Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሞተር ብስክሌቶችን አገር ውስጥ መገጣጠም ተጀመረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ስኩተር ከሚለው ተለምዷዊ ስያሜ በመውሰድ ስኩቲ የሚል መጠሪያ የተሰጣቸውንና አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ሞተር ብስክሌቶች የሚገጣጥመው የህንዱ ባላጂ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ፣ ለገጣፎ አካባቢ በመሠረተው ፋብሪካ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ነዳጅ አልባ ሞተር ብስክሌቶችን ለገበያ ማቅረብ ጀመረ፡፡

  በለገጣፎ 3,600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ፋብሪካ በቀን 15 ሞተር ብስክሌቶችን መገጣጠም እንደጀመረ ለሪፖርተር የገለጹት፣ የኩባንያው ዳይሬክተር አሩን ጂናዳል ናቸው፡፡ ኩባንያው ሥራ በጀመረ በአሥር ወራት ውስጥ 150 ሞተር ብስክሌቶችን መገጣጠሙንና ለገበያ ዝግጁ ማድረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በሰዓት እስከ 60 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉት ሞተር ብስክሌቶች፣ በየቤቱ ቻርጅ መደረግ በሚችል ባትሪ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የሞተር ብስክሌቶቹ ባትሪ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ቻርጅ የሚደረግ ሲሆን፣  ስኩቲ ሞተር ብስክሌቶች ‹‹ኢግናይት››፣ ‹‹ዚፒ›› እንዲሁም ‹‹ስታር›› በተባሉ ሦስት ሞዴሎች አማካይነት ወደ ገበያ መግባት ጀምረዋል፡፡ በዋጋ ረገድም ከ24,200 ብር እስከ 25,500 ብር እንደሚያወጡ ጂንዳል ይፋ አድርገዋል፡፡ በአስፋልትና በኮብል ድንጋይ በተሠሩ መንገዶች ላይ መነዳት የሚችሉት የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌቶች፣ የአደጋ ጊዜ ወይም በስርቆት ሙከራ ጊዜ ጥሪ የሚያስተላልፍ፣ በራሱ ጊዜ አውቶማቲክ የኤሌክትሪክ ጥገና የሚያከናውን ሥርዓት፣ ሴንሰርና ሌሎችም መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው ሲሆኑ፣ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት አገልግሎ ሲያልቅ የሚቀየር እንጂ ጥገና የማያስፈልገው መሆኑም የሞተር ብስክሌቶቹ ከሚገለጹባቸው የቴክኒክ ይዘቶች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 

  አምና በሐምሌ ወር፣ በ250 ሺሕ ዶላር ካፒታል ፋብሪካውን ገንብቶ ሥራ ያስጀመረው ባላጂ ማኑፋክቸሪንግ፣ በአሁኑ ጠቅላላ ካፒታሉ ወደ 275 ሺሕ ዶላር ማደጉንና በወራት ጊዜ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ጂንዳል ይናገራሉ፡፡ 

  ኢትዮጵያ ውስጥ አማራጭ የግል ትራንስፖርት ዘዴ እንደሚሆኑ ታሳቢ የሚደረጉት ስኩቲ ሞተር ብስክሌቶች፣ ለቻርጅ የሚያስወጡት ወጪ በኪሎ ሜትር ከሁለት ሳንቲም እንደማይበልጥ ጥናት ማድረጋቸውን ህንዶቹ ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በታክሲ ሰባት ኪሎ ሜትር ለመጓዝ እስከ አሥር ብር እንደሚፈጅ፣ በመሆኑም አምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር በታክሲ የሚጓዝ ተሳፋሪ፣ ከሰባት ሺሕ ብር በላይ ወጪ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት ሁኔታ በማጥናት መገንዘባቸውን ጂንዳል አስረድተዋል፡፡

  ስኩቲ ሞተር ብስክሌቶች ለአምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር ከአንድ መቶ ብር በላይ እንደማይጠይቁ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኤሌክትሪክ የሚሠሩት ሞተር ብስክሌቶች በየነዳጅ ማደያው ከሚታየው ወረፋ አኳያና ከብክለት ነፃ መሆናቸው ጭምር በህንድ በስፋት ጥቅም ላይ ለመዋላቸው ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም መኪና መግዛት ለማይችሉ የከተማ ነዋሪዎችም በአማራጭነታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ 

  ይህም ቢባል ግን አዲስ አበባ ውስጥ በሚታየው የተሽከርካሪ ትራፊክ መጨናነቅና ትርምስ ላይ እንዲህ ያሉ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች የሚበራከቱ ከሆነ የትራፊክ ፍሰቱን ይበልጥ እንደሚያጨናንቁት ከወዲሁ ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡ ጂንዳል ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ይልቁንም ከድምፅና ከጭስ ብክለት ነፃ የሆኑት ስኩቲ ሞተር ብስክሌቶች፣ ለትራፊክ መጨናነቅ ዓይነተኛ መፍትሔ መሆናቸውን፣ ብዙ ቦታ የማይዙ በመሆናቸውም በቀላሉ ወደሚፈለገው ቦታ ለመድረስ የሚያስችሉ አማራጭ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን በመግለጽ ይሞግታሉ፡፡

  አሩን ጂንዳል እንደሚገልጹት በስኩቲ ሞተር ብስክሌቶች የተጀመረው የመገጣጠም ሥራ፣ ወደ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችም እንደሚያመራ ይጠበቃል፡፡ በተለምዶ ባጃጅ የሚባሉትን ተሽከርካሪዎች ነዳጅ አልባ በማድረግ በኤሌክትሪክ እንዲሠሩ አድረጎ ለመገጣጠም ኩባንያው ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡ የገበያው ሁኔታ ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የስኩቲ መገጣጠሚያ ፋብሪካውን ሙሉ ለሙሉ ማምረት ወደሚችልበት አቅም እንዲደርስ ለማድግ የረጅም ጊዜ ውጥን እንዳላቸው የኩባንያው ባለንብረቶች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በመደበኛና በገጠራማ መንገዶች ላይ የሚሽከረከሩ፣ ከፍተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ሞተር ብስክሌቶችንም ወደ ገበያ ማምጣት ባላጂ አምራች ፋብሪካ ወደፊት ከሚያሳካቸው ተግባራት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች