Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የገቢዎችና ጉምሩክ ወንጀል ምርመራ አስተባባሪ ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ፍርድ ቤት እንደጠራቸው ያወቁት በጋዜጣ መሆኑን ተናገሩ

  የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ለ24 ሰዓታት ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈባቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ፣ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ታስረው አድረው ጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ በባለሥልጣኑ የምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ አቶ ተመስገን ጨዋቃ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው፣ ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለድርሻ የሆኑት አቶ ፀጉ ብርሃነ ገብረ እግዚአብሔር ላይ ስላወጡት የፍርድ ቤት የመያዣና ከአገር እንዳይወጡ የዕግድ ትዕዛዝ ቀርበው እንዲያስረዱ በተደጋጋሚ ተጠርተው ባለመቅረባቸው ነው፡፡ አቶ ፀጉ ብርሃነ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረው አቶ ፀጉ ብርሃነ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ መከሰስም ካለበት ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ድርጅቱ ሆኖ የሚመራው ሥራ አስኪያጁ እንጂ፣ ‹‹አቶ ፀጉ ብርሃነ ሥራ አስኪያጅ ባልሆኑበት ምክንያት እንዴት የመያዣና የዕግድ ትዕዛዝ ይወጣባቸዋል?›› በማለት ለፍርድ ቤቱ በማመልከታቸው፣ የወንጀል መርማሪ ቡድን አስተባባሪው ታስረው ቀርበው አስረድተዋል፡፡ አቶ ተመስገን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በምርመራ ክፍሉ ላይ አመልካቹ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ስለማቅረቡና ፍርድ ቤቱም የሰጠው ትዕዛዝ ስለመኖሩ መረጃ ያገኙት ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ታትሞ ገበያ ላይ ከዋለው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡ በተጠርጣሪው (አቶ ፀጉ ብርሃነ) ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በፍርድ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ ስለመኖሩ ቢገነዘቡም፣ ትዕዛዙ በቀጥታ እሳቸው ላሉበት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መላክ ሲገባው፣ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት የተላከ መሆኑን ሲረዱ ወደ ክፍላቸው እንዲመጣ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለእሳቸው ክፍል የደረሰው አስተያየቱን ማቅረብ ከነበረባቸው የፍርድ ቤት ቀነ ገደብ እጅግ የዘገየ ቢሆንም፣ ለፍርድ ቤቱ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ማመናቸውን የገለጹት አስተባባሪው አቶ ተመስገን፣ ተጠርጣሪ ስለሚሏቸው አቶ ፀጉ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ውስጥ ስላላቸው ድርሻና ፀጉ ብርሃነ አስመጪና ላኪ ድርጅት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ለምርመራው መነሻ የሆናቸው፣ አቶ ፀጉ ብርሃነ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በተጭበረበረ መንገድ አንድ ተሽከርካሪ ለሁለት ግለሰቦች መሸጡንና ከገዢዎቹ 2.3 ሚሊዮን ብር ሲቀበል ደረሰኝ አለመቁረጡ መረጃ ስለደረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር በሚያደርጋቸው ግብይቶች ደረሰኝ እንደማይቆርጥ አመላካች መረጃዎች በማግኘቱና በቂ ጥርጣሬ ስለነበረ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ የድርጅቱ የሒሳብ ሰነዶችን መውሰዳቸውን የተናገሩት አስተባባሪው፣ ለፍርድ ቤቱ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በማለት የምርመራ መዝገቡን ይዘው ቀርበዋል፡፡ የአቶ ፀጉ ብርሃነ ጠበቆች የተጠርጣሪው ዕግድ እንዲነሳ ጠይቀው፣ ለተሸጠው ተሽከርካሪ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ አልተቆረጠም በተባለበት ወቅት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ያልነበሩ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ባለድርሻ በመሆናቸው ለድርጊቱ መፈጸም ተቀዳሚ ተዋናዩ መሆናቸው በሰው ማስረጃ መረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለደረሰኝ የተሸጡ ሽያጮችና ተዛማጅ ድርጊቶች በኦዲት ተጣርቶ ለሚገኘው የግብር ዕዳ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ገልጸዋል፡፡ ያለ ባለሥልጣኑ ዕውቅና በሕገወጥ መንገድ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ በመጠቀም ገቢ እንደሚሰበስቡና የታክስ ሥወራ ተግባር እንደሚፈጽሙ ከተደረገው ምርመራ መገንዘብ መቻሉን አቶ ተመስገን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በአቶ ፀጉ ብርሃነ ላይ የወጣው የዕግድ ትዕዛዝ የሚነሳ ከሆነ፣ በኦዲት ምርመራ የሚገኝ የመንግሥት ግብርና ዕዳ የማይፈከልበትና ከአገር ሊወጡ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑን አስረድተው ትዕዛዙ ባለበት ፀንቶ እንዲቆይ ጠይቀዋል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በሕግ ዕውቅና የተሰጠው ተቋም ማለትም ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ መክሰስ መከሰስ እየቻለ ለምን ባለድርሻው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ዕግድ እንዲጣልባቸው እንደተደረገ እንዳልገባቸው አስረድተዋል፡፡ ያለደረሰኝ ተሽከርካሪ ተሽጧል የሚባለው ከእውነት የራቀ መሆኑን ያስረዱት ጠበቆቹ፣ ተሽከርካሪ ለገዢ የሚተላለፈው ደረሰኝ ተቆርጦ ሰሌዳ ቁጥርና ቁልፍ ሲሰጥ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ የዕግድ ትዕዛዙ በወጣበት ወቅት አቶ ፀጉ ብርሃነ አገር ውስጥ እንዳልነበሩ የገለጹት ጠበቆቹ፣ ዕግዱ እንደተጣለባቸው በመስማታቸው ወደ አገራቸው ተመልሰው ‹‹ለምን ተፈለግሁ? ጥፋቴስ ምንድነው?›› በማለት ፍርድ ቤት ቀርበው በመጠየቃቸው፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ አቶ ተመስገን ጨዋቃ ቀርበው እንዲያስረዱ መታዘዛቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች