Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የሒሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮችን የሚቆጣጠር አዲስ ቦርድ ተቋቋመ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአገሪቱ ባለሙያዎችና ድርጅቶች እስከ ሐምሌ ይመዝገቡ ተባለ

  በፌደራል ዋና ኦዲተር ጄነራል፣ በብሔራዊ ባንክና በሌሎችም ተቋማት ለሒሳብ ባለሙያዎችና ለኦዲተሮች የሙያ ፈቃድ፣ የብቃት ማረጋገጫና መሰል የዕውቅና አሰጣጥ ሥርዓት በመሻር፣ ለአዲሱ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሰጠው አዋጅና እሱን ተከትሎ የወጣው ደንብ መተግበር ጀመረ፡፡ ለአዲሱ ቦርድ የቦርድ አባላትና የሥራ ኃላፊዎች ተሹመውለታል፡፡

  የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ቦርዱ ለብቻው ተለይቶ በሒሳብ ሙያና በኦዲት አሠራር ላይ የበላይ አካል ሆኖ እንዲሠራ የተቋቋመው የሕዝብ ጥቅም ባለባቸው በመንግሥት የልማትና በግል ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚነት ያለው አንድ ወጥ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ እንዲኖር ለማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም በመላ አገሪቱ አንድ ወጥ የፋይናንስ ሪፖርት ሥርዓት የሚዘረጋ ሲሆን፣ የፋይናንስ ሥርዓቱም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን እንዲከተል ለማድረግ ቦርዱ መመሥረቱን አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

  መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችና የግል እንዲሁም የውጭ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በተለያየ መለኪያ የሚለኩበት የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት ከእንግዲህ አይኖርም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በሌሎች አገሮችም እንደሚደረገው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም መመሥረት ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የኢኮኖሚ ቀውሶችን ለመቀነስ እንዲቻልም የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

  አዲሱ ቦርድ 12 የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፣ አባላቱ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከግሉ ዘርፍ ከሒሳብና ኦዲት ባለሙያዎችና ለሙያው ቅርበት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት መሆናቸው ሲታወቅ፣ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመራ ግለሰብ በዳይሬክተርነት ከመቅጠሩም ባሻገር ባለሙያዎችን እያካተተ እንደሚገኝ አቶ ዓለማየሁ ጠቅሰዋል፡፡

  ከዚህ ቀደም በፌደራል ዋናው ኦዲተር ጄነራል ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ለሒሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ፈቃድ የመስጠትና የማደስ ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ ቦርዱን ለማቋቋም በወጣው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁጥር 847/2006 መሠረት መሻሩን አቶ ዓለማየሁ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ፣ በመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ በምርት ገበያ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ፣ በኤክሳይስ ታክስ አዋጅ፣ በገቢ ግብር አዋጅ፣ በባንክ ሥራዎች አዋጅ፣ በመንድን ሥራ አዋጅ እንዲሁም በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ውስጥ ስለ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት የተደነገጉ አንቀጾች መሻራቸው ታውቋል፡፡

  የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅን፣ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድን አሠራርና ዓላማዎች ለማስረዳት መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተጠራ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መሥሪያ ቤቶች ተሳትፈዋል፡፡ ጥያቄዎችንም ለሚኒስትር ዴኤታውና ለባልደረቦቻቸው አቅርበዋል፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም በአዋጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶችን አይመለከትም መባሉ በምን አግባብ እንደሆነ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡ ከዋናው ኦዲተር ጄነራል በመውሰድ የክልል ኦዲተር ጄነራሎች ለባለሙያዎች ፈቃድና ዕድሳት እየሰጡ እንደሚገኙ በመጥቀስ ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን ጠይቀዋል፡፡

  አቶ ዓለማየሁ በምላሻቸው እንደገለጹት ቦርዱ፣ በተማከለ አሠራር እየተንቀሳቀሰ በክልሎች ቅርንጫፎችን እንደሚከፍትና በመላው አገሪቱ ከአሁኑ በኋላ ከቦርዱ በስተቀር የሙያ ፈቃድ የመስጠትና የማደስ ሥልጣን ሌሎች የክልል መሥሪያ ቤቶች እንደማይኖራቸው አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ቀደም ሲል ክልሎች በነበሯቸው ሕጎች መሠረት ለኦዲተሮችና ለፋይናንስ ሪፖርት አቅራቢዎች ፈቃድ መስጠታቸውን ያቆማሉ፡፡ ሕጎቻቸውንም ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከዚህ ቀደም በነበራቸው የኦዲትና የሒሳብ አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት መሠረት ይቀጥላሉ ስለመባሉ ምክንያትአዊነት ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህ የተደረገው ከሌሎች አገሮች ልምድ ተወስዶ ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዲሱን ቦርድ ለማቋቋም፣ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው ደንብ ቁጥር 332/2007 መሠረት በሥራ ላይ ያሉ የኦዲት ድርጅቶችና ኦዲተሮች፣ የሒሳብ ባለሙያዎችና የፋይናንስ ሪፖርት አቅራቢዎች እስከ መጪው ሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ማመልከቻቸውን ለቦርዱ በማቅረብ መመዝገብና ፈቃድ የማግኘት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማመልከቻ ያላቀረቡ ፈቃድ አያገኙም ተብሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር አዲስ ፈቃድ መስጠት እንደቆመና ለነባር ባለሙያዎችና ድርጅቶች፣ በትምህርትና ሥልጠና ላይ ለሚገኙትም ጭምር በቦርዱ የሚቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት የማይችሉ ከሆነ ግን እስከ አምስት ዓመት የሚቆይ የእፎይታ ጊዜ መሰጠቱንና በዚያ ጊዜ ውስጥ የአገሪቱ የሒሳብ ባለሙያዎችና ድርጅቶች መስፈርቶችን አሟልተው መገኘት እንደሚገባቸው ተመልክቷል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች