Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልኬንያና ጂቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያተኮረ ድራማ እየተዘጋጀ ነው

  ኬንያና ጂቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያተኮረ ድራማ እየተዘጋጀ ነው

  ቀን:

  ጂቡቲና ኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሕይወት የሚያሳይ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አስታውቋል፡፡ ቴአትር ቤቱ ወደ ጂቡቲና ኬንያ ለድራማው ግብዓት የሚሆን መረጃ እንዲያሰባስብ የላከው ቡድን አባላት ጥናታቸውን አጠናቀው የተመለሱ ሲሆን፣ በቅርቡ የሕገ ወጥ ስደተኞች ውጣ ውረድ ላይ ያተኮረ ባለ 52 ክፍል ድራማ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጣቢያ እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የጥናት ቡድኑ በቀጣይ ለድራማው ተጨማሪ ግብዓት ከሱዳን የሚሰበስብ ሲሆን፣ ከሁለት ወራት በኋላ ቀረጻው ይጀመራል፡፡ የድራማው ደራሲና ከአዘጋጆቹ አንዱ ደረጄ በቀለ እንደተናገረው፣ ድራማው ሕገ ወጥ ስደተኞች ከኢትዮጵያ አንስቶ በየአገሮቹ የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በስደት ሳቢያ የሚፈጠረውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያሳየው ድራማው ለችግሩ መፍትሔ የሚያመላክትም ይሆናል ብሏል፡፡

  ከአፍሪካ አገሮች ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ ወደ የመን ለመሄድ ጂቡቲና ኬንያን እንደመሸጋገሪያ የሚጠቀሙ ስደተኞች በጉዞ ወቅት በደላሎች የሚደርስባቸውን እንግልት እንዲሁም በየአገሩ ፍርድ ቤት የሚገጥማቸውን ችግር የሚያሳይ እንደሆነ አክሏል፡፡ የድራማው መቼት በርካታ ሕገ ወጥ ስደተኞች የሚፈልሱባቸው ክልሎችና በጂቡቲና ኬንያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሚገኙባቸው ቦታዎች ይሆናል፡፡ እነዚህም በኬንያ ናይሮቢ፣ የሚገኘው ኩኩዩ ፖሊሲ ጣቢያ፣ አስሊ የስደተኞች መንደር፣ ጂቡቲ ያለው ታጁራና የከተማዋ ወደቦች አካባቢ ያለውን ቦታ ይሸፍናል፡፡

  አጥኚዎቹና የድራማው አዘጋጆቹ መጋቢት 10፣2007 ዓ.ም. በሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል ጥናታቸውን ይፋ ባደረጉበት ቀን እንዳስታወቁት፣ ድራማው ሕገ ወጥ ስደት በተለያየ መንገድ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ሕዝቡ እንዲገነዘብ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

  አጥኚዎቹ እንዳሉት፣ ኬንያ ያሉት ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ በእግራቸው ለመሄድ እንደመሸጋገሪያነት ኬንያን ይጠቀማሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱት ባጠቃላይ ወንዶች ሲሆኑ፣ በብዛት ከከንባታና ሃዲያ አካባቢዎች የተሰደዱ ናቸው፡፡ በድንበር ጠባቂዎች ተይዘው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እስራት፣ የገንዘብና የጉልበት ሥራ ቅጣት ይፈረድባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ከ14 እስከ 46 ዓመት ክልል ውስጥ ሲገኙ፣ በ3 ቀን በአማካይ ከ50 እስከ 100 የሚሆኑ ሕገወጥ ስደተኞች በኩኩዩ ፖሊሲ ጣቢያ ይታሠራሉ፡፡

  በሌላ በኩል ጂቡቲ ውስጥ ታጁራና አቦክ ከተማዎች ከ13 እስከ 40 ዓመት ያሉና ወደ 10,000 የሚጠጉ ወንድና ሴት ስደተኞች ወደየመን ለመሸጋገር ይጠባበቃሉ፡፡ አብዛኞቹ ለዓመታት የተጠባበቁ ሲሆን፣ በረሃብና በበሽታ የተጠቁ ጥቂት አለመሆናቸውን ጥናቱ ያመላክታል፡፡ ስደተኞቹ ከሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣ ወሎና ትግራይ የመጡ ናቸው፡፡ አጥኚዎቹ እንዳሉት፣ ኬንያ ውስጥ ስደተኞች ከ60,000 እስከ 80,000 ሺ ብር ለደላሎች ይከፍላሉ፡፡ በጂቡቲ ደግሞ ከ4,000 እስከ 10,000 ብር ለደላሎች ይከፍላሉ፡፡

  አጥኚዎቹ ስደተኞቹ ለደላሎች የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ መሆኑ የስደታቸው መንስኤ የገንዘብ አጦት እንዳልሆነ ያስረዳል ቢሉም፣ መደምደሚያው ጥናቱን ይከታተሉ ከነበሩ ታዳሚዎች ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ሕይወት ፍለጋ መሰደዳቸው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ሆኖ ሳለ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግር የለባቸውም ማለት ሐቁን የሚፃረር እንደሆነ አንዳንድ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ ለስደት ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና መንስኤዎች በደንብ መጠናት እንዳለባቸው ያስረዱም ነበሩ፡፡

  ጥናቱን ከታደሙ መሀከል ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት፣ የሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ ባለሙያዎቹ ስደት በኢትዮጵያውያን ላይ ሕይወት እስከመቅጠፍ ድረስ እያስከተለ ያለው ጉዳት በድራማው መንፀባረቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  ድራማው በየአገሮቹ ያለውን እንግልት በማሳየት ግንዛቤ አስጨብጦ የስደተኞችን ቁጥር የመቀነስ ዓላማ ይዞ ከተነሳ፣ ተደራሽነቱን ለማስፋት ሌሎች ሚዲያዎችንም መጠቀም አለበት ያሉም ነበሩ፡፡ ድራማው ተአማኒት ባለው መልኩ የስደትን መንሥኤና አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ካላስቀመጠ ለውጥ የማምጣት አቅሙ አናሳ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

  ከአጥኚዎቹ አንዱ ቴዎድሮስ በላይነህ እንደተናገረው፣ ለስደተኞቹ ከአገር መውጣት ምክንያት ከሆኑ መሀከል የጓደኛ፣ የቤተሰብና አጠቃላይ የማኅበረሰቡን ግፊት ማንሳት ይቻላል፡፡ አገር አቋርጠው ለመሰደድ ሲነሳሱ የሚገጥማቸውን አስከፊ ችግር ባለመረዳትና ገና ለገና ጠቀም ያለ ገንዘብ እናገኛለን በሚል ይሰደዳሉ ብሏል፡፡ በድራማው ከሚካተቱት አንዱ ሕገወጥ ደላሎች ሲሆኑ፣ በሕገ ወጥ ስደት ትልቁን ሚና የሚጫወቱት እነሱ እንደሆኑ ያክላል፡፡ ድራማው የችግሩን አሳሳቢነት ለማሳየትና መፍትሔ ለማመላከት አንድ ዕርምጃ ይሆናል ብሏል፡፡

  ቴዎድሮስ እንደተናገረው፣ ጥናቱ እስካሁን ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን፣ ወጪው የተሸፈነው በውጪ ጉዳይ እና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች ነው፡፡ ጂቡቲና ኬንያ ውስጥ ስደተኞች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ላይ ካሉ ኢትዮጵያውን ስደተኞች የተገኘው መረጃ ከድራማው 38 ክፍል የሚይዝ ሲሆን፣ የተቀረው ክፍል በሱዳን በሚደረገው ጥናት ተሸፍኖ በቅርቡ ለእይታ ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...