Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ይገነባል የተባለው የጋራ ፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት ፈንድ አላገኘም

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – የመላው አፍሪካ ቆዳ ዓውደ ርዕይ ዛሬ ይጠናቀቃል

  በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ብልከት ከሚያስከትሉ የኢንዱስትሪ መስኮች አንዱ የሆነው የቆዳ ኢንዱስትሪ፣ የጋራ የፍሳሽ ማስወገጃ ይገነባለታል ከተባለ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመተግበር 800 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የመንግሥት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ይህንን ገንዘብ ከአበዳሪዎችና ከለጋሾች ለማግኘት ሲጠባበቅ ቢቆይም ፈንድ የሚያቀርብ እስካሁን አለመገኘቱ ታውቋል፡፡

  ለአምስት ዓመታት ያህል ሲንከባለል የቆየው የጋራ ፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት፣ ‹‹ሌዘር ሲቲ›› የሚል ስያሜ ባተረፈችው በሞጆ ከተማ ይመሠረታል ተብሎ ሲጠበቅ የቆየ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ያስፈለገበትን ምክንያት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደሚደመጠው፣ በእያንዳንዱ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ውስጥ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት መትከል ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑና ይህንን ሥርዓት በተናጠል ለመዘርጋት ለፋብሪካዎቹ ከባድ ሆኖ በመገኘቱ ነው ይላል፡፡

  በመሆኑም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱት 29 የቆዳ ፋብሪካዎች ቢያንስ መጀመሪያ ደረጃ ፍሳሽ ማስወገጃ እንዲኖራቸው፣ ቀስ በቀስ ግን ሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ደረጃ ማጣሪያዎችን እንዲተክሉ ይጠበቃል፡፡ እስካሁን በሁለተኛውና በሦስተኛው ደረጃ የበካይ ፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ የተከሉ ፋብሪካዎች በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው ባሻገር፣ እስከቀርብ ጊዜ ድረስ አዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የፍሳሽ አወጋገዳቸውን በማያስተካክሉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ሲያስጠነቅቅ መክረሙ አይዘነጋም፡፡ ቀነ ገደብ አስቀምጦ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን በአንዱም ፋብሪካ ላይ የማሸግ እርምጃ አልወሰደም፡፡ ይህም በመካከሉ ስምምነት ተደርጎ ስለነበር እንደሆነ፣ ፋብሪካዎች የተቀመጠላቸውን ዝቅተኛ ግዴታ ለመወጣት ፈቃደኛ ሆነው በመገኘታቸው የተነሳ እንደሆነ ይታሰባል፡፡

  አርብ የተከፈተውና ዛሬ፣ የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው መላው አፍሪካ የቆዳ ዓውደ ርዕይ (የኦል አፍሪካ ሌዘር ፌር) ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ መንግሥት ምንም እንኳ ለጋራ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ራሱን የቻለ ፈንድ ባያገኝም፣ በአገሪቱ ትልቁ ቆዳና ጫማ አምራች ፋብሪካ ተብሎ ከተመዘገበው የታይዋኑ ጆርጅ ሹ፣ ማጣሪያ ማስወገጃ ዲዛይን ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

  በሌላ በኩል ዘርፉን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚጠቅሱት፣ በአገሪቱ ያለው የጥሬ ቆዳ አቅርቦት ሳይሻሻል፣ ይባሱን የጥራት ደረጃው ቁልቁል እየተንደረደረ ባለበት ወቅት መንግሥት ከፍተኛ የገቢ መጠን ለማግኘት መነሳቱና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ኢንዱስትሪውን መሸከሙ እየተተቸ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች የጥሬ ቆዳ ኤክስፖርት መፈቀድ አለበት የሚል መከራከሪያ ማቅረብ መጀመራቸውም እየታየ ነው፡፡ አቶ ወንድይራድ ሰይፉ የተባሉ ጸሐፊ፣ ኢትዮኦንላይን በተሰኘው ድረ ገጻቸው ላይ ከሚያሰፍሯቸው የቆዳ ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ ትችቶች ውስጥ የጥሬ ቆዳ አቅርቦትን የተመለከተው አንዱ ነው፡፡

  እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ አገሪቱ ከደርዘን ከማይበልጡ የቆዳ ፋብሪካዎች ስታገኝ የቆየችው የወጪ ንግድ ገቢ መጠን 60 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ወንድይራድ፣ አሁን ላይ የተበራከቱት ፋብሪካዎች ቀድሞ የነበረውንና ብዙም ያልተሻሻለውን የጥሬ ቆዳ አቅርቦት አሁንም እየተጋሩ መሆናቸውን በመጥቀስ ትችታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ባለፉት ሦስት አሥርት ውስጥ ኢንዱስትሪው ሲቀርብለት የቆየው የ18 ሚሊዮን ጥሬ ቆዳና ሁለት ሚሊዮን ሌጦ ቢሆንም ዘርፉ፣ ተመንድጓል በተባለበት በዚህ ወቅት ግን እያገኘ ያለው የገቢ መጠን ግን ከ100 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም የጥሬ ቆዳ አቅርቦት እስካልተሻሻለ ድረስ የአገሪቱን ቆዳ ኢንዱስትሪ ወደፊት ማራመድ ከባድ ሥራ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ጥሬ ቆዳ ከውጭ እንዲገባ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት፣ አብዛኞቹ ያለቀለት ቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለመንቀሳቀስ መቻላቸው ይታያል፡፡

  ከጥሬ ቆዳ አቅርቦት ማነስ ባሻገር ዘርፉን የሚፈታተኑ ሌሎች ችግሮችም እየተበራከቱ መምጣታቸው እየታየ ነው፡፡ ይኸውም የቆዳና ሌጦው የጥራት ማዘቅዘቅና የንግድ ማጭበርበሮች ጎልተው በመንግሥትና በቆዳ ኢንዱስትሪ ማኅበሩ በኩል ተደጋግመው ሲገለጹ፣ የዘርፉ ተቺዎችም የሚስማሙባቸው ችግሮች ናቸው፡፡ በተለይ በንግድ ማጭበርበርና ባልተገባ፣ ኢፍትሐዊ የንግድ አሠራር ውስጥ ተዘፍቀዋል እየተባሉ የሚተቹት የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ መንግሥት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፎች ላይ የጎላ የንግድ ማጭበርበር፣ ገንዘብ የማሸሽ ተግባራት እየታዩ መምጣታቸውን በመግለጽ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡

  ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ድረስ የመንግሥት ትኩረት ከፍተኛ ነው፡፡ ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መስኮች ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘ ነው፡፡ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ይገኝበታል፣ በርካታ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የቴክኖሎጂ ለውጥ ያመጣል ወዘተ. ተብሎ የሚነገርለት ነው፡፡ አቶ ታደሰ ዘርፉ ላይ ትኩረት የተደረገባቸውን ምክንያቶች ሲገልጹም እነዚህ ነጥቦች ጠቅሰዋል፡፡

  በሌላ በኩል በዓለም ገበያዎች ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚገኝበት የቆዳ ኢንዱስትሪ አፍሪካን ተጠቃሚ አላደረገም ያሉት፣ በዓውደ ርዕዩ የተገኙትና በደቡባዊ ምሥራቃዊ የአፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)፣ የቆዳና ቆዳ ምርቶች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤም. ምዊኒጃ ናቸው፡፡ ዶክተሩ እንዳሉት በአፍሪካ የጥሬ ዕቃ ክምቸትና ሀብት ቢኖርም፣ ከቆዳ ኢንዱስትሪ አኳያ ተጠቃሚ መሆን የተቻለው ግን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ነው፡፡ ዓለም ከሚያጋብሰው 300 ቢሊዮን ዶላር የቆዳ ንግድ ገቢ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ ከሦስት በመቶ በታች ነው፡፡ በአንፃሩ ከመላው አፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ማዕቀፍ በመቅረፅ ብቸኛዋ አገር መሆኗንም ዶክተሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

  በዓውደ ርዕዩ ላይ የታደሙት ሌላዋ እንግዳ በአውሮፓ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ተጠሪ ልዑክ አምባሳደር ሔበርት ቻንታል በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቆዳ ኢንዱስትሪ መስክ ከሚጠቀሱ አገሮች ውስጥ አንዷ እየሆነች መምጣቷን ጠቅሰው፣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሎጂስቲክስ፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ በሠለጠነ ሰው ኃይልና በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በኩል ችግሮች እያጋጠማቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አምራቾችም ስለሚጋጥሟቸው ችግሮች ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉ አምራቾች፣ ከውጭ ለሚያስገቡት እንደ ጨርቅና ሸራ የመሳሰለው ጥሬ ዕቃ ሱር ታክስ እንዲከፍሉ መገደዳቸው፣ በአንፃሩ ከውጭ የሚገባው ጫማ ከሱር ታክስ ነፃ መሆኑ መታየት ያለበት ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

  ለስምንተኛ ጊዜ እየተካሔደ ባለው የመላው አፍሪካ ቆዳ ዓውደ ርዕይ ላይ ከሱዳን የመጡ ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ 200 አገር በቀልና የውጭ ኩባንያዎች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 49 የውጭ ኩባንያዎች ከአፍሪካ፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ የተውጣጡ ኩባንያዎች የታደሙበት ሲሆን፣ ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል፡፡ ከጎብኚዎቹ ውስጥም 1500 ያህሉ ከውጭ የሚመጡና የመግዛት አቅም ያላቸው እንደሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ማኅበር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች