[ክቡር ሚኒስትር ቢሮአቸው ውስጥ ጋዜጦችን እያነበቡ ነው፡፡ ጸሐፊያቸው በሩን በርግዳ ገባች]
- አንቺ ብለሽ ብለሽ እንደ ጎረምሳ በሩን በርግደሽ ትገቢያለሽ?
- ውይይይ…. ውይይይ……
- ምን ሆነሻል?
- አለቅን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው የሆንሽው?
- አለቅን እኮ ነው የምልዎት፡፡
- የምን እልቂት ነው የምታወሪው?
- አልሰሙም እንዴ?
- ምኑን?
- ወገኖቻችን አለቁ እኮ፡፡
- እ?
- የመን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አሁን ደግሞ ሊቢያ ወገኖቻችን ታረዱ፡፡
- እስኪ ተረጋጊ፡፡
- ምኑን ተረጋጋሁት ወገኖቼ አልቀው፡፡
- ለእኔም እኮ ወገኖቼ ናቸው፡፡
- ለመሆኑ መንግሥት ምን እያደረገ ነው?
- ጉዳዩን በጥብቅ እየተከታተለው ነው፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንሽ?
- እየተከታተለ ነው ያሉኝ?
- አዎን፡፡
- ኧረ በአስቸኳይ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡
- መጀመሪያ ሁኔታዎች ይታወቁ፡፡
- እስከ መቼ ነው ክትትሉ?
- የተጨበጠ ነገር እስኪገኝ፡፡
- ምኑ ነው የሚጨበጠው?
- እንግዲህ በደመነፍስ አይገባበት፡፡
- የመንግሥት ነገር ግን ግርም ይለኛል፡፡
- ምኑ ነው የሚገርምሽ?
- አንድ ችግር ሲፈጠር መዘግየት ልማዱ ነው፡፡
- አሪፍ አይቸኩልም፡፡
- ለተፈጠረው ችግር በቂ ምላሽ ሲጠፋ ግን ሌላ ምክንያት ይደረደራል፡፡
- ምን ዓይነት ምክንያት ይደረደር ይሆን?
- ማጣፊያው ሲያጥር አፈጻጸም ላይ ችግር አለ ይባላል፡፡
- እንደሱ ለምን እንደሚባል ይገባሻል?
- አዎ!
- ምንድነው?
- በአግባቡ አቅዳችሁ ስለማትንቀሳቀሱ አፈጻጸሙ ይበላሻል፡፡
- የአሁኑን ጉዳይ ከዚህ ጋር ምን አገናኘው?
- ክትትሉ ሳይሳካ ሲቀር ሰበብ ይፈለጋል፡፡
- ምን ተብሎ፡፡
- እረኛው እንዳለው፡፡
- እረኛው ምን አለ?
- ሳስበው ሳስበው ደከመኝ፡፡
- ወሬኛ!
- ከእናንተ መንቀርፈፍ የእኔ ወሬ ይሻላል፡፡
[ክቡር ሚኒስትር ከቢሮ ከመውጣታቸው በፊት አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው አደጋ በተመለከተ ቶሎ መግለጫ ማውጣት አለብን፡፡
- እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ በማዕከል በመንግሥት ነው መውጣት ያለበት፡፡
- እኛ ብናወጣስ?
- ምን ብለን?
- እናወግዛለን ብለን ነዋ፡፡
- ለማውገዝማ ሕዝቡም እኮ በተለያዩ መንገዶች እያወገዘ ነው፡፡
- የእኛ የውግዘት መግለጫ በአስቸኳይ ተጽፎ በቴሌቪዥን መተላለፍ አለበት፡፡
- በፓርላማ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ ተወስኗል፡፡ የሚመለከተው የሕዝብ ግንኙነት መሥሪያ ቤትም የመንግሥትን መግለጫ ያወጣል፡፡
- በዚህ ወቅት የእኛ ሚና ምን መሆን አለበት ታዲያ?
- ክቢር ሚኒስትር ሥራችንን መሥራት ብቻ፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- ሥራችንን እንሥራ፡፡
- እየሠራን አይደለንም?
- አዎ!
- እንዴት?
- ሕገወጥ ስደትን ማስቆም አልቻልንም፡፡
- ወደ ዓረብ አገሮች ዜጎች እንዳይሄዱ ዕግድ አስጥለን የለም ወይ?
- በቦሌ ቢዘጋ ሰው በየአቅጣጫው እየነጎደ ነው፡፡ በቦሌም ቢሆን ያው ነው፡፡
- እኛ ምን እናድርግ ታዲያ?
- ኃላፊነት አለብን፡፡
- እንዴት?
- ሕገወጦችን በመቆጣጠር፡፡
- ለምን አቃተን ታዲያ?
- ወዳጅ ተብዬዎች በኔትወርክ እየጠለፉን ነዋ፡፡
- እኛን?
- አዎ!
- እነማን ናቸው?
- በኤክስፖርተርነት ስም እርስዎን የተወዳጁት፡፡
- ምን?
- ለበዓል ሰሞን በስጦታ ያንበሸበሹዎት፡፡
- አንተ ምን እያልክ ነው?
- የሚያውቁትን ነው የነገርኩዎት፡፡
- አንተ የለሁበትም ልትል ነው?
- እኔማ እጄን እንደ እንትና ታጥቤያለሁ፡፡
- እንደማ?
- እንደ ጲላጦስ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ በንዴት እንደበገኑ ለምሳ ወደ ቤት እየሄዱ ነው፡፡ ሾፌራቸው ሙዚቃ ከፍቷል]
- ዝጋው ነው የምልህ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼን ሙዚቃ ዝጋ፡፡
- ምን ሆኑ?
- ወገኖቻችን ያልቃሉ አንተ ትዝናናለህ፡፡
- እኔማ አልቅሼ ወጥቶልኛል፡፡
- ከዓይንህ እንባ ወጥቶ?
- አዎን፡፡
- አይመስለኝም፡፡
- ለምን?
- ትንሽ እንኳ የምትደነግጥ አትመስልም፡፡
- ልቤ ግን ሩህሩህ ነው፡፡
- አንተ?
- አዎ!
- አንተ ልብህ ሩህሩህ ከሆነ ሌላው ምን ሊባል ነው?
- እኔ ደሃ ስለሆንኩ ደሃ እንጀራ ፍለጋ ሄዶ ሲያልቅ ያስለቅሰኛል፡፡ ያንገበግበኛል፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- ደሃ ሌላ ደሃ ወገኑ መከራ ሲደርስበት ሐዘኑ አጥንቱ ድረስ ነው ዘልቆ የሚሰማው ማለቴ ነው፡፡
- አሁን ድህነትን እዚህ ጋ ምን አመጣው?
- በድህነት ላይ የከበሩትንም የድህነት መርግ የተጫናቸውንም ለማነፃፀር እንዲረዳን ነው፡፡
- እነማን ናቸው የከበሩት? እነማን ናቸው የደኸዩት?
- የከበሩትማ ወጣቶችን ከአገር በሕገወጥ መንገድ የሚያስኮበልሉትና ደጋፊዎቻቸው ናቸው፡፡
- ወይ ጉድ፡፡
- በስደት ያሉ ወገኖቻችንን ጉዳይ ሳስብ ለእነዚህ ሕገወጦች ሕግ የለም ወይ እላለሁ፡፡
- ሕግማ አለ፡፡
- ታዲያ የሚወሰደው ዕርምጃ የታለ?
- እንግዲህ ለመክሰስ መረጃ ያስፈልጋል እኮ፡፡
- መረጃውም ማስረጃውም ሞልቷል እኮ?
- ምን ዓይነት መረጃና ማስረጃ?
- የድምፅ፣ የምሥል፣ የጽሑፍና የሰው ማስረጃ እኮ በሽ ነው፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለ?
- ችግርማ አለ፡፡
- የምን ችግር?
- ገንዘብ አልተቻለም፡፡
- ገንዘብ ምን አደረገ?
- የባለሥልጣንም የፍትሕንም አፍ አዘጋ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ሰምተውኛል፡፡
[ክቡር ሚኒስትር ከጠዋት ጀምሮ እንደተነጀሱ ለምሳ ቤት ሲገቡ ባለቤታቸው እየጠበቁዋቸው ነበር]
- ምነው የተቆጣህ ትመስላለህ?
- ስንት አናዳጅ አለ መሰለሽ?
- ከበላይ አካል ቁጣ መጣብህ እንዴ?
- ኧረ የታችኛው ነው፡፡
- የታችኛው ደግሞ ምን እያለ ነው?
- አጉል የወገን ተቆርቋሪ ነን እያሉ ያበግኑኛል፡፡
- የምን ወገን?
- በየመን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ የደረሰውን አደጋ አስመልክቶ የሚፈላሰፈው በዛ፡፡
- በወገን ጉዳይማ ሁሉም ያገባዋል፡፡
- እንደሚያገባው አውቃለሁ፡፡ ግን ይንዛዛሉ፡፡
- ይልቅ እሱን እርሳውና ያን ጉዳይ እንዴት አደረግክልኝ?
- የቱን?
- ያ ወዳጃችን አስመጣልሻለሁ ያለኝን ነዋ?
- እ?
- ለበዓሉ ሰሞን በስጦታ ያንበሻበሸን፡፡
- ለጊዜው እሱን እርሺ፡፡
- ለምን?
- በእሱ የተነሳ እሳት እየተቀጣጠለብኝ ነው፡፡
- የምን እሳት?
- እሳት አልኩሽ፡፡
- እሱ ኤክስፖርተር ነው እንጂ ከእሳት ጋር ምን ያገናኘዋል?
- የምን ኤክስፖርተር እንደሆነ ታውቂያለሽ?
- ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጫት፣ ወርቅና የመሳሰሉትን እንደሚልክ ነግሮኛል፡፡
- አንደኛውንስ አልነገረሽም?
- የቱን?
- ሰብዓዊ ፍጡራንን እንደሚልክ፡፡
- ምን አልክ?
- ሰዎችን ወደ ህንድ ውቅያኖስና ወደ ሜድትራኒያን ባህር እንደሚያሸጋግር አልነገረሽም?
- አንተ በስመ አብ በል፡፡
- አልልም፡፡
- ለምን?
- የአይኤስ አራጆች ያሉትን አልሰማሽም?
- ምን አሉ?
- እናርዳለን፡፡
- ከወዳጃችን ጋር ይኼ ምን ያገናኘዋል?
- የእሱም ጉዳይ እሳት ይቆሰቁሳል አልኩሽ እኮ?
- ታዲያ ምን ይሻላል?
- ለምኑ?
- የፈራህ መሰለኝ፡፡
- አዎ ያስፈራል፡፡
- መፍትሔው ምን ይሆን?
- አንድ ነገር ማድረግ ብቻ፡፡
- ምን ይደረግ?
- ተፀፅቶ ከክፉ ተግባር መታቀብ፡፡
- ከዚያስ?
- ለወገን በጎ ነገር ማድረግ፡፡
- አንተን ይኼን ያህል ምን አሳሰበህ?
- ወቀሳ ሲበዛ ጥሩ አይደለም፡፡
- ማንም ተራ ሰው ወቀሰኝ ብለህ ትፈራለህ?
- እንደዚህ አትበይ፡፡
- ምን ልበል ታዲያ?
- ወደ ህሊና ተመለሽ፡፡
- ህሊና ደግሞ ማን ናት?
- እስከ ዛሬ ባላውቃትም ምቹ ትራስ ናት ይሉዋታል፡፡
- ከእኔ ወይ ከእሷ አንዱን ምረጥ፡፡
- ይኼ እኮ ከምርጫ በላይ ነው፡፡
- ከምርጫ በላይ ምን አለ?
- የአገር ህልውና!