Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ‹‹ዳያስፖራው በገንዘብና በቁሳቁስ ከመደገፍ ውጪ ፖለቲካው ውስጥ በቀጥታ መግባት አይችልም›› አቶ አበባው መሐሪ፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  አቶ አበባው መሐሪ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተሰጠው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ፓርቲው ከአመራር ችግር ጋር በተያያዘ ላለፉት አራት ዓመታት በርካታ ውዝግቦችን አስተናግዶ ነበር፡፡ በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት፣ በፓርቲው ውስጥ ስለተፈጠረው የአመራር ቀውስ መንስዔ፣ የቦርዱን ውሳኔና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ተከትሎ እርስዎ መኢአድን ወክለው ወደ ምርጫ እንዲገቡና በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተወስኗል፡፡ ከዚህ አኳያ ፓርቲው በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ እያከናወናቸው የሚገኙ አጠቃላይ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

  አቶ አበባው፡- ፓርቲው ላለፉት አራት ዓመታት በእነዚህ ግለሰቦች (እነ ማሙሸት አማረ) ታውኮ ነው የቆየው፡፡ በብዙ መንገድ፡፡ እዚህ በር ድረስ እየመጡ ከአባላት ጋር እየተደባደቡ ብዙ ሁከት ሲፈጥሩ የቆዩና እንዲሁም በየክፍለ አገሩ እየሄዱ ፓርቲው አባላቱን እንዳያደራጅ ብዙ መሰናክል ሲፈጥሩ ነው የቆዩት፡፡ በዚያ የተነሳ ችግር አለ፡፡ አሁን ፓርቲውን ከተረከብን ወዲህ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ዕጩዎችን ለማስመዝገብ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ነገር ግን ለእኛ የተሰጠን የሰባት ቀን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች ፓርቲዎች ዕጩዎች እንዲያስመዘግቡ ከወር በላይ ጊዜ ተሰጥቶ፣ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ለእኛ የተሰጠን የሰባት ቀናት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድም ራሱ ሲያጓትት ቆይቶ የሰጠን ሰባት ቀናት ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ደግሞ ብዙም መሥራት አንችልም፡፡ እየሞከርን ነው ያለነው፡፡ ላለመቅረትና ፓርቲውን ላለመዝጋት ሲባል ጥረት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ እንሠራለን ብለን ተስፋ አናደርግም፡፡

  ሪፖርተር፡- ባለፉት አራት ዓመታት ፓርቲው ውስጥ ከአመራር ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ እርስዎ ፓርቲውን እየመሩ ነበር፡፡ በመሀል እነአቶ ማሙሸት አማረ ፓርቲውን ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ ከዚያም ተመልሰው እርስዎ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት አራት ዓመታት በዋነኛነት ፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ችግር ምንድነው?

  አቶ አበባው፡- መቼም እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ፓርቲዎች ችግር አለባቸው፡፡ የመኢአድ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ ይኼ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ይህን ፓርቲ ይመሩ በነበሩበት ጊዜ ፓርቲው ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ በአቶ ማሙሸት አማረ የሚመራና በኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የሚመራ በሚል በ2002 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እነአቶ ማሙሸት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልን ከፕሬዚዳንትነት ሲያግዱ፣ ከዚያ አባላት ተቆጥተው በብዙ ትግል ሥልጣን ያዙ፡፡ ምርጫ ቦርድም ለኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ዕውቅና ሰጠ፡፡ እነአቶ ማሙሸት ተባረሩ፡፡ ከዚህ ቡድን ጋር አቶ ማሙሸት አማረን ጨምሮ 14 ሰዎች ተባረሩ፡፡ ብዙ ሰዎች እነርሱን ተከትለው የሄዱ ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ሦስት ዓመት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ከመሩት በኋላ ሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ እኔ ፕሬዚዳንትነቱን ተረከብኩኝ፡፡ እኔ ተረክቤ ሥራ ስጀምር ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ቢለቁም ቅሉ ያ ቁስል ቀጠለ፡፡ በውጭ አባላትን ይደበድባሉ፣ እዚህ መጥተው ይረብሻሉ፣ የመገናኛ ብዙኃንን ይዘው መጥተው ብዙ ሥራ ይሠሩብናል፣ ብዙ ተባባሪ አካላት ነበሯቸው፡፡ ይህን ሲያደርጉ በርካታ መሰናክሎች ፓርቲውን ይገጥሙታል፡፡ ከዚያ በኋላ እባካችሁ እርቀ ሰላም ይውረድ ፓርቲውን ወደኋላ ያስቀረዋል በሚል እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ በዚህም መሠረት ሽማግሌ አቋቋምን፡፡ ሽማግሌ አቋቁመንም ስናይ የእነርሱ ዓላማ በኃይል የመውረር እንጂ እርቀ ሰላም የመፈለግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከዚህ አስወጥተውን እነርሱ ለመቆጣጠር ነው የፈለጉት፡፡ በዚህን ጊዜ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል እርቀ ሰላም ይውረድ የሚል ሐሳብ ይዘው መጡ፡፡ ከእሳቸው ጋር የተነጋገርነው 14 ሰዎች እንዲገቡና ለጠቅላላ ጉባዔ አባላት ችግራቸውን እንዲያስረዱ ነበር፡፡ ነገር ግን ሲመጡ 151 ሰዎች ነበሩ፡፡ አባል ያልሆነ እንዴት ይገባል ስንል እርሳቸው በኃይል አስገቡ፡፡ የነበረውን አመራር ፈንቅለው ሄደው እነዚያን አስገቡ፡፡ በአጠቃላይ መነሻው ይኼ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ይህን ማድረግ የፈለጉት ለምንድነው?

  አቶ አበባው፡- አላውቅም፡፡ ይህ ተልዕኮ እንግዲህ በ97 ቅንጅትን በማፍረስ የሚጀምር ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም. ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተጨባብጠው መኢአድን አፈር ድሜ አበሉት፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በዚህ በኩል መጡ፡፡ በተከታታይ ነው ይህን የሚያደርጉት፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር መኢአድን ያፈርሱታል፡፡ በዚያን ወቅት ሥራ አስፈጻሚ ነበርኩ (በ2002 ምርጫ ወቅት)፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡን ጉዳይ ለስብሰባ አቀረቡት፡፡ አይሆንም እኛ እዚህ ውስጥ አንገባም ይቆይ የሚል አስተያየት ነበር የሰጠነው፡፡ ነገር ግን እሳቸው ገልብጠው ሄደው ተዋዋሉ፣ ተፈራረሙ፡፡ ነገሩ በዚያው አለቀ፡፡ መኢአድም ከሁሉም ፓርቲዎች መጨረሻ ሆኖ መጣ፡፡ አሁን ደግሞ ለፍተን ከሠራን በኋላ መጥተው እንዲህ አፍርሰውት ሄዱ፡፡ ምክንያቱን አናውቅም፡፡ ምክንያቱን የኢትዮጵያ ሕዝብና እግዚአብሔር ይወቀው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከመኢአድ ጋር ሊያደርገው የነበረው ውህደት ከጫፍ ከደረሰ በኋላ ምርጫ ቦርድ በ2005 ዓ.ም. የተካሄደው የመኢአድ ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔው አልተሟላም በማለቱ ውህደቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ምርጫ ቦርድ እርስዎን ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የወሰነው ይህንኑ ምልዓተ ጉባዔ አልተሟላም የተባለውን ጠቅላላ ጉባዔ በመጥቀስ ነው፡፡ ይህን ተቃርኖ እንዴት ያዩታል?

  አቶ አበባው፡- ምርጫ ቦርድ አሁን በሕገ ደንቡ መሠረት እነአቶ ማሙሸት አመራር ለመሆን መጀመሪያ አባል መሆን አለባቸው፣ ስለዚህ ዕውቅና አልሰጥም ማለቱ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ መጀመሪያውኑ የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔ አልሞላም ብሎ ለአንድ ዓመት ያህል ገትሮ ይዞ ነው የቆየው፡፡ ይኼ ስህተት ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ የምለው ምንድነው? ምርጫ ቦርድ የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ዕውቅና አልሰጥም ያለበት ምክንያት ጠንክረን እንዳንወጣ፣ ከአንድነት ጋር እንዳንዋሀድና የመሳሰሉትን ነው ያደረገብን፡፡ ስለዚህ ውሳኔው ትክክል ነው ብዬ ብልም የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ በወቅቱ አልቀበልም ማለቱ ፈጽሞ ስህተት ነበር፡፡

  ሪፖርተር፡- እነአቶ ማሙሸት አማረ ቢሮውን በያዙበት ወቅት እርስዎ ምርጫ ቦርድና የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አካላት የሚደግፏቸው ግለሰቦች ፓርቲውን ተቆጣጥረውታል፣ እንዳንንቀሳቀስም አድርገውናል በማለት፣ ምርጫ ቦርድና የተወሰኑ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን ተችተው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለእርስዎ ሲወሰን ትክክል ነው እያሉ ነውና እንዲህ ዓይነት ነገሮች በድጋሚ እንደማይከሰቱ ያላችሁ ማረጋገጫ ምንድነው?

  አቶ አበባው፡- እኛ የገጠመን ችግር ምንድነው? ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን የሚያስተዳድር በመንግሥት የተወከለ አካል ነው፡፡ ፍትሐዊ፣ እውነተኛ የሆነ ፓርቲዎች የሚጠነክሩበት መንገድ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደምም እንደተናገርኩት ለምሳሌ እነአቶ ማሙሸት ለምርጫ ቦርድ ያመለክቱ ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድም ተቀብሎ ያስተናግዳቸው ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድ ለኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ዕውቅና ሰጥቶ ፍርድ ቤት ሰው ልኮ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ናቸው ትክክለኛው ፕሬዚዳንት ብሎ ምስክርነት ከሰጠ በኋላ፣ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ለአራት ዓመታት ያህል ከምርጫ ቦርድ ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር፡፡ ደብዳቤ ይቀበላቸው ነበር፣ ያነጋግራቸው ነበር፣ ብዙ ነገር ነበር፡፡ ያ በፍፁም ስህተት ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ምን እንደሆነ አላውቅም ምርጫ ቦርድ ያንን ሲያደርግ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ሕጋዊ እንዳልሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድም በግልጽ ያውቃል፣ ሁሉም በግልጽ ያውቃሉ፡፡ ለወደፊቱ ይህንን ሁኔታ የሚከለክል ምን ማረጋገጫ አለ ለሚለው አይታወቅም፡፡ አሁን እየተደረገ እንዳለው ፓርቲውን የሚያፈርሱት በውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እኛ ከአንድነት ጋር ለመዋሀድ ቅድመ ውህደት ፈርመን ሁሉን ነገር ጨረስን፡፡ በማነው የቆመው? በምርጫ ቦርድ፡፡ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አልሰጣችሁም አለ፡፡ መጀመሪያ መኢአድ ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጎ ምልዓተ ጉባዔ የተሟላበትን ሪፖርት ያቅርብ የሚል ነገር አመጣ፡፡ ችግሩ ይኸው ነበር፡፡ ለወደፊት ያለውን እግዚአብሔር ይወቀው፡፡

  ሪፖርተር፡- ምርጫ ቦርድ ምልዓተ ጉባዔ አልተሟላም ሲል እናንተ ተረስቶ የቀረ ነው በሚል የ41 ሰዎች ስም ዝርዝር አስገብታችሁ ውድቅ ተደርጓል፡፡ አሁን ደግሞ የእነዚህን 41 ሰዎች አባልነት በጥልቅ መርምሮ ማፅደቁን አስታውቋል፡፡ ከዚህ አንፃር ውሳኔውን እንዴት ያዩታል?

  አቶ አበባው፡- በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ መጀመሪያውኑ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሄደናል፡፡ የምርጫ ቦርድ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ወደሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ሄደናል፡፡ ከቦርዱ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ተነጋግረናል፡፡ ነገር ግን መፍትሔ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ አሁን ግን እኛ አመልክተን ነበር፡፡ ያመለከትነው ምንድነው ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ውጤት ትክክል አይደለም፡፡ አንደኛ እነዚህ ሰዎች ወደ አመራርነት ለመምጣት አባል መሆን አለባቸው፡፡ ሁለተኛ የመኢአድ አባል ያልሆነ 151 ሰው ይዘው ገብተዋል፡፡ አቶ ማሙሸትን መረጥን ያሉት 164 ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት አቶ ማሙሸትን የመረጡት ከመደበኛ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት መካከል 13 ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ኢንጂነሩ ያመጧቸው 151 ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ስህተት ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድም ይህን ተከትሎ የአሁኑን ውሳኔ መስጠቱ ትክክለኛ ነው፡፡ ነገር ግን ከበፊቱ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ቦርዱ ይህንን ውሳኔ መስጠት የነበረበት በጥቅምት 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ ያን ሳያደርግ እስካሁን ቆይቷል፡፡ ያን እንግዲህ ምርጫ ቦርድ እንጂ እኔ አይደለሁም የምመልሰው፡፡

  ሪፖርተር፡- ቦርዱ የተቀበለው የሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ውጤትን ነው?

  አቶ አበባው፡- አዎ ትክክል ነው፡፡ መቀበል የነበረበት ግን ድሮ ነው፡፡ አቤት እያልን፣ እያለሰቅን በነበረበት ጊዜ መቀበል ነበረበት፡፡ አሁን ያንን ተንተርሶ ውሳኔ መስጠቱን እንግዲህ ምርጫ ቦርድ የሚመልሰው ጥያቄ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ውሳኔውን ተከትሎ አቶ ማሙሸት በርካታ አባላት አሁንም አብረዋቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ እርስዎም ቢሮ ተረክበው አባላትን እያደራጀን ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የፓርቲው አባላት ጉዳይ እንዴት እየታየ ነው? ፓርቲውስ ምን ያህል አባላት አሉት? በመላው አገሪቱ ያለው የቢሮ ብዛትስ ምን ያህል ነው?

  አቶ አበባው፡- እነአቶ ማሙሸት አባላትን ይዘን ሄደናል የሚሉት ነገር በምንም ተዓምር የሚሆን አይደለም፡፡ ከእነርሱ ጋር ያለ አንድም አባል የለም፡፡ እኛ በሁሉም ዞኖች መዋቅር አለን፡፡ ወደ 22 በሚሆኑ ዞኖች ቢሮዎች አሉን፡፡ አሁን እንግዲህ የፋይናንስ ችግር ስለሚገጥመን ሊቀጥል የሚችል አይመስልም፡፡ ስለዚህ ይህ ሆኖ ሳለ እነ አቶ ማሙሸት አባላት ይዘን ሄደናል፣ ከእኛ ጋር ናቸው የሚሉት በምንም ዓይነት ተዓማኒነት የሌለው ነው፡፡ አባላትን በተመለከተ የመኢአድ ስትራቴጂ ቢሮ መክፈት ብቻ አይደለም፡፡ መዋቅር እየሠራ ሰዎችን በሚመቻቸው ቦታ እየሰበሰበ የፓርቲውን ሥራ እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ፓርቲውን ከዚህ አንስተን እስከ ደቡብ ኦሞ ሴሚናር የሚባል ቦታ ድረስ፣ እስከ ገሊላ ድረስ፣ ሱዳን ጫፍ፣ ኬንያ ጠረፍ፣ አፋር ሙሉ በሙሉ፣ አማራ በሙሉ፣ ደቡብ በሙሉ፣ በምዕራብና በኦሮሚያ እንዲሁ ቢሮዎች አለን፡፡ ስለዚህ መዋቅራችን በሁሉም ቦታ ነበር፡፡ ነገር ግን ገዢው ፓርቲ ስለፈራ ነው ይህን ሁሉ መሰናክል የሚጥልብን፡፡ ጊዜ እንዳይኖረን አድርጓል፡፡ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታችን ተወስዶ ለሌላ ተሰጥቷል፡፡ የምርጫ ቦርድ አዋጅ 573/200 አንድ ምልክት ለአንድ ፓርቲ ከተሰጠ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት አይወስድበትም ይላል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ይህንን ጥሶ ምልክታችንን ለመኢብን ሰጥቶብናል፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ወይም ደግሞ ገዢው ፓርቲ ታላቅ ተወዳዳሪዎች፣ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ሆነን እንዳንቀርብ ያደረገው ዘዴ ነው፡፡ ይህ በግልጽና በግልጽ የኢትዮጵያ ሕዝብም የማያውቀው ነው፡፡ ለዚህ ነው ይኼ ሁሉ ድራማ የተሠራው፡፡

  ሪፖርተር፡- የአባላትን ቁጥር አልነገሩኝም?

  አቶ አበባው፡- ከሚሊዮን በላይ አባላት አሉን፡፡

  ሪፖርተር፡- የተመዘገቡ?

  አቶ አበባው፡- አዎ የተመዘገቡ፡፡ የመኢአድ ልጆች ከሚሊዮን በላይ በመላው አገሪቱ አባላት አሉን፡፡

  ሪፖርተር፡- የአንድነት ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የፓርቲውን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ሲለቁ ካስቀመጡት ምክንያት ዋነኛው የዳያስፖራው ተፅዕኖ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በመኢአድ ውስጥ የዳያስፖራው ተፅዕኖ ምን ይመስላል? ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህን የዳያስፖራ ተፅዕኖ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል? ዳያስፖራው ፓርቲው ውስጥ ችግር እንዳይፈጠርስ እንዴት ነው የምትከላከሉት?

  አቶ አበባው፡- አንድነትን በተመለከተ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ እንደ ምሳሌ ሊነሳ ይችላል፡፡ እንደ መኢአድ ግን ዋና ደጋፊያችን ዳያስፖራው ነው፡፡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሞራል የሚደግፈን ዳያስፖራው ነው፡፡ ይህንን መቀበል መቻል አለብን፡፡ ያም ቢሆን ግን ዳያስፖራው ገንዘብ ሰጠን ብለን በፖለቲካው ውስጥ በቀጥታ ገብቶ ሊሠራ አይችልም አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካው የሚካሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ፡፡ ነገር ግን አገራቸው ነውና አገራቸው ውስጥ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የተቻላቸውን ያህል ማድረግ አለባቸው፣ አድርገዋልም፣ እያደረጉም ነው፡፡ ይኼ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ከእነርሱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካው እየተሠራ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ያ ነው ይኼ ነው የሚሉት ነገር አያስኬድም፡፡ በእኛ ዘንድ እንዲህ ያለው ነገር ብዙም አይደለም፡፡ እስካሁን ገጥሞን አያውቅም፣ ለወደፊቱም ይገጥመናል አንልም፡፡ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓና አውስትራሊያ ውስጥ ቻፕተር አለን፡፡ እነዚያ ፓፕተሮች ዓላማቸው ምንድነው? ምክር መስጠት፣ ስትራቴጂ ማውጣትና በገንዘብ ፓርቲውን መደገፍ ነው እንጂ ፖለቲካው ውስጥ ገብተው እከሌ ይሾም፣ እከሌ ይሻር የሚል ብዙም የለም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሁንም በእነአቶ ማሙሸት መምጣት ላይ ከኢንጂነር ኃይሉ ጋር ሆነው ወዲህ ወዲያ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ እከሌ እከሌ ማለት አልፈልግም፡፡ የሠሩትም መልካም ሥራ ስላልሆነ ማንሳትም አልፈልግም፡፡ የሠሩት ሥራ ኢትዮጵያን የሚጠቅም አይደለምና፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ በእኛ ቤት ብዙም ተፅዕኖ የለብንም፣ ተስማምተን ነው የምንሠራው፡፡ ለወደፊቱ የሚሆነውን እናያለን፡፡

  ሪፖርተር፡- ፓርቲው ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተመዘገቡ አባላት አሉት ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ ዳያስፖራው ፓርቲውን በገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ የፓርቲው የገንዘብ ምንጭ የአባላት መዋጮ ነው ወይስ የዳያስፖራው አስተዋጽኦ?

  አቶ አበባው፡- ሁለቱም ነው፡፡ ከአባላት መካከል ገበሬ አለ፣ ተማሪ አለ፣ ደሃ አለ፡፡ ያንን አባል አስር ብር ሃያ ብር አዋጣ አንልም፡፡ የቻልከውን ያህል ክፈል ነው የምንለው፡፡ 50 ሣንቲም ሊከፍል ይችላል፣ ሁለት ወይም ሦስት ብር ሊከፍል ይችላል፡፡ ያ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የዚያ ክፍተት መደጎሚያው ማነው? ዳያስፖራው ነው፡፡ አባላት እንደ አባላት ወርኃዊ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ ነገር ግን የዳያስፖራው ድጋፍ ተጨማሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ በምናካሂድበት ጊዜ ዕጩዎችን ለማስመዝገብ፣ ታዛቢ ለማስቀመጥና ለመሳሰሉት በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ያ ከአባላት ሊዋጣ አይችልም፡፡ በዚህን ጊዜ ዳያስፖራው ይደግፈናል ማለት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ እየተዘጋጃችሁ ስለሆነ አሸንፋችሁ ብትመረጡ ለሕዝቡ የምታቀርቡት አማራጭ ምንድነው?

  አቶ አበባው፡- የመኢአድ ዋና ዋና ፖሊሲ አንደኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ጥላ ሥር መኖር አለባቸው፡፡ በጎሳና በዘር ተከፋፍለው የጎሪጥ መተያየት የለባቸውም፡፡ ችግሩንም ደስታውንም አብረው መካፈል አለባቸው፡፡ ይህ የመኢአድ አቋም ነው፡፡ ሁለተኛ ዜጎች ጥሪት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሬት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም ሆነ በክልል ከተሞች መሬት የዜጎች መሆን መቻል አለበት፡፡ መሬት እኮ ተርፎናል፡፡ ስለዚህ ኢንቨስተሮች በጠረፍ ሄደው አልምተው ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤቱን እያፈረስን የምናባርረው ከሆነ፣ በክልል ያለውን የምናባርረው ከሆነ፣ አራሹን ገበሬ አስነስተን ለአበባ ወይም ለሌላ ልማት የምንሰጠው ከሆነ ይኼ አገር የሚጠቅም አይደለም፡፡ ከውጭ ለልማት ተብሎ እዚህ መጥተው ሾፌር ሆነው፣ የቀን ሠራተኛ ሆነው፣ ብሎኬት እያመረቱ፣ ግንበኛ ሆነው የሚሠሩ የውጭ ዜጎች አሉ፡፡ ይኼ ሁሉ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን መያዝ አለበት የሚሉትና የመሳሰለው ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- መኢአድ የዘንድሮን ምርጫ በተመለከተ አዲስ ሚኒፌስቶ አለው?

  አቶ አበባው፡- እያዘጋጀን ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- መቼ ይደርሳል?

  አቶ አበባው፡- አንድ ወር ያህል ይወስድብናል፡፡

  ሪፖርተር፡- በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የምርጫ ቅስቀሳ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡ ከዚህ አንፃር ማኒፌስቶ የማዘጋጀቱ ነገር በአንድ ወር ያህል መዘግየቱ አያስቸግርም?

  አቶ አበባው፡- እኛ ያለንበትን ሁኔታ ተመልከትልን፡፡ ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል በሥልጣን ላይ ሆነው ምሁራን እየተባረሩና እየወጡ ደቃቃ ሰዎች ነው እዚህ የተቀመጡት፡፡ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች በእሳቸው የተነሳ ከዚህ ቤት ለቀዋል፡፡ ስለዚህ እርሳቸውን ይዘው የቆዩ፣ እርሳቸውን እንደ ጣዖት የሚያመልኩ፣ ያልተማሩና ዝቅተኛ ሰዎችን ነው ይዘው የቆዩን፡፡ ስለዚህ መኢአድ አሁን ሰው የለውም፡፡ በግልጽ ለመናገር በቂ ሰዎች ስለሌሉ ያሉትን ሰዎች እያዘጋጀን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከአንድ ወር በፊት ሊደርስልን አይችልም፡፡

  ሪፖርተር፡- ምን ያህል ዕጩዎችን ለማቅረብ አቅዳችኋል?

  አቶ አበባው፡- ከ400 በላይ ዕጩዎችን ለማቅረብ አዘጋጅተን ነበር፡፡ ግን ጊዜ የለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግፋ ቢል 100 ያህል ዕጩዎች ብናስመዘግብ ነው፡፡ ያም ገና አልተረጋገጠም፡፡ ፎርሙን ልከን እንዲመዘገቡ አድርገናል፡፡ አሁንም ብዙ መሰናክሎች አሉ፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -