Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊሰባት ሥራ ፈጣሪዎች ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት አገኙ

  ሰባት ሥራ ፈጣሪዎች ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት አገኙ

  ቀን:

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ስኬታማና ፈጠራ አገዝ ሥራዎችን በመጀመር፣ በአካባቢ ተፅዕኖና በሌሎችም መስኮች ላይ ውጤታማ ተብለው ለተመረጡ ሰባት ሥራ ፈጣሪዎች በጠቅላላው ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ (60 ሺሕ ዶላር) ሸለመ፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ሽልማታቸውን የተቀበሉት የኢንተርፕረነርሺፕ ተሸላሚዎች፣ በሰባት መስኮች ተወዳድረው መመረጣቸውን የልማት ፕሮግራሙ ይፋ አድርጓል፡፡ የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት በሸራተን አዲስ የተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኩባንያ ባለቤቶችና ባለሙያዎች የታደሙበት ነበር፡፡

  በተመድ የልማት ፕሮግራም ቋሚ ተወካይ፣ የተመድ ቋሚ አስተባባሪና የተመድ ሰብዓዊ ተግባራት አስተባባሪ ኦውጂን ኦውሱ እንዳስታወቁት፣ ዓመታዊ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን መጀመር ያስፈለገው፣ በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ኢኮኖሚውን መደገፍ የሚችሉ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት ስለሚያስችል ነው፡፡ በንግግራቸው መሀል የዓድዋ ድልን ተምሳሌትነትን የጠቀሱት ኦውሱ፣ የቀድሞዎቹ የዓድዋ አባቶች ለአፍሪካ ኩራትን ያጎናጸፈ ገድል መፈጸማቸውን፣ የዛሬዎቹ ተዋጊዎች ግን ድህነትን ለመፋለም የሚታጠቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ንግግራቸውን በኮልታፋ አማርኛ ሲጀምሩ በድጋፍና በፈገግታ የታጀበ ጭብጨባ የተስተጋባለቸው ኦውሱ፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ብትገኝም፣ በንግድ አሠራር ኋላቀር ከሚባሉት አገሮች ተርታ በሚያሠልፋት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የዓለም ባንክ የዓመቱ ‹‹Doing Business›› በሚል ርዕስ ይፋ የሚያደርገውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ እንደጠቆሙት፣ እ.ኤ.አ. በ2014 ኢትዮጵያ ከ189 አገሮች 132ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ በተለይ በአነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች ላይ ከምትከተላቸው የቁጥጥር ሥርዓቶች አኳያ ደካማ ያስብላታል፡፡

  ይህም ሆኖ በዚህ ዓመት የሥራ ፈጠራ ውጤታማ ናቸው ተብለው ከተሸለሙት ውስጥ የ20 ሺሕ ዶላር ወይም የ400 ሺሕ ብር አሸናፊ የሆነው ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከበደ ላቀው የተባለው የሥራ ፈጠራ ባለቤት ሲሆን፣ የዓመቱ ኢንተርፕረነር ተብሏል፡፡ እያንዳንዳቸው የአሥር ሺሕ ዶላር ሽልማት ያገኙት ደግሞ በወጣት ወንዶችና በወጣት ሴቶች የዓመቱ ኢንተርፕረነርስ ዘርፍ የተወዳደሩት ወጣት ሶንያ ወልደ ሩፋኤልና ወጣት ሜሮን ሰዒድ ናቸው፡፡ ወጣት ሶንያ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችን ማዕከል ያደረጉ ተዘጋጅተው የታሸጉ ቅመማ ቅመሞችን ወደ ውጭ በመላክ ሥራ ዘርፍ ላሳየው ውጤታማ ሥራ ሽልማት ተቀብሏል፡፡ ወጣት ሜሮን በበኩሏ በቆዳ ውጤቶች መስክ ከዲዛይን እስከ ምርት ባለው ሒደት ሥራ ፈጥራ በርካቶችን በመቅጠር ላደረገችው ተግባር፣ ከሶል ሬቤልስ ኩባንያ መሥራቿና ባለቤት ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን እጅ ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡

  በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናው እየናኘ የመጣው የሶል ሬቤልስ ኩባንያ፣ በተለይ ለአካባቢ ብክለት ነፃ በሚያደርገው አስተዋጽኦና ከውድቅዳቂ ጎማዎች ጫማ በማምረት የሚሸጥ በመሆኑ ምክንያት መሥራቿና ባለቤቷ ቤተልሔም፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለማግኘት በቅታበታለች፡፡ የተመድ ልማት ፕሮግራም የመልካም ስም አምባሳደር የሆነችው ቤተልሔም ለሽልማቱ ሥነ ሥርዓት የአሥር ሺሕ ዶላር ድጋፍ ማድረጓም ታውቋል፡፡ እንደ ቤተልሔም ሁሉ ሌሎችም ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ኦውሱ አስታወሰዋል፡፡ አራት ተሸላሚዎች እያንዳንዳቸው የአምስት ሺሕ ዶላር ሽልማት በአስተኛና ጥቃቅን፣ በገጠር ሥራ ፈጠራ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት ለዚሁ ተግባር በተመሠረተውና ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ማዕከል የጀማሪ ሥራ ፈጠራ መስክ ሊያሸንፉ ችለዋል፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ማዕከል በበኩል፣ የሥራ ፈጠራ ውድድሩን ይፋ ያደረገው ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም፣ በየዓመቱ ይካሄዳል የተባለውን የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን የጀመረው ግን ዘንድሮ ነው፡፡ በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ማዕከል ላለፉት ሁለት ዓመታት ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች በሥራ ፈጠራና በቢዝነስ ልማት መስክ ድጋፍ እንዳገኙ ኦውሱ ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተመድ የልማት ፕሮግራም የሚሰጠውን ሥልጠና፣ በመቶ ሺሕዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በማዳረስ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...