Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የጥጥ አምራቾች የግብይትና የዋጋ ጥያቄ አነጋግሯል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች የጥጥ አምራቾችን ዋጋ ይኮንናሉ
  • መንግሥት የ50 ሺሕ ቶን እጥረት እንዳለ ይናገራል

  ለዓመታት በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሲዋልል እንደከረመ ይነገርለታል፡፡ አሁንም ቢሆን ከችግሮቹ ተላቋል ማለት እንደማይቻል የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ፡፡ በተደጋጋሚ ሲገለጹ የሚደመጡት ችግሮች ከባንክ ብድር፣ ከመሬት አቅርቦት፣ ከግብይትና ከዘርና ዝርያ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እነዚሁ ችግሮችን የጠቃቀሰ ስብሰባም ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾች፣ የጥጥ መዳመጫ ባለንብረቶችና ላኪዎች ማኅበር በኩል ተስተናግዷል፡፡

  ማኅበሩ ባካሔደው ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔው ላይ መነጋገሪያ ያደረገው መሠረታዊ ችግር የወቅቱ የግብይት ውጣውረድ መሆኑም ታይቷል፡፡ ተደጋጋሚ ውይይቶችም በጥጥ ዋጋ ዙሪያ ከመድረክ ጀርባ ሲካሔዱ ሰንብተዋል፡፡ በቅርቡ እንኳ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል የጥጥ አምራቾች ዋጋ እንዲቀንሱ፣ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችም ጥጡን በተስማሙበት ዋጋ እንዲገዙ ለማግባባት ስብሰባዎች ሲካሔዱ እንደነበር ታውቋል፡፡ በግብይት ዙሪያ ሲነሱ ከተደመጡት መሠረታዊ ጥያቄዎች አንዱ በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ መካከል ያለው የጥጥ ዋጋ ልዩነት ነው፡፡

  በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ጥጥ የሚሸጥበት ዋጋ በኪሎ 35 ብር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአንፃሩ በአገር ውስጥ በኪሎ 45 ብር እየተሸጠ በመሆኑ፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ይህንን እንደማይቀበሉት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ይህንኑ አስታውቀዋል፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጥያቄ ዓምናም በጥጥ አምራቾች ሲነሳ ተሰምቷል፡፡ አምና የጥጥ ዋጋ ውድ ሆነ በሚል ምክንያት በግድ ዋጋ እንዲቀንሱ መደረጋቸውን ጥጥ አምራቾች ያስታውሳሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ጥጥ በገፍ አምርተን የሚገዛ በማጣታችን ጥጥ ከማምረት እየወጣን ነው የሚል አስተያየት ሲሰጡም ተደምጠዋል፡፡ ጫት፣ በቆሎ፣ ማሽላና ሌላውም የግብርና ምርት ጥጥን እየተኩ መምጣታቸው ሥጋት መፍጠሩም ተሰምቷል፡፡

  በጥጥ ዘርፍ ላይ ከግብይት ባሻገር በርካታ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ መንግሥት ትኩረት አልሰጠውም እየተባለ፣ ባለቤት የለውም የሚል ስሞታና ትችትም በመንግሥት ላይ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከደቡብ ክልልና ከሌሎች ጥጥ አምራች አካባቢዎች የተወከሉ አምራች ኩባንያዎች ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት መንግሥት የጥጥ ምርትን ችላ ብሎታል፡፡ ከአፋር ክልል የመጡ ጥጥ አምራቾች፣ አዋሽን የሚገድበው አጥቶ እንዲሁ በባዶ ሜዳ እየፈሰሰ፣ የጥጥ ማሳቸው ውኃ በማጣት ምርት መታጎሉን ጠቅሰዋል፡፡ ከደቡብ ኦሞ ዞን የመጡ ባለሀብትም ከወይጦ ወንዝ ውጪ ሌላ የውኃ ምንጭ ማግኘት ስላልቻሉ 38 ሔክታር መሬት ላይ የዘሩት ጥጥ ምርት ሳይሰጥ ሙሉ በሙሉ መድረቁን በስብሰባው ወቅት ለተገኙት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ ገልጸውላቸዋል፡፡ በመሆኑም የወይጦ ወንዝ ውኃ ሥርጭትና ክፍፍል መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

  በመተማ አካባቢ እንቅስቃሴ የጥጥ እርሻ ልማት ከሚያከናውኑ ኩባንያዎች የተደመጠው ቅሬታ ሠራተኞች እንደልብ ማግኘት አለመቻሉን ይጠቁማል፡፡ ያለወቅቱ የጣለው ዝናብ በሰሊጥ ምርት ላይ ጉዳት ካደረሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ምርቱን በወቅቱ የሚያነሳ የሰው ኃይል ማግኘት ባለመቻሉ መሆኑን ኩባንያዎቹ ይጠቅሳሉ፡፡ የጥጥ ለቀማ ለማካሔድም ተመሳሳይ ችግር እያጋጠማቸው እንደሚገኝ፣ በርካታ የጉልበት ሠራተኞችም ወደ ሱዳን በመሔድ ላይ እንደሚገኙና፣ በቀን ለአንድ ሠራተኛ እስከ 600 ብር በመክፈል እንደሚገኙ ለሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡ በደቡብ ኦሞ ዞን ለጥጥ ለቀማ የሰው ኃይል የሚያገኙት ከወላይታ አካባቢ መሆኑን፣ ነገር ግን ለስኳር ፕሮጀክቶች እየተባለ የሰው ኃይል በአብዛኛው ወደ ስኳር ዘርፍ በመሔዱ ማሳ ላይ የሚገኝ ጥጥ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹ ነበሩ፡፡

  ‹‹የጥጥ ልማትን የሚመራው ባለቤት የለውም፤›› የሚሉትን ጨምሮ፣ በተደጋጋሚ የሚሰማውንና በአፋር ክልል በመሬት አሰጣጥና ባለቤትነት ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች፣ በብድር አቅርቦት፣ በኬሚካልና በምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በዘላቂ ገበያ ዕጦትና በሌሎችም ችግሮች ላይ ጥጥ አምራቾቹ ጥያቄዎቻቸውን ለሚኒስትር ዴኤታው አሰምተዋል፡፡

  መንግሥት በዚህ ዓመት 98 ሺሕ ሔክታር መሬት መልማቱን፣ ከዚህ በመነሳት 60 ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለሪፖርተር የገለጹት፣ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የጥጥ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንቴ ካሤ ምኅረቱ ናቸው፡፡ አቶ ባንቴ እንዳስታወቁት ከ60 ሺሕ ቶን ውስጥ አሥር ሺሕ ያህሉ ለአገር ውስጥ ባህላዊ አልባሳት ምርት ይውላል ተብሎ የሚታሰብ ነው፡፡ ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው 50 ሺሕ ቶን ብቻ ሲሆን፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ግን 100 ሺሕ ቶን ጥጥ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የአቅርቦት ክፍተቱን ለመሙላት ቀሪው 50 ሺሕ ቶን ጥጥ ከውጭ መምጣት እንዳለበት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በጥጥ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርት እያቆሙ ነው ያሉት አቶ ባንቴ፣ እስካሁን ከ3,500 ቶን በላይ ጥጥ ከውጭ መግባቱንም አስታውቀዋል፡፡

  በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ጥጥ አምራቾች፣ የዓለም የጥጥ ዋጋ ቢቀንስም አገር ውስጥ የሚሸጡበትን ዋጋ ለመቀነስ እንደማይፈልጉ፣ ይህም ደግሞ ከማምረቻ ከፍተኛነት በመነሳት እንደሆነ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በአንፃሩ ኤጀንሲው ዋጋ ተምኖ ማውጣቱንና ይህም ተቀባይነት እንደሌለው የሚናገሩም አሉ፡፡

  አቶ አብርሃም ገብረዮሐንስ የጥጥ አምራቾች፣ የመዳመጫ ባለንብረቶችና ላኪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት (የሥራ ጊዜያቸውን እስከጨረሱበት እስከ ትናንት በስቲያ) ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የውጭ ዋጋና የጥራት ጉዳይ መታየት አለበት ይላሉ፡፡ ‹‹የዓለም ዋጋ ይታወቃል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አውጥተው ከውጭ ከሚያመጡ ይልቅ አገር ውስጥ ያለውን ምርት በተመሳሳይ ወይም በተሻለ ዋጋ መውሰድ አይችሉም ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፤›› ይላሉ፡፡ ጥያቄው የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ ዋጋ ልዩነት ብቻ አይደለም የሚሉት አቶ አብርሃም፣ ‹‹ወደ ውስጥ ተገብቶ ሲታይ ችግሩ ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የፋይናንስ አቅማቸው ደካማ ስለሆነ መንግሥት ከውጭ የሚያመጣውን የሚገዙት ቀስ ብለው መክፈል ስለሚችሉ ሊሆን ይችላል፤›› በማለት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ከውጭ እንዲገባ ስለሚፈልጉባቸው አዝማሚያዎች ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ከጥጥ አምራቹ ሲገዙ ወዲያውኑ ክፍያ እንዲፈጽሙ ስለሚጠየቁ ከፋይናንስ አኳያ እንደማይፈልጉት ይገልጻሉ፡፡

  በአንፃሩ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ግን የዓለም ዋጋ እየቀነሰ ባለበት ወቅት፣ የአገር ውስጥ ጥጥ አምራቾች ያውም በጥራትና በብዛት ከማምረት ጋር በተያያዘ ከሚነሳባቸው ትችት ሳይወጡ ለሚያቀርቡት ጥጥ የሚጠይቁት ዋጋ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ይኮንናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መሠረት ሁለቱ ማኅበራት (የጥጥ አምራቾችና የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች) በዋጋ ተጣልተው እንደማያውቁ፣ በጋራ ዋጋውን ይወስኑ እንደነበር ጭምር ተናግረዋል፡፡ በሁለቱም በኩል በተስማሙት መሠረት የጥጥ መሸጫ ዋጋ በዓለም ገበያ መሠረት እንዲሆን ስምምነት ተደርጎ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ላይ ለምን የዋጋ ጥያቄ እንደተነሳ ግልጽ አይደለም ይላሉ፡፡ ሆኖም በዋጋው ልዩነት ሁለቱ ማኅበራት ተደራድረው ለመገበያየት መስማማታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በሁለቱም በኩል የጋራ ፌደሬሽን ተመሥርቶ ለመብቶቻቸውና ለሌሎች ጉዳዮቻቸው መፍትሔ የሚሰጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ሐሳብ ሲያቀርቡም ተደምጠዋል፡፡

  በሁለቱ ማኅበራት አባላት የሚነሱት ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው የጥጥ አምራቾች ማኅበር ባቀረበው ጽሑፍ መሠረት፣ በአገሪቱ ከሦስት ሚሊዮን ሔክታር በላይ ለጥጥ ልማት ተስማሚ መሬት አለ፡፡ ይህ ሁሉ መሬት ባይለማም በተለይ ከአራት ዓመታት ወዲህ ግን የአገሪቱ የጥጥ ምርት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎችን ፍላጎት ማሟላት እንደተሳነው በጽሑፉ ተጠቁሟል፡፡ በስድስት ክልሎች ባለሀብቶችና አነስተኛ ገበሬዎች በጥጥ ልማት ላይ መሳተፋቸው ሲታወቅ፣ በዚህ ዓመት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው የተዳመጠ የጥጥ መጠን 76 ሺሕ ቶን እንደሆነ የማኅበሩ ጽሑፍ ያመለክታል (መንግሥት 100 ሺሕ ማለቱን ልብ ይሏል)፡፡ ይህንን ያህል መጠን የጥጥ አምራቾች እንደማያቀርቡም ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

  መንግሥት የጥጥ ልማትን ዘንግቶታል፣ ባለቤት የለውም፣ የጥጥ ልማት በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው፣ የሚሉትን ጨምሮ በህንድና በቻይና እንደሚደረገው ለጥጥ አምራቾች ድጎማ ይደረግ፣ ከውጭ የሚገባው ጥጥ የጥራት ደረጃ አገር ውስጥ ከሚመረተው በታች በመሆኑ መንግሥት ለአገር ውስጥ ጥጥ ትኩረት ያድርግ የሚሉ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት እንደ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ላሉት መስኮች የሰጠውን ትኩረት፣ ለጥጥ ልማትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡

  አሁን በሚታየው አኳኋን የጥጥ ልማት አካሔድ የሚቀጥል ከሆነ፣ አገሪቱ ውስጥ ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀውን የጨርቃ ጨርቅ ምርት ማምረት እንደማይቻል ተነግሯል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታ ታደሰ ኃይሌ ይፋ እንዳደረጉት፣ መንግሥት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይጠብቃል፡፡ እርግጥ ባለፈው በጀት ዓመት ከዘርፉ ይገኛል ተብሎ የታሰበው አንድ ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ሊገኝ የቻለው ግን ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ መሆኑም ታውቋል፡፡

  ለጥጥ አምቾቹ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ታደሰ፣ ሚኒስቴራቸው የጥጥ ልማት ዘርፍን በባለቤትነት እንዲመራ ሥልጣን እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የመዋቅር ለውጦችና አደረጃጀቶች እስኪስተካከሉ ድረስ በተፈጠረ ክፈተት ምክንያት ዘርፉ መጎዳቱን ጠቅሰቀው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የግብዓት ግዥ እንዲያከናውን የጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ) መሰየሙን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የጥጥ ልማት ዳይሬክቶሬት፣ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሥር መቋቋሙም ለጥጥ ትኩረት ለመሰጠቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

  በአፋር መሬት አጠቃቀምና ባለቤትነት ችግሮች ላይ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን የተናገሩት አቶ ታደሰ፣ በተለይ በዘረመል ምኅንድስና አማካይነት ይመረታል ተብሎ በሚጠበቀው ጥጥ ላይ እንደ ሺቦ፣ ኤችኤንድኤም የመሳሰሉት ኩባንያዎች ጥያቄ እያነሱ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም በላቦራቶሪ የሚመረተው ጥጥ በሚኒስቴሩ ክትትል ይደረግበታል ብለዋል፡፡ በተፈጥሮ ጥጥ ዝርያዎች ላይም ክትትል እንደሚደረግና ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

  ከ60 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾች፣ የመዳመጫ ባለንብረቶችና ላኪዎች ማኅበር ከስድስት ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ በአባልነት ካቀፋቸው መካከል የቱርክ ባለሀብቶችም አሉበት፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች