Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊጫት ከምን ጊዜውም የበለጠ በገጠርም ሆነ በከተማ በስፋት ጐልቶ የወጣበት ጊዜ ነው...

  ጫት ከምን ጊዜውም የበለጠ በገጠርም ሆነ በከተማ በስፋት ጐልቶ የወጣበት ጊዜ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

  ቀን:

  ጫት ከምን ጊዜውም የበለጠ በገጠርም ሆነ በከተማ በስፋት ጐልቶ የወጣበት ጊዜ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በገጠሩ መልክአ ምድር፣ በከተማው ገበያ፣ ማስታወቂያና በመቃሚያ ቤቶች በብዛት ጫት እዚህም እዚያም እንዲታይ ሆኗል፡፡ አነቃቂው ዕፅ ጫት ሚሊዮኖች የሚጠቀሙት፣ አነስተኛ ደረጃ አምራች ገበሬዎች የሚመርጡት፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ፣ በጥቅሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ከባድ የሆነ ምርት ሆኗል፡፡ ከጫት ታክስ ለመሰብሰብ በመፈለግ የድንበር ግጭት የተፈጠረባቸው አካባቢዎች መኖር ደግሞ የጫት ፖለቲካዊ አንድምታም ቀላል ላለመሆኑ ምስክር ነው፡፡  

  ከአምራች ገበሬዎች ጀምሮ በአዘገጃጀት፣ በትራንስፖርት፣ በሥርጭት፣ በሽያጭ ላይ የተሰማሩ ብዙዎች ከጫት በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ ተጠቃሚነቱ ለውዝ፣ ውኃ፣ ሲጋራ፣ ሻይ ቡና ለሚሸጡ እታች ድረስ ወርዷል፡፡ ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ቀዳሚዎቹ ደረጃ ላይ የሚገኘው፣ የብዙዎች የሀብት ምንጭና እንጀራ የሆነው ጫት በተለያየ መልኩ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት እየሆነ መሆኑንም በሚመለከት ብዙ ተብሏል ጥናቶችም ተሠርተዋል፡፡

  በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ እስያና አውስትራሊያ መስፋፋቱን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃም የጫት ጥቅምና ጉዳት አወዛጋቢና አከራካሪ ሆኗል፡፡ በጫት ዙሪያ ያለው ክርክር በዓለም አቀፍ ደረጃ አደንዛዥ ዕፅን መዋጋት፣ የሽብርተኝነት ፍርኃትና የምዕራባውያን የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል የበላይነትን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የተቃኘ መሆኑን የሚያሳይ ጥናት አለ፡፡

  ወደ አገራችን የጫት እውነታ ሲመጣ ጫትን በሚመለከት የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ የተሠሩ ጥናቶችም ሲታዩ አንዳንዳቹ የጫት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ተፅዕኖ ላይ ሲያተኩሩ ሌሎቹ በጫት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ጥናቶቹ አንዱ የአንዱን ግኝት ውድቅ የሚያደርጉበት ሁኔታም ይታያል፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጫት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ውስንና አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ መሆናቸውን በመግለጽ ጫት እንደዚህ ነው እንደዚያ ለማለት ነገሩ በሚገባ ሊጠናና ሊታወቅ እንደሚገባ የሚከራከሩ አሉ፡፡

  ከጥቂት ቀናት በፊት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሠተብርሃን አድማሱ የጫትና የሺሻ ሥርጭትና ንግድ ላይ ገደብ የሚጥል ረቂቅ ሕግ በፍትሕ ሚኒስቴር መዘጋጀቱንና በረቂቁ ላይ ሕዝባዊ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ በውይይት የሚንፀባረቁ ሐሳቦች ጫት ቃሚነትና የሚያደርሰው የጤና ተፅዕኖ ላይ ከማተኮር ዘልለው የጫትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አንድምታ ያላገናዘቡ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡ ሰዎች ለምን ጫት ይቅማሉ? የጫት ምርት ምን ያህል እየተስፋፋ ነው? በጫት ዙሪያ ያሉ እንቅስቃሴዎች የፖሊሲ አንድምታ በጥናት አለመገለጹና አለመተንተኑም በጥናቶች ተመልክቷል፡፡

  በጫት ላይ ጥናት የሠሩት ዶ/ር ዘሪሁን መሐመድ ስለጫት በአገር ውስጥ የተሠሩ ጥናቶች ጥቂት መሆናቸውን በመግለጽ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ምን ያህል ስለጫት ታውቆ ወደ ቁጥጥር ሊገባ ይችላል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በጫት ዙሪያ የተለያዩ ክርክሮች ቢኖሩም ጫት በአሁኑ ወቅት በብዙዎች የዕለት ተዕለት ዕይታ ውስጥ ያለ፣ የሚሊዮኖችን ኑሮ የሚነካ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አምራቾች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን በመያዝና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በማስገኘት በአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነት ራሱን ሁነኛ ቦታ ላይ ያሳረፈ ምርትም ሆኗል፡፡

  ‹‹የወጣት ሥራ››  

  ጥናታቸውን በሰሜን ሲዳማ በሚገኙ ጠፈራና ቱላ በተባሉ ሁለት የጫት ገበያዎች (እሳቸው እንደሚሉት ከገበያ ይልቅ ጫት ማደራጃ የሚለው ይገልጻቸዋል) ላይ ያደረጉት ዶ/ር ግርማ ነጋሽ፣ ጫት በሚመረትባቸው አካባቢዎች በብዙ መልኩ ወጣቶችን የቀጠረ የወጣት ሥራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከእያንዳንዳቸው በቀን እስከ አሥር አይሱዙ ጫት ተጭኖ በሚወጣባቸው በእነዚህ ገበያዎች ጫት የመቁረጥ፣ የማሰር የመቀላቀል፣ የመጫንና የማጓጓዝ ሥራ የሚሠራው በወጣቶች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህ ገበያዎች ጫት በማሠር፣ በመቀላቀል ሥራ የተሰማሩ ሕፃናት መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡ አንዳንዶቹ ሕፃናት ለሥራቸው የሚከፈላቸው በገንዘብ ሳይሆን በጫት ቅጠል መሆኑንም የሚገልጹ አሉ፡፡   

  ጫት በአጭር ጊዜ (በ48 ሰዓት) የሚበላሽ ከመሆኑ አንፃር ጫትን በማደራጀትና በማጓጓዝ የፍጥነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች እንቅስቃሴ ወጣቶች በምን ዓይነት ኃይል ሥራውን እየሠሩና እየተጠቀሙ እንደሆነ እንደሚያሳይ የሚናገሩት ዶ/ር ግርማ፣ በተቃራኒው ጫት ወጣቶችን እየጐዳ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው ጥናታቸውን ባቀረቡበትና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ማኅበራዊ ጥናት መድረክ) ‹‹ጫትና ወጣቶች›› በሚል ርእስ ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ጫት ምን ያህል ወጣቶችን ጠቅሞ ወጣቶችን ተጠቃሚ አደረገ? አስገኘ የሚባለው ጥቅምስ ወጣቱ ላይ እያደረሰ ካለው ሥነ አእምሮአዊ፣ ሥነ አካላዊና ማኅበራዊ ኪሳራ አንፃር ይገመታል ወይ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው ነበር፡፡ የቃሚ ቁጥር መብዛትን፣ በተማሪዎች በተለይም የወጣት ቃሚዎች መብዛትን በመጥቀስ ጫት መታገድ አለበት የሚል አቋምም በተለያየ መልኩ ይንፀባረቃል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የጫት ምርት እየተስፋፋ፣ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪም እየጨመረና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ከፍተኛ መሆኑ ቀጥሏል፡፡

  ጫትን ማገድ?

