Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሦስት የመንግሥት ተቋማትን አስጠነቀቁ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሦስት የመንግሥት ተቋማትን አስጠነቀቁ

  ቀን:

  ‹‹የውኃ ሥራዎች በሞትና በሕይወት መካከል ያለ ዘርፍ ነው››

  ‹‹ማኘክ ከሚችሉት በላይ የጎረሱ ስላሉ ጀርባቸውን በመምታት ማስወጣት ይገባል››

  ለሦስት ቀናት በመላ አገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ከአራት ሺሕ በላይ ድርጅቶችና ባለሙያዎች በተሳተፉበት ኮንፈረንስ፣ ከተሳታፊዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በሦስት የመንግሥት ድርጅቶች ላይ ፍተሻ እንደሚደረግ አስጠነቀቁ፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ በሙያተኞችና በተቋራጭ ድርጅቶች ማኅበራት አማካይነት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ በነበረው ኮንፈረስ ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አከራዮች ማኅበር ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የፌደራል ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የክልል ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ ከአንድ ዓመት በላይ ክፍያ ሳይፈጽሙ በማዘግየት የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እንደማይለቁላቸውና አስተዳደራዊ በደል እየፈጸሙቸው እንደሚገኙ፣ የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ሁነኛው አየለ ተናግረዋል፡፡

  በርካታ ማነቆዎች አሉብን ያሉት አቶ ሁነኛው ቁልፍ ብለው ካቀረቧቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ ለሆነውና ሦስቱን መንግሥታዊ ተቋማት በሚመለከት ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ፣ ምንም እንኳ በሦስቱ ተቋማት ላይ ፍተሻ ይደረጋል ቢሉም፣ መሣሪያ አከራዮችና ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በሚደረግ የማሽን ኪራይ ውል ሙስና ወይም ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› በመኖሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸው የሚያውቋቸው በርካታ ማጭበርበሮች እንደሚፈጸሙ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አከራዮች ፍርድ ቤት ሄደው ሲከሱና ሲከራከሩ እንደማይታዩ ገልጸዋል፡፡

  እንዲህ ያሉ ውሎች በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሱት ጫና ከባድ በመሆኑ ምኅረት የለሽ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስጠንቅቀው፣ መሣሪያ አከራዮች በስም በጠቀሷቸው የመንግሥት ተቋማት ላይ ፍተሻ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መንግሥት በተለይ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽንን ያቋቋመው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና የግል ተቋራጮች ባለመኖራቸው መሆኑን አውስተው፣ ክፍተቱን ለመሙላት ሲል እንዳቋቋመውም አስታውቀዋል፡፡

  ከዚህ ጋር በተያያዘ የውኃ ሥራዎች ተቋራጮች ማኅበር በመስኩ ያሉበትን ችግሮች በተመለከተ በማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን ታገሠ በኩል በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሲሰጡም፣ ‹‹የውኃ ሥራዎች በሞትና በሕይወት መካከል ያለ ዘርፍ ነው፤›› በማለት ዘርፉ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በውኃ ሥራዎች ማኅበር በኩል ዘርፉ ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ያሉበት መሆኑ መነገሩን ተቃውመው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሙያዊ ብቃት አለን ካላችሁ ችግር አለ፡፡ ገና ናችሁ፤›› በማለት የዘርፉን ሙያተኞች ሲተቹ፣ ከፍተኛ ወጪና ኪሳራ አስከትሏል ያሉትን ተቋም በምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡

  የውኃ ሥራዎች ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ የኦሞ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ዲዛይንን እንዲሠሩ ለሙያተኞቹ ተሰጥቶ እንደነበር፣ ነገር ግን ይህንን ሥራ ሊወጡ ባለመቻላቸው ለጣሊያን ባለሙያዎች ሥራው ተሰጥቶ ዲዛይኑ መሠራቱን በምሳሌነት አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በዚህ መስክ ገና ነን፡፡ ሳንደባበቅ በመወያየት መፍትሔ ማምጣት አለብን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በውኃ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ‹‹ከፍተኛ ሰቃዮች›› ቢሆኑም፣ በሥራው ላይ ግን ብዙ እንደሚቀራቸው ተናግረዋል፡፡

  ‹‹እናንተ ውል መፈራረም አትችሉም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን የጠቀሱት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በውኃ ሥራዎች የፕሮጀክት ውል ላይ እኩል አንታይም የሚል ጥያቄ ባቀረቡላቸው ወቅት ነበር፡፡ ‹‹ውል ስትዋዋሉ በሕግ አስገዳጅነትና ተቀባይነት ያለው ውል ተዋዋሉ፡፡ ፈረንጆቹ እንያዳንዷን ነገር አውቀው ነው የሚፈራራሙት፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡

  ከአንደኛ ተቋራጮች ማኅበር፣ በማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ተክለ ብርሃን አምባዬ አማካይነት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ በመንገድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋራጮች በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ሳቢያ መሥራት እንዳቃታቸውና አንዳንዶቹም ‹‹እየሞቱ›› በመሆናቸው፣ ፕሮጀክቶችን ነጥቆ ለውጭ ኩባንያዎች ከመስጠት ይልቅ ችግራቸው እየታየ ቢደገፉ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹በገበያ ሥርዓት የሚሳካለት እንዳለ ሁሉ ታዝሎ ተወስዶም የማይሳካለት አለ፡፡ ይኼንን በግድ ማውረድ ይገባል፡፡ መንገዶች ባለሥልጣንና ሌሎቹም ማሰብ ያለባቸው ማኘክ ከሚችሉት በላይ ማጉረስ እንደማይገባ ነው፡፡ ማኘክ ከሚችሉት በላይ የጎረሱ ስላሉ ጀርባቸውን በመምታት ማስወጣት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

  ከጠያቂዎቹ ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሾች ጠጣር ሆነው በታዩበት ኮንፈረንስ ላይ ማኅበራት የመሬት፣ የቀረጥ ነፃ ዕድልን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት ማበራታቻዎች እንዲሰጡዋቸው፣ በተለይ የውኃ ሥራዎች ተቋራጮችና መሣሪያ አስመጪዎች የመሣሪያ ማከማቻ ቦታና የማሽን ከቀረጥ ነፃ ዕድል እንዲፈቀድላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ማኅበርም ሆነ ሥራ ተቋራጭ ወይም መሣሪያ አስመጪ እንዲህ ያሉ ድጋፎች እንደማይሰጡ አቶ ኃይለ ማርያም አስተውቀዋል፡፡

  ከአርክቴክቶች ማኅበር እስከ ኢትዮጵያ ተቋራጮች ማኅበር ባለው መስክ ከስድስት በላይ ማኅበራት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሏቸውን ጥያቄዎች አሰምተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮንስትራክሽን መስክ የሙያ፣ የክህሎት፣ የብቃት፣ የልምድ፣ የተቋማዊ አደረጃጀትና የመሳሰሉት በርካታ ችግሮች ስላሉ ይህንን ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

  የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሚመራበትን አዲሱን ፖሊሲ  እንደሚቀበሉና አንዳንድ ጥያቄዎቻቸውም በፖሊሲው እንደተመለሱላቸው የገለጹት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማኅበራት፣ በኮንፈረንሱ ማብቂያ ላይ ባለአሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ ያሰሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም መጪውን ምርጫ ለማሳካት ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹበት ይገኝበታል፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አገሪቱን ከአምራች እንዱስትሪው ይልቅ በዓለም ገበያ ላይ በቀላሉ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚችል መንግሥት አስታውቋል፡፡ ከአገሪቱ ጠቅላላ በጀት ውስጥ የ60 በመቶና ከጠቅላላው የሥራ ዕድል ውስጥ የአሥር በመቶ ድርሻ ለያዘው ለዚህ ዘርፍ ድጋፍ ያደርጋሉ የተባሉትን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትና የውኃ፣ የመስኖና ኢነርጂ ኢንስቲትዩት መቋቋማቸውን አቶ ኃይለ ማርያም አስታውሰዋል፡፡

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...