Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ስለአክሲዮን ማኅበራት ዝም አይባልም

  ‹‹አክሲዮን በመግዛት የንግድና ኢንዱስትሪ ተቋማት ባለቤት ስለመሆን ቀደም ብሎ ምስጢሩ የተገለጸላቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምንሊክ ናቸው፤›› ይላል፣ በቅርቡ በመቐለ ከተማ አክሲዮን ኩባንያዎችን በተመለከተ በተደረገ ውይይት መድረክ ላይ የመድረኩ መሪ ለውይይቱ መግቢያ ያቀረቡት ጽሑፍ፡፡ አፄ ምንሊክ፣ የአክሲዮን ኩባንያዎች ጥቅም የገባቸው ስለመሆኑም እ.ኤ.አ. በ1909 በኒውዮርክ ታይስም ላይ የሰፈረውን ጽሑፍ በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡ አፄ ምንሊክ ‹‹በፓሪስ ቡርሳ›› (የፓሪስ አክሲዮኖች ገበያ) በኋላም በአሜሪካን የባቡር መንገዶች ልማት ሒደት ላይ አክሲዮኖች ይገዙና ይሸጡ እንደነበር በወቅቱ መዘገቡን ጠቅሰዋል፡፡

  የአፄ ምንሊክ አክሲዮን መሸጥና መግዛት ታሪክን ባሮን ደ ያቪስበርግ የተባለ የቤልጄም ተወላጅ ኢትዮጵያንና አፄ ምንሊክን ጎብኝቶ ሲመለስ እ.ኤ.አ. ኖቨምበር 17 ቀን 1909 በኒውዮርክ ታይምስ ላይ ያሳተመው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመድረክ አጋፋሪው ይኼንን ታሪክ አገላብጠው ለውይይት መግቢያ ያደረጉት ያለ ምክንያት አይመስለኝም፡፡ የአክሲዮን ኩባንያዎች ጥቅም አለው ለማለት ብቻ ሳይሆን ስለአክሲዮን ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያን የቆየ ታሪክ እንዳላቸው ለማስገንዘብም ጭምር ይመስላል፡፡

  በመቐለ የተካደውን የውይይት መድረክ ካዘጋጁት አካላት መገንዘብ እንደቻልኩት፣ በአክሲዮን ኩባንያዎች ዙሪያ መወያየት የተፈለገበት አንዱ ምክንያት የአክሲዮን ኩባንያዎች ሚና ለመጠቆምና በአክሲዮን ኩባንያዎች ዙሪያ ስላሉ ችግሮች መቀረፍና ወደፊትም እንዳይስፋፉ ለማስቻል ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት ከፖሊሲ አውጪው አካል የተወከሉ ተሳታፊዎችም ስለነበሩ የተፈለገውን ዓላማ ለመምታት ያስችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡

  የውይይት መድረኩ የተዘጋጀበት ምክንያት በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ዘርፉ አሉበት የሚባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተፈለገ አስፈላጊና ተከላካይ ሕጋግትን መንግሥት በአፋጣኝ እንዲያወጣ ለመገፋፋት ነው፡፡ በእርግጥም ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ በሚገኙ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት በአክሲዮን ደረጃ የተቋቋሙና በመቋቋም ላይ ያሉት ኩባንያዎች ውስጥ የታዩ ግድፈቶች እንዲታረሙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

  - Advertisement -

  በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የተቋቋሙ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት በሌሎች ዘርፎች ላይ በሚንቀሳቀሱ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሊያስገኙ የሚችሉትን ጥቅም ያህል ለምን እንዳልታየ በመመርመር መፍትሔ መፈለግ ያሻል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሊጠቅሙ የሚችሉበትን ያህል በአንዳንድ ብልጣ ብልጦች ምክንያት በሚፈጠር ችግር ኅብረተሰቡ በትክክል ሊሠሩ ከሚችሉ አክሲዮን ኩባንያዎች እንዲቀር ወይም እንዳይቋቋም እንቅፋት ሆኗል፡፡ አዋጭነት እንዳላቸው ለተረጋገጡ ኩባንያዎች መመሥረቻ የሚሆን ካፒታል አሰባስበው እንዳይሠሩም ጫና እየፈጠረ መሆኑን በመረዳት መንግሥት ጉዳዩን እንዲያስብበት ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡

  ባለፈው ሳምንት በይፋ ሥራ በጀመረው የራያ ቢያ ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ከአክሲዮን ማኅበሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደተደመጠውም በሥራ ሒደታቸው ከፍተኛ ችግር ሆኖ የቀረበው ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአክሲዮን ኩባንያዎች አካባቢ የተፈጠሩ ግድፈቶች ትልቅ ኢንቨስትመንት ለመፍጠር እንቅፋት ሊሆን መቻሉን ነው፡፡ ክፍተቱ በዚህ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አክሲዮን ለመግዛት ችሎታ ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኩባንያዎች፣ ባደረባቸው ጥርጣሬ እጃቸውንም፣ ገንዘባቸውንም በመሰብሰባቸው ዕድሉን የውጭ ኩባንያዎች እየወሰዱት ይገኛል፡፡ አክሲዮን ሊገዙ የሚችሉ ሰዎች በፍራቻ አክሲዮን ግዥ የሸሹትም መንግሥት ለንግድ አክሲዮን ማኅበራት ከለላ የሚሰጥ ሕግ ሊያወጣ ባለመቻሉ ስለመሆኑም እየተነገረ ነው፡፡

  በዚህ ረገድ ራያ ቢራና በተመሳሳይ የቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ አክሲዮን ሲያሰባስቡ የነበሩት ዘቢዳርና ሐበሻ ቢራን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የቢራ ቢዝነስ አዋጭ መሆኑ እርግጥ ሆኖ ሳለ የሚፈለገውን አክሲዮን ከሕዝቡ ለማሰባሰብ ግን ጥርጣሬ በማሳደሩ የቢራ ፋብሪካዎችን አብላጫ የባለቤትነት ድርሻ በውጭ ኩባንያዎች ሊወሰድ ችሏል፡፡

  በሦስቱም አክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ እንዲይዙ ያደረጓቸው ብዙዎች አክሲዮን ኩባንያዎች ላይ ያላቸው አመኔታ በጥርጣሬ የተሞላ በመሆኑ፣ የሚፈለገውን ኢንቨስትመንት ለሟሟላት ሲባል የውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛውን ድርሻ ገዝተው እንዲገቡ በመደረጉ ነው፡፡ እንደ አገር ሲታይ ይህ አደጋ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ከፍተኛ ካፒታል ለማሰባሰብ የአክሲዮን ኩባንያዎች ቀዳሚ አማራጮች በመሆናቸው፣ በዚህ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት በቶሎ መድፈኑ የግድ ቢሆንም መንግሥት ግን አዝጋሚ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ የአክሲዮን ኩባንያዎችን የሚገዛ ሕግ ለማውጣት ለምን ቸልተኛ መሆን እንዳስፈለገም ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ እስካሁን ያለውን ግድፈት የሚቀርፍ፣ ከዚህ በኋላም በርካታ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ የመንግሥት ዕርምጃ ፈጣን መሆን አለበት፡፡ የታዩ ግድፈቶችን በሕግ ማስተካከል በርካታ አክሲዮን ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ያስችላል፡፡

  የሕዝብ ኩባንያዎች መበራከታቸው ሌላኛው ጥቅሙ የአገሪቱ ውሱን ሀብት ወደ ውጭ እንዳይጋዝ ለማቀብ የሚያስችል በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ለመመልከት የሚረዳን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተበራከተ የመጣውን የውጭ ኩባንያዎች ስንመለከት ነው፡፡

  አገሪቱ በምትከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሳቢያ ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከሌሎችም የዓለም ክፍሎች ኢንቨስተሮች እየመጡ ነው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች ይዘው የሚወጡት ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስ በአገር ውስጥ ማሰባሰብ ቢቻል ኑሮ ወደ አገራቸው የሚወስዱትን ትርፍና ጥቅማ ጥቅሞች ማስቀረት በተቻለ ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን በአክሲዮን ተደራጅቶ፣ ከብዙዎች የሚሰሰቡ ጥቂት ገንዘብ በአግባቡ ሲገኝና ሥራ ላይ ሲውል ነው፡፡

  ሕዝባዊ የንግድ ተቋማት መበራከታቸው የግለሰቦችን ይዞታና የበላይነት በመቀናቀን ካፒታልና ሌሎች መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሀብቶችን በጋራ ለመጠቀም ብሎም አገሪቱን ለማበልፀግ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ የአክሲዮን መበራከት የእያንዳንዱን ግለሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድም ድርሻቸው ጉልህ ነው፡፡ ይህም ሲባል ግን  አጋጣሚውን ተጠቅመው የሚወሰልቱ፣ የሕዝብ ገንዘብ ሰብስበው እብስ የሚሉ መኖቸው እየታየ፣ መንገድ ጀምረው ዳር ሳያደርሱ ከስመው የሚጠፉ ባሉበት አገር ውስጥ መንግሥት ያሳየው ቸልታ ተደጋግሞ ተተችቷል፡፡ ከዘገየም ቢሆን ሕግ ሊያወጣ፣ አክሲዮን ማኅበራትን የሚቆጣጠር ተቋም ሊያዋቅር መሆኑን መግለጽም ካለመኖሩ የሚረዳ ነው፤ ይግፉበት፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት