነው የሰጣችሁት?
- ይኸው ተቃዋሚዎችን እየፈታን አይደል እንዴ?
- የሕዝቡ ጥያቄ ከዚህም የዘለለ ነው፡፡
- ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?
- ክቡር ሚኒስትር በየቀኑ ሰዎች እየሞቱ እኮ ነው፡፡
- ለምን የተቃውሞ ሠልፍ ይወጣሉ?
- ሕዝብ እኮ የመቃወም መብት አለው፡፡
- መብቱን የሰጠነው እኛው አይደለን እንዴ?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አትቃወም ስንለውም መስማት አለበት፡፡
- ሕዝብ እናንተን ለምን ይሰማችኋል?
- ለምን አይሰማንም?
- እናንተም ስለማትሰሙት ነዋ፡፡
- ምን ይደረግ እያልክ ነው?
- አገሪቷ ወደ ከፋ ነገር እንዳትገባ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡
- ለእሱማ ይኸው ጥልቅ ተሃድሶ ላይ ነን፡፡
- እናንተ የሚያስፈልጋችሁ ጥልቅ ተሃድሶ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- ፈርሶ መሠራት!