Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የፈጠረው ቁጣ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  እሑድ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የዳግማዊ ትንሳኤ በዓልን በተለያየ ሥፍራ በመሆን በማክበር ላይ ይገኙ ነበር፡፡ የበዓሉን ደስታና የመልካም በዓል ምኞት ለመጋራትና ለመመኘት የተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾችን ለጐበኙ ኢትዮጵያዊያን ግን አስደንጋጭ ነበር፡፡ ከዚህ የመልካም በዓል ምኞት መልዕክት ይልቅ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ዜናዎች እየተሰራጩ ነበር፡፡ በአብዛኛው የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ዘንድ የበዓሉ የደስታና የመልካም ምኞት ስሜት ወደ ሐዘንና ቁጭት የተቀየረው በደቂቃዎች ፍጥነት ነው፡፡

  ይህን የበዓል ድባብና ስሜት ወደ ሐዘን፣ ቁጭትና እልህ የቀየረው ዜና ደግሞ፣ 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በስደት ከሚኖሩበት ሊቢያ በአረመኔው አይኤስኤስ አማካይነት በግፍና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ መጨፍጨፋቸውን መግለጹ ነበር፡፡

  የእነዚህ 30 ንፁኃን ስደተኛ ዜጐችን ጭፍጨፋ ዜና ተከትሎ አገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዜጐች ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት የተለያዩ የድረ ገጽ የዜና ማሠራጫዎችን ጐበኙ፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችን ተከታተሉ፡፡ ዜናዎቹም ይህን አረመኔያዊ ድርጊት የሚያረጋግጡ መሆናቸው ታወቀ፡፡

  ከሟቾቹ መካከል በአዲስ አበባ በተለምዶው ጨርቆስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች የነበሩ ጐረቤታሞችና አብሮ አደግ ጓደኞች የነበሩት ባልቻ በለጠና ኢያሱ ይኩኖአምላክ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ የከተማው ነዋሪዎች በሐዘንና በቁጭት ተሞልተው ሐዘናቸውንና ቁጭታቸውን ለማጋራት ወደ ጨርቆስ አቀኑ፡፡ ሐዘኑም የሁለቱ በግፍ የተገደሉት ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆነ፡፡

  በአረመኔያዊ ፍጅት ሕይወታቸውን ካጡት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆነው ባልቻ በለጠ 15 ወንድሞችና እህቶች ያሉት ሲሆን፣ ለቤተሰቦቹ ደግሞ አሥራ አራተኛ ልጅ ነበር፡፡ ዕድሜው ደግሞ 38 አካባቢ፡፡

  በስደት ወደ ሊቢያ ሲያመራ ለማንም የቤተሰቡ አባል ሳይናገር በሚስጥር መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት ታላቅ ወንድሙ አቶ ፋሲካ በለጠ ናቸው፡፡

  ከአገር የወጣው ከሁለት ወራት በፊት እንደነበር የሚያስታውሱት ታላቅ ወንድሙ፣ በእነዚህ ሁለት ወራት ውስጥ የስልክም ሆነ በሌላ ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ግንኙነት በቤተሰቡና በግፍ ሕይወቱን ባጣው ባልቻ መካከል አለመደረጉንም እያስታወሱ፣ በመብሰልሰልና በማዘን ገልጸዋል፡፡

  በአስነዋሪው የጽንፈኛው ኃይል አረመኔያዊ ድርጊት ሕይወቱን ያጣው ባልቻ በለጠ፣ ትዳር መሥርቶ የፈታ መሆኑን የገለጹት ታላቅ ወንድሙ፣ ከትዳሩ ያፈራው ልጅ አለመኖሩንም እንዲሁ ገልጸዋል፡፡

  ከአገር ሲወጣ የመጀመርያው የሆነው ባልቻ በአገር ውስጥ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ውስጥ የሰብ ስቴሽን ሠራተኛ ሆኖ ያገለግል እንደነበር፣ ታላቅ ወንድሙ አቶ ፋሲካ በሐዘንና በእንባ ታጅበው አስረድተዋል፡፡

  በፕሬስ ቲቪ የወንድማቸውን ሞት የተረዱት አቶ ፋሲካ በመቀጠል በፌስቡክ አማካይነት የኢትዮጵያውያኑን የግፍ አሟሟት መመልከታቸውን በምሬት ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ወንድሜ በጥይት ሲመታ በቀጥታ እያየሁት ነው ያረፈው፤›› በማለት በሐዘንና በእንባ የገለጹት አቶ ፋሲካ፣ ‹‹ሌሎች ወንድሞቻችን ዘግናኝና አሳፋሪ በሆነ መንገድ ደማቸው ፈሷል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ደማቸውን ይክፈል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

  አራት ልጆች ከሚገኙበት ቤተሰብ አንዱ የሆነውና ለቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ የሆነው እያሱ ይኩኖአምላክ እንዲሁ ወላጅ እናቱን ለመጦር በማሰብ፣ ይህን የስደት ጉዞ ማድረጉን የገለጸው ታላቅ ወንድሙ ሥዩም ይኩኖአምላክ ነው፡፡

  ከሁለት ወራት በፊት ከልጅነት ጓደኛው ባልቻ ጋር ወደ ሱዳን ጉዞ የጀመረው እያሱ፣ ከአንድ ወር በፊት ድረስ ከታላቅ ወንድሙ ሥዩም ጋር በስልክ ይገናኝና ወንድሙም ገንዘብ ይልክለት የነበረ መሆኑን፣ ካለፈው አንድ ወር ጊዜ ወዲህ ግን ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረውም ተብሏል፡፡

  ‹‹ከዚህ ሲነሳ የተነጋገርነውና የማውቀው መጀመርያ ወደ ሱዳን እንደሚጓዝና ከዚያም በአውሮፕላን ወደ ሌላ አገር እንደሚሄድ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሱዳን እንዴት ሊቢያ እንደገቡ ምንም መረጃ የለኝም፤›› በማለት ግንኙነታቸው ከተቋረጠ ካለፈው አንድ ወር ወዲህ የተፈጠሩትን ነገሮች ምንም እንደማያውቅ ወንድሙ ሥዩም አስረድቷል፡፡  

  ‹‹የጉዞው መነሻ ምክንያት ደካማ እናታችንን ለመጦር ነበር፡፡ ትንሽ ሳንቲም ነበረችው፡፡ በእርሷም መኪና መግዛት ፈልጐ ነበር፡፡ ነገር ግን የነበረው ገንዘብና ሊገዛ ያሰበው መኪና በዋጋ ሊመጣጠኑ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ተነስቶ ሄደ፤›› በማለት አቶ ሥዩም ያስረዳል፡፡ ትዳር ያልመሠረተና ልጅም ያልወለደው እያሱ ከአገር መውጣቱ ለወላጅ እናቱ አኻዛ ካሳዬ ያልተነገራቸው ሲሆን፣ ከቤት ውስጥ በተደጋጋሚ ላለመታየቱ በታላቅ ወንድሙ አማካይነት ሲቀርብ የነበረው ምክንያት ደግሞ ለመስክ ሥራ ከከተማ ወጥቷል የሚል ነበር፡፡

  ነገር ግን እናቱ መሰደዱን ከጐረቤት እንደሰሙና በሰቀቀን የመመለሻውን ቀን ይጠብቁ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ በአረመኔዎች የተፈጸመ ተግባር ተጧሪ እናትንና ጧሪ ልጅን ዳግም ላይገናኙ አቆራረጣቸው፡፡

  የእነዚህ ኢትዮጵያውያን የግፍ ግድያ በመቃወም በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደረጉ ሲሆን፣ ሌሎች እንቅስቃሴዎችም በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

  የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀጽ 22/2/ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 አንቀጽ 49/4/ መሠረት፣ ከሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጇል፡፡ በዚህም መሠረት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና ሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች፣ በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች፣ በቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤቶች፣ በቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች፣ በንግድ ጽሕፈት ቤቶችና በኢትዮጵያ መርከቦች ላይ የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ይህን አረመኔያዊ ድርጊት ለማውገዝ ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

  በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የደረሰውን አሰቃቂ ድርጊት በፅኑ ያወገዙት ሲሆን፣ ‹‹የሃይማኖት ጭንብል ለብሶ መምጣቱ ሳያዘናጋን፣ መላውን የሰው ዘር ለማጥፋት የተወጠነ መሆኑን በመገንዘብ በአንድነት በአንድ ሐሳብ መቆም አለብን፤›› በማለት ጉዳዩን በጋራ መታገል አለብን በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ ‹‹በሃይማኖት መቻቻልና በእኩልነት ላይ በተመሠረተ የዜጐቿ አብሮ የመኖር አኩሪ ባህል በፅንፈኛ ኃይሎች መሠሪ ፍላጐትና ተግባር በሯን ያልከፈተችው አገራችን ኢትዮጵያ፣ የራሷንና የቀጣናውን አገሮች ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአጋሮቿ ጋር እየተረባረበች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የአይኤስ ፅንፈኛ ቡድን በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ ያደረሰው አረመኔያዊ ግድያ የከተማችን ነዋሪዎችና መላው የአገራችንን ሕዝቦች ልብ በሐዘን የሰበረ አሰቃቂ ክስተት ነው፤›› በማለት ገልጿል፡፡

  ጽሕፈት ቤቱ በማከልም፣ ‹‹የፅንፈኛው ኃይል ድርጊት የጀመርነው የፀረ ሽብር ዘመቻ ይበልጥ እንድናቀጣጥልና አገራችን ኢትዮጵያ በሃይማኖት ሽፋን ለሚደረግ የፅንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባር፣ መቼም ቢሆን ሥፍራ እንደሌላት ደግመን የምናረጋግጥበት አጋጣሚ ነው፤›› በማለት የንፁኃን ዜጐች ሞትን በፅኑ አውግዟል፡፡ ይህን የንፁኃን ዜጐችን ግድያ ያወገዙት በርካታ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ተቋማት ሲሆኑ፣ ከአገር ውስጥ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትየጵያ የውጭ ሥራ ሥምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አሠሪ ማኅበር ለሪፖርተር የሐዘን መግለጫ ልከዋል፡፡

  ከእነዚህ አገር አቀፍ ተቋማት በተጨማሪም የአሜሪካ፣ የግብፅና የእስራኤል መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች አካላት በንፁኃን ዜጐች ላይ የደረሰውን አረመኔያዊ በደል በፅኑ አውግዘዋል፡፡

  በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የውጭ ሥራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አሠሪ ማኅበር፣ ‹‹የአይኤስ አሸባሪ ቡድን ታጣቂዎች በንፁኃን ኢትዮጵያውያን ዜጐች ላይ ያደረሱትን ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃትና ግድያ በምንም መሥፈርት ተቀባይነት የለውም፤›› ከማለቱም በተጨማሪ፣ ‹‹ማኅበራችን አጥብቆ የሚያወግዘው ነው፤›› በማለት ገልጿል፡፡

  ‹‹በመሆኑም ዜጐች ወደተለያዩ አገሮች ለመሄድ በሚያደርጉት ጥረት እንደዚህ ባሉ ሰብዓዊነት በሌላቸው ጨካኞች እጅ በቀላሉ እንዳይገቡና ምንም ዓይነት ከለላ በማያገኙበት ሁኔታ ለጥቃቱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ፣ መንግሥት የሚሰጠውን አመራር በመቀበል ከመንግሥት ጐን መሆናችንን እንገልጻለን፤›› በማለት አስታውቋል፡፡

  የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ለሪፖርተር የሐዘን መግለጫ የላኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ፣ ሰማያዊ ፓርቲም በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

  መድረክ፣ ‹‹በኢትዮጵያውያን ላይ በሊቢያ የተፈጸመው የአሸባሪዎች አረመኔያዊ ጥቃት የሕዝባችንን ፀረ ሽብር አቋም ይበልጥ ያጠናክራል እንጂ አያላላውም፤›› በማለት፣ የንፁኃን ዜጐችን ግድያ በመቃወም ያወጣው መግለጫ በጉዳዩ ክፉኛ ማዘኑን ይገልጻል፡፡

  ‹‹አይኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በስደት ሲኖሩ የነበሩትን በርካታ ወገኖቻችንን ከነበሩበት የስደተኞች ካምፕ አውጥቶ በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ ይህንኑ ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ተግባሩን እንደ ጀብዱ ቆጥሮ በመገናኛ ብዙኃን ማሠራጨቱን ስንመለከት፣ መላው የመድረክ አባላት እጅግ ከፍተኛ ሰቀቀንና ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል፤›› በማለት በመግለጫው አስታውቋል፡፡

  በተጨማሪም አሸባሪ ቡድኑን ‹‹በእስልምና ሃይማኖት ስም የሚነግድ›› በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹የዚህ ቡድን ፋሽስታዊ ተግባር የቡድኑ መሪዎችና አባላት ስለእስልምና በማያውቁበት ጥንታዊ ዘመን የእስልምናን ሃይማኖት ከክርስቲያን ሃይማኖት ጐን ተቀብሎና ተቻችሎ አብሮ በመኖር በሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መፈጸሙ፣ የቡድኑን ድንቁርናና አረመኔያዊ ባህሪ በግልጽ የሚያሳይ ነው፤›› በማለት መድረክ የንፁኃን ዜጐችን ግድያ አውግዟል፡፡

  ‹‹ኢትዮጵያውያን አደባባይ ወጥተው ሐዘናቸውንና ተቃውሞአቸውን እንዲገልጹ የተጠራውን ሠልፍ እንደግፋለን፤›› በማለት መግለጫ ያወጣው ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡

  ‹‹ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በርከት ያሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መንግሥት በዜጐቻችን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ግድያ ትኩረት እንዲሰጠው ለማሳሰብና ቸልተኝነቱን ለመቃወም፣ ወደ ቤተ መንግሥት በማቅናት ላይ እያሉ ፖሊስ በኃይል እንዲመለሱ አድርጓል፤›› በማለት ፓርቲው ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ ‹‹ቢሆንም ግን ሰማያዊ ፓርቲ ዜጐቻችን አደባባይ ወጥተው የአሸባሪ ቡድኑን አረመኔያዊ ድርጊት እንዲያወግዙ ካለው ፅኑ እምነት የተነሳ፣ ዜጐች መስቀል አደባባይ ወጥተው የተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፤›› ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

  ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ማለዳ ሁለት ሰዓት ከሩብ አካባቢ ሐዘንተኞች ቤት የተገኙ የተወሰኑ ዜጐች ‹‹እንግዳ ተቀባይ ምላሹ ይህ ይሁን?››፣ ‹‹መንግሥት የዜጐችን ደም ይፋረድልን!!!››፣ ‹‹ዝምታው ይቁም!!!›› እንዲሁም ‹‹ኢትዮጵያን ከልቡ የሚወድ ሆ ይበል!›› የሚሉ መፈክሮችን በማንገብ ወደ ቤተ መንግሥት ጉዞ ጀምረው ነበር፡፡

  ምንም እንኳን ወደ ቤተ መንግሥት እየተጓዙ የነበረ ቢሆንም፣ ሠልፈኞቹ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከፍ ብሎ ከሚገኘው መስቀለኛ መንገድ በላይ ግን ማለፍ አልቻሉም፡፡

  ፖሊስ ብሔራዊ የሐዘን ቀን በመታወጁ በነገው ዕለት ሠልፍ ይካሄዳል በማለት ወደመጡበት እንዲመለሱ አስታውቋል፡፡ ሠልፈኞቹ ደግሞ አሁኑኑ ወደ ቤተ መንግሥት እንሂድ በሚል ለ30 ደቂቃዎች ያህል ከተወዛገቡ በኋላ ሐዘንተኞችን አጅበው ወደ ሐዘኑ ቤት ተመልሰዋል፡፡

  የሟች እያሱ ይኩኖአምላክ ታላቅ ወንድም አቶ ሥዩም ይኩኖአምላክ የሁለቱን በግፍ የተገደሉ አብሮ አደግ ጓደኛሞች ግንኙነት የገለጸው፣ ‹‹የሁለቱ ጓደኝነትና ቅርርብ ከእኔ ከወንድም በላይ ነው፡፡ አንድ ላይ ነው የሚተኙት፣ ሲወጡ ሲገቡ አንድ ላይ ነው፣ ወደ መዝናኛ ሲሄዱም በአንድ ላይ፤›› በማለት ነበር፡፡

  ይኼው የአብሮነት ጉዞ በመጨረሻ በአንድ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በአረመኔያዊው አሸባሪ ቡድን ተፈጸመ፡፡

   

   

       

   

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -