Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ንብ ኢንሹራንስ በ11 ሚሊዮን ብር የቴክኖሎጂ ግዥ ስምምነት ፈረመ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር፣ የኦፕሬሽንና የፋይናንስ ሥራውን ሙሉ በሙሉ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በማደራጀት ዘመናዊ ለማድረግ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበለትንና ‹‹ጄኔሲስ ኮንፊዩግሬተር›› ተብሎ የሚታወቀውን ምርት ለመግዛት ከሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት አደረገ፡፡

  ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የቴክኖ ብሬን ግሎባል አጋር ከሆነው ኤፍዜድኢና በህንዱ ታታ ኩባንያ ግሩፕ አባል ከሆነው ከሲኤምሲ ሊሚትድ ኩባንያ ጋር የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋናው መሥሪያ ቤት ስምምነት ፈርሟል፡፡

  ስምምነቱን የፈረሙት የንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ማርያም አሰፋና የቴክኖ ብሬን አገር አቀፍ ዳይሬክተር አቶ መኮንን ተስፋዬ ናቸው፡፡

  የኮር ኢንሹራንስ ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከ12 እስከ 14 ወራት እንደሚፈጅ ያስታወቀው ንብ ኢንሹራንስ፣ የቴክኖሎጂው ዝርጋታ ሲጠናቀቅ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚገኙ ቅርንጫፎቹን በኔትወርክ ያቀናጀ አሠራር እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

   በኩባንያው የዋስትና ውል ሰነድ አዘገጃጀት፣ በካሳ ክፍያ፣ በጠለፋ ዋስትና፣ በብሮከሮችና በሽያጭ ወኪሎች ኮሚሽንና የፋይናንስ አሠራር ሒደት ላይ ለውጥ ያመጣል የተባለለት ይህ ሥርዓት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት አሰጣጡን በማፋጠን የደንበኞችን ፍላጎት እንደሚያሟላለት ንብ ኢንሹራንስ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የሥራ ክፍሎችና ቅርንጫፎች መካከል የሚኖረውን የመረጃ ልውውጥ ፈጣንና ቀላል ያደርገዋልም ብሏል፡፡

  ኩባንያው ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ለመሳተፍ ሰነድ የገዙ 18 ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ በውድድሩ የተሳተፉት ግን ስድስቱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በህንድና በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሰው ኢንፎቴክ/ፕሪማ፣ የኬንያው ተርንኪ፣ የቡልጋሪያው ፋዳታ፣ በኢትዮጵያ የሚሠራው የህንዱ ኢንፎሽን፣ በኢትዮጵያና በህንድ የሚሠራው ቴክኖ ብሬን እንዲሁም በኬንያና በእንግሊዝ የሚገኘው ኮፒካት ተሳታፊ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

  ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ድርጅቶች በንብ ኢንሹራንስ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ሥርዓቱ እንዴት ሊዘረጋና ሊሠራ እንደሚችል ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ሁለቱ ቴክኒካዊ መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው ከጨረታው ሊወጡ መቻላቸው ታውቋል፡፡ የቴክኒክና የፋይናንስ የስምምነት ድርድሮች ከተካሄዱ በኋላ ቴክኖ ብሬን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የጨረታው አሸናፊ ለመሆን መብቃቱን ንብ ኢንሹራንስ አስታውቋል፡፡ የሲኤምሲ ሊሚትድን የኮር ኢንሹራንስ ሶሉሽን ተግባራዊ ወዳደረጉና በህንድና በታንዛኒያ በሚገኙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዘንድ የመስክ ጉብኝት መካሔዱንም አስታውቋል፡፡ በጉብኝጡም ይህ ሥርዓት  ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠራበት እንደሚችል ማረጋገጥ እንደተቻለ ኩባንያው ይገልጻል፡፡

  ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት በጠቅላላው ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የኔትወርክ መዘርጋት ሥራውን አስቀድሞ በማጠናቀቅ፣ ቀጣዩን የኮር ኢንሹራንስ ሥርዓትና ተዛማጅ የሀርድዌር ግዢዎችን እየፈጸመ ይገኛል፡፡

  ንብ ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት ስምምነት የተፈራረመበት ይህ የኮር ኢንሹራንስ  ፕሮጀክት፣ ኩባንያው ከሚያከናውናቸው ኢንቨስትመንት ሥራዎች አንዱ መሆኑን አስታውቆ፣ በተጓዳኝ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ትላልቅ ሕንፃዎችን በማስገንባት ላይ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡

  ኩባንያው ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት በተከታታይ በትርፋማነት የቆየና በአሁኑ ወቅትም 935 ባለአክሲዮኖችና 186 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንዳስመዘገም ታውቋል፡፡

  የንብረትና የሕይወት ኢንሹራንስ እንዲሁም ወደ አውሮፓና ሸንገን አገሮች ለሚጓዙ ደንበኞች የጉዞ ኢንሹራንስ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች