Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶችን የሚመለከቱ ሁለት መመርያዎችን አሻሻለ

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶችን የሚመለከቱ ሁለት መመርያዎችን አሻሻለ

  ቀን:

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀበሌ ቤቶችንና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የወጡ ሁለት መመርያዎችን አሻሻለ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ያሻሻላቸው ሁለት መመርያዎች በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ተግባራዊ እንዲደረጉ ተሠራጭተዋል፡፡

  በእነዚህ ሁለት መመርያዎች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራትና የኤጀንሲው የቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ራቢራ ዓለሙ፣ ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

  የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር መመርያ ቁጥር 3/2007 ለማሻሻል የወጣው የመጀመርያው መመርያ ቁጥር 4/2009 ነው፡፡ ሁለተኛው መመርያ ደግሞ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር የወጣው መመርያ ቁጥር 1/2008 ለማሻሻል የወጣው መመርያ ቁጥር 2/2009 ነው፡፡

  ሁለቱንም መመርያዎች ካቢኔው ያፀደቀው በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ሲሆን፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ መስከረም 2010 ዓ.ም. ለሚመለከታቸው ተቋማት አሠራጭቶታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

  የዚህ መመርያ አስፈላጊነት ለዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩ አምስት ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

  አንደኛ ማካካሻ ቤት ያላቸው የመልሶ ማልማት ተነሺዎችን ጥያቄ ምላሽ መስጠት፣ ሁለተኛ በውክልና የቀበሌ ቤት ውል ማደስ ያልቻሉ ሕጋዊ የቀበሌ ቤት ተከራይ ግለሰቦች ጥያቄ እየበረከተ በመምጣቱ፣ ሦስተኛ የቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሕጋዊ ተከራዮች የሚኖሩበት ቤት ረዥም ጊዜ ከመቆየቱ የተነሳ ለማደስ በሚፈልጉበት ጊዜ በተመሳሳይ ማቴሪያል ብቻ መሆን እንዳለበት ስለሚጠየቅ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ክፍተትን የፈጠረና ጥያቄው እየሰፋ በመሄዱ፣ አራተኛ የቀበሌ ንግድ ቤቶች ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚተላለፉበት መንገድ በግልጽ ያልተቀመጠ በመሆኑ፣ አምስተኛና የመጨረሻው በቀበሌ ቤት ተከራይተው ከሚኖሩ ተከራዮች ጋር በሕጋዊ መንገድ በደባልነት የሚኖሩ ደባል ተከራዮች ግልጽ የሆነ የመብት ጥያቄያቸውን መመለስ አስፈላጊ ስለሆነ መመርያውን ማሻሻል ማስፈለጉ ተገልጿል፡፡

  በመመርያ ቁጥር 3/2007 ያልተካተቱ ሦስት ጉዳዮች በተሻሻለው መመርያ ላይ ተጨምረዋል፡፡ የመጀመርያው የቀበሌ ቤቶች ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ኃላፊነት የክፍላተ ከተሞች ይሆናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኤጀንሲው በልዩ ሁኔታ የቀበሌ ቤት ተጠቃሚዎች አገልግሎት እንዲያገኙ ክፍት ቤት በሚገኝበት በሌላ ክፍለ ከተማ እንዲመደብ ሊያደርግ እንደሚችል መደንገጉ ነው፡፡

  ሁለተኛው የቀበሌ ቤት ተከራይ በሕግ ጥላ ሥር የሆነ ሰው በውክልና የቤት ኪራይ ውል ማደስ ያልቻለ ከሆነ፣ ከማረሚያ ቤት በሚሰጥ ማስረጃ መሠረት ውክልና በተሰጠው ሰው አማካይነት የቤት ኪራይ ውሉ ይታደስለታል የሚል ነው፡፡

  ሦስተኛ ተከራይ ከሚስት/ከባል፣ ከልጅ፣ ከሞግዚት ውጪ ለሌላ ወገን በውክልና ስም አስተላልፎ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ በውጭ አገር ከኖረ የቤት ኪራይ ውሉ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ መንግሥት ቤቱን ይረከባል የሚል ነው፡፡

  በመመርያ ከተቀመጡ ማሻሻያዎች መካከል የቀበሌ ቤትን የተከራየ ማንኛውም ሰው በሞት ሲለይ ወይም በተለያየ ምክንያት ሲለቅ፣ ቤቱን ለኤጀንሲው እንዲመልስ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ሟች በተከራየው ቤት ውስጥ ሕጋዊ የጋብቻ ሰነድ ያላቸው ባል ወይም ሚስት ካሉ፣ የተከራይ ልጆች ካሉ፣ እንደ ልጅ ሆነው የሚኖሩ ከወረዳው ማረጋገጥ ሲችሉ በችግር ምክንያት ከተከራይ ጋር በጥገኝነት የሚኖሩ ወላጅ እናትና አባት ቤቱን በአዲስ ውል ሊከራዩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፍርድ ቤት ወይም በመንግሥት ውሳኔ ለሦስተኛ ወገን ሊተላለፍ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ ደባል የሚኖርበት ቤት በልማት ምክንያት ቢፈርስ ተተኪ ቤት ያገኛል፡፡ የቤቱ ተከራይ በሞት ከተለየ ደባሉ ሰው ግማሽ መብት እንደሚኖረውም ተደንግጓል፡፡

  የቀበሌ ንግድ ቤት ለሦስተኛ ወገን ስለማስተላለፍ በተደነገገው ርዕስ ሥር የንግድ ቤት ተከራይ በሞት ከተለየ፣ በፍርድ ቤት ወይም በመንግሥት ውሳኔ ሲሰጥ ለሦስተኛ ወገን ይተላለፋል፡፡

  በተለይም አንድ የመንግሥት ንግድ ቤት ተከራይ ቤቱን ከሌሎች ሽርኮች ጋር በንግድ ሕጉ መሠረት በንግድ ማኅበራት ሲደራጅ እንደ አዲስ ውል ይዋዋላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተከራዩ ቤቱን በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 በሚፈቅደው መሠረት ከሚመለከተው አከራይ ፈቃድ ሲያገኝ፣ የንግድ መደብሮችን በስጦታ ወይም በሽያጭ መልክ ለሌላ ወገን ሲያስተላልፍ በስሙም ውል ይዋዋላል፡፡

  በአዲስ አበባ በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተለያዩ የንግድ ተቋማት ተገንብተዋል፡፡ እነዚህን ተቋማት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተረክቦ እንደሚያስተዳድር በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

  ሁለተኛው መመርያ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር የወጣው መመርያ ቁጥር 1/2008 ለማሻሻል የወጣው መመርያ ቁጥር 2/2009 ነው፡፡

  በዚህ መመርያ የተሻሻሉት ዓብይ ጉዳዮች ሕጋዊ ማስረጃ ሳይኖራቸው የቀበሌ ቤት የያዙ፣ በቀበሌ ግቢ ውስጥ ቤት ሠርተው የሚኖሩ ሰዎች በመመርያው እንዲስተናገዱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

  በአንድ የቀበሌ ቤት ውሉ በ‹‹እነ›› ወይም ከዚህ በፊት ከሕጋዊ ወራሽ ልጆች መካከል በአንደኛው ስም ብቻ በተገባ ውል የሚኖሩ ነዋሪዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ በአዲስ መመርያ ከአንድ በላይ ወራሾች ሆነው ነገር ግን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በአንድ ወራሽ ስም ብቻ የቤት ኪራይ ውል ከተፈረመ፣ ወራሽነታቸው በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ የልማት ተነሺ የሆኑ ወራሾች በሙሉ የቤት ኪራይ ውል እንዲዋዋሉና ሕጋዊ የቀበሌ ቤት ተከራይነት መብት ይጠበቅላቸዋል ይላል፡፡

  ማካካሻ ቤትን በሚመለከት በተለይ በክልል ከተማ ላለው የቀድሞ ቤት ምትክ ወይም ማካካሻ በአዲስ አበባ የተሰጠው ነዋሪ፣ አሁን የያዘው ቤት እንደ ግል ይዞታ ተቆጥሮ እንዲስተናገድ የሚደነግግ አንቀጽ ባለመኖሩ፣ በቀድሞ መመርያ ችግሩ አልተፈታም ነበር፡፡

  በአዲሱ መመርያ በማካካሻነት የግል ቤቱን ለመንግሥት አካል ያስያዘ፣ በማካካሻነት ያስያዘው ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ከሆነና አሁን ያለበት ቤት ያለበት ቦታ ለልማት ከተፈለገና ከከተማው ውጪ ያለው ቤቱ እንዲመለስለት ከፈለገ፣ የያዘውን ቤት ለከተማው አስተዳደር በማስረከብ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ያለው ቤቱ ሊመለስለት ይችላል ይላል፡፡

  ከዚህ ጋርም የግል ቤቱን በማካካሻ ለመንግሥት አካል ያስያዘ የልማት ተነሺ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ የሚገኘውን ቤቱን መልሶ መረከብ የማይፈልግ ከሆነ፣ በቤቱ ላይ የይገባኛል ጥያቄ እንደማያነሳ ግዴታ ከገባ በያዘው ቤት ላይ የግል ቤት ባለቤትነት መብት ይፈጠርለታል ይላል፡፡

  በሁለቱ መመርያዎች ላይ ክፍላተ ከተሞች ከነዋሪዎች ጋር ባለፈው ሳምንት መወያየት ጀምረዋል፡፡ አቶ ሽመልስ እነዚህ መመርያዎች ለዘመናት የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሆኑ ማነቆዎችን ይፈታሉ ብለው ያምናሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ 144 ሺሕ የቀበሌ ቤቶች እንዳሉ አቶ ሽመልስ ገልጸው፣ እነዚህ ቤቶች መኖርያንና የንግድ ቤትን ያጠቃልላሉ ብለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...