Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜና‹‹የንጉሡ መግለጫ ለደረሰው ጥቃት መባባስ ምክንያት ስለመሆኑ ምርመራ ይደረጋል››

  ‹‹የንጉሡ መግለጫ ለደረሰው ጥቃት መባባስ ምክንያት ስለመሆኑ ምርመራ ይደረጋል››

  ቀን:

  የዙሉ ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ የሌሎች አገር ዜጎች ከአገራችን ውጡ የሚል ቅስቀሳ በማድረጋቸው በአንድ ኢትዮጵያዊና በአምስት አፍሪካውያን ላይ ግድያ እንዲፈጸምና ንብረታቸው እንዲዘረፍ ምክንያት ሆኗል በመባሉ፣ በንጉሡ ላይ ምርመራ እንደሚደረግ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ገለጹ፡፡

  አምባሳደር ንሲንጋ በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፣ ኢትጵያውያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ በርካታ አፍሪካውያን ላይ ለደረሰው የዘረኝነት ጥቃት መንስዔ እንደሆነ የሚነገርለት ንግግር፣ እንደሚባለው ለተከሰተው ጥቃት ምክንያት ነው መባሉን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ ምክንያት ያደረጉትም ዘረኝነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከዚህ ቀደምም ደጋግመው ሲከሰቱ በመቆየታቸው ሳቢያ፣ የንጉሡ መግለጫ ፀብ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል መባሉ መታየት ያለበት እንደሆነ ገልጸው፣ የንጉሡ ንግግር ግን ብሶበት የቆየውን ጥቃት አባብሶታል ሊባል እንደሚችል አምባሳደሩ አምነዋል፡፡ ይህ በመሆኑም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በንጉሡ ላይ ምርመራ ሊያካሂድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  በደቡብ አፍሪካ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ፣ የሞትና የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ባሻገር በንብረቶቻቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እንዲገልጹ የተጠየቁት አምባሳደር ንሲንጋ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለመግለጽ እንደሚቸግራቸው አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኢትጵያውያን ንብረትና ይዞታ ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን፣ በገንዘብ ምን ያህል እንደሚገመትም ለመግለጽ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

  የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በአፍሪካውያኑ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ማስቆሙ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ነው ያሉት አምባሳደር ንሲንጋ፣ ለዘለቄታው ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ዜጎች ከደቡብ አፍሪካውያን ጋር ተጣምረው እንዲኖሩ የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መንግሥት እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡

  እንደ አምባሳደሩ መግለጫ በሌሎች ዜጎች ላይ የተቃጣው የዘረኝነት ጥቃት መነሻ ድህነት ነው፡፡ አብዛኞቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን በድህነት በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሆኖም በአካባቢው ከሚኖሩት ደቡብ አፍሪካውያን ይልቅ በርካቶቹ ስኬታማ የንግድ ሥራዎችን የሚያካሂዱ፣ መደብሮችን በመክፈት ጥሩ ገቢ የሚያገኙ ለመሆን ችለዋል፡፡

  ‹‹ከሌሎች አገሮች እየመጡ በገዛ አገራችን ሥራ አጥ አደረጉን፤›› የሚለው የደቡብ አፍሪካውያኑ ወቀሳም፣ ከሚኖሩበት ድህነት ሳቢያ የሚመነጭ በመሆኑ ለጥቃት እንዲነሳሱ ማድረጉን አምባሳደሩ ያምናሉ፡፡ መንግሥታቸው የድህነት መጠኑን ለመቀነስና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ እንደሚሠራም ይናገራሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከ24 በመቶ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ሥራ አጥ መሆናቸው፣ በሌሎች ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ምክንያት እንደሆናቸው ከመግለጽ ባለፈ፣ በርካታ ሕገወጥ ስደተኞች ድሆች ደቡብ አፍሪካውያን ሊሰማሩባቸው የሚችሏቸውን ሥራዎች በመውሰዳቸው ጭምር ቁርሾው መባባሱም እየተነገረ ይገኛል፡፡

  ምንም እንኳ በኢትዮጵያውያንና በሌሎች አፍሪካውያን ላይ የደረሰውን ጥቃት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን ጨምሮ በርካቶች ቢያወግዙትም፣ ግጭቱ ከተነሳበት ደርባን ከተማ በተጨማሪ በጆሃንስበርግ ከተማና አካባቢዎች ላይ እየተዛመተ መቀጠሉ ተሰምቷል፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የደርባን ከተማ ነዋሪዎችም ሠልፍ በመውጣት የተፈጸመውን ጥቃት ቢያወግዙም፣ ጥቃቱ ሊቆም እንዳልቻለና በስደተኞቹና በደቡብ አፍሪካውያኑ መካከል መፋጠጡ ቀጥሏል፡፡ ስደተኞችም ራሳቸውን ለመከላከል የተለያዩ ስለታም መሣሪያዎችን መታጠቃቸው ታውቋል፡፡ 

  በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሰደር ሙሉጌታ ከሊል የደቡብ አፍሪካውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማነጋገራቸውና የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለመታደግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

  እስካለፈው ዓርብ ድረስ ጥቃትና ዘረፋ በመፈጸም የተጠረጠሩ ከ70 በላይ ደቡብ አፍሪካውያን መታሰራቸው ተነግሯል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 ብቻ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ60 በላይ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ በዘረኝነት ጥቃት ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

   

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...