Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የእነ አቶ ትዕግሥቱ አወሉ አንድነት ፓርቲ ቁመና

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ‹‹ሰዎች የትግል ሥልታቸው ፀሐይና ንፋስ እየሆነባቸው ነው፤›› በማለት የተናገሩት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሠረት ዕውቅና የተሰጠው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲን (አንድነት) በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ያሉት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ናቸው፡፡

  ‹‹በአንድ ወቅት አንድ ጋቢ የለበሱ አዛውንትን ፀሐይና ንፋስ ከጀርባቸው ይመለከቱዋቸዋል፡፡ ከዚያም ሁለቱም በፍጥነት የለበሱትን ጋቢ እኔ አስወልቀዋለሁ እኔ አስወልቀዋለሁ የሚል ክርክር ይገጥማሉ፡፡

  ‹‹ንፋስ የእኝህን ሰው ክንብንብ በማስወለቅ ጥቂት ጊዜ ነው የሚበቃኝ ይላል፡፡ ፀሐይም እንዲሁ ይፎክራል፡፡ ከዚያም ዕጣ ይጣላል፡፡ ዕጣውም መጀመሪያ እንዲሞክር ለንፋስ ይወጣል፡፡

  ‹‹ንፋስም የሰውዬውን ክንብንብ ለማስወለቅ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ይወዘውዘው ጀመር፡፡ ነገር ግን ሰውዬው በንፋሱ ምክንያት ክንብንባቸውን ከማውለቅ ይልቅ በንፋሱ እየተንገላቱ የለበሱዋቸውን አልባሳት አጥብቀው በመያዝ የነፋሱን ኃይልና ልፋት ዋጋ ቢስ አደረጉበት፡፡

  ‹‹በመቀጠል የፀሐይ ተራ ደረሰ፡፡ እናም ቀስ እያለ ሙቀቱን መልቀቅ ሲጀምር ሰውዬው ክንብንቡን መፍታት ጀመሩ፡፡ በመቀጠል ጋቢያቸውን አወለቁ፡፡ ከዚያም ካፖርታቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች አልባሳትን ሁሉ አውልቆ ራቁታቸውን ሆኑ፡፡ የሙቀት አሸናፊነትም ተረጋገጠ፡፡››

  ይህንን ተረት የተረቱት አቶ ትዕግሥቱ ሲሆኑ፣ ‹‹ምናልባት የትናንትናዎቹ ንፋስ መሆን ይችላሉ፤›› በማለት ከምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፊት የነበሩትን የአንድነት አባላትንና አመራሩን ሸንቆጥ አድርገዋል፡፡ ያመጡትን ተረት የተጠቀሙበት ግን ለቀድሞ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ብቻ አይደለም፡፡ ‹‹ዛሬ በሙቀት ኃይል ኢሕአዴግን ራቁቱን እናስቀረዋለን፤›› በማለት መልዕክቱ ለኢሕአዴግም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  አቶ ትዕግሥቱ ይህን የገለጹት የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንትነታቸው በምርጫ ቦርድ ከፀናላቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀበና አካባቢ በሚገኘው የፓርቲው ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

  መግለጫው የተሰጠው ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመግለጫው ወቅት ከአቶ ትዕግሥቱ አወሉ በተጨማሪ አዲሱ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊም ተገኝተዋል፡፡ የፓርቲው መግለጫ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ፓርቲው ያስመዘገባቸውን የዕጩዎች ብዛትና ደረሰብኝ ያላቸውን ተግዳሮቶች የዳሰሰ ነበር፡፡

  የፓርቲውን ተግዳሮቶች በተመለከተ፣ ‹‹በምርጫ ቅስቀሳ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ክፍል የላክነው ጽሑፍ ሳንሱር ተደርጐብናል፤›› በማለት የከሰሱ ሲሆን፣ ፓርቲው በነፃ የአየር ሰዓት ክፍፍል መሠረት ለመጠቀም በተሰጠው ዕድል አዘጋጅቶ የላከውን የቅስቀሳ ሐሳብ ቆርጦብኛል በማለት ኢብኮን ተችቷል፡፡

  ፓርቲው ተቆርጦብኛል የሚለው ሐሳብ ደግሞ ከተመረጠ የፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ አደርጋለሁ ያለበት ክፍል ነው፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ የፓርቲው አቋም ከመሆኑም በላይ እነርሱ እንደሚሉት የሥነ ምግባር ደንቡን የሚፃረር አይደለም›› ብለዋል፡፡

  አንድነት ከክፍፍሉ በኋላ

  ከቦርዱ ውሳኔ በኋላ የፓርቲውን የመሪነት ሥልጣን የያዙት አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹አጠቃላይ የፓርቲው እንቅስቃሴና ተክለ ቁመና ጥሩ የሚባል ዓይነት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ፓርቲውን ተረክበው ማስተዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ስለአከናወኗቸው ተግባራት ገለጻ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፓርቲው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በችግር ውስጥም ቢሆንም በዘንድሮው ምርጫ መሳተፍ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

  ከውሳኔው በፊት የነበረው አንድነት ፓርቲ ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ 500 ያህል ዕጩዎችን ለማስመዝገብ እየሠራ እንደሆነ፣ በተለያዩ ወቅቶች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ይገለጹ እንደነበር መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

  አቶ ትዕግሥቱም ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ይህንን ያህል ቁጥር ለማስመዝገብ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ያስመዘገባቸው የዕጩዎች ብዛት ግን 230 ብቻ ነው፡፡

  የዕጩዎች ቁጥር መቀነስ አንዱ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ችግር ማሳያ እንደሆነ አቶ ትዕግሥቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ችግር ባይኖር የፓርቲው ዕቅድ ይህ አልነበረም፤›› በማለት የቁጥሩን መቀነስ ከተከሰተው ችግር ጋር አያይዘውታል፡፡ በፓርቲው የተፈጠረው ክፍፍል የዕጩዎችን ቁጥር ቢቀንሰውም ግን፣ ፓርቲው በተሰጡት አምስት ቀናት የሠራው ሥራ መልካም የሚባል እንደሆነ አትተዋል፡፡

  ‹‹በእነዚህ ውስን ቀናት ይህን ያህል ዕጩ ማስመዝገብ ከአንድነት ቁመናና ሕዝብ ይጠብቀው ከነበረው ተስፋ አንፃር በእጅጉ ያነሰ ነው፤›› ያሉት አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹በሌላ በኩል ደግሞ 50 ቀናት የዕጩ የማቅረቢያ ጊዜ ዕድል ከነበራቸው ገዥውን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሲመዘን ፓርቲያችን አንድነት የተሻለ አደረጃጀት ላይ ለመሆኑ ማሳያ ነው፤›› በማለት ቁጥሩ ቢቀንስም አሁንም አንድነት ፓርቲ የተሻለ ነው የሚል አንድምታ የሚሰጥ ገለጻ አድርገዋል፡፡

  ፓርቲው ከጋምቤላና ከሶማሌ ክልል በስተቀር ዕጩዎችን ማስመዝገብ መቻሉና 80 ያህል የምርጫ ክልሎችን መሸፈን መቻሉንም እንደ አንድ ሌላ ትልቅ ስኬት ቆጥረውታል፡፡

  ይህንኑ አስተያየት የሚደግሙት የአሁኑ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰፊው መኮንን፣ ‹‹የተመዘገቡት ዕጩዎች ብዛት አንድነት አሁንም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ቤት መሆኑን ያሳያል፤›› በማለት አክለዋል፡፡ ምንም እንኳን አንድነት ያቀረባቸው ዕጩዎች ብዛት ከሌሎች ፓርቲዎቹ ጋር በማነፃፀር ከፍተኛ ውጤት አምጥቻለሁ ቢልም፣ የተወዳዳሪዎቹ መቀነስ ያስከተለው ችግር እንዳለም በመግለጫው ወቅት ተነግሯል፡፡

  በፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር እየተሳተፈ እንደሆነ የሚታወቀው የአሁኑ አንድነት ፓርቲ፣ የሚሳተፍበት የመከራከርያ ነጥቦች ግን ከሦስት አይዘሉም፡፡

   በዘንድሮው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለዘንድሮ የምርጫ ክርክሮች ዘጠኝ አጀንዳዎችን ቀርጿል፡፡ ‹‹አንድነት በተመኘው ሳይሆን በተፈጠረበት ችግር ምክንያት ባስመዘገባቸው ዕጩዎች ቁጥር መነሻነት በሦስት ርዕሶች ላይ ይከራከራል፤›› በማለት የዕጩዎቹ ቁጥር መቀነስን ተፅዕኖ አቶ ትዕግሥቱ ገልጸዋል፡፡

  በዚህም መሠረት መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ላይ አንድነት ፓርቲ በእነ አቶ ትዕግሥቱ የተወከለ ሲሆን፣ በዕለቱም የመድበለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ክርክር ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በወጣለት ዕጣ መሠረት በፌደራሊዝምና በሦስተኝነት ደግሞ በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ላይ ይከራከራል፡፡

  እነዚህን ርዕሶች ዕድለኛ በመሆናቸው እንዳገኙት የገለጹት አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹አሠራሩ በዕጣ መሠረት የተከናወነ በመሆኑ ማንንም ለመኮነን አንዘጋጅም፤›› በማለት የሚኮነን አካል አለመኖሩን፣ ካለም ፓርቲው ያቀረባቸው ዕጩዎች ቁጥር መቀነስ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ፓርቲው አብዛኛውን ለምርጫ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እንዳዘጋጀ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የፓርቲው ማተሚያ ማሽንን የሚያንቀሳቅሰው ጄኔሬተር ቁልፍ ቀድሞ በነበረው አካል በመወሰዱ ምክንያት፣ ለሕትመት መግባት አለመቻሉንና ያንን እየተጠባበቁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

  ሕትመቱ ከመዘግየቱ ውጪ ያሉ ሌሎች ሥራዎችን ግን እያከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም የሥራ እንቅስቃሴ መሀል አንዱ ደግሞ ቅስቀሳ ሲሆን፣ በተጨማሪም በራሪ ወረቀቶችን መበተን፣ የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ምሥል ይዞ መቀስቀስ፣ እንዲሁም ፖስተሮችን መለጠፍና ቢል ቦርዶችን ማዘጋጀትም እንዲሁ የፓርቲው የምርጫ እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ ተገልጸዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ለፖለቲካ ፓርቲዎች በደለደለው ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል መሠረት ፓርቲው የተሰጠውን ሰዓት በሬዲዮ በተገቢው ሁኔታ እየተጠቀመበት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ በቴሌቪዥን በኩል ግን ያጋጠሙት ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

  ፓርቲው አጋጠመኝ ያለው ችግር ደግሞ ለቅስቀሳ የላካቸውን የፓርቲውን አቋም የሚገልጹ ሐሳቦች ከሥነ ምግባር ደንቡ ጋር ይጋጫል በሚል ምክንያት ሳንሱር መደረጋቸውን ነው፡፡ ይህንን አሠራር የሚተቹት አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹አንድነት ከሥነ ምግባሩም ሆነ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ሥራ አይሠራም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

  ‹‹በተጨማሪም ያለውን ሥርዓት (ገዥው ፓርቲን) እየታገለ ራሱ ሕግ አይጥስም፤›› በማለት አንድነት የሚታገለው ለሕገ መንግሥቱ መከበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  አቶ ትዕግሥቱና የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የፓርቲውን የምርጫ ዕቅድና ስትራቴጂ ሲያብራሩም፣ አንድነት አሁንም ከፍትጊያ ያልፀዳ መሆኑን የሚያሳይ ሌላ እንቅስቃሴም እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

  ከቦርዱ ውሳኔ በፊት ፓርቲውን ያስተዳድር የነበረው የነአቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን የቦርዱን ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡ በዚህ የተነሳም የሁለቱ ቡድኖች ክርክር እንደከዚህ ቀደሙ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሳይሆን በፍርድ ቤት ይሆናል ማለት ነው፡፡

  የካቲት መጀመሪያ ላይ ክስ መመሥረቱን ያስታወሱት የቀድሞው አንድነት ዋና ጸሐፊ አቶ ሥዩም መንገሻ፣ በመቀጠልም የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲሁ ክስ በተመሠረተበት ከፍተኛው ፍርድ ቤት 11ኛው ችሎት ሁለቱም ወገኖች የቃል ክርክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

  ‹‹ሁለቱ ወገኖች ያካሄዱት ክርክር በዋነኛነት ያጠነጠነው ፓርቲው ያካሄዳቸው ጠቅላላ ጉባዔዎች የተከናወኑት በሕጉ መሠረት እንደሆነና ትክክል መሆናቸውን ለማስረዳትና የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ነበር፤›› በማለት አቶ ሥዩም አክለዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ መተዳደሪያ ደንቡ እንዲቀርብለት ትዕዛዝ በሰጠው መሠረት እርሱን አቅርበው ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጥሮ መስጠቱንም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ይህ ደግሞ አንድነት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሠረት ፍፃሜ ያገኘ ቢመስልም፣ አሁንም ቢሆን በቦርዱ ዕውቅና የተነፈገው ቡድን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዱ ምክንያት መጨረሻው አለየም ማለት ነው የሚያሰኝ ነው፡፡

  አንድነት አንድ ነው?

  የቦርዱ ውሳኔና መዋቅር ተከትሎ ዕውቅና የተነፈገውም ሆነ ዕውቅና ያገኘው ቡድን የአንድነት ዋነኛ ክፍል አብሮት እየተጓዘ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የአንድነት አባላትና አመራር ከማን ጋር ነው የተሠለፈው? የሚለው ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ቢሆንም፣ብዙኃኑ ግን እነ አቶ ትዕግሥቱን ጥለው ኮብልለዋል፡፡

  ፓርቲውን ይመሩ ከነበሩት ግለሰቦች መካከል በጣም ጥቂቶቹ ሰማያዊ ፓርቲን ሲቀላቀሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከአዲሱ አመራር ጋር አብረው እንደማይሠሩ አስታውቀዋል፡፡ ወደ ፍርድ ቤትም ሄደዋል፡፡ አሁን ሕዝባዊ መሠረት አለኝ የሚለው አንድነት ፓርቲ መሠረቱ በግልጽ የት እንደሆነ መግለጽ አልቻለም፡፡ በደፈናው መከራከሩ የሚጠቅመው ምንም ነገር ባለመኖሩም አንድነት ምን ያህል አባላት ነበሩት? አሁን ምን ያህል አባላት በፓርቲው ውስጥ ታቅፈው እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው የአንድነት የአሁኑ ቁመና ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡

  አሁን ባለው ሁኔታ የነ አቶ በላይ ቡድን የነ አቶ ትዕግሥቱን ቡድን ይተቻል፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የነ አቶ በላይ ቡድን ያለበትን ቅሬታዎች በማዥጐድጐድ ላይ ይገኛል፡፡ እነ አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የነአቶ በላይ ቡድን ለፓርቲው ውስጠ ደንብ አልተገዙም በማለት ትችቱን ያቀርባል፡፡ ‹‹ከቦርዱ ውሳኔ በኋላ አመራሩ ሲለይ ቅር የተሰኙት ወገኖች አንድነት የለም፣ ፈርሷል ነው ያሉት፡፡ ይኼ ደግሞ ጠርዝ የያዘ አስተሳሰብ ከመሆኑም ባሻገር እኔ ከሞትኩ ዓይነት የአህያዋ ተረት ነው የሚሆነው፤›› በማለት አቶ ትዕግሥቱ አክለዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም የነ አቶ በላይ ቡድን በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚያካሂዱት ዘመቻ ‹‹ተራ ነው፤›› ያሉት አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹እኛ አሁን አመራር ነን፡፡ አመራር ደግሞ የመፍትሔ አካል ነው እንጂ የሚሆነው የችግር ምንጭ አይሆንም፡፡ በተቃራኒው ሰለባዎች ናቸው የችግር ምንጭ የሚሆኑት፤›› በማለት እርሳቸው ለፓርቲው ችግሮች መፍትሔ እየፈለጉ እንደሆነ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

  ፓርቲው ሲያንቀሳቅሳቸው ስለነበሩት ልሳኖችና ለማዘጋጀት አቅዶት ስለነበረው የርዕዮተ ዓለም ንድፈ ሐሳብና ትንተና መጽሔት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹›የጋዜጦቹ ሕትመት ይቀጥላል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችለን ቡድን እያዋቀርን ነው፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ የርዕዮተ ዓለም መጽሔቱን በተመለከተም ‹‹ዳንዲ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መጽሔቶችም በሌሎች ቋንቋዎች እናዘጋጃለን፤›› ብለዋል፡፡ ሙቀት ተገቢ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ትዕግሥቱ የፓርቲው ሙቀት ምን ያህል ሰዎችን እንደሚነካና መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የተቀጠረው የፍርድ ቤት ውሎ የወደፊቱን የሚጠቁሙ አመላካች ይሆናሉ ብለዋል፡፡

  ነገር ግን የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች አቶ ትዕግሥቱን በክህደት ከመፈረጃቸውም በተጨማሪ፣ ፓርቲው ከሚታወቅበት በጣም ጠንካራ የሆነ አቋም በተፃራሪ፣ በቅርቡ በተደረገው የፓርቲዎች ክርክር ላይ አቶ ትዕግሥቱ እጅግ የተለሳለሰ አቋም በማሳየት ሌላ ተልዕኮ እንደነበራቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋል በማለት ይተቹዋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የፓርቲውን የሕትመት ዝግጅቶች በተመለከተ አቅምም ሆነ ችሎታ ስለሌላቸው የትም አይደርሱም በማለት ያንኳስሱዋቸዋል፡፡      

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -