Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ከመንግሥት የመጣና ሳናምንበት ወደ ፍርድ ቤት የወሰድነው ክስ የለም››

  አቶ ልዑል ካህሳይ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የክርክር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ

  በኢትዮጵያ ስላለው የፍትሕ ሥርዓት የተለያዩ አስተያየቶች ሲነገሩ ይሰማል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በጥቂት አምባገነኖች እጅ እንደ ወደቀ፣ ፍትሐ አለመኖሩን፣ ዜጎች እየተበደሉ እንደሚገኙ፣ የሐሰት ክስ በመመሥረትና ሐሰተኛ ማስረጃ በማቅረብ ዜጎች ያለ ጥፋታቸው በማረሚያ ቤት እንዲሰቃዩ እየተደረገ መሆኑን፣ ዳኞች ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሆንም፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሹማምንቶች ተፅዕኖ እየተደረገባቸው፣ ውሳኔዎችን ሳያምኑባቸው እንደሚወስኑና ሌሎችንም ትችቶች በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ የተነሱ ቅሬታ አዘል ትችቶችንና ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ በፍትሕ ሚኒስቴር የክርክር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ልዑል ካህሳይን ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- በፍትሕ ሚኒስቴር ላይ በርካታ ቅሬታዎች ይነሳሉ፡፡ በዜጎች ላይ እውነትነት የሌላቸው በሐሰተኛ ማስረጃ ክሶች እንደሚመሠረቱ፣ ተከሳሾች የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በፍርድ ቤት በሒደት ተረጋግጦ ወንጀለኛ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ‹‹ወንጀለኛ›› ተብለው እንደሚፈረጁና የፍርድ ቤት ሒደቶች ሳይጠናቀቁ ዶክመንተሪ ፊልሞች ተሠርተው ለሕዝብ እንደሚተላለፉ ከሚነሱት ቅሬታዎች ውስጥ ናቸው፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

  አቶ ልዑል፡- የክስ አመሠራረት ሥርዓታችንን ስንመለከት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ አብረው የሚሠሩበት ዕድል አልነበረም፡፡ በአብዛኛው በፖሊስ ተመርምሮ የሚመጣን ጉዳይ መሠረት አድርጎ፣ ዓቃቤ ሕግ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ያንን መነሻ ያደርግ ነበር፡፡ አሁን ግን የለውጥ ትግበራ (ቢፒአር) ከጀመርን በኋላ፣ በዋነኛነት ዓቃቢያ ሕጎቻችን እስከ ጣቢያ ድረስ ወርደው እየሠሩ ነው፡፡ ይኼ የተደረገበት ምክንያት ዓቃቤ ሕግ ክስ የሚመሠርተው የፖሊስን ምርመራ መዝገብ ብቻ መሠረት አድርጎ ሳይሆን፣ ቅሬታ የቀረበበትን ጉዳይ በተጨባጭ ከጅምሩ አንስቶ አውቆ፣ ለክስ አመሠራረትም ሆነ ለሌሎች ውሳኔዎች መነሻ እንዲሆነውና በቅርብ ርቀት እንዲያገኝ ታስቦ ነው፡፡ በአብዛኛው ከባድና መካከለኛ ብለን የለየናቸው የወንጀል ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ አብረው ይመረምራሉ፡፡ አብረው ሲመረምሩ የማስረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱ፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተጠርጣሪውን የሚያስጠይቅ መሆን መቻል አለበት፡፡ ፖሊስ በቀረበለት ጥቆማ መሠረት ምርመራ ጀምሮ ከሆነና የወንጀል ባህሪ ከሌለው፣ ከወዲሁ ‹‹የወንጀል ባህሪ የለውም፣ ምርመራው መቋረጥ አለበት›› ብሎ ለመወሰንም የሚያስችል አደረጃጀትንና ሥርዓትን የሚፈጥር ነው፡፡ ምናልባት ሪፖርቶቻችንን የማየት ዕድል አግኝተህ ከሆነ፣ ዓቃቤ ሕግ የቀረቡለትን ጉዳዮች ሁሉ ወደ ፍርድ ቤት ይዞ አይሄድም፡፡ በርከት ያሉና ቀለል ያሉ ጉዳዮች በዕርቅ የሚያልቁበት ሁኔታ አለ፡፡

  ወደ ዋናው የፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት፣ ዜጎች ያላቸውን አለመግባባት በመፍታት ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ውጪም ካየን ካልተሳሳትኩ አንድ አራተኛ የሚሆኑ ጉዳዮች በቂ ማስረጃ አልቀረበባቸውም ተብለው የሚዘጉ አሉ፡፡ ሁሉም ወደ ፖሊስ ወይም ወደ ምርመራ የመጣ ጉዳይ ሁሉ ክስ አይመሠረትበትም፡፡ ለማረጋገጥ መረጃውን ማየት ይቻላል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 መሠረት ‹‹ወንጀል አይደለም›› ተብሎ የሚዘጋ አለ፡፡ እንዲሁም በወንጀል ሕግ 42(1ሀ)ም መሠረትም የሚዘጉ መዝገቦች በርካታ ናቸው፡፡ ይኼ የሚያሳየው ዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን ጉዳይ ዝም ብሎ ይዞ አለመሄዱን ነው፡፡ የክስ ጥራቱ በየጊዜው እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ክስ ይሻሻል እየተባለ ክርክር የሚነሳባቸው በተለይም ፍርድ ቤት ‹‹ክስህን አሻሽል›› ብሎ ክሶች የሚመለሱበት ሁኔታ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲመሠረት ጥራት ያላቸውን ክሶች እያቀረበ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ክሶች ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ በፈጸሙት ወንጀል ፍርድ ቤት ‹‹ጥፋተኛ ናቸው›› ብሎ የወሰናቸው ውሳኔዎች አሉ፡፡ እነዚህን ውሳኔዎች ብናይ ከ94 በመቶ በላይ የማስቀጣት አቅም አላቸው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤት ‹‹ያቀረባችሁት ክስ ትክክለኛና በማስረጃ የተደገፈ ነው›› ማለቱ ነው፡፡ ተከላክለው ነፃ የሚወጡት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ከምርመራ ጀምሮ ጥራትን ለማረጋገጥ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡

  በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ወንጀል ያልፈጸመ ተጠርጣሪን ወደ ፍርድ ቤት እየወሰደ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይኼም ሆኖ ግን በሁሉም ጉዳዮች ላይ ከሰው ስህተት የሚፈጠሩ ችግሮች አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ ኅበረተሰቡ የሚያቀርባቸው የተደራጁ የሐሰት ወንጀሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ተደራጅቶ በሐሰት የሚመሰክር ኅብረተሰብ አይጠፋም፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የሚኖር ክፍተት አያጋጥምም ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ግን ገዥ ችግሮች አይደሉም፡፡ ከብቃት አንፃር ካየነው ብቃት አንፃራዊ ነው፡፡ በርከት ያሉ አዳዲስ ዓቃብያነ ሕጎች እንቀጥራለን፡፡ ነባሮቹ የሚለቁበት ሁኔታም አለ፡፡ በአዲሶቹ ጠበቆች ምክንያት የሚፈጠሩ ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡ ከብቃት ችግር አንፃር፡፡ ነገር ግን ተቋሙ በየጊዜው የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት እንዲበቁ ያደርጋል፡፡ እያደረገም ነው፡፡ ዕጩ ሆነው ቆይተው ብቃታቸው ሲረጋገጥ ነው ወደ መደበኛ ሥራ የሚገቡት፡፡ ከብቃትና አዲስ ከመሆን አንፃር ክፍተቶች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ሁሉንም ዝም ብሎ አይቀበልም፡፡ የራሱን ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡

  ሪፖርተር፡- በፍትሕ ሚኒስቴር አዲስ የለውጥ ትግበራ በመደረጉ፣ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ አብረው የሚሠሩበት አሠራር ተፈጥሯል፡፡ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ አብረው መሥራታቸው ለተጠርጣሪም ሆነ ለተቋማቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው የሚገልጹ አሉ፡፡ ጉዳት አድርገው የሚገልጹትም ሁለቱ ተስማምተው ከከሳሽ ወይም ከተሰካሽ ጋር በመመሳጠር መከሰስ የሌለበትን እንዲከሰስ የማድረግና መከሰስ ያለበትን እንዳይከሰስ እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

  አቶ ልዑል፡- ጥያቄው በመረጃ ላይ ተደግፎ የቀረበ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩን መሠረት አድርገን ለመወያየት ያስችለን ነበር፡፡ አንደኛ አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱ ሰፊ የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ በዚህ ሒደት አሠራሩ ለሙስና (ለብልሹ አሠራር) የተጋለጠ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ከጠየቅከኝ፣ እኛም ዕቅድ አውጥተን እየሠራንበት ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት የአመለካከት ተግባር ነው፡፡ አብረው ስለሠሩ ብቻ ሳይሆን አመለካከቱ ካለና ተግባሩ ካለ፣ ለብቻም ሆኖ ይፈጸማል፡፡ ከዚህ በፊትም በተናጠል እየሠሩ እያሉ እነዚህን ችግሮች እያስወገዱ ነበር ማለት አንችልም፡፡ እንዲያውም ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ አብረው መሥራታቸው ጥቅም አለው፡፡ መቀጠል የሌለባቸው ጉዳዮች ባጭሩ እንዲቋረጡ ለማድረግ ይረዳል፡፡ በተለይ ደግሞ ‘ቼክ ኤንድ ባላንስ’ የማድረግ ሥርዓት ይኖራል፡፡ የቅሬታ አሰማም ሥርዓትም አለ፡፡ እያንዳንዱ በጣቢያ ላይ የተወሰነን ጉዳይ ብቻ አይደለም መሠረት አድርገን የምናየው፡፡ ቅሬታ ያለው ሰው እስከ ሚኒስትሩ ድረስ ቅሬታውን የሚያቀርብበት ሥርዓት አለ፡፡ ችግር የሚፈጥረው መቀናጀቱ አይደለም፡፡ እንደኛ እምነት ተቀናጅተው በመሥራታቸው ችግሮች እየተቀረፉ ነው፡፡ ችግርና ቅሬታ ካለ የሥርዓቱ ችግር ሳይሆን የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ባለሙያዎች የሚፈጥሩት ችግር ነው፡፡ ድርጅቱ ወይም ተቋሙ የሚፈጥረው ችግር አይደለም፡፡ በሁሉም ባይሆንም በፖሊስና በዓቃቤ ሕግ መካከል ከቅንጅታዊ አሠራር አንፃር የተወሰነ አስተሳሰብ አለ እንላለን፡፡ ይኼ የሚሆነው አመጣጥኖ የመሥራት ሥርዓቱ አለ ማለት ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየን ጤናማ የሆነ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲስተሙን ለራሳቸው መጠቀሚያ የሚያደርጉ የሉም ብዬ ግን አልደመድምም፡፡

  ሪፖርተር፡- ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ዜጎችን ከመክሰሱም በተጨማሪ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸውም የከሰሳቸው እንዳሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

  አቶ ልዑል፡- ይኼ ጉዳይ በአገራችን በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ዓቃቢያነ ሕጎቻችን የመሠረቷቸው ክሶች ግን ያነሳኸውን ጥያቄ ሀቅነት የሚያረጋግጡ አይደሉም፡፡ በአብዛኛው የሚቀርቡ ክሶችን አይቶ የሚወስነው ታች ያለው ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ ወደ ሚኒስትሮች የሚቀርቡ ጉዳዮች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በራሱ የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ በዚህ ሒደት ካየነው ገለልተኛ ሆኖ እየወሰነ ነው፡፡ አንተ ካነሳሃቸው ጥያቄዎች አንፃር ስናየው ሁለት የተቀላቀሉ ነገሮች አሉ፡፡ ምርመራና የክስ ሥራ ስናካሂድ ሕግንና ማስረጃን መሠረት አድርገን ነው፡፡ ሕግንና ማስረጃን መሠረት አድርገን ሥንሠራ፣ በአጋጣሚ የሚጮኸው የእነዚህ አካል መሆኑ ነው እንጂ ሌላውም ላይ ሊሠራ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዓመቱ ውስጥ 60,000 የክስ መዝገቦችን ካየን፣ በ60,000 የክስ መዝገቦች ውስጥ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤቶች የሆኑ ይኖራሉ፡፡ ይኼ ሲሆን ደግሞ በባዶ ሳይሆን መነሻ አለው፡፡ አንተ እንዳልከው የፖለቲካ አመራሮች ተጠይቀው ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ግን የምንጠይቀው ወይም ክስ የምንመሠርትባቸው በፖለቲካ አመራርነታቸው አይደለም፡፡ በጣሱት ሕግና በፈጸሙት ወንጀል ነው፡፡ ሰው ግን ‹‹የታሠሩት በፖለቲካ አመለካከታቸው ነው›› ሊል ይችላል፡፡ ይኼ የራሱ ስሜት ነው፡፡ መዝገቡ ግን እንደዚያ አይልም፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሰው እንደሚለው ወይም አለ እንደተባለው ክስ ቢመሠርት፣ ጥያቄው የሚነሳው በሕገ መንግሥቱ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በተቋቋመው ፍርድ ቤት ላይ ጭምር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን አለማክበር ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተቋቋሙት ተቋማት አመኔታ እንዲያጡ የማድረግ ሒደት ነው፡፡ በጥሩ አመለካከት ማየት የሚችል ካለ በአብዛኛው ክስ የሚመሠረትባቸው ደረቅ ወንጀሎች ናቸው፡፡

  ለምሳሌ ከሽብር ጋር፣ ከአክራሪነትና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነው ክስ የተመሠረተው፡፡ መዝገቦችንም ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ አገር ላይ እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ ይዘው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ መንግሥት አይኖርም ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጥሶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሰው ይከሰሳል፡፡ ይኼ ሰው ሃይማኖቱን እንደ ሽፋን ይጠቀምበት እንጂ ተግባሩ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ጋዜጠኛውም እንደዚሁ ነው፡፡ የማሰብ፣ የመጻፍ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመናገር ነፃነቱን ተጠቅሞ እየሠራ እንደሆነ ቢገልጽም፣ በግልጽ ፈጽሞ የሚገኘው ተግባር ግን ወንጀል ነው፡፡ ጋዜጠኝነቱን የሚጠቀመው ለሽፋን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እናንተ ጋዜጠኞችም እንደዚህ የሚያነጋግሩ ጉዳዮችን ቀረብ ብላችሁ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ሰው እየቀላቀለው ስለተቸገረ እንጂ፣ ክሱ የሚቀርበውም ሆነ የሚታየው በግልጽና በግልጽ ችሎት ስለሆነ ቀረብ ብሎ ማየትና መመርመር ይችላል፡፡ የምንከሰው የፖለቲካ አመራርን ብቻ አይደለም፡፡ ጋዜጠኛንም ብቻ አይደለም፡፡ በዕምነት አመራር ላይ ያለን ብቻም አይደለም፡፡ ከእነዚህ ውጪ የማይጮህለት የተከሰሰም ሰው አለ፡፡ በሙያው በፈጸማቸው ወንጀሎች የተከሰሰ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ዶክተሮች በቸልተኝነት የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች አሉ፡፡ ይከሰሳሉ፡፡ ሌሎችም ብዙዎች ይኖራሉ፡፡ ሐኪም በመሆኑ፣ መምህር በመሆኑ፣ ወይም የሌላ ሙያ ባለቤት በመሆኑ የተከሰሰ ሳይሆን፣ ሕገ በመጣሱ ብቻ ነው የሚከሰሰው፡፡ ይኼም የሚሆነው በቂ ማስረጃ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡

  እኔ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ከመጣሁ ስድስት ዓመታት ሊሞሉኝ ነው፡፡ ከመንግሥት የመጣና ሳናምንበት ወደ ፍርድ ቤት የወሰድነው ክስ የለም፡፡ ለፍትሕ ሚኒስቴር ቀርበው ነገር ግን ክስ አይመሠረትባቸውም ብለን የዘጋናቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ቢሆኑም በቂ ማስረጃ ስላልቀረበባቸው ብቻ በጣም ብዙ ጉዳዮችን ዘግተናል፡፡ ፍርድ ቤትንም ብንወስድ የቀረበለትን ብቻ የሚያይና በቀረበለት ማስረጃ ብቻ የሚወስን አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ገለልተኝነቱ (Constitutional Independence) የተረጋገጠ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ችሎት ላይ ሳይቀር ቀርበው በፍርድ ቤቶች ላይ የማንቋሸሽ ተግባራት ሲፈጽሙ እየታዩ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመን የሕዝብ ተቋም መናቅ ነው፡፡ አመኔታ እንዲያጣ ማድረግ ነው፡፡ ከኋላው የተለዮ ርዕዮተ ዓለም ስላለው እንጂ፣ እኛ የምንሠራው ሥራ ሕጉንና ማስረጃን ተከትሎ የበኩሉን ከማድረግ ያለፈ ሌላ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ይኼንን ሲያደርግ ግን ከአቅም ውስንነትና ከሌላ ሌላ ነገሮች የሚፈጠሩ ጉድለቶች ወይም ችግሮች ግን የሉም ብዬ መደምደም አልችልም፡፡

  ሪፖርተር፡- ልምድ ያላቸው ዓቃቢያነ ሕግ እየለቀቁ ቢሆንም ብዛት ያላቸው አዲስ ዓቃቢያነ ሕግ እየተቀጠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዓቃብያነ ሕጉ አዲስ ከመሆናቸውና ልምድ ከማጣት የተነሳ፣ በችሎት ላይ ቆመው ሲከራከሩ ይዘውት የቀረቡትን የክስ ጭብጥ በአግባቡ ማስረዳት እንደማይችሉና የሚያቀርቧቸውም የማስረጃ ሰነዶች፣ ከክሱ ጋር የማይገናኙ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ በተለይ የሚያቀርቧቸው የሰው ምስክሮች በዓቃብያነ ሕጉ የተመለመሉ፣ እንደተመሠረተው ክስ እንዲያስረዱ ተነግሯቸውና አጥንተው የሚቀርቡ በመሆናቸው፣ ዓቃቤ ሕጉ ለሚያቀርብላቸው ጥያቄ እንጂ የተከሳሽ ጠበቃ የሚያቀርብላቸውን መስቀለኛ ጥያቄ መመለስ ስለማይችሉ፣ አብዛኛው የችሎት ሰዓት የሚያልፈው ‹‹ተቃውሞ አለን?›› የሚል መቃወሚያን በማድመጥ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ዓቃቢያኑ ሕጉ በክርክር ቢረቱም ፍርድ ቤቶች ከባለሥልጣናት በሚደርሳቸው የስልክ ትዕዛዝ ውሳኔ እንደሚሰጡ ይገለጻል፡፡ ይኼንን እርስዎ እንዴት ያዩታል?

  አቶ ልዑል፡- ይኼ አጠቃላይ ስሜት ነው፡፡ በየትኛው ክስ ላይ ይኼ እንደሚሆንና ማን እንዳለ ብጠይቅህ አትነግረኝም፡፡ ወይም ላንተም ቢሆን የትኛው ጉዳይ ላይ ይኼ ችግር እንደሚከሰት አይነግርህም፡፡ በእርግጥ የተወሰኑ ሰዎች እንደነዚህ ያሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ ይደመጣሉ፡፡ ‹‹የትኞቹ ፍርድ ቤቶችና ችሎቶች ወይም ክሶች ናቸው በመንግሥት ጫና እንዲወሰኑ የተደረጉት?›› ተብለው ቢጠየቁ የሚናገሩ የሉም፡፡ ውይይቱ ወይም የሚነሳው ክስ እየተጠቀሰ ቢሆን ኖሮ ምላሽ ለመስጠት ይቀለን ነበር፡፡ ጠቅላላ የሆነ ፍረጃ ይሆንና ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ያስቸግራል፡፡ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ፍርድ ቤቶች የቀረበውን ክስና ማስረጃ መርምረው በነፃ የሚለቁት ተከሳሽ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹እነ አቡበከር›› ከሚባሉት ተከሳሾች ውስጥ ከ12 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት በነፃ ተሰናብተዋል፡፡ በሥርዓቱ ይግባኝ ተብሎ ግን በተወሰኑት ላይ መከላከል አለባቸው ተብለው በድጋሚ እንዲቀርቡም ተደርጓል፡፡ ይኼንን ስንመለከት በአጠቃላይ ፍረጃ ትክክል አይደለም፡፡ እንኳን አሁንና የፍትሕ ሥርዓቱ እንጭጭ በነበረበት ጊዜ፣ በዳኝነት አሠራር ላይ ጣልቃ ገብነት አልነበረም፡፡ ግለሰቦች፣ ባለሥልጣናት ሀብታም ነጋዴዎች ወይም ሌሎችም ዜጎች የፍትሕ ሥርዓቱን እንደፈለጉ ሊገለገሉበት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ለዚህ ግን በየደረጃው ያሉ የፍትሕ አካላት ጥንካሬ ይወስነዋል፡፡ ሕግን የጣሰ ጣልቃ ገብነት ካለ፣ ‹‹አይሆንም›› የሚል ያስፈልጋል፡፡ እኛም እየሠራን ያለነው፣ ከታች ያለ ዓቃቤ ሕግ ያላመነበትን ጉዳይ ፍርድ ቤት ይዞ ሄዶ እንዳይከራከር የሚያስችል ሥርዓት ለመፍጠር ነው፡፡ ጣልቃ ገብነት ዓቃቢያነ ሕጉ አዲስ ስለሆኑ የሚፈጠር አይደለም፡፡ አዲስ ዓቃቢያነ ሕግ ስንል ዝቅተኛው መሥፈርት የሕግ ዲግሪ ነው፡፡ የተግባር ልምምድም ሞክረው የሚመጡ ናቸው፡፡ የተወሰኑትም በፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ፣ በክልልም ይሁን በፌደራል ሥልጠና ወስደው የሚመጡ ናቸው፡፡ እዚህም ሲመጡ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ የሚባሉት ዓቃብያነ ሕገ ከዜሮ የሚነሱ አለመሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ ወደ ሥራው ለመግባት የተወሰነ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ ተቀጣሪዎቹ ዓቃብያነ ሕጎች በተሻለ ውጤት (ከ3.6 በላይ) እና መጠነኛ ሥልጠና ያላቸው ናቸው፡፡ በጥቅል ሳይሆን በተጨባጭ ያሉትን ችግሮች እያነሳን ብንወያይ፣ ችግር ካለም ተወያይተን መፍትሔ ለማምጣት ያስችለናል፡፡ እኛ እያልን ያለነው ዓቃቤያነ ሕጉ ወደ ፍርድ ቤት የወሰደውን ጉዳይ መቶ በመቶ መርታት አለበት ነው፡፡ ይኼንን ስንል ሁሉንም ክሶች ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ አይደለም፡፡ ከወዲሁ በምርመራ ላይ እያለ የማያዋጣ ጉዳይ ከሆነ እንዲዘጋ ነው፡፡ የሆነ ያልሆነውን ነገር ወደ ፍርድ ቤት ይዞ ሄዶ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት እንዳይጋፋ መጠንቀቅ አለበት፡፡ በጥንቃቄ መርምሮና ወደ ፍርድ ቤት የሚሄደውን ለይቶ ይዞ ከሄደ ግን ሙሉ በሙሉ መርታት አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቶች (በተለይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ) በክፍላተ ከተሞች እየተከፈቱ ነው፡፡ በዚያው ልክ የዓቃቢያነ ሕግ ጽሕፈት ቤቶችም እየተከፈቱ ነው፡፡ ነገር ግን የዓቃቤ ሕገ ጽሕፈት ቤቶች የሚቀርብላቸውን የወንጀል ድርጊት ጥቆማና አቤቱታ ችላ በማለታቸው ዜጎች ‹‹ለማን አቤት እንበል?›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡ የወንጀል ድርጊቶችን ቢቀበሉም ተጠርጣሪውን በፍጥነት መርምረው ክስ ከመመሥረት ይልቅ፣ ዋስትና በመፍቀድ ወንጀል ፈጻሚው በተበዳዮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥርበት ሁኔታ እየተበራከተ መምጣቱም ይነገራል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር እነዚህን የዓቃቢያነ ሕግ ጽሕፈት ቤቶች የሚቆጣጠረው እንዴት ነው?

  አቶ ልዑል፡- በክስ ጥራት ላይ በተወሰነ መንገድ ውስንነት ሊኖር ይችላል፡፡ አብዛኛው ከአቅም ውስንነት የሚመጣ ነውና ገዢ አይደለም፡፡ የቅሬታ ማስተናገጃ ሥርዓቱ በእኛ ተቋም ውስጥ አለ፡፡ ቅሬታ የቀረበባቸውን መዝገቦች መርምረን ስናይ ግን፣ በአብዛኛው እታች የተወሰኑ ጉዳዮች ትክክል ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ትክክል ያልሆኑት ቅሬታዎች ከአንድ በመቶ በታች ናቸው፡፡ ቅሬታዎች ግን ይቀርባሉ፡፡ እኛም የማስተናገድ ኃላፊነት ስላለብን እናስተናግዳለን፡፡ ዜጎች የፈለጉትን ዓይነት ቅሬታ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ አላግባብ የተዘጋበት ካለ፣ ተቀባይነት ያጣም ከሆነና ሌሎች የሚፈልጋቸው ነገሮች ካሉ ቅሬታዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በዚህ ዓመት እንኳን የቀረቡ ቅሬታዎች ቀርበው ከተስተናገዱ ከ50 እና 60 ሺሕ ጉዳዮች አንፃር አሥር የማይሞሉ ናቸው፡፡ ይኼ ማለት ግን ሁሉም የምንወስዳቸው ጉዳዮች ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው ማለት አንችልም፡፡ በክሳችን ላይ የጥራት ጉድለት ያሉ መሆናቸውን ያረጋገጥንበት ሁኔታም አለ፡፡ የጥራት ጉድለት ሲያጋጥም በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች ጉዳዩን በድጋሚ እየመረመሩ የሚያስከስስ ከሆነ ክስ እንዲመሠረት፣ ያላግባብ ክስ የቀረበበት ከሆነ እንዲቋረጥ እያደርግን ነው፡፡ በድምሩ ስናየው በተለይ አዲስ አበባ ላይ አንድ ጉዳይ ከተገኘ ሰውም ሆነ ሚዲያው የማጋነን ጉዳይ ስላለ ነው፡፡ እናንተም እየተከታተላችሁ ሪፖርት የምታደርጓቸው የሚጋነኑ ነገሮች ስላሉ ብዙ ነገር የተፈጸመ ይመስላል፡፡ የግለሰቦች ጉዳይ ሆነው ሳለ በመገናኛ ብዙኃን ሲተላለፉ አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱ ‹‹እንደዚህ ነው›› የሚያስብሉ መልዕክቶች ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ ከብዛት አንፃር ሲታይ ግን ይኼንን ያህል አይደለም፡፡

  ሪፖርተር፡- አንድ የክስ ሒደት በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ ካገኘ በኋላ፣ የተወሰነበት አካል ይግባኝ በማለት እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ሄዶ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል፡፡ በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ውሳኔ ያገኘን ጉዳይ የመጨረሻ አድርጎ ከመቀበል ውጪ አማራጭ እንደሌለው አድርጎ የሚቀበለው ነው፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ በሰበር ሰሚ ችሎት የተዘጉ ጉዳዮች ወደ መጀመርያ ደረጃና ሌሎች ችሎቶች ተመልሰው እንደገና እንደ አዲስ ክርክር ሲካሄድባቸው ይታያሉ፡፡ ይኼ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ቢያብራሩልን?

  አቶ ልዑል፡- ምናልባት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ‹‹ያስቀርባል›› ብሎ ሲያይ በድጋሚ እንዲታይ የሚፈልገው ነገር ይኖራል፡፡ ሰበር ደግሞ ለመጀመርያ ጉዳዮች የተመቻቸ አይደለም፡፡ ከተቻለ ጉዳዩን መጀመርያ ያየው አካል መልሶ እንዲያየው፣ ነጥቦቹን ዘርዝሮ መዝገቡን ይመልሰዋል፡፡ ወይም በተመሳሳይ ሥራ ላይ ያለ ሌላ ችሎት እንዲያየው የሚመራበት ሁኔታም አለ፡፡ ራሱ ጉዳዩን ማየት ስለማይችል ወደ ታች ፍርድ ቤቶች ተመልሶ እንዲታይ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ፡፡ አንተ እንዳልከው ሒደታቸውን በአግባቡ ተከትለው የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች ከሆኑ ግን ተመልሶ ለማየት የሕግ ሥርዓታችንም አይፈቅድም፡፡ አንድ ሰው እስከ ሰበር ድረስ ተከራክሮ ነፃ ከወጣ፣ በድጋሚ በተመሳሳይ ጉዳይ የሚከሰስበት ሥርዓት የለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ አግኝተው በድጋሚ የተከፈቱ ክሶች እንዳሉ አናውቅም፡፡ እስካሁን የደረሰን ጉዳይ ወይም ቅሬታ የለም፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ውሳኔዎችን ካሳለፉ በኋላ የተለያዩ ትዕዛዞችን ያዛሉ፡፡ በፍርድ ቤቶቹ ውሳኔና ትዕዛዝ መሠረት አፈጻጸም ተከፍቶ እንቅስቃሴ ቢጀመርም፣ ፈጻሚ አካላት ለምሳሌ የወረዳ፣ የክፍላተ ከተሞችና የከተማ አስተዳደሩ ሳይቀር በማናለብኝነት ‹‹አንፈጽምም›› ሲሉ ይስተዋላሉ፡፡ የፍርድ ቤቶች የ2007 በጀት ዓመት የሰባት ወራት ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን በቀረበበት ወቅት ይኼው ጉዳይ እንደ ዋና ችግር ተነስቷል፡፡ ‹‹ማንም ከሕግ በላይ አይደለም›› የሚለውንም የጣሰ አካሄድ በመሆኑ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ‹‹የፍትሕ ሥርዓቱ አብቅቶለታል፣ ፍትሕ የለም፣ ሥርዓት አልበኝነት እየነገሠ ነው፣ ፍትሕ ባለመከበሩና ባለመኖሩ የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲንሰራፋ ሆኗል፤›› እየተባለ ነውና እርስዎ ምን ይላሉ ?

  አቶ ልዑል፡- አሁንም ይኼ የአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱ መገለጫ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ጥቂቶች እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ እገነዘባለሁ፡፡ በተለይ አስፈጻሚዎች ምክንያት በመፍጠር የማጓተትና የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዳይፈጸም አድርገው ከሆነ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ የራሱ አስፈጻሚ ከሆነ የሚያጓትተው የራሱ የሆነ የሚወስደው የዲሲፒሊን ሥርዓት አለው፡፡ በዚህም የሚጠየቅበት አግባብ ይኖራል፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ የአስተዳደር አካል ግን ፈጽም ተብሎ ‹‹የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አልፈጽምም›› ካለ፣ ሥርዓት አልበኝነት ነው ማለት ነው፡፡ ይኼ በሚሆንበት ጊዜ ‹‹ምንድነው መደረግ ያለበት?›› ብለን ካሰብን ግን ትዕዛዝ የሰጠው አካል እስከ መጨረሻው ተከታትሎ ማስፈጸም አለበት፡፡ በፍርድ ቤት ቀርቦ የሚጠየቅበት ሥርዓትም አለ፡፡ ሥርዓቱን ግን ምን ያህል ተጠቅመንበታል የሚለው መታየት አለበት፡፡ ‹‹ትዕዛዝ ሰጪውስ ለማስፈጸም ምን ያህል ርቀት ሄዷል? ጉዳዩን የሚከታተለው አካል ወይም ግለሰብ፣ ፈጻሚው የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በመጣስ አልፈጽምም ማለቱን ሥልጣን ላለው አካል አቅርቧል?›› የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡ ፈጻሚው በፍርድ ቤት ቀርቦ ለምን እንዳልፈጸመ ማስረዳት ካልቻለ መጠየቅ አለበት፡፡ ይኼ በአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱ መገለጫ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ ጥቂት ፈጻሚ እንቢተኞች አይጠፉም፡፡ ይኼ ማለት ግን በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት የለም የሚያስብል አይደለም፡፡ ፈጻሚ ተብሎ በሹመት የተቀመጠን ሰው እንዲጠየቅ አለማድረጋችን ነው ክፍተት ያለ ያስመሰለው፡፡ የሥርዓቱ ችግር አይደለም፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ምን ያህሉ እንደተፈጸሙና ምን ያህሉ ሳይፈጸሙ እንደቀሩ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ጥቂት ችግሮች ቢኖሩም ይኼንን ያህል ‹‹የፍትሕ ሥርዓት የለም›› የሚያስብል ግን አይሆንም፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠበትን ውሳኔ ‹‹አላስፈጽምም›› ማለትም ሕገወጥነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ እያለ ግለሰቦች ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ከሆነ መጠየቅ አለባቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቶች ዕግድ የጣለባቸውን ነገሮች ‹‹አልሰማሁም አላየሁም›› በሚል ሁኔታ ዕግዶችና ትዕዛዞች ሲጣሱ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ቤት እንዳይፈርስ፣ ግንባታ እንዳይካሄድ፣ ሁከት ይወገድልኝ፣ ንብረቱ ባለበት እንዲቆይ፣ ወዘተ›› የሚሉ ዕግዶች በፍርድ ቤቶች ቢተላለፉም፣ የማይከበርበትና ጥሰት ሲፈጸም ይስተዋላል፡፡ ይኼ አግባብ ነው ይላሉ?

  አቶ ልዑል፡- አይኖርም ብዬ አልከራከርም፡፡ ግን የሥርዓቱ መገለጫ አይደለም፡፡ ግለሰቦች ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የሚጠየቁበት ሥርዓት ግን አለ፡፡ በርካታ ጉዳዮች አላግባብ ተፈጽመው በመገኘታቸው በጉለሌ፣ በየካ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ የተጠየቁ አሉ፡፡ ይኼንን የሚከታተለው አካል እስከ መጨረሻው ተከታትሎ ጫፍ ላይ የማድረስ አለማድረስ ካልሆነ በስተቀር፣ በመሰለው መንገድ ሕገወጥ ሆኖ የሚኖር ሰው አይኖርም፡፡ ይጠየቃል፣ ይከሰሳል፡፡ ከሕግ በላይ ለመሆን የሚሞክር ሰው አይጠፋም፡፡ ሁላችንም ግን መታገል አለብን፡፡

  ሪፖርተር፡- ‹‹ፍትሕ የለም፣ ሥርዓት አልበኝነት ነግሷል›› በሚል እየቀረበ ያለው የሕዝቡ አቤቱታና ክስ ትክክል አይደለም? የፍትሕ ሥርዓቱ በአግባቡ እየሠራ ነው እያሉ ነው?

  አቶ ልዑል፡- በትክክል፡፡ በአግባቡ እየሠራን ነው፡፡ ሕግን የሚጥሱ ግለሰቦች ግን የሉንም እያልኩህ አይደለም፡፡ ይኖራሉ፡፡ በሚጠየቁበት አግባብም ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ግልጽ የሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን የማይፈጽም አካል ካለ ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችል ማወቅ አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- ጋዜጠኞች በነፃነት የመጻፍ፣ መረጃ የማግኘትና ለኅብረተሰቡ የማስተላለፍና ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፡፡ ይኼንን ነፃነታቸውን ሲጠቀሙም መጠንቀቅ ያለባቸው ነገር እንዳለ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በሚሠሩበት ወቅት ሕግን ሲተላለፉ የሚመለከተው የፍትሕ አካል በራሱም ሆነ ‹‹መብቴ ተነካ›› ብሎ አቤቱታ ከሚቀርብለት አካል መረጃ በመነሳት፣ መርምሮ በወቅቱ ዕርምጃ አይወሰድም ወይም አያስጠነቅቅም፡፡ በራሱም ሆነ በሌሎች የሚቀርብለትን ቅሬታ አከማችቶ ይከርምና ወደኋላ በመመለስ አሰባስቦም የወንጀል ክስ በመመሥረት፣ ጋዜጠኞች እንዲታሠሩ ወይም እንዲኮበልሉ ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማንም ጋዜጠኛ በጻፈው ጽሑፍ አልተከሰሰም፣ አይከሰስምም  ሲል ቢሰማም፣ በጻፉት ጽሑፍ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ግን አሉ፡፡ ይኼንን እርስ በራሱ የሚጋጭ አባባልና አካሄድ እንዴት ያዩታል?

  አቶ ልዑል፡- በዚህ ነገር ላይ መነጋገር ካለብን በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ሕጋዊ ነው? አይደለም የሚለው? መነሳት አለበት፡፡ እየተጠየቁ ያሉት ሕግ ጥሰው ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ማየት አለብን፡፡ እየተጠየቁ ያሉት ሕግ ጥሰው ነው፡፡ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸው የሚለው፣ በሕግ ሥርዓቱ ማስጠንቀቂያ የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ ማንኛውም ሰው የሕግን ሥርዓት አክብሮ መሥራት አለበት፡፡ ሕግን ተላልፎ ከተገኘ ይጠየቃል፡፡ ለጋዜጠኛው ሳይሆን ከኋላው ላለው ኅብረተሰብ ሲባል የተወሰነ ትዕግሥት አድርገን ‹‹ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያርሙ ዕድል አንሰጣቸውም›› የሚል ነው፡፡ ‹‹ልንከሳችሁ ነውና ተጠንቀቁ›› ካልሆነ በስተቀር በተለያየ መንገድ ይነገራል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ሲቀርብና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ ሲሰጡ፣ የሚመለከተው የኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤትም በራሱ ሐሳብ ይሰጥበታል፡፡ ነገር ግን ባለሙያው ወይም ኅብረተሰቡ ለራሱ እንደተሰጡ አድርጎ አያስበውም፡፡ ከዚህ ሁኔታ ሕግን እየጣሱ መሆኑን አውቀው መታቀብ እንዳለባቸው ከላይ በተጠቀሱ አካላት ከሚቀርቡ ሪፖርቶች ምላሾችና ከተለያዩ ዝግጅቶች መረዳት አለባቸው፡፡ ‹‹እነዚህ አባባሎች እኔንም ስለሚያካትቱ ሥርዓት ይዤ መሄድ አለብኝ›› የሚለውን አስተሳሰብ ካለመቀበል እንጂ፣ ሳይገነዘቡትና ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡ ክስ የሚመሠረትበት የይርጋ ጊዜ አለው፡፡ ይኼ የይርጋ ጊዜ እስካላለፈ ድረስ በተፈለገበት ጊዜ ክስ ሊመሠረት ይችላል፡፡ በተለያዩ አካላት የሚሰጠውን የማስተዋያና የማስጠንቀቂያ ጊዜያት በማለፍ ወዳልተፈለገ የወንጀል ድርጊት ሲያመራ ግን ሥርዓት መከበር አለበት፡፡ ይኼንን ስል ሁሉንም ማለቴ አይደለም፡፡ የሙያ ሥርዓቱን (Professional Ethics) ጠብቀው የሚሠሩ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ አንዳንዱን ግን ልክሰስ ብትል በየጋዜጣው ገጽ የሕግ አንቀጽ ሊጠቀስባቸው የሚችሉ ጥሰቶች አሉ፡፡ ሚዲያውን ወይም ጋዜጠኛውን ከሶ ማስቀጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከኋላው የሚገለገልበት ሕዝብ ስላለ ትዕግሥት እናድርግ በሚል ነው ችላ የሚባለው፡፡ መከሰስ ካለበት ጠንከር ያለ ክስ ቀርቦበት ሌላውም አካል ሊማርበት ይችላል ተብሎ ሲታሰብ ይከሰሳል፡፡ አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲቀጣ ይደረጋል፡፡ ሁልጊዜ ስለሚተላለፈው የሕግ ጥሰት አይነሳም፡፡ ጎልቶ የሚነሳው ስለመከሰሱና ስለመቀጣቱ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ግዴታውንና መብቱን ጠብቆ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ዴሞክራሲ ነው ይባላል፡፡ ዴሞክራሲ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ቢላዋ ነው፡፡ በአብዛኛው በአንድ በኩል ስላለው ስለት ብቻ ይነገራል፡፡ ያንን በአንድ በኩል ያለውን ስለት አትንኩት ይባላል፡፡ ግን ከሁለቱም በኩል ስለት መኖሩን መርሳት የለብንም፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የወጡ ማስፈጸሚያዎችን ተከትለን ብንሠራ ሊያስታርቀን ይችላል፡፡ ሁላችንም ማዕቀፍ የምናደርገው እሱን ብቻ ነውና፡፡ በጋዜጠኛውም አካባቢ እንደማንኛውም ሙያ የክህሎት ችግር አለ፡፡ የግንዛቤም እጥረት ይስተዋላል፡፡   

  ሪፖርተር፡- ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋማት በራሳቸው ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርተው በፍርድ ቤት ክርክር ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ሕግ አውጪው የሚያወጣቸው ሕጎች ሲደራረቡና ሲጣረሱ ይስተዋላል፡፡ ይኼ ደግሞ በአንድ አገር ወጥ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት ከማስፈን አንፃር የራሱ ችግር አለው፡፡ ዜጎችም መጠየቅ በሌለባቸው የወንጀል ሕግ እንዲጠየቁ ከመደረጋቸውም በተጨማሪ ተገቢ ያልሆነ ቅጣት ሊጣልባቸው ይችላል፡፡ አግባብነቱ እስከምን ድረስ ነው?

  አቶ ልዑል፡-  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጎች በምክር ቤቱ አባላት ሙሉ ድምፅ አግኝተው ሕግ ሆነው ከመፅደቃቸው በፊት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር መታየት እንዳለባቸው ያስቀመጠው አቅጣጫ አለ፡፡ ይኼ በመሠረቱ ችግሩን ሊፈታው ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ሕጎች ፀድቀው ሲወጡ ግን የተወሰነ ችግር ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የጥራት ችግሩ ደግሞ በአብዛኛው የሚመጣው ከአቅም ውስንነት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሠለጠነ የሰው ኃይል የለንም፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር እንኳን በድራፍቲንግ (ማርቀቅ) ያለን አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቶች የሕግ ረቂቅ ሲያዘጋጁ በቂ ባለሙያ ካለመኖርና ከአቅም ውስንነት የተነሳ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ይኼንን እኛም ገምግመናል፡፡ ሕጎቹ ሲወጡ ሕገ መንግሥቱን መነሻ አድርገው ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- አንዳንድ ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ውጪ በሆነ መንገድ ተተርጉመው በመውጣታቸው ሕገ መንግሥቱን የጣሱ ናቸው ይባላል፡፡

  አቶ ልዑል፡- በግልጽ ሕገ መንግሥቱን እንዲጥስ ተደርጎ የወጣ ሕግ የለም፡፡ ትርጉም ሲሰጥ ግን ያጋጥማል፡፡ ሕግ ማኅበራዊ ሳይንስ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለን ባህሪ ለመቆጣጠር የሚወጣ መሣሪያ ነው፡፡ ሁሉንም ነገሮች ቆጥሮ ማስቀመጥ ስለማይቻል ረቂቅ በሚዘጋጅበት ጊዜ የሚፈጠር ችግር ይኖራል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን ‹‹ይኼ ረቂቅ ሕግ ይኼንን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ጥሷል›› በሚል የቀረበ የለም፡፡ ትርጉም ሲሰጥ ግን ‹‹ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል›› የሚል አለ፡፡ ይኼ ደግሞ የእኛ የባለሙያዎች አካዳሚክ ‘ዲስኮርስ’ አይደለም፡፡ ሕጉ ተግባር ላይ ውሎ ማንኛውም አካል ሕገ መንግሥት ይጥሳል ብሎ ካሰበ፣ ሥርዓቱን ጠብቆ ትርጉም የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ችግሮች እንዲፈቱ የሚደረገው በውይይት ይሆንና ትክክለኛ መፍትሔ ሳይገኝ ይቀራል፡፡ ሁሉም ሕጎቻችን አንቀጾቻቸው ሲታይ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ አዝማሚያ አላቸው ከመባል ያለፈ፣ በትክክለኛው ‹‹ይኼ ሕግ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው›› ተብሎ የቀረበ እስካሁን አላጋጠመኝም፡፡ ጎላ ብለው የወጡት ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ፣ የበጎ አድራጎት ድርጀቶችና ማኅበራት ሕግን በመጥቀስ ስህተት እንደተፈጸመ የሚነገር ቢሆንም ዝም ብለው የሚሰጡት ትርጉም እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱን የጣሱ ሕጎች አይደሉም፡፡ ለአገራችን ሥርዓት የሚጠቅመን ግን፣ የሕግ ስህተት አለ ከተባለ የራሱን መንገድ ተከትሎ በሚመለከተው አካል እንዲስተካከል ቢደረግ፣ ለሕግ ‘ጁሪስፕሩደንስም’ (ሥነ ሕግ) የተሻለ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በሌሎች አካላት እንዲስተካከል ማድረግ ከፊሉ ከፖለቲካ አንፃር ሌላው ከሌላ አንፃር ተመልክቶ ትርጉም ስለሚሰጠውና የየራሱን አቋም ስለሚይዝ፣ እስካልተፈታ ድረስ በየጊዜው እያከራከረ መሄዱ አይቀርም፡፡

  ሪፖርተር፡- ዳኞች የዲሲፕሊን ግድፈት ሲፈጽሙ ከሥራ ታግደው በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በኩል የሚጠየቁበት አሠራር አለ፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴር ደግሞ በሚኒስትሩ ተወክሎ የጉባዔው አባል ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር ከሳሽ በሆነበትና የዲስፕሊን ግድፈት ተፈጽሞበታል በተባለ ጉዳይ ላይ ዳኞች ተጠይቀው ሲቀርቡ፣ የእሱ ውክልና ተፅዕኖ ስለሚፈጥር መኖር የለበትም ይባላል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

  አቶ ልዑል፡- እስካሁን ድረስ በፍትሕ ሚኒስቴር ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የቀረቡ ብዙ የዲሲፕሊን ግድፈቶች የሉም፡፡ ግልጽ የሆኑ የሕግ ጥሰቶች ሲፈጠሩ እንደማንኛውም ባለጉዳይ አቤቱታ አቅርበን ይሆናል፡፡ ሚኒስትሩ እዚያ ሲሰየሙ የእኛን ጉዳይ ሊያዩ አይደለም፡፡ አባል እንደመሆናቸው መጠን የቀረበላቸውን ጉዳይ ያያሉ፡፡ ይኼ የመረጥነው አደረጃጀት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ብቻቸውን የሚሠሩ አካላት አይደሉም፡፡ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይሠራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ፍትሕ ሚኒስቴር የሆነው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ያስችለዋል የሚል ዓላማ ስላለ ነው፡፡ ከውሳኔ አሰጣጥ አንፃር ካየኸው ፍትሕ ሚኒስቴር ሐሳብ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ውሳኔ የሚወሰነው ግን በድምፅ ብልጫ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያመጣው ተፅዕኖ የለውም፡፡ ከአደረጃጀት አንፃር ካየኸው ግን በዚህ ዓለም ወጥ የሆነ አደረጃጀት የለም፡፡ እንደ ሥርዓቱ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ተጠሪነታቸው ለፓርላማ ቢሆንም፣ የዕለት ከዕለት አስተዳደር ሥራቸው ውስጥ ወጥ የሆነ አካሄድ አለ፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የጉባዔው አባል በመሆኑ የመወሰን መብታቸውን እየተጋፋ መሆኑን የሚገልጽ ቅሬታ እስካሁን አልሰማሁም፡፡ ተቋሙን እንጂ እያንዳንዱን ጉዳይ ወክሎ አይደለም በጉባዔው የሚገኘው፡፡ ፈጻሚው የዳኝነት ተፅዕኖ ያለበት ተደርጎ ይወሰዳል የሚለው ስህተት ነው፡፡ የዳኝነት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያገኘ ነፃነት አካል ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴርም ይኼንን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የማክበርና የማስከበርም ኃላፊነት አለበት፡፡ የዳኝነትን ነፃነት የሚጋፋ ነገር ሲመጣ የሚታገል ተቋም ነው ተብሎ ሊታሰብ ይገባል፡፡ የዳኝነትን ነፃነት የሚያረጋግጥ ደጋፊ የሕግ ተቋም ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  በዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኝ ነፃ የትምህርት...

  በደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች ተገደሉ

  በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ኢትዮጵያ የግብፅን ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ያሉ አገሮችን ጫና የምትቋቋመው የማይቋረጥ የኃይል መሠረተ ልማት ሲኖራት ነው›› ሳሙኤል ተፈራ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ...

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ በጃፓን ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአፍሪካና በእስያ ጥናት ትምህርት...

  ‹‹ባንኮች በየዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ እያገኘን ነው እያሉ ከሚከፋፈሉ ካፒታል ማሳደግ ላይ በሚገባ መሥራት አለባቸው›› አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር

  በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ የፋይናንስ ተቋማት የትርፍ ምጣኔ እያደገ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የውስጥና የውጭ ችግሮች አሉ በሚባልባቸው ጊዜያት ሁሉ...

  ‹‹ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ ይህች አገር አሁን በምናያት መንገድ አትኖርም›› ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ የኢዜማ ሊቀመንበር

  ለረዥም ጊዜ በዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የኢዜማ ምርጫም የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ጥናቶችን በማበርከት የሚታወቁም ሲሆን፣ በተለይ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ...