Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት አደረገች

  ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት አደረገች

  ቀን:

  ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከ30 ዓመታት በኋላ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ የመጀመርያ ናቸው

  ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አራት ዓመታት ሞቅና ቀዝቀዝ ሲል ለነበረው የምሥራቅ ናይል (ዓባይ) ተፋሰስ አባል አገሮች ግንኙነት፣ ወደ ተሻለ የትብብርና መንፈስ ከፍ ያደርጋል ተብሎ የታመነበት የመርህ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ለመጀመርያ ጊዜ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት አድርገዋል፡፡

  በሥልጣን ላይ ጥቂት የማይባሉ ወራት ያስቆጠሩት አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ስምምነት ባለፈው ሰኞ በካርቱም በተፈረመበት ማግሥት፣ የንግድና የዲፕሎማሲ ከፍተኛ ልዑካንን በመምራት ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡

  ፕሬዚዳንት አልሲሲ በሦስት ቀናት ቆይታቸው የመጀመሪያው ቀን ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ቀጥለውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ተብሎ የሚታመንበት ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

  በርከት ያሉ ሰዓታት የወሰደውን የሁለቱን አገሮች መሪዎች ውይይትና ምክክር ተከትሎ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በመሆን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሁለቱን አገሮች መልካም ትስስርና ጥቅም ያስጠብቃልና የሦስቱን አገሮች ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ያረጋግጣል ያሉትን በካርቱም የተፈረመውን ፖለቲካዊ ሰነድ ጠቅሰው፣ ‹‹ታሪካዊ አጋጣሚ›› ብለውታል፡፡ ‹‹የጋራ ጥቅም የሚያስጠብቅ መፍትሔ ነው፤›› ያሉትን ይህ ስምምነት መፈረሙ፣ የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት በአዲስ ምዕራፍ የሚያስኬድም ብለውታል፡፡

  ‹‹ዛሬ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሰውን የመጀመርያውን መሠረት ጥለናል፡፡ ይኼንን የሰላምና የትብብር መልዕክት ይዤላችሁ ነው የመጣሁት፡፡ የሁለቱም አገሮች መሪዎች እንዲህ ዓይን ለዓይን እየተያየን ነው፡፡ የጋራ ትብብሩ በቃ ተጀምሯል፡፡ እዚህ ለመድረስ እጅግ ከጊዜ ጋር የሮጥነው በከፍተኛ ፍጥነትና ቆራጥነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በሚኒስትሮች ደረጃ የተፈረመው ይኼንን የሦስቱ አገሮች ስምምነት፣ ወደ ላቀ የፖለቲካ አመራር ለማምጣትም እንደሚጥሩ አልሲሲ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ ‹‹የእንኳን ደህና መጡ›› መልዕክት አስተላልፈው ግብዣቸውን አክብረውና ተቀብለው እዚሁ ድረስ በመምጣታቸውን በማድነቅ ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት በመሉ ትክክል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ውይይቱ በአራት ደረጃ የተከፋፈለ ሲሆን፣ የመጀመርያው በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር በተለይ ሽብርተኝነት በጋራ ለመታገል ወስነዋል፡፡ ውይይቱ በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነትም ላይ ያተኮረ እንደነበር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት በሚኒስትሮች ደረጃ ያለው የጋራ ኮሚቴ ወደ ኮሚሽን ከፍ ለማድረግና ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር እንዲረከበው ለማድረግ መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡

  አሁን የተፈረመው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አጠቃቀም ስምምነትም ‹‹አዲስ ምዕራፍ›› ይከፍታል ብለዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በትክክል እንዳሉት አሁን የተጀመረው መልካም ግንኙነት ወደኋላ አይመለስም፤›› በማለት ነበር ሲጠበቅ የነበረውን ንግግራቸውን የቋጩት፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ በቆይታቸው በኢትዮጵያ የግብፅ ባለሀብቶችን ፎረም ያነጋገሩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የግብፅ የኢንዱስትሪ ዞን ለማቋቋምም ስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ስምምነቱ ምን አካቷል?

  ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የግድቡን አጠቃቀም በተመለከተ የፈረሙት ‹‹የመርህ መግለጫ›› ስምምነት በውስጡ በርካታ ጉዳዮች ያካተተ ሲሆን፣ አሥር ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ይዟል፡፡ የመጀመርያው የትብብር መርህን የተመለከተ ሲሆን፣ ስምምነቱ የጋራ ፍላጎትና ጥቅም፣ እንዲሁም መልካም ፈቃደኝነትና ዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ያትታል፡፡

  በተለይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይኼ ስምምነት በሁለተኛው አንቀጽ ያካተተውን ነጥብ፣ የግድቡ ዋና ዓላማ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሆነና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትም የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ መሆኑን፣ አስተማማኝ ታዳሽ ኃይል በማመንጨት አካባቢያዊ ውህደት ለመፍጠርም ምክንያት ይሆናል የሚል መንፈስ አለው፡፡ ግድቡ ለመስኖ ግብርና ጥቅም ይዋል አይዋል የተለገጸ ነገር የለም፡፡

  እንዲሁም በዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) አንድ አወዛጋቢ የነበረው ጉዳይ ‹‹ጉልህ ጉዳት›› የሚለው አገላለጽ በሦስተኛ መርህ ላይ የሰፈረው ሲሆን፣ አንድ አገር በወንዙ ለመጠቀም በሚያደርገው እንቅስቃሴ በሥርዓተ ፍሰቱ ላይ በሌላው አባል አገር ‹‹ጉልህ ጉዳት›› ላለመድረስ መጠንቀቁን ያትታል፡፡ ጉዳት በደረሰ ጊዜም አስፈላጊውን ካሳ ለመክፈል እንደሚገደድ በዚሁ አንቀጽ ሰፍሯል፡፡

  በአራተኛው አንቀጽ ፍትሐዊና ተገቢ የውኃ አጠቃቀም መርህን የተመለከተ ሲሆን፣ ሦስቱም አገሮች በግዛታቸው ውስጥ የሚገኘውን ውኃ በፍትሐዊነትና በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጾች ተካተውበታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በተፋሰሱ ዙሪያ ያለው ተፈጥሮአዊ ሥነ ምኅዳርና የአየር ንብረትን በማያዛባ መልኩ፣ የአባል አገሮቹ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ፣ በወንዙ ላይ ሕይወታቸው ለተመሠረተ ነዋሪዎች በአሁኑና በቀጣይ የሚኖር የውኃ ተጠቃሚነት መጠን፣ የውኃ ምንጮችን መጠበቅና ማልማት፣ በተፋሰሱ ዙሪያ እያንዳንዱ አገር ያለው የውኃ ድርሻና የተፋሰሱ የቆዳ ሽፋን መጠን ይገኙባቸዋል፡፡

  በአምስተኛው አንቀጽ የተካተተው የግድቡን የውኃ አሞላል ሥርዓት የተመለከተ ነው፡፡ በግድቡ ላይ ጥናት ያካሄደው ዓለም አቀፍ የውኃ ባለሙያዎች ቡድንና የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ምክረ ሐሳብ ለመተግበር ይተባበራሉ ይላል፡፡ ይህም ሦስት ግቦች ያለው ሲሆን፣ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የግድቡን የመጀመርያ የውኃ አሞላል ሥርዓት በተመለከተ መመርያ ለማውጣት፣ የግድቡ ዓመታዊ አጠቃቀም ፖሊሲን በተመለከተ ባለቤቱ በየዓመቱ ሊቀያይረው የሚችል መመርያ ለመውጣት ይጠቅማል፡፡ እንዲሁም የውኃ ክምችት አገባብን ለማቀናጀት እንዲመች ሲባል፣ በግድቡ ግንባታ ላይ ለውጥ የሚያስከትል አስቸኳይ ጉዳይ ሲፈጠር ግብፅንና ሱዳንን ቀድሞ ማሳወቅን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሦስቱ አገሮች በውኃና መስኖ ሚኒስትሮች አማካይነት ተገቢውን ሥርዓት ያበጃሉ ይላል፡፡

  ይህ ዓለም አቀፍ የቴክኒክ ባለሙያዎች ኮሚቴ በግድቡ ላይ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተቀመጠው ቀነ ገደብ 15 ወራት መሆኑንም ተካቷል፡፡ እንዲሁም ሰነዱ የታችኛው ተፋሰስ አባል አገሮች ከግድቡ የሚመነጭ ኃይልን ለመግዛት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ሦስቱ አገሮች የመረጃ ልውውጥ የሚያደርጉበት ሥርዓት እንዲኖራቸውም ያስገድዳል፡፡

  በስምንተኛው አንቀጽ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ ቀደም የሰጠውን ምክረ ሐሳብ ለመተግበር እስካሁን ያደረገችውን ጥረት በማድነቅ፣ ከግድቡ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ቡድኑ ያስቀመጠውን ምክረ ሐሳብ ለመተግበር በመልካም ፈቃኝነት (good will) ትተገብራለች ይላል፡፡

  በዘጠነኛው አንቀጽ የሰፈረው መርህ የዓባይ ወንዝን በተቻለ መጠን ጥቅም ላይ ለማዋልና የወንዙ ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን ሦስቱ አገሮች የእያንዳንዱን አገር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የግዛት አሃዳዊነት መርህ ላይ በተመሠረተ ትብብር ያደርጋሉ ይላል፡፡

  የዚህ ‹‹የመርህ መገለጫ›› (Declarations of Principles) ስምምነት አተገባበር ላይ የትርጉም ልዩነትና ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ በመልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ድርድርና ውይይት እንዲደረግ የሚያዝ ሲሆን፣ ይህ ካልተቻለም ጉዳዩ ለአገር ፕሬዚዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር (መሪ) ይተላለፋል ወይም ጣልቃ እንዲገቡ ይደረጋል ይላል፡፡

  ከየት ወዴት?

  ከአሥር ዓመት በላይ አሥሩ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ተጋሪ አባል አገሮች ኢትዮጵያን ከግምት ያላስገቡ የሱዳንና የግብፅ (በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን) እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙ አግላይና አሮጌ ሰነዶችን ይተካል ተብሎ የታመነበትን አዲሱን የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት (የናይል ውኃ አጠቃቀም ሁለገብ ስምምነት CFA) በአብዛኞቹ (ስድስቱ አባል አገሮች) ፈራሚነት በተፋሰሱ ላይ የመጀመሪያ ሕጋዊ ሰነድ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ዋነኞቹ ተቀናቃኝ የሆኑት የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ግብፅና ሱዳን አሻፈረኝ በማለታቸው በእምቢተኝነት ፀንተው ነበር፡፡ ከሰነዱ መፈረም በኋላ ሊቋቋም የታሰበው የበላይ ኮሚሽንም ደብዛው ጠፍቷል፡፡

  ይሁን እንጂ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ከሱዳን ድንበር በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ልዩ ስሙ ጉባ በተባለው አካባቢ፣ በአፍሪካ ትልቁን ግድብ ለመገንባት ‹‹ሚሌኒየም›› (የአሁኑ ህዳሴ) በሚል ስያሜ መሠረተ ድንጋይ ሲያስቀምጡ ግብፅ ተቃውሞዋን አሰማች፡፡

  ወቅቱ በግብፅ የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንቱ ሁስኒ ሙባረክ አስተዳደር ላይ አመፅ የተቀጣጠለበት የነበረ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ላይ ጣታቸውን በመቀሰር የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ ዝተው ነበር፡፡ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ምልከታ ከውስጥ የመነጩ የዴሞክራሲና የነፃነት ጥያቄዎችን ያነሳሳው ተቃውሞ አቅጣጫ ለማሳት፣ ኢትዮጵያን እንደ መወጣጫ ሊያደርጓት የሞከሩ ሲሆን፣ በአብዮቱ ከሥልጣናቸው ተሽንቀጥረው አሁን ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

  በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ከግብፅ አካባቢ የሚሰነዘሩ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች ሳይበግሩት የግድቡን ሥራ አጧጧፈው፡፡ ይኼው በዚህ ወር አራተኛ ዓመቱ የሚከበረው የታላቁ ህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የጣና ሐይቅ የውኃ መጠን እጥፍ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ ከስደስት ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግንባታው ከ50 በመቶ መድረሱ እየተነገረ ሲሆን፣ ግድቡ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የሚያቁረው የውኃ መጠን እንዲቀንስና ከፍጆታው ዝቅ እንዲል ዓለም አቀፍ የማኅበራዊና የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ጥናት እንዲደረግበት በማለት በግብፅ በኩል የተለያዩ የፖለቲካና የሕግ ጥያቄዎች መቅረባቸው ቀጥሎ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን አብዮት ተከትሎ አመርቂ ባልሆነ ውጤት (በድጋሚ ምርጫ) ሥልጣን ላይ የወጡት የሙስሊም ወንድማማቾች ተወካይ ሙሐመድ ሙርሲ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመጡም፣ እሳቸውም የግብፅ አብዮተኞችን ጥያቄዎች መመለስ አልቻሉም፡፡ አመፅ መልኩን ቀይሮ ቀጠለ፡፡ እሳቸውም እንደ የበፊቶቹ የግብፅ መሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ማምለጫ ለመጠቀም በተለይ በግድቡ መነሻ በኢትዮጵያ ላይ የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ ቢዝቱም፣ በኋላ በአብዮተኞቹ ከሥልጣናቸው ተባረዋል፡፡

  በግብፅ ወገንተኛና የተዛባ የሚዲያ ዘገባዎች ታጅበው ፖለቲከኞቹ በኢትዮጵያ ላይ የተለያየ እንቅስቃሴዎች ቢያደርጉም አልተሳካም፡፡ ይልቁንም በሦስቱ አገሮች መካከል ሊደረስ የሚችል ስምምነት እንቅፋት ሆኖ ነበር የቀጠለው፡፡ በዚህ መካከል የሱዳን አቋም መገልበጥ የጎዳት ግብፅ፣ የድርድር የኃይል ሚዛኑ ተዛብቶባታል፡፡ በተለይ በሦስቱም አሮች ስምምነት ታዋቂ የውኃ ባለሙያዎች ያሉበት ዓለም አቀፍ የውኃ ባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴ ተቋቁሞ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ግብፅ የሪፖርቱን ውጤት ለመቀበል ማቅማማቷ አይዘነጋም፡፡ ሱዳን ከሞላ ጎደል ሪፖርቱን በፀጋ ነበር የተቀበለችው፡፡ የሪፖርቱ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ በተደጋጋሚ የተደረገው ጥረትም አንዴ ሞቅ ሌላም ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የሦስትዮሽ ውይይቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይል አዛዥ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ ነበር አዎንታዊ እንቅስቃሴ የታየው፡፡

  ከግብፅ አብዮት በኋላ በጊዜያዊነት ሥልጣን የተቆጣጠረው የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ወደ ካይሮ በመሄድ በከፍተኛ ደረጃ የመሪዎች ጉብኝት የተደረገ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የሆስኒ ሙባረክ ጉብኝት (በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ሲመጡ) በመስተጓጎሉ ምክንያት፣ በ30 ዓመታት ውስጥ የግብፅ ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ሲያደርግ የአሁኑ ፕሬዚዳንት አልሲሲ የመጀመሪያው ናቸው፡፡ ምናልባትም በዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ አጠቃቀም አምነው እንዲህ ዓይነት ስምምነት የተፈራረሙ የግብፅ መሪ የመጀመርያ ሳይሆኑ አይቀሩም እየተባለ ነው፡፡ የስምምነቱን ፋይዳ በተመለከተ ግን ሁለቱ መንግሥታት በየፊናቸው ደስታቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ይዘቱን በተመለከተ በገለልተኛ ወገን ወደፊት የሚታይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር ይወያያሉ፡፡ መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ በፓርላማ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...