Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር በድምፅ ብክለት ምክንያት 12 ብሎኬት ፋብሪካዎችን ዘጋ

  የአዲስ አበባ አስተዳደር በድምፅ ብክለት ምክንያት 12 ብሎኬት ፋብሪካዎችን ዘጋ

  ቀን:

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የድምፅ ብክለት እያደረሱ ነው ያላቸውን 12 የብሎኬት ፋብሪካዎች ዘጋ፡፡

  ባለሥልጣኑ ዓርብ ኅዳር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኙ ብሎኬት ፋብሪካዎችን መዝጋቱን አስታውቋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዱኛ ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የብሎኬት ፋብሪካዎቹ የሚያወጡት ድምፅ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ችግር ሆኖ ነበር፡፡

  ‹‹ፋብሪካዎቹ በተደጋጋሚ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና የሚያወጡትን ድምፅ እንዲቀንሱ ሙያዊ ምክር ቢሰጣቸውም፣ ሊያስተካክሉ ባለመቻላቸው ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፤›› ሲሉ አቶ አዱኛ ተናግረዋል፡፡

  የአስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 15/2001፣ የብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995 እና የብክለት ቁጥጥር ደንብ ቁጥር 25/2000 አማካይነት አዲስ አበባ ከተማን ከብክለት የመጠበቅ፣ ብክለት ደርሶ ከተገኘም ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

  በዚህ መነሻ በተያዘው በጀት ዓመት ለአካባቢ አደገኛ የሆኑ ሦስት የፕላስቲክ ፋብሪካዎችን ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ዘግቷል፡፡ ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎችን ደግሞ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ዘግቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ70 የማያንሱ የምሽት ክለቦችን እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ደግሞ 12 የብሎኬት ፋብሪካዎችን ዘግቷል፡፡

  የፕላስቲክ ፋብሪካዎቹና የምሽት ክለቦቹ ማስተካከያ በማድረጋቸው ሥራ እንዲጀምሩ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

  በካይ ተብለው የታሸጉት ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅሬታ በማቅረባቸው፣ ለመጨረሻ ጊዜ የስድስት ወራት የማስተካከያ ጊዜ ተሰጥቷቸው በድጋሚ ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡

  አቶ አዱኛ ኅብረተሰቡ ለአካባቢ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በሁሉም ወረዳዎች የአካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤቶች አሉ፡፡ ችግር በሚገጥምበት ወቅት ኅብረተሰቡ በአቅራቢያ ለሚገኙ ወረዳዎች ሪፖርት ቢያቀርቡ ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ ከኢንዱስትሪ ብክለት በተጨማሪ የድምፅ ብክለት ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የድምፅ ብክለት ለመማር ማስተማር ሒደትና ለሕሙማን አስከፊ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩ ቅሬታ ይቀርብበታል፡፡

  በተለይ የሃይማኖት ተቋማት፣ የምሽት ክለቦች፣ ጋራዦች፣ የእንጨትና የብረታ ብረት ሥራ ድርጅቶችና የመሳሰሉ ተቋማት ከፍተኛ ድምፅ የሚያወጡ በመሆናቸው ነዋሪዎች ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...