በረዥም ርቀት ሩጫ ታላቅ ሯጭ የሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ በጋና መዲና አክራ አዲስ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር እንደሚጀምር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ አደረገ፡፡
ወርልድ ራኒንግ ዶት ኮም በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ ዘ ሚሌኒየም ማራቶን ሩጫ ግማሽ ማራቶንና አምስት ኪሎ ሜትር ውድድሮችን ያቀፈ ሲሆን ውድድሩ ጳጉሜን 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአክራ ከተማ ይካሄዳል፡፡ ውድድሩ በምዕራብ አፍሪካ ሲካሄድ የመጀመርያው ነውም ተብሏል፡፡
‹‹አክራ ውብና ደማቅ ከተማ እንዲሁም ለረዥም ርቀት ሩጫ አመቺ ናት፤›› በማለት ውድድሩን ይፋ ያደረገው የአትላንታ እና የሲዲኒ ኦሊምፒክ የ10,000 ሜትር ሻምፒዮኑ ኃይሌ አውስቷል፡፡ ‹‹ዘ ሚሌኒየም ማራቶን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ዝነኛ የሩጫ ውድድሮች አንዱ ይሆናል፤›› በማለትም ተናግሯል፡፡ እርሱ እንደፈጠረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሁሉ የጋናው ውድድር ስኬታማ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ያለው ኃይሌ፣ ‹‹ጋና ሰላማዊትና የተረጋጋች አገር በመሆኗ በርካታ ዓለም አቀፍ ሯጮችና ቱሪስቶች ወደ አገሪቱ በየዓመቱ ሊመጡና በማራቶን ውድድሩ ሊሳተፉ ይችላሉ፤›› ብሏል፡፡
አያይዞም፣ ‹‹ውድድሩ ለጋናውያን ጤናማ ሕይወትና የአካል ብቃት ልምምድ ባህልን እንደሚፈጥር ተስፋ አለኝ፤›› ሲልም አስረድቷል፡፡
ውድድሩን የሚያዘጋጀው ዘ ሚሌኒየም ማራቶን ስፖርትስ ካምፓኒ ከጋና መንግሥት፣ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአክራ ሜትሮፖሊታን ሸንጎ፣ እና ከጋና ፖሊስ ጋር በመተባበር ነው፡፡
ያገሪቱ ፕሬሶች እንደዘገቡት በመጪው ጳጉሜን በሚካሄደው ውድድር 15,000 ሯጮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