  እስካሁን ጫትን የሚያግድ ምን ምን ዓይነት ሕግ በአገሪቱ የለም፡፡ ይልቁንም ከጫት ጋር የተያያዙ አሉታዊ አመለካከቶች መሠረት ማኅበራዊ  እሴት መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ ‹‹ጫት ይውደም ይታገድ›› የሚል አቋም የሚያራምዱ ቢኖሩም፡ ፍላጐት እያለ ማገድ ውጤታማ እንደማይሆን ዶ/ር ግርማ ይናገራሉ፡፡ የእሳቸውን ሐሳብ የሚጋሩት ዶ/ር ዘሪሁንም ጫት ይታገድ ቢባል የጫት ንግድ በኮንትሮባንድ እንዲቀጥል ከማድረግ በዘለለ የሚያመጣው ውጤት ይኖራል ብለው አያምኑም፡፡ የሰው ልጅ አእምሮአዊ ጤና ጉዳት ኪሳራ እንዴት ከገንዘብ ጥቅም ጋር ሊነፃፀር ይችላል? የሚል ጥያቄ ያነሱትና በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ወ/ሮ ዘሚ የኑስ ጫትን ከማስቆም ውጭ ጫት እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ችግር በምንም ዓይነት መንገድ ማስቀረት እንደማይቻል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

  ጫት ለብዙዎች እንጀራ ቢሆንም በጫት ይበልጥ የተጠቀመና የበለፀገው ማነው? የሚል ጥያቄ በመድረኩ የቀረበው ጥናት ገምጋሚ በነበሩት ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ጨምሮ በሌሎችም በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡ በትምህርት ዓለም መሆን የሚገባቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች በጫት ንግድ ላይ መሰማራት ብሎም በዚህ ዕድሜ መቃም መጀመር ስለ ጥቅም ሲወራ ከግንዛቤ መግባት ያለባቸው ነገሮች እንደሆኑ ዶ/ር አሉላ ይገልጻሉ፡፡ ተጠቀሙ የሚባሉ ወጣቶች ወጣቶችን ይወክላሉ ወይ? ብዙዎችን በያዘውና በረዥሙ በተዘረጋው የጫት ንግድ ሰንሰለት ማን ነው የበለጠ እየተጠቀመና እየበለፀገ ያለው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ይሆናል፡፡

  ከጫት ተገኘ እየተባለ ያለው ገቢ ትርፍ ሳይሆን ነገ አገሪቱ በተለያየ መንገድ ዋጋ የምትከፍልበት ብድር መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አገኘን የምንለው ነገ የምንከፍለው ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር የራስወርቅ፣ ዛሬ ጫት እያደረሰ ያለው ቀውስ ነገ አገሪቱ የምትሸከመው እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡

  የዝምታ ፖሊሲ

  ፖሊሲ አለማውጣት ራሱ ፖሊሲ ነው የሚል አስተያየታቸውን የሚሰነዝሩ ቢኖሩም እንደ ኢትዮጵያ ጫት በስፋት የሚያመርትና የሚጠቀም አገር እንዴት ጫትን የሚመለከት ፖሊሲ አይኖረውም? መንግሥት በጫት ላይ ያለው አቋም የማበረታታት ወይስ የጫትን መስፋፋት የመግታት?  ምርቱን ማሻሻል አይፈለግም? አይሞከርም? ከጫት ገቢ የሚገኘውን ግብር ከፍ ማድረግስ አይታሰብም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡

  አምና የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረዙበበት ወቅት ወጣቱ ላይ ችግር እያስከተለ ያለው ጫትን በሚመለከት፣ ምርቱ እየተበረታታ እንዲቀጥል ወይስ እንዲገታ የማድረግ አቅጣጫ በመንግሥት እንደተያዘ በአንድ የፓርላማ አባል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹ጫትን ለማበረታታት የምንሠራው ሥራ የለም ለግብርና ምርታችን የኤክስቴንሽን ሠራተኛ መድበን እናበረታታለን፤ የማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ምርጥ ዘርም እናቀርባለን፡፡ በጫት ላይ ግን የምንሠራው ምንም ድጋፍ የለም፡፡ ግን በራሱ ጉልበት እየቀጠለ ነው፡፡ እኛም እንደ ንግድ ሚኒስቴር እየሸጥን ተጠቃሚ መሆን አለብን፣ እየሸጥንም ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ መንግሥት የጫት ምርትን እንደማያበረታታ እንደማያዳክምም አስረግጠዋል፡፡

  የ2007 ዓ.ም. የኤክስፖርት ዕቅድ እንደሚያሳየው፣ ኤክስፖርት የሚደረግ የጫትን በ15 በመቶ በመጨመር 60,435 ቶን፣ በገቢ ደግሞ በ9.9 በመቶ በማሳደግ 331.5 ሚሊዮን ዶላር የማድረስ ውጥን አለ፡፡ የንግድ ሚኒስቴር የ2007 ዓ.ም. የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ በግማሽ ዓመቱ 30,384.69 ቶን የጫት ምርት በመላክ 166.67 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 27,153.77 ቶን በመላክ 149.75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2013 “Favouring a Demonised Plant” [የተወገዘ ተክልን መደገፍ] በሚል ርእስ በሠሩት ጥናታቸው ጫት በአገር፣ በክልልና በቤተሰብ ደረጃ ጥቅም እያስገኘ እንደሆነ ያስቀመጡት ዶ/ር ገሠሠ ደሴ፣ ምንም እንኳ ጐን ለጐን ጫት በተጠቃሚዎች ላይ የጤና፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ቀውስ እያስከተለ ቢሆንም አሉታዊ ጐኑ ብቻ መጉላት እንደሌለበት ያመለክታሉ፡፡ ይልቁንም እንደ አልኮልና ትምባሆ ሁሉ የጫት አጠቃቀምን በመቆጣጠር የጫትን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡

  የጫት ይውደም፣ ይታገድ፣ ዝምታ አካሔድ ሳይሆን ጫትን መቆጣጠር ተመራጭ ዕርምጃ እንደሚሆን ዶ/ር የራስወርቅም ይስማማሉ፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አንድ ነገር፣ ንግድ ሚኒስቴር ሌላ ሲል የተደበላቀ መልዕክት እየተላለፈ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ዘሪሁን፣ መንግሥት ጫትን በሚመለከት ጥርት ያለ አቋም ሳይዝና አቅጣጫ ሳያስቀምጥ እንዴት ወደ ቁጥጥር ይገባል? ይላሉ፡፡ በተጨማሪ ጫትን በሚመለከት የወጣ አንድ መጽሐፍ ብቻ መኖሩን በመጥቀስ ስለጫት ጥቅምና ጉዳት በደንብ ሳይጠናና ሳይታወቅ ወደ ቁጥጥር መግባት ውጤታማ አይሆንም የሚል ሥጋታቸውን ያንፀባርቃሉ፡፡

  የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለሥልጣንና ፌደራል ፖሊስ በባለድርሻነት የተሳተፉበትና የጫትና የሺሻ አቅርቦት፣ ሥርጭትና አጠቃቀምን በሚመለከት በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ የጫት አቅርቦትን በመገደብ ጫትን በመቆጣጠር እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ጫት መሸጥ ያለበት ለማን፣ የት፣ በምን ሰዓት፣ መቃም የሚቻለው የት ነው? የሚሉና ሌሎች ነገሮች በረቂቁ መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማስታቂያም ሌላ የታየ ጉዳይ ነው፡፡

  ባለፈው ጥቅምት ወር ሊካሔድ የነበረው የጫት ሲምፖዚየም በአጭር ጊዜ ማስታወቂያ መሠረዙ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ረቂቅ ሕግ ላይ በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚዘጋጅ ሲምፖዚየም ሕዝባዊ ውይይት እንደሚደረግ ዶክተር ከሠተ ብርሃን አድማሱ የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን በተዘጋጀ መድረክ ላይ ገልጸዋል፡፡

  ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ሪጅን ቢሮ ተወካይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ውይይት መሠረት፣ ጫት እያደረሰ ያለው ጉዳትን በሚመለከት ጥናት እንዲሠራና የጥናቱ ውጤት የፖሊሲ ግብዓት እንዲሆን ታስቦ ነበር፡፡ ታስቦ የነበረው የሲምፖዚየም ውይይትም የፖሊሲ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን የክልል ፕሬዚዳንቶች በውይይቱ ላይ ሊገኙ እንደማይችሉ በመታወቁ ሲምፖዚየሙ ተሠርዟል፡፡

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...