Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ከሠራተኞቹ ተቃውሞ ገጠመው

  የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ከሠራተኞቹ ተቃውሞ ገጠመው

  ቀን:

  ‹‹ድርጅቱ በአግባቡ እየሠራ ቢሆንም ዘመቻ ተይዞበታል›› የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት

  የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሠራተኞች በተቋሙ የመልካም አስተዳደር እጦት መማረራቸውን ገለጹ፡፡

  ግዙፍ የሆኑ የግድብ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን በመጠቆም ‹‹በሕይወትና በሞት መካከል ያለ ድርጅት ነው›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መተቸታቸው ይታወሳል፡፡ ሠራተኞቹም ይህንን ትችት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ተጋርተዋል፡፡

  ከ2,100 በላይ ቋሚና ከ8,000 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት የሚነገረው የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ በኪራይ ሰብሳቢዎች ውድመት እየደረሰበት መሆኑን በመግለጽ፣ ሙሉ በሙሉ ህልውናውን ሳያጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲታደጉት ሠራተኞች በሠራተኛ ማኅበራቸው አማካይነት ደብዳቤ መጻፋቸው ታውቋል፡፡ ድርጅቱ በአመራሮቹ ሙስና እየተፈጸመበትና የመልካም አስተዳደር እጦት ወይም ማናለብኝነት እየነገሠበት መሆኑን ሠራተኞች ባገኙት መድረክ ሁሉ ሲገልጹ መክረማቸውን የሚገልጸው ደብዳቤው፣ በአመራሮቹ የሚፈጸምን የሙስና ተግባር ለተመደቡት የሥነ ምግባር መኮንን የተጠቆመ ቢሆንም፣ የጠቋሚዎችን ማንነት በሚስጥር መያዝ የሚገባቸው መኮንኑ ግን ለኃላፊዎቹ አሳልፈው በመስጠት፣ በሠራተኞቹ ላይ የአስተዳደር በደል እንዲፈጸምባቸው ማድረጋቸውን ያትታል፡፡

  ድርጅቱ አብዛኛዎቹን ፕሮጀክቶች የሚሠራው በክልሎች በመሆኑ፣ ኃላፊዎቹ ፕሮጀክቶችን ከመጎብኘት ጋር በማያያዝ አግባብነት ካለው የውሎ አበል ውጪ፣ ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ድርጅቱ ወደ ኪሳራ የሚንደረደርበትን መንገድ እየጠረጉ መሆኑን ሠራተኞቹ ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ለፕሮጀክቶች ከሚከራዩዋቸው የተለያዩ ማሽነሪዎች ላይ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙም አስረድተዋል፡፡ ማሽነሪዎችን ያለድርድር ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር በየትኛው ፕሮጀክት ላይ መሥራት እንደሚፈልጉ በመጠየቅ፣ የመሥራት አቅማቸው ደካማ የሆኑ ማሽነሪዎችን በከፍተኛ ገንዘብ መከራየትና የኪራይ ሰብሳቢነቱን አሠራር ውስብስብ በማድረግና እርስ በርስ በማያያዝ፣ ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ መሆኑንም አክለዋል፡፡ የድርጅቱ አሠራር ትክክል እንዳልሆነ የሚሟገቱ ሠራተኞች ላይ ቂም በመያዝና ተከታትሎ አስተዳደራዊ በደል በማድረስ ከሚወዱት ሥራ እንዲለቁ እንደሚደረግም በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡

  ከ500 በላይ ሠራተኞች በድርጅቱ አመራሮች ተማረው ሥራቸውን ሲለቁ፣ ‹‹ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው›› በማለትና በመፈረጅ ድርጅቱን የማራቆት ተግባራቸውን እንደቀጠሉ፣ ሠራተኞቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ ጠቁመዋል፡፡ የድርጅቱ አጠቃላይ ዕዳ ሁለት ቢሊዮን ብር አካባቢ መድረሱን የሚጠቁሙት ሠራተኞቹ፣ ሠራተኛው ሌሊትና ቀን እየሠራ በማሽን ኪራይ ሰበብ ገንዘቡ በመመዝበሩ እንጂ፣ እውነተኛ ኪሳራ ደርሶበት እንዳልሆነ ለማወቅ ሊመረመር እንደሚገባው አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡ በአንድ በኩል ሁለት ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት የሚነገርለት ድርጅቱ፣ በሌላ በኩል በተለይ ባለፈው ዓመት ትርፋማ መሆኑ እንደተለገጸና ሠራተኛው ቦነስ እንደሚሰጠው የተነገረ ቢሆንም፣ የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱንም ሠራተኞቹ አክለዋል፡፡ ‹‹ድርጅቱ አትራፊ ከሆነ ለምን የተወሰነ በጀት ተይዞ ከኪራይ እንድንወጣ አይደረግም?›› በማለት የሚጠይቁት ሠራተኞቹ፣ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ያለበት ሁኔታ (በበጀት ዓመቱ እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ) የሥራ አፈጻጸሙ ከ25 በመቶ በታች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ድርጅቱ ያለጨረታ ግዥ እንደሚፈጽም፣ ያላግባብ ነዳጅ እንደሚጠቀምና በዘር ሐረግና በጥቅማ ጥቅም በመያያዝ ያለ ምንም ማስታወቂያ፣ ከሚሠሩት ሥራ ጋር የሚዛመድ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ የሌላቸው ሰዎች እንደሚቀጠሩም በስም እየጠቀሱ በደብዳቤው አሳውቀዋል፡፡ በሙስና ተጠርጥረው ይሠሩበት ከነበረው መሥሪያ ቤት የተባረሩ፣ በልምምድ ሥልጠና ላይ የነበሩ ዘመዶቻቸውን በማስገባት፣ አመራሮቹ የድርጅቱን ውድቀት እያፋጠኑት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተለይ በዋና ሥራ አስፈጻሚውና ሌሎች በየዲፓርትመንቱ ያሉ ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርጉት ሠራተኞቹ፣ ድርጅቱ በቦርድ የሚመራ ቢሆንም ቦርዱ በተደጋጋሚ የሚቀርብለትን ጥያቄ ተስፋ የሚሰጥ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ፣ አንድም ጊዜ ዕርምጃ ሲወስድ አለማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ምናልባትም የሥራ አመራሩን የሥነ ምግባር ጉድለት የሸፈነለት ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሬያቸውን አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ በድርጅቱ ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙ ዘመድ አዝማድና ጓደኛማቾችን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ አስቸኳይ ዕርምጃ በመውሰድ ድርጅቱን ከውድቀት፣ ሠራተኞችን ደግሞ ሥራ እያለ ሥራ አጥ ሆነው ከመበተናቸው በፊት እንዲታደጉት ጠይቀዋል፡፡ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ለፀረ ሙስና ኮሚሽንም የደብዳቤያቸውን ግልባጭ አስገብተዋል፡፡

