በባዶ እግሩ ሮጦ የኦሊምፒክ ጫማ ማራቶን አሸናፊ በነበረው አበበ ቢቂላ ስም ያለፈቃድ ጫማ ያሰራጨው ታዋቂው የጫማ አምራች ኩባንያ ቫይብራም ላይ የአበበ ቢቂላ ቤተሰብ ክስ መመሥረቱን ዘ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ባለአምስት የእግር ጣቶች ጓንት መሰል የሩጫ ጫማ አምራቹ ቫይብራም ኩባንያ ከሚያመርታቸው ጫማዎች ጥቂቶቹን ‹‹ቢቂላ›› በሚል መጠርያ ከአምስት ዓመት በፊት ሰይሞ በአሜሪካ በሽያጭ ማሰራጨቱም ታውቋል፡፡
ክስተቱን ተከትሎ ባለፈው ሐሙስ በአገሪቱ ፌዴራል ፍርድ ቤት ክሱን የመሠረተው የአበበ ቢቂላ ልጅ ተፈሪ ቢቂላ ኩባንያው አንዳች ፈቃድ ያልተሰጠውና ቤተሰቡም ተጠቃሚ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡
ለአበበ ፈለግ ክብር መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም የ45 ዓመቱ የቲጋርድ ኦሪገን ነዋሪው ተፈሪ አበበ ቢቂላ የገለጸ ሲሆን፣ ጠበቃቸው አሌክስ ትራውማን እንደተናገረውም፣ ቤተሰቡ ቢያንስ የ15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ይፈልጋል፡፡
ከ41 ዓመት በፊት ሕይወቱ ያለፈው አበበ ቢቂላ በጳጉሜን 1952 ዓ.ም. የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር በሮም አውራ ጎዳናዎች፣ በባዶ እግሩ ሮጦ በ2 ሰዓት 15 ደቂቃ 16 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመፈጸም፣ የወቅቱን የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን መስበሩና ከአራት ዓመት በኋላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ (ጥቅምት 1957 ዓ.ም.) የማራቶን ድሉን መድገሙ ይታወሳል፡፡