Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምየሩሲያውን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ መሪን ማን ገደላቸው?

  የሩሲያውን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ መሪን ማን ገደላቸው?

  ቀን:

  የሩሲያው ክሬሚሊን ቤተ መንግሥት አካባቢ ለከርሞው በማንም ታጣቂ ተደፍሮ አያውቅም፡፡ በአካባቢው የተገጠሙ የቁጥጥር ካሜራዎች፣ የደኅንነት አካላትና ጥበቃው በአካባቢው ግድያ እንዲፈጠር የሚጋብዙ አይደሉም፡፡ ሆኖም ባለፈው ዓርብ ምሽት ክሬምሊን አካባቢ የሚገኘው ቀዩ አደባባይ ግድያ አስተናገደ፡፡ ሩሲያውያንም  የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በግልጽ የሚተቹላቸውን የተቀናቃኝ ፖለቲካ መሪ ቦሪስ ኔምፆቭ በሞት አጡ፡፡

  ኔምፆቭ ከተገደሉ ቀናት ቢቆጠሩም ገዳያቸው አልታወቀም፡፡ ባለፈው እሑድ ‹‹በዩክሬን የሚደረገው ጦርነት ይብቃ›› በሚል ሰላም የማውረድ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የከረሙት ኔምፆቭ፣ 50 ሺሕ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ የተገመተው ሰላማዊ ሠልፉ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ነበር በክሬምሊን ቤተ መንግሥትና አቅራቢያው በሚገኘው ቀዩ አደባባይ አካባቢ በአራት ጥይት ተደብድበው የተገደሉት፡፡

  ዓርብ ምሽት ከመገደላቸው ሰዓታት ቀደም ብሎ ከሩሲያው ኢኮ ሞስኮቪ ሬዲዮ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ኔምፆቭ፣ ‹‹በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እብደት ነው፣ ስሜታዊነት ነው፣ የሞት ፖሊሲ ነው፣ ሁላችንም ሰላም የማውረድ ሰላማዊ ሠልፍ እንውጣ፤›› ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ ሆኖም ሰላም ለማውረድ ለእሑድ የተጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ለእሳቸው ሐዘን የመግለጫ ቀን ሆነ፡፡

  ሳይንቲስትና የሊበራል ፖለቲካ አቀንቃኝ የነበሩት ኔምፆቭ ለሩሲያ ኢኮኖሚ ካፒታሊዝምን ካስተዋወቁ የአገሪቱ ዜጐች ዋነኛው ነበሩ፡፡ በ1990ዎቹ በፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን የሥልጣን ዘመንም በሩሲያ ፖለቲካ ታላቅ ሥፍራ ነበራቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2002 ጀምሮ ፕሬዚዳንት ፑቲንን በመተቸት የሚታወቁት ኔምፆቭ፣ ከአሥር ዓመት በፊት የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 ወዲህ ደግሞ የያርሶላቭ አብላስት ሪጅናል ፓርላመንት ተመራጭና የአውሮፓውያን ሊበራል ዴሞክራቲክ አሊያንስ አባል የሆነው ‹‹ሪፐብሊካን ፓርቲ ኦፍ ሩሲያ ፒፕልስ ፍሪደም ፓርቲ›› ተባባሪ መሪ ነበሩ፡፡

  የፕሬዚዳንት ፑቲንን ፖሊሲ በመንቀፍ የሚታወቁት ሚስተር ኔምፆቭ ለሩሲያ ሕዝብና መንግሥት የፖለቲካ አማራጮችንና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመጠቆም፣ ስህተቶችን በመንቀፍ ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ምዕራባውያኑና ሩሲያ የሚፋለሙባትን ዩክሬን አስመልክተው ሩሲያ የምታደርገውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ይተቻሉ፡፡ ከመሞታቸው ሳምንት አስቀድሞም ሩሲያ በዩክሬን ስለምታደርገው ጣልቃ ገብነት፣ ስለሞቱ ሰዎች ቁጥር የያዘ ዶክመንተሪ ለመልቀቅ በዝግጅት ላይ እንደነበሩም የቅርብ ወዳጆቻቸውን ጠቅሶ አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

  በፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ በሚሰነዝሩት የሰላ የፖለቲካ ትችታቸው የሚታወቁት የ55 ዓመቱ ኔምፆቭ፣ በደኅንነት አካላቷ ጥንካሬ በምትታወቀው፣ መረጃ ሰብሳቢ ካሚራዎቿን በየቦታው በተከለችው ሩሲያ በተለይም በክሬምሊን ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ሲገደሉ ገዳያቸው ማን እንደሆነ አለመታወቁ፣ በሞታቸው ዙሪያ የተለያዩ መላምቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

  ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ ያላቸውን አቋም በመተቸታቸው ምክንያት በሩሲያ መንግሥት እንደተገደሉ የሚነገር ቢሆንም ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ‹‹ኔምፆቭን መግደል አስፈላጊ አይደለም፤›› ሲሉ የሟቹ ትችት ለሩሲያ መንግሥት የሚያሰጋ እንዳልሆነና ግድያ መፈጸም ደረጃ እንደማያደርስም ተናግረዋል፡፡

  የእስልምና አክራሪዎች ወይም ዩክሬን ከአውሮፓ ኅብረት እንዳትቀላቀል የሚፈልጉ አካሎች ገድለዋቸዋል የሚሉ መላምቶችም እየሰነዘሩ ነው፡፡ ሚስተር ኔምፆቭ ዩክሬን ብቻ ሳትሆን ሩሲያም ጭምር የአውሮፓ ኅብረት አባል እንድትሆን እንደሚፈልጉ፣ ይህንንም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር፡፡ ሐሳባቸውን ሩሲያውያንና ከፊል ዩክሬናውያን የማይደግፉት ሲሆን፣ ይህ አመለካከታቸው ለሞት እንዳበቃቸው ይነገራል፡፡

  የፕሬዚዳንት ፑቲን ወዳጅና የቺቺኒያው ፕሬዚዳንት ራምዛን ካድዮሮቭ ለግድያው የምዕራባውያንን የስለላ ኤጀንሲዎች ኮንነዋል፡፡ ከሩሲያ ፌዴራል ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ ጋር ቅርበት እንዳለው የሚነገረው ላይፍኒውስ ድረ ገጽ ደግሞ፣ ሚስተር ኔምፆቭ ሲገደሉ አብራቸው በነበረችው ዩክሬኒያዊት የ23 ዓመት ወጣት ሞዴል ላይ አነጣጥሯል፡፡

  ሞስኮ ውስጥ ከተሰጡ መላምቶች የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪው ሩሲያ በስውር ዩክሬን ውስጥ በምታደርገው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት፣ የሞቱ ስድስት ሺሕ ሰዎችን በመረጃ አስደግፈው ይፋ ሊያደርጉ ከመሆኑ ጋር ስለመያያዙ የጠቀሱት ነገር እንደሌለ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

  በሌላ በኩል ባለፈው ዓርብ ከሬዲዮ ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ የሰነዘሩት የሰላ ትችት ለሞታቸው ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩም አሉ፡፡ በሩሲያ ከሚገኙ ጥቂት የሊበራል ፖለቲካ አራማጆች ውስጥ፣ ከዩክሬን ነፃ መውጣት ለሚፈልጉ ዩክሬናውያን ሩሲያ የምታደርገውን እገዛ በግልጽ የሚቃወሙት ኔምፆቭ፣ በሬዲዮ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የፑቲንን ፖለቲካና የኢኮኖሚውን አስተዳደር ውድቀት ተችተው ነበር፡፡

  የሚስተር ኔምፆቭ ትችት ምናልባትም ለሞታቸው ምክንያት ይሆናል ተባለ እንጂ፣ የመገደላቸው ምክንያትም ሆነ ገዳያቸው እንደ ፍልስጤሙ መሪ ያሲር አራፋት ተዳፍኖ እንደሚቀር ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ‹‹ሚስጥሩ መቼም አይገለጽም›› ሲሉም እሑድ በሞስኮ በተዘጋጀው የሐዘን መግለጫ ሠልፍ ላይ የተናገሩም ነበሩ፡፡

  የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪው የተገደሉት ከክሬምሊን ቤተ መንግሥት፣ የሩሲያ መግለጫ ከሆነው የቅዱስ ባስሊካ ካቴድራል፣ እንዲሁም ከቀዩ አደባባይ አቅራቢያ ቢሆንም፣ መቼውንም የቁጥጥር ኔትወርካቸው ይዘጋልና ይበላሻል ተብለው የማይገመቱትና አካባቢበውን የሚቀርፁት ሲሲቲቪ ካሜራዎች አይሠሩም ነበር መባሉ፣ በተገደሉበት ጊዜ አብራቸው የነበረችው ወጣቷ ዩክሬናዊት ሞዴልም ‹‹ገዳዮቹን አላየሁም ስትል›› ቃሏን መስጠቷ፣ የገዳዮቹ ጉዳይ ተዳፍኖ እንደሚቀር አመላካች ነው ተብሏል፡፡

  በሩሲያ የፌዴራል ሴኪዩሪቲ ቢሮ የዋና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እንቅስቃሴ የሚከታተል ቢሆንም፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪው በተገደሉበት ወቅት የት እንደነበሩ እንደማያውቅ ነው የተነገረው፡፡

  የሚስተር ኔምፆቭ ግድያ በምርመራ ላይ ሲሆን፣ ጉዳዩ የተያዘውም በፕሬዚዳንት ፑቲን ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ ይህም ሁለት ዓይነት ጥርጣሬዎችን አጭሯል፡፡ አንዱ ፑቲን በሕዝቡ ዘንድ ዓመኔታን ለማግኘት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ለማደናገር ነው፡፡

  በተለያዩ አገሮች ዋና የተባሉ የተቀናቃኝ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች ሲገደሉ ይታያል፡፡ በአብዛኛው ደግሞ ገዳዮቻቸው ሲገኙ አይስተዋልም፡፡ ከተገኙም ደግሞ እጅ ሊሰጡ ስላልቻሉ ተገደሉ ይባላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘገባ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የራሱን ቅርፅና ዓላማ ይዞ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

  በአሜሪካ ብዙዎች ተገድለው ገዳያቸው ደብዛው ጠፍቷል፡፡ በፈረንሳይ፣ በሩሲያና በሌሎች አገሮችም እንዲሁ፡፡ ሚዲያዎች የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ ከሌላቸው በስተቀር ገዳዩን ቢያውቁት እንኳን ግልጽ ሲያወጡት አይስተዋሉም፡፡ የሟቹ ቦሪስ ኔምፆቭ ሞት ምክንያትና ገዳይስ ግልጽ ይወጣ ይሆን? ወይስ እንደ ፍልስጤሙ መሪ ያሲር አራፋት ተዳፍኖ ይቀራል?          

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...