Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአቶ እስክንድር ነጋና ዶ/ር መረራ የመከላከያ ምስክር ሆነው ፍርድ ቤት ቀረቡ

  አቶ እስክንድር ነጋና ዶ/ር መረራ የመከላከያ ምስክር ሆነው ፍርድ ቤት ቀረቡ

  ቀን:

  በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተደረጉ ተቃውሞዎችና ግጭቶች እንዲባብሱ አድርገዋል ተብለው የሽብር ወንጀል የተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው  አቶ እስክንድር ነጋ (ጋዜጠኛ) እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ፍርድ ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩትን ዶ/ር መረራ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሲሰጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይቀርቡ የከረሙ ቢሆንም፣ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ቀርበዋል፡፡

  የተከሳሽ ዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ ሁለቱም የመከላከያ ምስክሮች በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ተቃውሞና ግጭት ምክንያት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ዓላማ ለማስፈጸም ሳይሆን፣ ሕዝቡ ተቃውሞ ያሰማው በሰላማዊ መንገድ መሆኑንና አቶ ዮናታንም በግል የፌስቡክ አድራሻቸው ያሰራጩት መጣጥፍ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው መሆኑን እንደሚያስረዱላቸው ጭብጥ አስይዘዋል፡፡

  ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ጭብጡን በመቃወም ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን የሰነድ ማስረጃ በመመርመር የተጠቀሰውን ድርጊት አቶ ዮናታን እንደፈጸሙት በማረጋገጥ እንዲከላከሉ ስላላቸው፣ የመከላከያ ምስክሮቹ ያሰሙታል የተባለውን ጭብጥ የማይወክል በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቶ ነበር፡፡ የዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ቀደም ብሎ በነበሩ ችሎቶች ተነስቶ ብይን እንደተሰጠበት ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ተቃውሞውን ውድቅ በማድረግ የመከላከያ ምስክሮቹ እንዲሰሙ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

  ቀድመው የመከላከያ ምስክርነታቸውን የሰጡት ዶ/ር መረራ ናቸው፡፡ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ የተከሰተውን ተቃውሞና ግጭት ምክንያት እንዲያስረዱ ከአቶ ዮናታን ጠበቃ ጥያቄ ቀርቦላቸው አስረድተዋል፡፡

  ዶ/ር መረራ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በኦሮሚያ ክልል አንድ የእግር ኳስ ሜዳ በሕገወጥ መንገድ በመፍረሱ ምክንያት ተቃውሞ ተከሰተ፡፡ እሱን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞው ቀጠለ፡፡ ሕዝቡ በመንግሥት ሹመኞች በሚደርስበት ብሶት ቁጣው ገንፍሎ ለተቃውሞ ወጣ፡፡ መንግሥትም ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ፡፡ ተቃውሞው በተለያዩ ነገሮች ብሶት ላይ የነበረውን ሕዝብ ብሶቱ ሳይበርድ በመቀጠል፣ ሕዝብ ሳይወያይበት ሊፀድቅ የቀረበው የኦሮሚያው ልዩ ዞንና የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላንም ተከትሎ በመምጣቱ ሌላው የተቃውሞ ምክንያት እንደነበር ዶ/ር መረራ ገልጸዋል፡፡

  የእሳቸው ፓርቲ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ነገሩ በጥሞና እንዲታይና ሕዝብን እንዲያወያይ ለገዥው መንግሥት በተደጋጋሚ ደብዳቤ መጻፋቸውን የገለጹት ዶ/ር መረራ፣ ስለረብሻውም ሆነ ግጭቱ ከበስተጀርባው ምንም ነገር እንደሌለ መንግሥት ማመኑን አስታውሰው ችግሩ የሕዝብ ብሶት ገንፍሎ መውጣቱ መሆኑን መስክረዋል፡፡

  በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች በተለይ ደግሞ የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ሕዝቡን ተስፋ ስላስቆረጠው ተቃውሞው አይሎ መቀጠሉን፣ ይኼ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን በዓለም የተለመደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  ሕዝቡ ያነሳው ተቃውሞ በየትኛው የሰላማዊ ትግል መርህ ውስጥ እንደሚያርፍ የተጠየቁት ዶ/ር መረራ፣ ሕዝብ ብሶቱን ሲያሰማ ሽብር ፈጽሟል ሊባል እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሦስት መንግሥታትን እንዳዩ የሚናገሩት ዶ/ር መረራ፣ ያልታጠቀ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ብሶቱን ሲያሰማና ፍትሕ ሲጠይቅ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆን ሲገባው፣ በኢትዮጵያ በነፃነት ሐሳብን መግለጽ ጭምር ሽብር መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

  በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ በማቅረብ መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ መጠየቅ ሽብር ሊያሰኝ እንደማይገባም አክለዋል፡፡

  በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎች የሽብር ተግባር ሊባሉ እንደማይችሉም ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ሕዝብ ብሶት ሲበዛበት ተቃውሞ በሚያነሳበት ጊዜ መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ ያለበት በአስተዳደር ኃላፊዎች ላይ መሆኑን፣ በወቅቱ የተወሰደው ዕርምጃ ጠቋሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ የተለያዩ ኃላፊዎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ የመልካም አስተዳደር እንዳልነበረ ከማረጋገጡም በተጨማሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ያረጋገጡት እውነታ በመሆኑ ሽብር ሊባል እንደማይገባ ዶ/ር መረራ ተናግረዋል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ በመስቀልኛ ጥያቄ ሰላማዊ ሠልፍ ሲወጣ የአገሪቱን ሕግና ሕገ መንግሥት በኃይል እንዲናድ የሚፈቅድ ሕግ ስለመኖሩ ጠይቋቸው፣ ዶ/ር መረራ  ሕዝብ ፈቃድ እንደማይጠይቅ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የብዙ ዘመናት ብሶት ሲያንገፈግፈው የሕግ ወሰን ይጠፋዋል፡፡ የኦሮሚያው ግጭትም የዚሁ ውጤት ነው፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ሕዝቡ ሕግን ለመጣስ ሳይሆን ሕግና ሕገ መንግሥቱ ይከበር ማለቱን ገልጸዋል፡፡

  አቶ እስክንድር ነጋ በበኩሉ በሰጠው ምስክርነት እንደተናገረው ስለሰላማዊ ትግል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ሰላማዊ ትግል በሁለት እንደሚከፈልና በዴሞክራሲያዊ አገሮች የሚደረግና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አምባገነናዊ አገሮች የሚደረጉ ሰላማዊ ትግሎች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ዴሞክራሲ ባለባቸው አገሮች መንግሥት በሕዝብ ምርጫ እንደሚመረጥ አክሏል፡፡ ዴሞክራሲ በሌለባቸው አገሮች ደግሞ ሰላማዊ የሕዝብ አመፅ እንደሚደረግም ተናግሯል፡፡

  በሰላማዊ ትግል ውስጥ ሦስት ዓይነት አመፆች እንዳሉ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው አቶ እስክንድር፣ አንደኛው መሣሪያ ባልታጠቀ ሕዝብ የሚደረግ ሰላማዊ አመፅ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ መሣሪያ በታጠቀ ኃይል ሕዝብን ሳይነካ ከመንግሥት ታጣቂዎች (ወታደሮች) ጋር ብቻ የሚደረግ አመፅ መሆኑን አስረድቷል፡፡ እነዚህ አመፆች በዓለም ደረጃ የሚታወቁና የሕግ ከለላ ያላቸው መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ የተደረጉ አመፆች ያለጦር መሣሪያ በሰላማዊ መንገድ ያለምንም የኃይል ዕርምጃ የተከናወኑ መሆናቸውንም አብራርቷል፡፡

  ሦስተኛው አመፅ ግን በሙሉ ትጥቅ የሚደረግ መሆኑን፣ ትኩረት የሚያደርገው በሕዝብ ላይ ወይም ሕዝብን መፍጀት በመሆኑ፣ ‹‹ይህ ሽብር ወይም የሽብር ተግባር›› አመፅ እንደሚባል እስክንድር አስረድቷል፡፡

  ከአቶ ዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ እንደተረዳው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ የሽብር ተግባር ወንጀል ሊሆን እንደማይችልና በሰላማዊ ትግል አመፅ ውስጥ የሚያርፍ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በህንዶች ማኅተመ ጋንዲ፣ በአሜሪካ ደግሞ ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለሰላማዊ ትግል አመፅ በሰፊው ማስተማራቸውን ገልጾ፣ ‹‹ዮናታንን አውቀዋለሁ፡፡ የሕዝብ ልጅ ነው፡፡ ሰላማዊ ታጋይም ነው፡፡ ይኼንን አገርም ያውቀዋል፤›› ብሏል፡፡

  ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄ ‹‹የት ነው ያሉት?›› የሚል ጥያቄ ለአቶ እስክንድር አቅርቦለት ማረሚያ ቤት መሆኑንና አምስት ዓመት እንደሆነው ገልጾ፣ ‹‹የህሊና እስረኛ ነኝ፤›› ብሏል፡፡ ሌሎች የመከላከያ ማስረጃዎችን ለማየት ለመጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...