የኢቦላ ቫይረስ በምዕራብ አፍሪካ ያደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ 25 ቢልዮን ዶላር እንደሚገመት የዓለም ባንክ አስታወቀ፡፡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዓለም ባንክን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ክፉኛ የተጠቁት ጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን ኢኮኖሚያቸው አሁንም እየተጎዳ ነው፡፡ በእነዚሁ አገሮች በተያዘው የአወሮፓውያኑ ዓመት በሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት የ1.6 ቢልዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያደርስ የተገመተ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከተገመተው የ2 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ መሻሻልን አሳይቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ሲል ወረርሽኙ ታይቶባቸው የነበሩት ማሊ፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል በአሁኑ ጊዜ ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆናቸው ነው፡፡ የኢቦላን ሥርጭት በመቆጣጠር ብሎም በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጎዱት አገሮች ወደ ጎረቤት አገሮች እንዳይዛመት ፖሊሲ አውጪዎችና የዕርዳታ ሠራተኞች ያደረጉት እገዛ በኢኮኖሚው ላይ ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን ኪሳራ እንዳይጨምር ማገዙንም ባንኩ ገልጿል፡፡