Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየሕክምና አገልግሎት ጉድለቶች ተገኝተውባቸዋል የተባሉ 82 የጤና ተቋማት ታሸጉ ዝርዝራቸው ግን...

  የሕክምና አገልግሎት ጉድለቶች ተገኝተውባቸዋል የተባሉ 82 የጤና ተቋማት ታሸጉ ዝርዝራቸው ግን አልተጠቀሰም

  ቀን:

      የሙያ ፈቃድ የሌላቸውን የሕክምና ባለሙያዎችን በማሠራት፣ የታካሚዎችን የሕክምና መረጃ በማጥፋትና በአግባቡ መዝግቦ ባለመያዝ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን በመድኃኒት ቤቶቻቸውና በመጋዘን ውስጥ አስቀምጠው በመገኘትና በመሳሰሉት የተጓደሉ አገልግሎቶች ሲሰጡ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 82 የጤና ተቋማት መታሸጋቸው ታወቀ፡፡

        ከጠቅላላ ሆስፒታል እስከ መለስተኛ ክሊኒክ ድረስ ደረጃ ያላቸው የጤና ተቋማትን ያሸገው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡

  የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋማቱ የታሸጉት አንድ የጤና ተቋም ማሟላት የሚገባቸውን በአዋጅ፣ በደንብና በመመርያ የተቀመጡትን አራት መሥፈርቶች መካከል አንዱን፣ ሁለቱን ወይም ሁሉንም ሳያሟሉ በመቅረታቸው ነው፡፡ የጤና ተቋማት ማለትም ጠቅላላ ሆስፒታል ከሆነ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ተዘርዝሮ ደረጃ የተሰጠው በመሆኑ ያንን አሟልቶ መገኘት እንዳለበት ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ገልጸዋል፡፡ ሌሎችም ከፍተኛ ክሊኒኮችም ቢሆኑ እንደዚያው በሚያሟሉት መሠረት ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  ሌላው ተቋማቱ በተፈቀደላቸው ደረጃ ማሟላት ያለባቸውን የሕክምና ባለሙያዎችን ማለትም ምን ያህል ሐኪሞች፣ ነርሶችና የጤና ረዳቶች ወዘተ. ሊኖራቸው እንደሚገባም ምክትል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

  በሦስተኛ ደረጃ የሕክምና ተቋማቱ ማሟላት ያለባቸው ጥራታቸውን የጠበቁ የሕክምና ግብዓቶች ኖሯቸው ለኅብረተሰቡ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች እንዲያገኙ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለሥልጣኑ የተጠቀሱትን ሁሉ ከማረጋገጥ ባለፈ በአግባቡና በትክክለኛው ሁኔታ በተግባር ላይ እያዋሉ መሆናቸውን በቋሚነት በመፈተሽ ጉድለት በተገኘባቸው ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

  ባለሥልጣኑ ተቋማቱን በመቆጣጠር አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሚል ደረጃ እንደሰጣቸው የገለጹት ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ፣ ባለፉት አምስት ወራት በተደረገ ቁጥጥር ጉድለት የተገኘባቸው 82 የሕክምና ተቋማት መታሸጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

  ሌሎቹ የታሸጉት ወይም ቀይ ደረጃ የተሰጣቸው የሕክምና ተቋማትን ዝርዝር እንዲገልጹ የተጠየቁት ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ፣ ‹‹የተቋማቱን ስም መናገር አያስፈልግም፡፡ ሁሉንም ነገር በመገናኛ ብዙኃን መግለጽም ተገቢ አይደለም፡፡ አልናገርም፤›› ብለዋል፡፡

  የሕክምና ተቋማቱ እስከ መታሸግ ያደረሳቸው ለኅብረተሰቡ እየሰጡ ባሉት ከሕክምና ጋር በተገናኘ ጉድለት ከመሆኑ አንፃር ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የተቋማቱን ስም መግለጽ አስፈላጊ መሆኑን ቢጠየቁም፣ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ግን ‹‹ለሚመለከተው አካል እናስታውቃለን፤›› ከማለት ባለፈ ለሕዝብ ይፋ ማድረግን አልፈቀዱም፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣንን በአዋጅ ያቋቋመው የጤና ተቋማትንና ሌሎች የሚቆጣጠራቸው ተቋማትን በመቆጣጠር ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ወይም አስፈላጊውን ዕርምጃ ወስዶ ለሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ይፋ ማድረግ ቢሆንም፣ ምክትል ዳይሬክተሯ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

  ከታሸጉት 82 የሕክምና ተቋማት በተጨማሪ የአራት ነርሶች፣ የአንድ ሐኪምና የአንድ የሰመመን (ኤኔስቴዢያ) ባለሙያ ፈቃዳቸውንም መነጠቃቸውን ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ተናግረዋል፡፡ ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጓቸው ሦስት የሕክምና ተቋማት ፈቃቸው ተሰርዞ መዘጋታቸውንም አክለዋል፡፡

  በ1996 ዓ.ም. በአዋጅ የተቋቋመውና በ1997 ዓ.ም. የመቆጣጠር ሥራውን የጀመረው የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥር ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለከንቲባው ነው፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...