Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  የትራንስፖርት ታሪፍ አተገባበር ውርስና መዘዝ

  መንግሥት አዲስ የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወቅቶች ከተደረጉ የትራንስፖርት የዋጋ ለውጦች አንፃር ሲታይ ለየት ያለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

  ምክንያቱ ደግሞ በተለይ በመካከለኛ ርቀት ላይ የተደረገው የዋጋ ለውጥ የ30 ሳንቲም መሆኑ አንዱ ነው፡፡ 40 ሳንቲም ቅናሽ የተደረገበት መስመርም አለ፡፡ በአንድ ጊዜ የዚህን ያህል ጭማሪም ሆነ ቅናሽ የተደረገበት ወቅት ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡

  ከዚህ ቀደም የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች ላይ የዋጋ ማስተካከያ ሲደረግ ቅናሹም ሆነ ጭማሪው ከአምስት ሳንቲም እስከ 20 ሳንቲም ባለው መካከል ነበር፡፡ የአሁኑ የታሪፍ ለውጥ ግን ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ የተደረገበት ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

  ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የነበሩ የዋጋ ማስተካከያዎች ከ20 ሳንቲም ባነሰ እየጨመሩ መጥተው በጥቂት ዓመታት ልዩነት ዋጋቸው ከፍ ሊል ችሏል፡፡ ለምሳሌ የአጭር ጉዞዎች ታሪፍ ከሳንቲሞች ተነስቶ በአሁኑ ወቅት አንድ ብር ከ40 ሳንቲም ደርሷል፡፡

  - Advertisement -

  ከስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት አንድ ብር ከ25 ሳንቲም ዋጋ ተቆርጦለት ሲሠራበት የነበረው የመካከለኛ ርቀት የታክሲ ጉዞ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ሁለት ብር ከ80 ሳንቲም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሁለት ብር ከ50 ሳንቲም ሆኗል፡፡

  ይህ የታሪፍ ቅናሽ ከቀድሞዎቹ ጭማሪዎችም ሆነ ቅናሾች አንፃር ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ የከተማ ታክሲ አገልግሎት ታሪፍ በዚህን ያህል ደረጃ መቀነሱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ቀንሷልና፡፡ ኅብረተሰቡም የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ሊስተካከል እንደሚገባው ያምን ነበር፡፡

  በሌላ አንፃር የዓለም የነዳጅ ዋጋ በቀነሰበት ልክ በአገር ውስጥ እየተሸጠበት ያለው ዋጋ አሁንም ተመጣጣኝ ያለመሆኑ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በቀነሰበት ልክ የአገር ውስጥ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ ያላደረኩበት የራሴ የሆነ ምክንያት አለኝ ብሏል፡፡ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የነዳጅ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ ቀንሷል፡፡ ሆኖም የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ዓለም አቀፍ ገበያን መሠረት አድርጎ ቢሰላና ግብይቱ ቢካሄድ ኖሮ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ አሁን ከቀነሰው በላይ ዝቅ ይል እንደነበር ይታመናል፡፡

  ያም ሆነ ይህ የአዲሱ ታሪፍ መቀነስ መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ታሪፍ አንድ ብሎ ከጀመረበት ቀን ጀምሮ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት ጋር ተያይዞ በመንግሥት ይተግበር ተብሎ የተተመነው ታሪፍ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም፡፡

  ሰሞኑን የወጣው ታሪፍ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ለምሳሌ የመካከለኛ ጉዞ ዋጋ ሁለት ብር ከ80 ሳንቲም መሆኑ እየታወቀ፣ ኅብረተሰቡ ሲከፍል የቆየው ግን ሦስት ብር ነበር፡፡ ለአጭር ጉዞ ደግሞ አንድ ብር ከአርባ ሳንቲም መሆኑ እየታወቀ፣ ሲከፈል የቆየው አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው፡፡ በሌሎች የጉዞ መስመሮች ላይ የተተመነው ዋጋ ላይ ያሉ ዝርዝር ሳንቲሞች እየታጠፉ፣ አገልግሎቱ አራት ብር፣ አምስት ብርና ስድስት ብር፣ እንዲከፈልበት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

  ትክክለኛው ታሪፍ ሥራ ላይ እንዳይውል ዋነኛ ምክንያቶች የሆኑት ተገልጋዩ ለጉዳዩ ቁብ አለመስጠቱና አገልግሎት ሰጪዎችም በትክክለኛው ታሪፍ ለማስከፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው፡፡

  ይህ መሆን የሌለበት ቢሆንም በትክክለኛው ታሪፍ አገልግሎት መስጠትና መቀበል ያለመቻሉ ልምድ፣ ሰሞኑን ሥራ ላይ የዋለውን ታሪፍ ለማስተግበር እንቅፋት ሆኖ እያየ ነው፡፡ ይህ ክስተት በትክክለኛው ታሪፍ የመጠቀም ልምድ ያለመኖሩን፣ ውሎ አድሮ ችግር እንደሚያስከትል ያየንበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

  የታክሲ አገልግሎት ታሪፍ ከሁለት ብር ከሰማንያ ሳንቲም ወደ ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሲወርድ አገልግሎት ሰጪዎቹ ይህንን ለመቀበል ሲቸገሩ አይተናል፡፡ እንዲያውም አዲሱ ታሪፍ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሦስት ቀናት የታክሲ ረዳቶች ለመካከለኛ ርቀት ጉዞ ሦስት ብር ሲያስከፍሉ ነበር፡፡ አንዳንድ መንገደኞች ታሪፉ ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው ብለው ተከራክረው የከፈሉበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ለአጭር ጉዞዎችም አሁንም ድረስ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተጠየቀና እየተከፈለ ነው፡፡ እንዲያውም ባለፈው ሰኞ የተሳፈርኩበት አንድ የታክሲ ሾፌር በአዲሱ ዋጋ አላስከፍልም፤ መክፈል ያለባችሁ በቀድሞው ነው ብሎ ከተሳፋሪዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ እስከመግባት ደርሶ ነበር፡፡ በእሱ እሳቤ የቀድሞው ዋጋ ሦስት ብር ነው (ትክክለኛው ግን ሁለት ብር ከሰማንያ ሳንቲም ነው)፡፡ እኔ አዲሱ ዋጋ ስላልተነገረኝ ነው ብሎ፣ ተሳፋሪን አራግፎ ተጓዦች በሌላ ታክሲ ለመጓዝ እስከመገደድ ደርሰዋል፡፡

  በዚሁ ቀን ያጋጠሙኝ ሌላ ታክሲ አሽከርካሪ ደግሞ በዚህ አዲስ በተተመነው ዋጋ አልሠራም በማለት መሪውን እየደበደቡ የግዳቸውን አድርሰውናል፡፡ ከሁሉም በላይ የገረመኝ ደግሞ እስከ ሐሙስ ድረስ (አዲሱ ታሪፍ ከወጣ ከአምስት ቀናት በኋላ) ጥቂት የማይባሉ ተሳፋሪዎች የዋጋ ለውጡ ስለመደረጉ ባለማወቅ በቀድሞ ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸው ነው፡፡ የታክሲ ረዳቶችም ተሳፋሪው የዋጋ ለውጡ መደረጉን ያልተረዳ ከሆነ ቀድሞ በሚያስከፍሉት ዋጋ ማስከፈሉን ገፍተውበታል፡፡ የነቁት ይከራከራሉ፡፡  ይህ ክስተት በደንብ የጠራ ባለመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አዲሱ ታሪፍ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ አለባቸው፡፡

  በየታክሲው የሚታየው ክርክር እንዲጎላ ያደረገው ግን ከዚህ ቀደም አሥርና አምስት ሳንቲም መልስ ተሰጠ አልተሰጠ ተብሎ ችላ ብሎ የመተው ልማድ ነው፡፡ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ከዚህ በፊት በተሳፋሪዎች የማይጠየቁት አሥርና አምስት ሳንቲም አሁን ከቀነሰው ታሪፍ ጋር ሲደመር ዋጋው በአንድ ጊዜ በሃምሳ ሳንቲም በመቀነሱ እየተበሳጩ ነው፡፡ በትክክለኛው ታሪፍ ኅብረተሰቡን ቢያገለግሉ ኖሮ አሁን የተደረገው የዋጋ ለውጥ ብዙም ያለመሆኑን ይገነዘቡ እንደነበርም እገምታለሁ፡፡

  ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን አሁንም ድረስ የተስተካከለ ታሪፍ የማይጠይቅባቸው ቦታዎች መኖራቸው ነው፡፡ ቀድሞም ቢሆን ከትክክለኛው ታሪፍ በተለይ በአጭር ርቀት ሊካተት ለሚችል ጉዞ ሁለት ብር የሚጠየቅባቸው ቦታዎች አሉ፡፡

  እንዲህ ያሉ በተለምዶ ያልተገባ ዋጋ የሚጠየቅባቸው አካባቢዎች አሁንም ዋጋቸውን ሳይለውጡ በዚያው ቀጥለዋል፡፡ ይህም ጉዳይ ከሰሞኑ ታሪፍ ለውጥ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሲሆን፣ የአገልግሎት ክፍያው የጉዞ መስመሩን ርዝመት ተከትሎ መሰላትም ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ከሚተምነው የትራንስፖርት ዋጋ ባሻገር የአነስተኛ ታክሲዎች አገልግሎትም መዘንጋት የለበትም፡፡ በእነዚህ ታክሲዎች መገልገል በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ እነርሱም የአገልግሎት ዋጋቸውን ሊቀንሱ ይገባል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አጭር ጉዞ አገልግሎት ሲሰጡ አራት ሰዎችን ጭነው 40 ብር የሚያስከፍሉ አሉ፡፡ ይህም ለአንድ ሰው አሥር ብር መሆኑ ነው፡፡ ምሽት ላይ ወይም መካከለኛ ታክሲዎች በማይኖሩበት ጊዜ የሚሰጡት አገልግሎት በመሆኑ ብዙም ተቃውሞ ላያስነሳ ይችላል፡፡

  አንዳንዱ ለአጭር ርቀት ለአንድ ሰው 20 ብር በማስከፈል አገልግሎት የሚሰጡም አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ነዳጅ ከቀነሰም በኋላ የሚያስከፍሉት ቀድሞ በሚሠሩበት ዋጋ ነው፡፡ ማስገደዱ ምን ያህል እንደሚያስኬድ ባላውቅም፣ እነዚህም ታክሲዎች ቢሆኑ ነዳጅ በቀነሰላቸው ዋጋ ልክ ዋጋ ቀንሰው ቢሠሩ ይመረጣል፡፡ ለማንኛውም በትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ቀነሰም ጨመረ ተገልጋዩ ትክክለኛውን ዋጋ ይክፈል፡፡ የአገልግሎቱ ሰጪዎችም ይህንን በማክበር መሥራት ሕግን ማክበር ብቻ ሳይሆን ያልታሰበ የዋጋ ለውጥ ሲፈጠር ተግባብቶ ለመሥራት ያስችላልና ሁሉም የየራሱን ግዴታ ይወጣ፡፡ መብቱንም ያስጠብቅ፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት