የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውንና የበረራ ቁጥሩ ET-702 አውሮፕላን የካቲት 9 ቀን ለ10 አጥቢያ 2006 ዓ.ም. በመጥለፍ ወንጀል በሌለበት ክስ የተመሠረተበት ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ፣ መጋቢት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈበት፡፡
ተከሳሹ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን በሌለበት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎት ሦስት ክሶችን አቅርቧል፡፡ ክሶቹም አውሮፕላን መጥለፍ፣ የአውሮፕላን ደኅንነትን አደጋ ላይ መጣልና ኪሳራ ማድረስ ናቸው፡፡
በወቅቱ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ የነበሩት ጣሊያናዊው ሚስተር ፓትሪዚዮ ባርቤሪ የመጀመሪያው የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩ ሲሆን፣ የአውሮፕላን አስተናጋጆች (ሆስተሶች) ኃላፊም ቀርበው መስክረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሌላው ያቀረበው ክስ፣ አየር መንገዱ በረዳት አብራሪው ምክንያት ከ253,336.42 ዩሮ ኪሳራ እንደደረሰበት ነው፡፡
የዓቃቤ ሕግን ክስና ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ፣ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን በሌለበት አውሮፕላን በመጥለፍ ወንጀል ብቻ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠትም ለመጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ የካቲት 9 ቀን ለ10 አጥቢያ 2006 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7፡30 ሰዓት፣ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ሮም በመብረር ላይ የነበረውን የበረራ ቁጥር ET-702 ቦይንግ 767 ጠልፎ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ እንዲያርፍ ማድረጉንና በዚያው ጥገኝነት መጠየቁን በተከታታይ መዘገባችን ይታወሳል፡፡