የቻይና መንግሥት ከአገሩ ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራ በኢትዮጵያና በተመረጡ የአፍሪካ አገሮች ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ረዘም ላሉ ዓመታት ቀጥተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን የነደፈ መሆኑን ለመጀመርያ ጊዜ ልምድ ለመቅሰም ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር የሙከራ ሥራ በይፋ መጀመሩን፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሐጎስ ገመቹ፣ የቻይና መንግሥት በአገሩ የቀይ መስቀል ድርጅት አማካይነት ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረግ በአርባ ምንጭ የፓይለት ፕሮጀክት በይፋ ጀምሯል ብለዋል፡፡
ነገር ግን የቻይና መንግሥት ከቻይና ውጪ ሰብዓዊ ዕርዳታ አድርጎ የማያውቅ በመሆኑ፣ በቀጥታ ወደ ፕሮጀክት ከመግባት ይልቅ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ጋር በመሆን ሥራውን በመጀመር፣ ልምድ የመቅሰሙን ተግባር በመምረጥ መምጣቱን አቶ ሐጎስ አክለው ገልጸዋል፡፡
የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ በጥቂት አገሮች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉትን ሞዴል አገሮች በቅርቡ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በቀዳሚነት ኢትዮጵያን መምረጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለሙከራ በመረጠው የአርባ ምንጭ ፕሮጀክት ላይ በጤና፣ በትምህርትና በውኃ ሥራዎች የጀመረ መሆኑን፣ 286 ሺሕ ዶላር ስምምነት በማድረግ የቁሳቁስ ዕርዳታ መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ማቅረቡ ተገልጿል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ላ ይፋን የቻይናን ቀይ መስቀል በመወከል ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊዋ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ወርቁ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የአርባ ምንጩ የሙከራ ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ በ2008 ዓ.ም. ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚቆይ የቀጥታ ፕሮጀክት በስፋት ለመጀመር የቻይና መንግሥት መዘጋጀቱንም አቶ ሐጐስ ገልጸዋል፡፡
ቻይና ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ አገሮች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረቷ ይታወቃል፡፡ ዋና ግንኙነቷ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በብድር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ የምዕራባውያንን ያህል ይህ ነው የሚባል ሚና ባይኖራትም፣ ከመንግሥት ጋር ባላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለድህነት ቅነሳ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ስትሰጥ መቆየቷን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለአብነትም ያህል በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ሥራ የሚውል የጥሬ ገንዘብ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ መንግሥት ትለግስ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን የቻይና መንግሥትን በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ በሰብዓዊ ዕርዳታ የሚንቀሳቀሱ ምንም ዓይነት ድርጅቶች አይታወቁም፡፡
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ባላት የጠበቀ የንግድ ግንኙነት በምዕራባውያን ትችት የሚሰነዘርባት ቢሆንም፣ ቻይናም ሆነች የአፍሪካ አገሮች ያለው ግንኙነት በመተማመንና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን በመግለጽ ትችቶችን ያጣጥላሉ፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2012 484 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ስታገኝ፣ ይህም የዓለማችን ሰባተኛዋ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቀባይ አገር አድርጓታል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አሜሪካ 233 ሚሊዮን ዶላር በመስጠት ቀዳሚዋ ስትሆን፣ እንግሊዝ 68 ሚሊዮን ዶላርና የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት 58 ሚሊዮን ዶላር በመስጠት ቀጣዩን ቦታ ይዘዋል፡፡