አምስተኛው የባህል ሳምንት በስፋት ላልታዩ ባህላዊ እሴቶች ትኩረት እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡
በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከየካቲት 15 እስከ 20፣ 2007 ዓ.ም. የሚካሄደው የባህል ሳምንት ፌስቲቫል፣ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የየአካባቢያቸውን ባህላዊ እሴቶች እንደሚያሳዩ፣ ባዛርና ዐውደ ጥናት እንደሚካሄድ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር ዴኤታው በጽሕፈት ቤታቸው የካቲት 11 ቀን በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ኅብረ ብሔራዊነታችን ለሕዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የባህል ሳምንት ክልሎቹ ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁበትና መስህቦቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እልፍነሽ ኃይሌ እንደተናገሩት፣ ፌስቲቫሉ ከብሔር ብሔረሰቦች ቀንና ከቀደሙት አራት የባህል ሳምንቶች ተሞክሮ በመውሰድ ተጠናክሯል፡፡ እንደ ዶክተሯ ገለጻ፣ ፌስቲቫሉ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም. የተጀመረው የባህል ሳምንት በተከታታይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአዲስ አበባና በጎንደር መከበሩ ይታወሳል፡፡