  ሠራተኞቹ የድርጅቱን አመራሮችና አሠራራቸውን በመቃወም ስለሚያነሷቸው ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አታክልት ተካ፣ ‹‹ድርጅቱን የማፍረስ ዘመቻ ተይዟል፤›› ብለዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው እሳቸው ወደ ድርጅቱ ከመምጣታቸው በፊት በኪራይ ሰብሳቢዎች የታጠረና ህልውናውን ሊያጣ ትንሽ የቀረው ድርጅት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተለይ ከማሽነሪ ኪራይ ጋር በተገናኘ ሕጋዊ መንገዶችን በመከተል እንዲሰጥ በማድረጋቸው፣ ጥፋት በሚሠሩ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰድ በመጀመራቸውና ውጤት እየታየ በመምጣቱ የተከፉ ሠራተኞች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት ሳይቀር ድርጅቱ የነበረበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ ጠቁመው፣ ባለፈው የክረምት ወቅት ድርጅቱን እንደገና በማቋቋምና ተጨማሪ በጀት እንዲያገኝ መደረጉንም አክለዋል፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ መገባቱንና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ከነበረበት ዕዳ ወጥቶ ትርፋማ መሆኑንም አቶ አታክልት ጠቁመው፣ አንድ ድርጅት ትርፋማነቱን የሚያውጀው በወረቀት ላይ ሠርቶ በመሆኑ፣ ለሠራተኛው እንደሚሰጠው የተገለጸው ቦነስ ገንዘብ እስከሚሰበሰብ ሁለትና ሦስት ወራት መዘግየቱን እንደ መጥፎ ነገር በመቁጠር ለአሉባልታ መንቀሳቀሻ ያደረጉት ሠራተኞች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

  ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለተጻፈው ደበዳቤ ምላሽ መሰጠቱን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅቱ ቀደም ሲል ከነበረበት ችግር አንፃር ያነሱትን ነጥብ በመያዝ፣ ሥራ ትተው የድርጅቱን ስም ለማጥፋትና ተዓምር የተፈጠረ ለማስመሰል ዘመቻ የጀመሩ ሠራተኞች እንዳሉ እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡ ያላግባብ የወጣ ወጪ አለመኖሩን ቀደም ሲል ያለወረቀት በስልክ ጥሪ ብቻ የሚቀጠረው ሠራተኛ ዛሬ በማስታወቂያና በውድድር መቀጠር በመጀመሩ፣ የተገላቢጦሽ እንደሚወራ አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ ሠራተኞች ከተማሩት ትምህርት ጋር የማይገናኝ ሙያ ላይ ተመድበዋል የሚባለው እውነት ቢሆንም፣ ለቦታው ተመጣጣኝ የሆነ ሌላ ትምህርት መማራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቱ የመንግሥት ልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፣ ማንኛውም ነገር ሕጋዊ መንገዶችን ተከትሎ የሚጣራና የሚታወቅ በመሆኑ ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ከ4,000 በላይ ተዋናዮችን ከሦስት ሳምንታት በፊት ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት ወቀሳ፣ ከሰነዘሩባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ድርጅቱን ለማቋቋም የተገደደው በዘርፉ ብቃት ያላቸው ተቋራጮችና ባለሙያዎችን ባለማግኘቱ መሆኑን፣ ይህ በመሆኑም የውኃ ሥራዎች ዘርፍ በሞትና በሕይወት መካከል የሚገኝ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የዕውቅና የክህሎት ችግር ያለባቸው፣ የተሰጧቸውን ፕሮጀክቶች መፈጸም የተሳናቸው ስለመሆናቸው፣ የደቡብ ኦሞ የኩራዝ ፕሮጀክትን የስኳር ፋብሪካ ዲዛይን ሥራ መጓተትና ለኪሳራ መዳረግን መጥቀሳቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...